Saturday, 18 November 2017 13:09

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

     ሰውየው ወንደ ላጤ ነው፡፡… በመጥፎ አጋጣሚ የተለያት የቀድሞ ባለቤቱ ውጭ አገር ትኖራለች፡፡ ተስፋ ቆርጣ እስካገባች ድረስ ያለችበትን እያወቀ ችላ ብሏታል፡፡… እሷ ግን ሁልጊዜ አብራው ነበረች። … ይህን ደግሞ እሱ ሊረዳ አልቻለም፡፡…
ከቤቱ ወደ ስራው ወይም ወደ ሌላ ቦታ ደርሶ ሲመለስና በሩን ከፍቶ ሲገባ፤ የደስ ደስ ባለው ስሜት ይሞላል፡፡ … እቤቱ ውስጥ በቆየ ቁጥር ምቾት ይሰማዋል፡፡ አልፎ አልፎ ግን የሳሎኑ መቀመጫ ከነበረበት ትንሽ ፈቀቅ ብሎ፣ ጠረጴዛው ላይ አስቀምጦት የነበረው ዕቃ ቦታውን ቀይሮ፣ የት እንደ ነበሩ የረሳቸው የሙዚቃ ሸክላዎች ፊት ለፊት ተደርድረው በቀስታ እየተጫወቱ ያገኛቸዋል፡፡… አንዳንዴ ከመገረም በስተቀር…ልብ አይላቸውም።… የመጨነቅና የመፍራት ስሜት አላደረበትም፡፡ ቤቱን ተዘዋውሮ ሲመለከት ሁሉም ነገር እንደነበረ ነው። የተሰበረ መስኮት ወይም በር አላየም፡፡… ሆኖም ትንሽ ትንሽ መጠርጠሩ አልቀረም፡፡…”ምናልባት በተመሳሳይ ቁልፍ እየከፈተ የሚገባ ሌባ ሊኖር ይችላል”… በማለት አስቦ ነበር፡፡… ወደ ህግ እንዳይሄድ ደግሞ የጠፋው ነገር የለም፡፡… ተደብቆና አድብቶ ለማየት ሞከረ፡፡… ምንም የለም፡፡
በዚህ ሀኔታ ብዙ ጊዜ አለፈ፡፡ አንድ ቀን ወደ ሥራው ለመሄድ ሲነሳ… “እኔ በሌለሁበት የምትመጣ አንተ ማነህ?”… የሚል ማስታወሻ ፅፎ አስቀምጦ ሄደ፡፡… ሲመለስ ሁሉም ነገር እንደ በፊቱ ነበር፡፡… ሸክላ ማጫወቻው የሚያጫውተውን ሙዚቃ የሰማው ድንገት ድምፅ በመጨመሩ ነው።… እንደ ሌላው ጊዜ “አውቶማቲክ ሪቨርስ ላይ ስለነበር ነው”… በማለት አስቦ፡፡… በአንድ በኩል ደግሞ ጥርጣሬውን በዘዴ ሊያጣራ ፈለገ፡፡… ቤት የሚለቅ ለማስመሰል ዕቃውን ሁሉ ሰብስቦ በካርቶንና በጆንያ ካጎረ በሁዋላ… “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ቤቱን ለቅቄ እሄዳለሁ”… የሚል ማስታወሻ ፅፎ ለአንድ ቀን የመስክ ስራ ከከተማው ራቅ ብሎ ሄደ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ሲመለስ ቤቱ ባልተለመደ ሁኔታ በከባድና በሚገፍተር አየር ታምቆ ጠበቀው፡፡… መንፈሱንም አስጨነቀው፡፡… ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ዙሪያውን ቃኘ፡፡… ግድግዳው ላይ የተሰቀሉት ስዕሎችና ፎቶግራፎች አዝነውና ተክዘው ወደ’ሱ ላለማየት አንገታቸውን ያቀረቀሩ መሰለው፡፡ ትናንት ጠረጴዛው ላይ የተወውን ማስታወሻ ሲመለከት…ከስሩ፤ “…ካንተ በፊት ቤቱን ለቅቄአለሁ”… የሚል ተፅፎበታል፡፡ ደነገጠ፡፡… ጨለማ መንፈሱ ውስጥ ሲመላለስ ታወቀው፡፡
ምን እንደሚያስብ ባይገባውም ለረዥም ጊዜ ሲያስብ ቆየና እንደ መባነን ሲል ስሜቱ ሁሉ “ሙዚቃ፣ ሙዚቃ”… የሚል መሰለው፡፡ … ለመጀመሪያ ጊዜ እራሱን አዳመጠ፡፡ ወዲያውኑ ዕቃዎቹ የታጎሩባቸውን ካርቱኖች እየከፈተ መበርበር ጀመረ፡፡… አንደኛው ውስጥ የሙዚቃ ሸክላዎች ታጭቀው አገኛቸው፡፡… ትላንትና ሲጫወት የነበረውን ሸክላ ዛሬ አስታወሰ፡፡… ለምን እሱን መስማት እንደፈለገ ግን አልገባውም።… ከብዙዎቹ ውስጥ ፈልጎ አገኘው፡፡…ሁለት ቦታ ተሰንጥቋል፡፡… እንባው ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ፡፡… ብቸኝነት ጥላውን እንዳጠላበት አወቀ፡፡
ድሮ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ በስም ስህተት “ሞቷል” ተብሎ የተነገራትና ወደ አውሮፓ የተሰደደችው የልጅነት ፍቅሩን ሊፈልጋት ባለመፍቀዱ አግብታና ልጆች አፍርታ እዛው ትኖራለች፡፡ ይኼ በጁ ይዞት የሚያለቅሰውን “ሙዚቃ” … ትወደውና ሁሌም ታዳምጠው ነበር፡፡
ወዳጄ፤ ሙዚቃ መልዕክት አለው፡፡ የሰውየው የድሮ ፍቅር ካለችበት ቦታ መንፈሷ እየመጣ ብቸኝነት እንዳይሰማው ለማድረግ በሙዚቃ በኩል እየደጋገመ ቢነግረውም ሰውየው መረዳት አልቻለም፡፡… እንዲያውም ሸክላውን ከነበረበት አንስቶ ከሌሎች ዕቃዎች ጋር በማጎሩና በጥንቃቄ ባለማስቀመጡ ተሰበረ፡፡… መንፈሱ ሸሸ፡፡… ቤቱን ለቆ ወጣ፡፡… ኦና አደረገው፡፡… ሰውየው የገባው አሁን ነው፡፡… አሁን ደግሞ መሽቷል፡፡… “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” እንዲሉ!!
ወዳጄ፤ ረቂቅ ሙዚቃ “MYSTIC POWER” አለው፡፡… አንዳንድ ሊቃውንት የሙዚቃን ሚስጢር “በትምህርትና በምክኒያታዊነት ከምንረዳበት መንገድ ይልቅ በተፈጥሮ የመገንዘብና የማስተዋል ስጦታ (intuitive) … ወይም በእንስሳ፣ በዕፀዋትና በህፃናት ላይ በሚስተዋለው ደመ ነፍሳዊ የስሜት ስልጣኔ የበለጠ ሊዋሃደን ይችላል”… ይላሉ፡፡
ሙዚቃ በረቀቀና በተረዳነው ልክ በቃላት የማይገለፁ ስዕሎችን (Images)…አእምሮአችን ውስጥ ይስላል፡፡… ውስጣችንን በሚገፈትረንና በሚያነሳሳን፣ በሚያሳዝነን በሚያንቦጫቡጨን፣ በሚያስደስተንና አቅል በሚያሳጣን፤ ወይም ራሳችንን ከራሳችን በሚሰርቀን ስሜት ይሞላናል፡፡
ሞዛርት የጠላቱን ክፋት በሙዚቃው በመሳል ተቀናቃኙ ሞቱን እያየ፣ አንገቱን ያነቃው እየመሰለው እንዲታገለው አድርጎታል፡፡… ቤት ሆቨንም የናፖሊዮንን “ክህደት” አእምሮው ውስጥ በሙዚቃው ስሎ ነበር፡፡…mystic power ያልኩህ ይኸን ነው፡፡
አንድ ነገር ልብ በልልኝ፡፡.. ረቂቅ ሙዚቃ በጅምላ ስለተደመጠ ሁሉም ላይ ተመሳሳይ ስሜት ይፈጥራል ማለት አይደለም፡፡ በጊዜያዊነት ግን የየግል ውስጣዊ ስሜታችንን አዘናግቶ የጋራ በሚመስል ሃሳብ ያማልለናል፡፡.. ለምሳሌ ልጁን ወይም እናቱን በቅርቡ ያጣ ሰው፤ ፍቅር የያዘው ሰው፤ መነኩሴ፤ የካንሰር ህመምተኛ፤ ለዘመቻ የተዘጋጀ ወታደርና የመሳሰሉት አንድ ላይ ኦቴሎን መድረክ ላይ ቢመለከቱ፣ አዳራሽ ውስጥ እስካሉ ድረስ በተመሳሳይ የስሜት ማዕበል ሊናጡ እንደሚችሉት ማለት ነው፡፡… ወይም እንደ እግር ኳስ ተመልካቾች!!
የዚህ ዓይነት ስሜት ቆይታው ለብዙዎቻችን አጭር፣ ቶሎ የሚረሳና በሌላ አጋጣሚ በሚፈጠር ሌላ ስሜት ወዲያውኑ ሊተካ የሚችል ነው፡፡.. ምክንያቱም የተረዳንበት መንገድ በያንዳንዳችን የማሰብ አቅም ልክ የሚሰፈር በመሆኑ ነው፡፡
አንድ ሺ “የተማሩና ያውቃሉ” የሚባሉ ሰዎችን አሰልፈን አንድን ረቂቅ ሙዚቃ ወይም ረቂቅ ቅብ (abstract painting)… ለየብቻቸው አሳይተን ወይም አሰምተን ምን እንደተገነዘቡ ብንጠይቃቸው፣ ፈፅሞ የማይመሳሰሉ አንድ ሺ ሃሳቦችን ይነግሩናል።… ለዚህ ነው ረቂቅ ጥበባት (the highest forms of art) የምንላቸው የጅምላ ስሜት ምንጭ ከመሆን ያለፉና የዕውቀትና የብስለት ግላዊ ጉዳይ የሚሆኑት!!
መብላት፣ መጠጣት፣ መስራት፣ መውለድ ማሳደግ፣ ቤተክርስቲያን መሳለም፣ መስጊድ መሄድ፣ ቤት መስራት ወይም እነዚህን በከፊል ወይም በሙሉ ማድረግ መቻል ወይም አለመቻል፣ በአጠቃላይ “መኖር” የምንለውን አባዜ፤ ፍፁም፣ ንፁህ፣ ውብና ቆንጆ ከሆኑት በዓይን ከማናያቸው፤ በእጆቻችን ከማንዳስሳቸው የማሰብ ፀጋዎች ጋር ስናወዳድራቸው ኢምንት ናቸው፡፡ ምክንያቱም ወደ እውነተኛ ደስታ (the true sense of happiness) የሚመሩን ነፃነት፣ ፍትህ፣ ማወቅና ተፈጥሮን የመረዳት አቅም የሚጎለብተው በነዚሁ ረቂቅ ጥበባት አእምሯችን ሲዳብርና አስተውሎቱን መተርጎም ሲችል ነው፡፡… አለበለዚያ “ህይወት” የምንለው ነገር ዝም ብሎ መኖር ወይም እንደ ቀንና ሌሊት የመምጣትና የመሄድ ድግግሞሽ እየሆነ ያታክታል፡፡…
“Life without good music is a mistake, a mere malady (…ህይወት ያለጥሩ ሙዚቃ በሽታ ነው፤ መኖር ደግሞ ስህተት”) ይለናል ሾፐን ሃወር!!
“…ትልቅ ጥበብ ለአእምሯችንም ለስሜታችንም መድህን ነው፡፡… ልክ እንደ ሲምፎኒ ሙዚቃ ቅንብሩና ጣዕሙ ብቻ ሳይሆን የሚማርከን፤ አወራረዱና አቋቋሙም ጭምር እንጂ፡፡… ወደ ፍፁማዊ ደስታ ከፍ የምንልበትም የዕውቀት መንገድ ይኸው ጥበብ ነው፡፡ …The noblest art appeals to the intellect as well as to the feelings… as symphony appeals to us not only by its harmonies and sequences but by its structure and development… and this intellectual pleasure is the highest form of joy to which a man can rise… የሚለን ደግሞ ኢማኑኤል ካንት ይመስለኛል፡፡
ወዳጄ፤ ወደኛ ጉዳይ ስንመጣ እውነተኛና አለም አቀፋዊ የጥበብ ስራ የምናይበት ጊዜ እየራቀን የመጣ ይመስለኛል፡፡… ቀደም ብለው ከተሰሩት ረቂቅ ሙዚቃዎች ውስጥ (የግርማ ይፍራሸዋ ዓይነቶቹ ባለሞገሶች እንዳሉ ሆነው)… የማሆይ ፅጌን (the homeless wonderer and others)፣ የፕሮፌሰር አሸናፊን (fantasy of nirvana and others)፤ ሙዚቃዎች ባዳመጥኩ ቁጥር… መጪው ያሳሰበኛል፡፡… ተስፋ ግን አልቆርጥም፡፡
ወደ ባለታሪካችን ስንመለስ እያየ አለማስተዋሉ፤ እየሰማ አለማዳመጡ… በዚህም የልጅነቱን ፍቅር መንፈስ፣ ሰላምና ምቾቱን ከሁሉም በላይ ደግሞ “ሙዚቃ” ራሷን ማጣቱ አያሳዝንም?
ሠላም!!

Read 2580 times