Sunday, 19 November 2017 00:00

የምንኩስና እምነትና የምንኩስና ባህል ልዩነት አላቸው!!

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “ለኢትዮጵያ ኋላ ቀርነት ተጠያቂው ላሊበላ?” በሚል ርዕስ አቶ ዓለሙ ኃይሌ አንድ ፅሁፍ አስነብበውናል። የፅሁፋቸው መነሻ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው መፅሐፌ ውስጥ በተነሱት ሐሳቦች ላይ የማይስማሙበትን ነጥብ ለመግለፅ ነው፡፡ የአቶ ዓለሙ ትችት ጠቅለል አድርገን ስናስቀምጠው፡-
ለኢትዮጵያ ሀገራችን ኋላ ቀር መሆን ምክንያቱ ላሊበላዊነት (የምንኩስናና የብሕትውና ኑሯችን) ነው ተብሎ በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው ነገር ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ኋላ ያስቀረን ላሊበላዊነታችን ሳይሆን ማብቂያ የሌለው የእርስበርስ ጦርነት ነው። ሁልጊዜ በአርስበርስ ጦርነት ውስጥ የተዘፈቅን ስለነበረ ሰላም አግኝተን ሰርቶ ለመሻሻል፣ ለመማርና ለመመራመር፣ ለመጠየቅና ለማብሰልሰል፣ ለፈጠራና  ለመፈላሰፍ  ዕድል  አልነበረንም፤
የሚል ነው፡፡
እኔም በዚህ ፅሁፍ ውስጥ አቶ ዓለሙ በደንብ ያልተረዱትን ነገር ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ አቶ ዓለሙ “ማብቂያ የሌለው የእርስበርስ ጦርነት ነው ለዚህ ኋላቀርነት ያበቃን” ያሉት ነገር ላይ እኔም ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምንና እስራኤላዊውን ፕ/ር ሀጋይ ኤርሊክን ጠቅሼ ፅፌያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ችግሩን በእርስበርስ ጦርነት ላይ ብቻ አመካኝተን የምናልፈው ነገር አይደለም፡፡ ማህበረሰባችን ወደ እንደዚህ ዓይነት የእርስበርስ ጦርነት እንዲገባ የሚያስገድደው ማህበረሰባዊ ግፊት ከየት መጣ? ወደሚለው ሌላ ጥያቄ የግድ መሻገር አለብን፡፡ ፕ/ር መስፍን ለዚህ ጥያቄ ሲመልሱ፤ “ሥልጣንን ከክብርና ከሐብት ጋር ያስተሳሰረ ማህበረሰብ በመፈጠሩ ነው” ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ይህ የፕ/ር መስፍን መልስ በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለምንድን ነው የእኛ ማህበረሰብ ሥልጣንን ከክብርና ከሐብት ጋር ያስተሳሰረው? ወደሚል ሌላ ጥያቄ ስለሚወስደን፡፡ እኔም ለዚህ ጥያቄ፤ “ሥራንና የእጅ ሙያተኛን የሚያጥላላው የምንኩስና ባህል ከተንሰራፋ በኋላ በሥራ በኩል የሚገኘውን ሐብትና ክብር ስለበጠሰብን ነው “ሥልጣን ወይም ሞት” የሚል ማህበረሰብ የፈጠርነው” የሚል መልስ በመፅሐፌ ውስጥ አስቀምጫለሁ፡፡
ሆኖም ግን አቶ ዓለሙ “የምንኩስና ባህል” ስል ምን ለማለት እንደፈለግሁ የተረዱኝ ስላልመሰለኝ ላሊበላዊነት፣ የምንኩስና ባህል እና ብሕትውና የሚሉትን ፅንሰ ሐሳቦች በመጀመሪያ ግልፅ ማድረግ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እምነትንና ባህልን መለየት ይገባናል፡፡ ባህል ከእምነት በጣም የሰፋና ሁሉን አካታች ነው። እምነት የሃይማኖት ተከታዮችን ብቻ ያማከለ አስተሳሰብ በመሆኑ ከዚያ ሃይማኖት ውጭ ያሉ ሰዎችን አያካትትም፡፡ ሆኖም ግን እምነት በረጅም የጊዜ ሂደት ውስጥ ባህል እየሆነ ሊሄድ ይችላል፤ ያን ጊዜ ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች ይሆናል፤ ያለ ሃይማኖት ልዩነት የአጠቃላይ ማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ገዥ ሐሳብ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የሻደይ በዓል መነሻው እምነት ቢሆንም አሁን ግን ባህል ሆኗል፡፡ ባህል ስለሆነም ሁሉም ልጃገረዶች ይሳተፉበታል፡፡ የመስቀል በዓልም በደቡብ እንደዚሁ ነው፡፡
ሥርዓተ ምንኩስና መነሻው እምነት ነው፤ ያውም “ለተመረጡ ጥቂቶች ብቻ” የሚፈቀድ እምነት፡፡ የምንኩስና እምነት መነሻ ሐሳቡ “የዚህ ዓለም ነገር (ቤተሰባዊና ማህበራዊ ህይወት፣ የግል ንብረት ማፍራት…ወዘተ) መንፈሳዊ ህይወታችንን ስለሚጎትትብን ልንተወው ይገባል” የሚል ነው፡፡ በአጭሩ ምንኩስና ማለት ከዚህ ዓለምና ከለበስነው ሥጋ ጋር መጣላት ነው፡፡
አንድ ሰው ከዚህ ዓለም ጋር ተጣልቶ “አይ እኔ የዚህ ዓለም ነገር በቅቶኛል፤ ከዚህ በኋላ ቀሪ ዕድሜዬን ከሰው ተነጥዬ በጥሞና የእግዚአብሔርን ነገር ብቻ እያሰብኩ መኖር ይሻለኛል” ቢል ችግር የለውም፡፡ ምንኩስና “ለተመረጡ ጥቂቶች ብቻ” የተፈቀደ ስለሆነ ማህበረሰቡን የማናጋት አቅሙ አነስተኛ ነው፡፡ የኔ ሙግት “ምንኩስናዊ አስተሳሰብ ማህበረሰባዊ ችግር መፍጠር የሚጀምረው ከእምነት አልፎ አጠቃላይ የማህበረሰቡ ባህል ሲሆን ነው፤ የክርስትያኑም የሙስሊሙም ገዥ ሐሳብ ሲሆን ነው፤ ህዝቡ ዓለምን፣ ተፈጥሮን፣ የሰውን ልጅና የዕለተለት ኑሮውን የሚመለከትበት የማያወልቀው መነፅር ሲሆን ነው” የሚል ነው፡፡ ላሊበላዊነት ያልኩትም ይሄንኑ ባህል እንጂ ስለ ንጉሱ ላሊበላ፣ አሊያም ስለ ላሊበላ ኪነ ህንፃ አይደለም፡፡ ኪነ ህንፃው ተምሳሌታዊ ነው፡፡
ስለዚህ እኔ ምንኩስና ላይ ያለኝ ዋነኛ ትችት እምነት በመሆኑ ሳይሆን ከእምነት ወጥቶ ባህል በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የምንኩስና ባህል ስል ህይወታችንን ለመለወጥና ለማሻሻል እንቅፋት የሆኑትን አስተሳሰቦች ነው፡፡ ለምሳሌ ዓለምንና ምድራዊ ህይወትን ማጥላላት፣ የለበሱትን ሥጋ ማንቋሸሽ፣ ሐብትንና ብልፅግናን መናቅ፣ ይህን ዓለም የኮንትራት ዓለም አድርጎ መመልከት፣ ነፍስንና ሥጋን ባላንጣዎች አድርጎ ማየት …የመሳሰሉትን፡፡ በመሆኑም፣ አቶ ዓለሙ የምንኩስናን እምነትና የምንኩስናን ባህል በደንብ እንዲለዩልኝ እፈልጋለሁ፡፡
በርግጥ የላሊበላ ኪነ ህንፃ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ እንቆቅልሹ ግን የእጅ ሙያን የሚያንኳስስ ማህበረሰብ ከተፈጠረ በኋላ የእጅ ባለሙያተኞቻችንንም አብረን አጥተናል፡፡ ይሄ ከሆነ ታዲያ የላሊበላን አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስትያናት እነማን ሰሩት? ይሄ ጥበብስ በሌሎች አካባቢዎችና በቀጣዩ ትውልድ ላይ እንዴት አሻራውን ሳያሳርፍ ጠፋ? ወደ ታች ወደ ህዝቡስ ወርዶ እንዴት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኑሮ ውስጥ አልተገለፀም? የሚሉት ጥያቄዎች እስከ አሁን ድረስ እንቆቅልሽ ናቸው፡፡ በርግጥ ሁሉም የታሪክ ምሁራን ባይስማሙበትም፣ ቅዱስ ላሊበላ የኪነ ህንፃ ባለሙያዎችን ከእየሩሳሌም አስመጥቶ ውቅር አብያተ ክርስትያናቱን እንዳሰራቸው የሚነገሩ ታሪኮች አሉ፡፡
ምንም እንኳ የኔ ትችት “በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ምንኩስና ባህል ሆኖ ቆይቷል” የሚል ቢሆንም፤ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ግን ራሱ የምንኩስና እምነትን ነው የሚተቹት፡፡ ዘርዓያዕቆብ ለዚህ ትችቱ ሦስት ምክንያቶችን ያቀርባል፡፡ የመጀመሪያው፣ አንድ ባለትዳር በእግዚአብሔር ተጠራሁ ብሎ ትዳሩን አፍርሶ ሲሄድ ሌላኛውን የትዳር አጋሩን ለዝሙት ተጋላጭ አድርጎ ነው የሚሄደው የሚል ነው፡፡ መፅሐፉ ደግሞ “የፈታችውን ያገባ አመነዘረ” ይላል፡፡ ስለዚህ ራሳችንን ለማፅደቅ እያሰብን፣ ለሌላ ሰው መሰናክል መሆን ግን አይገባንም፡፡
ሁለተኛ፣ አሁንም በእግዚአብሔር ተጠራሁ ብሎ ልጆችን በትኖ መሄድ ከሞራሊቲ አንፃር ትክክል አይደለም፡፡ እንሰሳት እንኳ ልጆቻቸው እስኪጠነክሩና ራሳቸውን ከጠላት መከላከል እስኪችሉ ድረስ አይተዋቸውም፡፡ ደግሞም መፅሐፉም ቢሆን “ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” ይላልና፡፡ “እኛስ ይሄንን ካደረግን ከእንሰሳት ያነስን መሆናችን አይደለም ወይ?” ይላል ዘርዓያዕቆብም፡፡ ሦስተኛው ደግሞ፣ “በእግዚአብሔር ተጠራሁ እያለ የሚመነኩሰው ወጣት፤ ደክመውና ለፍተው ያሳደጉትን ወላጆቹን በመጦሪያ ዘመናቸው ለማንም ትቷቸው መሄዱ፣ አሁንም ከሞራሊቲ አኳያ ትክክል አይደለም” የሚል ነው፣ የዘርዓያዕቆብ ትችት፡፡
ይሄ እንግዲህ ዘርዓያዕቆብ በ17ኛው ክ/ዘ ላይ በኖረበት ማህበረሰብ ውስጥ በጣም የተስፋፋ ችግር መሆኑን በማየቱ የፃፈው ነገር ነው፡፡ በመሆኑም በፈላስፎቻችን አመለካከት፣ ምንኩስና ከእምነት አልፎ ባህል ባይሆንም እንኳ ማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረው ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡
ነገርዬው ባህል ሲሆን ደግሞ ሀገራዊ ጉዳት ማምጣት ይጀምራል፡፡ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ይበልጥ ሊደነቁበት የሚገባው ነገር፣ ህብረተሰቡ ውስጥ የሰረፀውን ምንኩስናዊውን አስተሳሰብ ከተቹ በኋላ ሌላ አማራጭ የኑሮ ዘዬ ይዘው መምጣታቸው ነው፡፡ እነዚህ ፈላስፎች በ17ኛው ክ/ዘ ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከቱት ትልቅ አስተዋፅዖም ማህበረሰቡ ከወደቀበት ቁሳዊ ህይወት የሚያንሰራራበትን መንገድ ማሳየታቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው የእነዚህ ፈላስፎች አስተሳሰብ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ሳይሆን ሐገራዊ ፕሮጀክት ነው የምለው፡፡ የፕሮጀክታቸው ማጠንጠኛም መንፈሳዊና ዓለማዊ ህይወትን፣ ነፍስንና ሥጋን፣ አክሱማዊነትንና ላሊበላዊነትን የሚያስታርቅ አዲስ (ኦሪጅናል) ሐሳብ ነው፡፡ ትችታቸው አቶ ዓለሙ እንዳሰቡት፣ ላሊበላዊነትን (መንፈሳዊነትን) የሚያወግዝ ሳይሆን ላሊበላዊነት ብቻውን አይጠቅመንም፤ ከአክሱማዊነት ጋር እንቀይጠው የሚል ነው፡፡ላስፎችውውንንንም
ሌላው አቶ ዓለሙ በደንብ ያልተረዱት ነገር “ብሕትውና” የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የተጠቀምኩበትን መንገድ ነው፡፡ ብሕትውና ከእምነት አንፃር ለእግዚአብሔር ሲሉ በዋሻ አሊያም በበረሐ ወይም ደግሞ በዱር በገደሉ በብቸኝነት መኖር ነው። ምንኩስና ተቋማዊ በሆነው ሥርዓት ውስጥ የሚታቀፍ ሲሆን በመነኮሳት መካከል ብቻም ቢሆን ማህበራዊ ህይወት አለ፡፡ ብሕትውና ግን ከዚህ ሁሉ ነገር ተነጥሎ በብቸኝነት መኖር ነው፡፡ እኔ በመፅሐፌ ውስጥ ብሕትውና የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት እንደ ማህበረሰብ ከዓለማቀፍ ንግድና ባህል ተነጥለን፣ “በክርስቲያናዊ ደሴትነት” ዓለምን ረስተንና ዓለሙም እኛን ረስቶን የኖርንበትን ረጅም ዘመን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ማህበረሰባዊ የብሕትውና ጉዞ” የሚል ቃል በተደጋጋሚ የተጠቀምኩት፡፡ በተለይም በ451 ዓ.ም በተካሄደው የኬልቄዶን ጉባዔ፣ ካቶሊክና ኦርቶዶክስ እምነቶች መለያየትን ተከትሎ፣ የምዕራቡን ዓለም በከፍተኛ ጥርጣሬ መመልከትና ግንኙነታችንንም በእምነት ከሚመስሉን አሌክሳንደሪያና ሶሪያ ጋር ብቻ ወስነን ቆይተናል። ይሄ ደግሞ ብዙ የታሪክ ምሁራንም የፃፉት ነገር ነው፡፡ በ20ኛው ክ/ዘ ላይ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝና እጓለ ገ/ዮሐንስም እንደ ሀገር ለመቀጠል ካሰብን፣ ማህበረሰባዊ የብሕትውና ጉዟችንን ትተን የምዕራቡን ዓለም የሕሊና ትሩፋቶች መቀበል እንዳለብን ሲወተውቱ የነበሩት ከዚህ ሐቅ በመነሳት ነው፡፡
ሌላው መርሳት የሌለብን ነገር ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ካህናት ሳይሆኑ ፈላስፎች ናቸው። ፍልስፍና ደግሞ የባህሪ ህይወቱ ትችት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ፈላስፎች እንዴት እንደዚህ ደፍረው ይፅፋሉ ልንላቸው አንችልም፡፡ ፈላስፋም ለሀገር ቆረቆራል፤ ዓላማው ሀገርን ማፍረስ ሳይሆን በእውነትና በእውቀት አለት ላይ የተገነባ መቼም ቢሆን የማይናወጥ ማህበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የሚበረብሩት፣ የሚፈትሹትና የሚያበጥሩት በርካታ ልማዳዊ አስተሳሰቦች ይኖራሉ፡፡ በርግጥ ያኔ መናወጥ ሊመጣ ይችላል፡፡
አቶ ዓለሙ፣ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ምንኩስናና መነኮሳት ላይ በሰነዘሩት ትችት ተደናግጠዋል። ይህ ድንጋጤ የመጣው የምንበይንበት መሳሪያ የተለያየ ስለሆነ ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መበየኛው ሃይማኖታዊው አስተምህሮ ሲሆን፣ የፈላስፎቹ መበየኛ ደግሞ የተፈጥሮ ህግና ሥርዓት ነው። በመሆኑም ሃይማኖታዊ መበየኛ ይዘን የዘርዓያዕቆብንና የወልደ ሕይወትን አስተምህሮ መመዘን ሊያስደነግጠን ይችላል፡፡ ስለሆነም ዘርዓያዕቆብንና ወልደ ሕይወትን በደንብ ልንረዳቸውና ሀገራዊ ራዕያቸውንም ልናውቅላቸው የምንችለው፣ ትችታቸውን በራሳቸው መበየኛ ስንመዝነው ብቻ ነው። የእኛ ማህበረሰብ ትችትን አያውቅም፡፡ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብና ባልተቋረጠ ልማድ ስለኖረ፣ ትችት ሀገር የሚያፈርስ ይመስለዋል፡፡ ፖለቲካችን አሁን ድረስ ትችት የሚያስበረግገው ከዚህ ልማዳችን የተቀዳ በመሆኑ ነው።
በስተመጨረሻም፣ ዶ/ር ዳኛቸው፤ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት” የሚለውን ሐሳብ በሐምሌ 2002 ዓ.ም ላይ ይዘው ሲመጡ ምሁራኑ አካባቢ የመወያያ አጀንዳ መሆን ባለመቻሉ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ሐሳቡ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው መፅሐፍ ውስጥ ተካትቶ መታተሙ ግን ይሄው የመወያያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ሲባል ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት ላይ ብቻ አንቆምም፤ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት” የሚለው የዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብም የግድ አብሮ ይነሳል እንጂ፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊው “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 2260 times