Sunday, 19 November 2017 00:00

የእግር ኳሱ ነገር!?

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

“የምንጠይቀው ነገር አለን፡፡ ወጣቶቹ የታሉ? ከዘመኑ የእግር ኳስ ሁኔታ ጋር ቅርብ የሆኑ ወጣቶች የታሉ? እንዴ… አንዳንድ ጊዜ እኮ “እስቲ ኑና ሞክሩት” ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ወጣቶቹ መጥተው ቢሞክሩት ምናልባት ነገሮች ቶሎ ላይሳኩ ይችላሉ እንጂ እግር ኳሳችን አሁን ባለበት ደረጃ የሚያጣው ነገር አይኖርም፡፡ ከዚህ የባሰ የት ይሄዳል? ከዚህ የባሰ ምን ያህል ይወርዳል?---”
    
   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አንድ የምናውቀው የከተማ ሰው ነበር፡፡ በቃ…አለ አይደል…በጊዜው ‘ቅልጥ’ ያለ፣ “ቀላል አራዳ መሰለህ!” የሚባልለት አይነት… (የ‘አራድነት’ ትርጉም እንዲህ ‘እንደፈቺው’ ባልሆነበት ጊዜ ማለት ነው፡፡) ታዲያላችሁ…ሚስት ሲያገባ ስንት ዘመን አብሯቸው “አሼሼ ገዳሜ” ሲል የከረማቸውን የከተማ ሴቶች ትቶ ከገጠር አምጥቶ አገባ፡፡ በሚያውቁት አካባቢ ‘ሰበር ዜና’ በሉት፡፡ ሚስቱ ምንም አይነት የከተማ ንክኪ የሌላትና ከቀለሙም ገና ያልሞከረችው ነበረች፡፡
“ምን ታይቶህ ነው ከገጠር አምጥተህ ያገባኸው?” ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“የከተማዋን አግብቼ ከእሷ ጋር በየቀኑ ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ ስል ምን አከራከረኝ!” ለነገሩ ‘ውሀዋን’ ይወዳል… በፍቅር፡፡ ብዙ ጊዜ ቤቱ የሚገባው ከምሽቱ አራት  ሰዓት ካለፈ በኋላ ነው፡፡ እናማ… በዛ ሰዓት ፊቱን ከልክ በላይ አምበሬ ጭቃ የተለቀለቀ መስሎ ሲገባ አለ አይደል…
“ለምን ስትጠጣ እንዳመሸህና ስለ መጠጥ አስፈላጊነት ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ” ምናም የሚል ክርክር የለበትም፡፡ ይልቁንም ሾርባ ነገር፣ የሹሮ ፍትፍት ነገር ተዘጋጅቶለት፣ “ጌታዬ እግርህን ልጠብህ” ተብሎ ነው ወደ መኝታው የሚሄደው፡፡
ለነገሩ ወዳጃችን እንደዛ አለ እንጂ…የምር እኮ “ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ” የሚል ሰው ማግኘት የናፈቀን ነገር ነው፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ሁለቱም የሆኑ የራሳቸው የሆኑ፣ ሊከራከሩባቸው የሚችሏቸው  ሀሳቦች አሏቸው ማለት ነው፡፡ እሱ ነው እኮ የጠፋን! “የምከራከርበት ሀሳብ አለኝ” የሚል እኮ ነው የጠፋን! “አንተንም እሰማሃለሁ፣ እኔንም ስማኝ” የሚል እኮ ነው የጠፋን!
ስሙኝማ …እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የእግር ኳሱ ሰዎች ምን ነካቸው! አሀ… ነገሩን ሁሉ የዳኛ ፊሽካ በሌለበት የሚካሄድ የኳስ ‘እርግጫ’ ምናምን ነገር አስመሰሉትሳ! ይሄ ሁሉ እሰጥ አገባ ምን አመጣው! የሆነች አገር “የመንግሥቴን አመራር በሊዝ ስለምሰጥ ተወዳደሩ” ያለች ነገር እኮ ነው የሚመስለው! በአንዲት የፌዴሬሽን ወንበር — ያውም የግል ጥቅም የማይገኝበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሚባል — ይህን ያህል ከሆንን አይደለም ሀገር፣ ጥቅም የሚገኝበት አንድ አውራጃ የሚሰጠን ቢሆን ምን ልንሆን ነበር!
እናላችሁ …የሰሞኑን የኳስ ፌዴሬሽናችንን ‘በአይነቱ ልዩ የሆነ ገመድ ጉተታ’ ነገር ስንሰማ፣ ምን ስሜት ሊሰማን እንደሚገባ ግራ የገባን ብዙ ነን፡፡ ሀፍረት! ግን ለምን፣ ለማን ብለን ነው ሀፍረት የሚሰማን! (ጥሩነቱ እንደ በፊቱ “ዓለም ምን ይለናል!” የሚሉት አይነት ስጋት መተዋችን!” ታዲያ…ሰዎቹ ራሳቸው ያላፈሩት እኛ ምን አሳፈረን! እንዴ በየስፖርቱ ፕሮግራሞች በቃለ መጠይቅ ይሰጡ የነበሩ ‘ሀሳቦች’ አንዳንዶቹ እኮ የሚገርሙ ናቸው። የምር…ለእቁብ ጸሀፊነት የሚወዳደሩት ሰዎች እንኳን ትንሽ ሀሳብ አያጡም፡፡
እናማ…ይሄኔ ነው ወይ “ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ” የሚሉ ሰዎች የሚናፍቁን! ይሄኔ ነው እስከ መቼ ነው በኋላ ቀር የመናናቅና የመናቆር ቀሺም ባህሪይ፣ ስፖርታችን የእንፉቅቅ እንኳን እንዳይሄድ የሚደረገው የምንለው!
ስሙኝማ …የሆነ ቦታ ላይ ደግሞ “ፊፋ ምን አገባው!” አይነት ነገሮች ነበሩ አሉ! ቂ…ቂ...ቂ... ለማለት ይፈቀድልንማ! ሸላይ አገር እኮ ነች!
በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ህጎች አሉ አይደል እንዴ! ሥራዎች በስርአት የሚሠሩባቸው አንቀጽ፣ ንኡስ አንቀጽ፣ ቁጥር ምናምን በሚል ተከፋፍለው የተቀመጡ ህጎችና ደንቦች አሉ አይደል እንዴ! ወይስ እዚህ አገር “ማን አለኝ ከልካይ ያሻኝን ባደርግ…” ምናምን እንደሚባለው “እባክህ ህጉን እርሳው!” ነገር ነው! ታዲያ ‘ህግ ካለ’፣ ይሄን ሁሉ ንትርክ ምን አመጣው!
ፉከራ ምናምን የሚመስሉ ነገሮች ምን አመጣቸው! ፉከራ ከድሮ አብዮት ጥበቃዎች ጋር ቀርቶ የለም እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… በዚህ ጊዜ ነው “ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ” የሚሉ የአሸር በአሸር ወሬ ሳይሆን የታሰበባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ያላቸው ሰዎች የሚያስፈልጉን፡፡
መቼም እዚህ አገር እኮ የማንከፋበት ነገር፣ የማይደርስብን ነገር፣ የማንሰማው ነገር የለም።  በነገራችን ላይ…ጥያቄ አለን፣ የማንኛውም ስፖርት ፌዴሬሽን አመራር መሆን፣ ነጻ አገልግሎት የሚሰጥበት ማለት አይደለም እንዴ! ሰዎች እዛ የሚገቡት የግል ጥቅም ለማግኘት፣ የወንበር ጥማት ለማርካት ሳይሆን በስፖርቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት አይደለም እንዴ!
እናማ…እንዴት መሰላችሁ፣ “እግር ኳስን በየክልሎቹ ማስፋፋት፣ የትምህርት ቤቶች ውድድር ማስጀመር፣ የወረዳና የክፍለ ከተማ ቡድኖች ማቋቋም…” አይነት ነገር እኮ..አለ አይደል..እቅድ አይደለም፣ ወሬ ነው፣ ዲስኩር ነው፣ ጽሁፍ የማያስፈልገው መነባንብ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አባባሎች ምኞት ናቸው…አንድ ኳስ ለሀያ ሁለት ሰው ሰጥቶ ማራገጥን የስምንተኛው ሺህ ማሳያ ክፋት አድርገው የሚያዩት እናት እንኳን ሊሉት ይችላሉ፡፡ እቅድ አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ የምንፈልገው እያንዳንዷ ሰባራ ስንጥር ሳትቀር የተዘረዘረችበት፣ የድርጊት መርሀ ግብር ተብራርቶ የተቀመጠበት፣ የአተገባበሩ ዘዴና የጊዜ ምጣኔ ምናምን የተካተተበት እቅድ ነው፡፡ አሁን ኳስን ለመምራት “እኔ ብቻ፣ እኔ ብቻ” ከሚሉት ሰዎች መሀል እንዲህ በስርአት ወረቀት ላይ የሰፈረ እቅድ ያላቸው ስንቶቹ ናቸው! ነው…ወይስ “የእኛ ሀላፊነት መመረጥ እንጂ እቅድ ማውጣት አይደለም” ነገር ነው፡፡ (አንድ ጊዜ አንዱ ፖለቲከኛ “የእኛ ተግባር መቃወም ነው እንጂ፣ አማራጭ ማቅረብ አይደለም” እንዳሉት ማለት ነው፡፡)
የምር ግን ምን መሰላችሁ… ዘንድሮ ድፍረትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ “ደግሞ ቅሪላ የሚያሳድዱ ክለቦች ማስተዳደር ምን ያቅታል!” አይነት ድፍረት የሌለ ወንዝ ሊያሻግር ይችላላ፡፡
የእግር ኳስ አመራርን በተመለከተ “ወጣቶቼን ማን ወሰዳቸው?” ማለት ያለብን አሁን ነው፡፡
ለመሆኑ እግር ኳሱን አሁን የደረሰበት ደረጃ ያደረሰው ማነው?  
እንደ እውነቱ እግር ኳሱ ፈረንጅ እንዳለው፤ ‘ሀውስክሊኒንግ’ ያስፈልገዋል፡፡ ‘ኒው ብለድ’ እንደሚባለው ኳሱን በሚያውቁ፣ ፍሪ ኪክ’ ማለት የተገጣሚ ተጫዋችን በካልቾ መምታት የማይመስላቸው ቂ…ቂ…ቂ… አይነት ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡
የምንጠይቀው ነገር አለን፡፡ ወጣቶቹ የታሉ? ከዘመኑ የእግር ኳስ ሁኔታ ጋር ቅርብ የሆኑ፣ ወጣቶች የታሉ? እንዴ… አንዳንድ ጊዜ እኮ “እስቲ ኑና ሞክሩት” ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ ወጣቶቹ መጥተው ቢሞክሩት ምናልባት ነገሮች ቶሎ ላይሳኩ ይችላሉ እንጂ እግር ኳሳችን አሁን ባለበት ደረጃ የሚያጣው ነገር አይኖርም፡፡ ከዚህ የባሰ የት ይሄዳል?  ከዚህ የባሰ ምን ያህል ይወርዳል?
እናማ… ቢቻል እስካሁን እዛ አመራር ውስጥ ያልተነካኩ ሰዎች ቢኖሩ አሪፍ ነው፡፡ አንደኛ ነገር የቆዩ ቁርሾዎች አይኖሩም፤ ሰሞኑን በተዘዋዋሪ አይነት የሰማናቸው የመናናቅ አይነት ነገሮች አይኖሩም፡፡
እናማ የእግር ኳስ አመራርን በተመለከተ “ወጣቶቼን ማን ወሰዳቸው?” መባል አለበት፡፡
ወጣቶቹን በማሳተፍ ቢያንስ ጠንካራ መሰረት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አሁን እያጣን ያለነው የሚቀመጥ መሰረት ነው፡፡ ደግሞ መሰረት መጣል የሚቻለው ለወጣቶቹም እድል ሲሰጥ ነው፡፡ የዛሬን የነገን ብቻ ሳይሆን የከነገ ወዲያንም ማሰብ የምንችለው፣ ለወጣቶቹም በአመራር የመሳተፍ እድል ሲሰጥ ነው፡፡ በዚች ያን ውድድር ለመሳተፍ፣ በዚያ የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ብቻ ሳይሆን ለዛሬ አምስትና አስር ዓመት እየታሰበ መሰራት አለበት፡፡ (የስፖርት ጋዜጠኞች ሥራ ላይ በቆረጣ ገባሁ እንዴ!)
ሆሊውድ የሆነ ነገር ነው፡፡ የ‘ካውቦይ’ ፊልሞች የሚተውነው ተዋናይ ብዙ ዓመታት ሠርቷል፡፡ ግን፣ አለ ከመባልና ከተሳትፎ ባለፈ እዚህ ግባ የሚባል ስሙን የሚያስጠራ የትወና ክህሎት አላሳየም፡፡ እና አንድ ጊዜ አንደኛውን ዳይሬክተር የሆነ ፊልም ላይ እንዲያሳትፈው ይጠይቀዋል፡፡ ጊዜው ደግሞ የጸሀይ መጥለቂያ ነበር፡፡ ዳይሬክተሩም እንዲህ ይለዋል…
“እኔ የምመከርህ፣ ፈረስህ ላይ ውጣና ወደዛች ወደምትጠልቀው ጸሀይ ጋልብ፡፡ ደግሞም ዘወር ብለህ አትይ!” እንዴት አይነት የተባረከች ምክር ነች!
እናማ የእግር ኳስ አመራርን በተመለከተ “ወጣቶቼን ማን ወሰዳቸው?” መባል አለበት፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3303 times