Sunday, 19 November 2017 00:00

“መንግስት የሚወዳቸው ህዝቦች”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

 … ልጆቼ እንቦቃቅሎቼ … ዛሬ የማወራላችሁ ተረት በአዲሱ የትምህርት ባለስልጣን ካሪኩለም ውስጥ በቅርቡ የተካተተ ነው፡፡ በተለይ በእናንተ እድሜ ላሉ ትንንሽ ልጆች በተደጋጋሚ መነበብ አለበት ተብሎ ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡ እና ልጆቼ … ምስኪን እንቦቃቅሎቼ፤ ይሄንን ተረት በደንብ አድርጋችሁ ስሙኝ .. እሺ፡፡
*     *      *
… በድሮ ድሮ ዘመን … አዳም ከገነት ተባሮ ወደ ምድር እየወደቀ ሳለ … እዚህ አለም ላይ ከማረፉ በፊት በደመናው ሸለቆዎች ውስጥ አንድ ሀገር ለትንሽ ጊዜ አረፍ ብሎ ነበር ይላሉ፤ የድሮ አባቶቻችን፡፡
ማናቸው ይሄንን ታሪክ ከዘመናት በፊት አስቀምጠው ለእኛ ያደረሱልን?
የድሮ አባቶቻችን (ህፃናቱ በአንድ ላይ)
አዎ ልጆች፤ ስለዚህ አባቶቻችን ያኖሩልንን የጥንት ታሪካችንን የትምህርት ባለስልጣን በመፅሐፍ አዘጋጅቶ ለእናንተ አድርሶላችኋል … ስለዚህ ተረቱን በጥሞና ስሙ እሺ!
ተረቱ ወይም ታሪኩ “መንግስት የሚወዳቸው ህዝቦች” ይሰኛል፡፡ … ተረቱ … ማነው … ታሪኩ ምን ይሰኛል ልጆች?
መንግስት የሚወዳቸው ህዝቦች (ህፃናቱ በአንድ ላይ)
*        *      *
… እና ልጆችዬ … ከዕለታት አንድ ቀን በደመናው ሸለቆዎች መሀል … ቅን … ትጉህ … አመፅ የማይወዱ … በፍቅር ተስማምተው … የሚኖሩ መንግስታቸው የሚወዳቸው ህዝቦች ነበሩ፡፡
መንግስታቸው እነዚህን ህዝቦች ከመጠን ያለፈ ነበር የሚወዳቸው፡፡ … (ልክ ወላጆቻችሁ እናንተን እንደሚወዷችሁ፡፡ … ወላጆቻችሁ ው.ድ.ድ.ድ.ድ.ድ…. አይደለ የሚያደርጓችሁ? …
አዎ! (በአንድ ላይ)
እነዚህን ህዝቦቹን ደግሞ መንግስት እንደዛ ነበር የሚወዳቸው፡፡ … በጣም ይራራላቸዋል፡፡ … መንግስት እነዚህን ህዝቦቹን “እኔ የምወደው ህዝቤ” ብሎ ነበር የሚጠራቸው፡፡ … ህዝቦቹ ብዙ ቢሆኑም በመሀላቸው ምንም ልዩነት የለም፡፡ ልክ እንደ አንድ አባትና እናት ልጆች፡፡
አባታቸው ማነው?
መንግስት!(በህብረ ዜማ)
መንግስት ለምንድነው ህዝቦቹን የሚወደው?
ልጆቹ ስለሆኑ! (በአንድ ድምፅ)
አዎ ልጆችዬ …
... እና በዛ በደመናማ ሸለቆ ሀገር ውስጥ … ህዝቡ ከጠዋት እስከ ማታ በእርሻው ላይ ተሰማርቶ ተግቶ ይሰራል፡፡፡ … በደመናማው ሀገር ጭቆና የለም፡፡ እርሻው በደመናው ላይ ነው፡፡ መሬቱ ራሱ ደመናው ስለሆነ ሰብሉ የውሀ እጥረት አይገጥመውም፡፡ … እርሻ ጠምደው የሚያርሱት በሰማይ አሞሮች ነው፡፡ የእርሻ ስራው በደመናው ሀገር በጣም ቀላል ነው፡፡
መንግስት የሚወዳቸው ህዝቦች ምን የሚባል ሀገር ነው የሚኖሩት ልጆች?
በደመናማው ሀገር! (ህፃናቱ በአንድ ድምፅ)
ደመናማው ሀገር የት ነው የሚገኘው?
በደመና ሸለቆዎች ውስጥ! (በአንድ ድምፅ)
መንግስት ህዝቦቹን ለምን ይወዳቸዋል?
ልጆቹ ስለሆኑ? (በአንድ ድምፅ)
… አዎ ልጆችዬ … ልጆቹ ስለሆኑ ነው። መንግስት ከመሀፀኑ አውጥቶ የወለዳቸው አባታቸው ነው። … አባታቸው ጥፋት ሲያጠፉ ይገስፃቸዋል፡፡ በጣም ትልቅ ጥፋት ያጠፉትን ደግሞ በአርጩሜ ይገርፋቸዋል፡፡
አባት ልጆቹን እንዴት ነው የሚቀጣው?
በአርጩሜ! (በአንድ ዜማ)
አርጩሜ ያማል እንዴ ልጆች?
(ግማሹ) ያማል … የተቀረው (ትንሽ ያማል)
(አስተማሪው) … የአባት አርጩሜ በፍፁም አያምም … እንደ ማር ይጣፍጣል … እስቲ እንደገና ድገሙት!
እንደ ማር ይጣፍጣል! (በአንድ ላይ)
ማር ታውቃላችሁ አይደል?
አዎ! (በአንድ ላይ)
ማር ምን ምን ይላል?
እንደ አርጩሜ ይጣፍጣል (ግማሾቹ) … እንደ ማር በፍፁም አያምም! (የተቀሩት)
አዎ ልጆች! … የእኛ የወደፊት ተስፋዎች … መንግስት ለእናንተም እንደ ደመናው ሀገር ህዝቦች ውድ.ድ ሊያደርጋችሁ ነው እኮ ይሄንን ተረት በትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ … እ.. አዘጋጅቶ እ… ያመጣላችሁ፡፡ አይደለም እንዴ ልጆች?
አዎ (በአንድ ዜማ)
*        *      *
… የደመናው ሀገር ልጆች፣ ወላጆቻቸውና አስተማሪዎቻቸው የሚነግሩዋቸውን በደንብ ይሰማሉ፡፡ የደመናው ሀገር ልጆች፤ መንግስታቸው ያዘጋጀላቸውን መፅሐፍት በደንብ ያጠናሉ፡፡ … ሰነፍ ተማሪን መንግስታቸው አይወድም፡፡ ሁሉንም ልጆቹንና ህዝቦቹን መንግስት ይወዳል፣ ሰነፍ ተማሪን ብቻ አይወድም … ስለዚህ በመንግስት መወደድ ሁሉም ልጅ ስለሚፈልግ ሰነፍ አይሆንም፡፡
እናንተስ ሰነፍ ተማሪ መሆን ትፈልጋላችሁ እንዴ ልጆችዬ?!
አንፈ…! (በአንድ ድምፅ)
…. በደመናው ሀገር ያሉ ወላጆች፤ የመንግስትን ግብር በደስታ ነው የሚከፍሉት፡፡ ለመክፈል ሲሽቀዳደሙ ሲያይ መንግስታቸውም በልጆቹ ይኮራል፡፡ በህዝቦቹ!
መንግስት መቼ ነው የሚኮራው ልጆችዬ?
ህዝቦቹ ግብር ሲከፍሉ (ግማሹ) … ሲሽቀዳደሙ (የተቀሩት)
አዎ ግብር ሲከፍሉ መንግስት ይደሰታል … በልጆቹ … በህዝቦቹ ይኮራል፡፡
በደመናው ሀገር መንግስት አባት ነው፡፡ አባት የህዝብ ወላጅ ነው፡፡ አባት አንድ ነው፡፡ … እናት አንድ ናት፡፡ የደመናው ሀገር ህዝቦችን መንግስት ይወዳቸዋል፡፡ መንግስት አባታቸው ነው፡፡ ሀገራቸው ደግሞ እናታቸው፡፡
የደመናው ሀገር ህዝቦች፤ መንግስት በምርጫ ልቀይር ይላሉ እንዴ ልጆች?
አይሉም! (በአንድ ዜማ)
ለምን እንቀይር አይሉም?
አባት አይቀየርም! (በአንድ ጩኸት)
እስቲ ድገሙት
አባት አይቀየርም!
አባት ምን አይደረግም!
አይቀየርም!
ምን አይደረግም?
አይቀየርም!!!
አባታችሁን መርጣችሁ ነው እንዴ እናንተ የተወለዳችሁት ልጆችዬ?
አልመረጥንም!!!
ለምን አልመረጣችሁም?
አባት አይመረጥም!!!!
መንግስትም እንደ አባት አይመረጥም እሺ፡፡ እንደ አባት ሳይመረጥ ይወደዳል!
….. የደመናው ሀገር ህዝቦች ውስጥ ምንም ችግር አልነበረም፡፡ ከመንግስታቸው ጋር በፍቅር ይኖሩ ነበር፡፡
እንዴት ይኖሩ ነበር?
በፍቅ-ቅ-! (በአንድ ድምፅ)
*        *      *
እና…ልጆችዬ፤ በፍቅር እየኖሩ ሳሉ አዳም ከገነት ተባሮ እየተንከባለለ ወጣ፤ ከሚስቱ ጋር፡፡ ሚስቱ ስሟ ሄዋን ነው፡፡… አዳምና ሄዋን በደመናው ሀገር ለመኖር ፈልገው መንግስቱ ፈቀደላቸው፡፡… ከዛም ሲኖሩ ሄዋን በየዕለቱ ልጅ እየወለደች አስቸገረች። አዳም ደግሞ ወሬ እንጂ ስራ አይወድም፡፡.. የደመናው ሀገር ህዝቦች ግን የሄዋንን ልጆች እንደ መንግስታቸው ልጆች አድርገው ለማሳደግ ፈቅደው ነበር፡፡ አዳምን እርሻ ያስተማሩት…እነማን ናቸው?
የደመናው ሀገር ህዝቦች (ደከም ባለ ዜማ)
.... እና እንዲህ ሲኖሩ ሲኖሩ… አዳም አንዱን የመንግስት ልጅ ከሌላው ጋር ማጋጨት ጀመረ። “መንግስታችሁ አባታችሁ አይደለም… የሰማይ አባታችሁ ነው እውነተኛ ፈጣሪያችሁ” እያለ ወሬ ማመላለስ ጀመረ፡፡… በተለይ አዳም ከሄዋን ጋር መኖር በጀመረበት መንደር ህዝቡ ስራ ፈታ፡፡፡ አዳም ከሄዋን ጋር የሚኖርበት መንደር ስሟ ጋዜጣ ይባላል፡፡
ማን ይባላል?
ጋዜጣ! (በዜማ ቅላፄ)
… በአዳም ወሬና ምክር የተሳሳቱት የጋዜጣ መንደር ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የጋዜጣ መንደር ነዋሪዎች ምን ተብለው ይጠራሉ ልጆቼ?
ጋዜጠኞች!!
ጋዜጠኞች በአዳም የተሳሳተ ምክር ሰክረው፣ ህዝቦቹን በሚወደው መንግስት ላይ በሀገሪቷ የማይታወቅ አመፅ መቀስቀስ ጀመሩ፡፡ ከራሳቸው መንደር አልፈው ወደ ሌላ መንደርና ግዛት በደመናው ሀገር ላይ እየተሽሎከሎኩ፣ ህዝብ ማሳሳትን ስራ አድርገው ያዙት፡፡
ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩት የምን ግዛት ነዋሪዎች ናቸው ልጆችዬ?
የጋዜጣ!!
ስማቸው ምን ተብሎ ይታወቃል?
ጋዜጠኞች!! (በህብረ ዝማሬ)
… እነዚህ ጋዜጠኞች ደጉን…ህዝቡን የሚወደውን መንግስት…በሌላ ለመቀየር ነበር እቅዳቸው፡ ልጆች መንግስት በሌላ ይቀየራል እንዴ?
አባት በሌላ አባት አይቀየርም ( በብስጩ ድምፅ)
መንግስት በምርጫ ይለወጣል እንዴ?
አይለወጥም!
ስለዚህ መንግስት ልጆቹ ሲያጠፉ ምን ያደርጋል ተባብለናል?
በአርጩሜ ይገርፋል (በለሆሳስ)
አርጩሜ ያማል እንዴ?!
እንደ ማር ይጣፍጣል (በዝግታ)
አዎ ልጆች … የአባት አርጩሜ እንደ ማር ይጣፍጣል!
… ከዛ በኋላ መንግስቱን የሚወደው ህዝብ ወደ አባቱ ጮኸ…እነዚህን መሰሪ ጋዜጠኞች አጥፉልን አለ፡፡ መንግስት ከመቀመጫው አርጩሜውን ይዞ ወረደ… በአርጩሜ ጥፋተኞቹን ቀጣ፡፡ ግን በተማሩት መጥፎ ስብከት ምክኒያት አርጩሜው ላይ ተዘባበቱበት፡፡ ከጋዜጠኛ መንደር የተነሳው ሰይጣን፤ አእምሯቸውን አበላሽቶታል፡፡…ይኼም አልበቃ ብሎ ጋዜጠኞቹ ግብር አንከፍልም አሉ፡፡… እንደዚህ ይባላል እንዴ ልጆች?
አይባልም (በጣም በጋዜጠኞቹ ትብብር ተናደዋል)
ምን መደረግ አለባቸው እነዚህ ጋዜጠኞች?
(ግማሹ) ከሀገር መባረር (ሌላው) መገደል (ሌላው) ሌላ- ሌላ
*        *      *
… ስለዚህ መንግስት ውሳኔ አደረገ፡፡ ከዚህ በፊት አድርጎ የማያውቀውን ከአዳምና ሄዋን ጋር የቆሙትን፣ የእፀ በለሱን ፍሬ ባይበሉም ከበሉት ጋር የዶለቱትን በሙሉ ወደ ምድር እንዲጣሉ አደረጋቸው፡፡… ስለዚህ ልጆች፤ የእናንተም ወላጆች የመጡት ከደመናው ሀገር መሆኑን በዛው አወቃችሁ። ወደ ጥንተ ቅድመ አያቶቻችሁ ሀገር እስቲ ስንቶቻችሁ በድጋሚ መመለስ ትፈልጋላችሁ?... እስቲ እጃችሁን እያወጣችሁ አሳዩኝ፡፡
እኔ- እኔ-እኔ (አንዱ በሌላው አናት ላይ እየቆመ፣ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማሳየት እየጣረ)
ወደ ደመናው ሀገር ተመልሳችሁ መንግስታችሁ የሚወዳችሁ ህዝቦች በድጋሚ መሆን ትፈልጋላችሁ?
አዎ …አዎ (ቅላፄው በእልህ ዜማውን አጥቷል)
ስለዚህ ወደ ቅድመ አያቶቻችሁ ሃገር ለመመለስ ምንድነው ማድረግ ያለባችሁ?
ትምህርታችንን በርትተን መማር!!
ሌላስ?
መንግስት የሚለንን መስማት
ሌላስ?!
የጋዜጠኛን ምክር አለመስማት!!!
ሌላስ?
ስራ ስንይዝ ግብር መክፈል!!!
ሌላስ?
መንግስት የሚወደን ህዝብ መሆን!!!!
ጎበዝ ልጆቼ… እንቦቃቅሎቼ…ለዛሬ ተረቱ በዚህ ያበቃል…ተረቴን መልሱ አፌን በዳቦ አብሱ…
ማስታወሻ
(“በየእለቱ ለተማሪዎቹ ከቁርስ በኋላ፣ ከምሳ በፊት እና ባንዲራ ሲወርድ ይሄ ተረት እንዲነበብ በትምህርት ባለስልጣን ተወስኗል” ይላል- ማስጠንቀቂያው፡፡ ልጆቹ በመደጋገም ለእያንዳንዱ ጥያቄ ምን መመለስ እንዳለባቸው ካወቁ ቆይተዋል- እንደ በቀቀን!)

Read 1590 times