Sunday, 19 November 2017 00:00

አዲስ የፌደራሊዝም ችግኝ ማጽደቅ ያሻል!

Written by  በድሉ ዋቅጅራ
Rate this item
(5 votes)

• ልዩነትን ሲኮተኩት የኖረ ፌደራሊዝም፣ አንድነትንና ፍቅርን ሊያፈራ ያዳግተዋል
             • የኮመጠጠውን የፖለቲካውን ዛፍ መግረዝ ወይም ነቅሎ መጣል ይገባል
              
   የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ጉዞውን የጀመረው ከ80 በላይ ብሄረሰቦችን በ9 ክልል ከልሎ ነው። እዚህ ላይ ‹‹ክልል›› የሚለው ቃል በራሱ ችግር አለው፡፡ (የከሳቴ ብርሀን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፣ ‹‹ከለለ›› የሚለውን ቃል፣‹‹ወሰንን፣ ድንበርን ለየ፤ አጥርን አጠረ፤ ጋረደ፤›› በማለት ይፈታዋል፡፡) ቃሉ በአንድነት ውስጥ ያለ ልዩነትን ሳይሆን፣ ርስትን ተከፋፍሎ፣ ለይቶ ማጠርን የሚያመለክት ነው። ይህንን ክልላዊ ፌደራሊዝም ይበልጥ አስቸጋሪ ያደረገው ደግሞ በቋንቋ ላይ መመስረቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውስጧ ያቀፈቻቸውን ጎሳዎች መዛነቅ ከግምት በማስገባት፣ የፌደራል ስርአቱን ከቋንቋና ከብሄር ብሄረሰብ ጽንሰ ሀሳብ በተሻለ መሰረት ላይ መገንባት ይቻል ነበር፡፡ እንደ ኦሮምያና አማራ የመሳሰሉትን ሰፋፊ ክልሎችን (በቆዳና በህዝብ ቁጥር) ብቻ እንኳ ብንወስድ፣ በውስጣቸው የሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችን ይዘዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች ገና ከጅምሩ ያለ ክልላቸው የሚኖሩ ‹‹መጤዎች›› ተደርገው እንዲቆጠሩ የፌደራሊዝም አከላለሉ መሰረት ጥሏል፡፡
በርግጥ በጎሳ ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም ስርአት ለመከተል ኢትዮጵያ የመጀመሪያ አይደለችም። በጎሳ ፌደራሊዝም ብልጽግናን እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን የተቀዳጁ ሀገሮች አሉ፡፡ እንደ ናይጄሪያና ዩጎዝላቪያ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ለአመታት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ ተማግደው ተጨራርሰውበታል፡፡ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ ስር የነበረችው ናይጄሪያ፤ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ነጻነቷን ስትቀናጅ የተከተለችው ጎሳዊ ፌደራሊዝምን ነበር፡፡  በአንድ በኩል የእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ በሚከተለው የነጣጥለህ ግዛ ፖሊሲ የተነሳ የህዝቡ የአንድነት ስሜት እጅግ ላልቶ ስለነበር፤ በሌላ በኩል ምዕራባውያን ሚሲዮኖች ክርስትናን በማስፋፋት ሰበብ በደቡቡ ክፍል ትምህርትን በማስፋፋታቸው የተነሳ፣ በተለይ በትልልቆቹ የደቡብ (ኢቦ) እና የሰሜን (ሀውሳ) ጎሳዎች መካከል ትልቅ ፉክክርና መቀናናት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሚሲዮኖች የተነሳ የትምህርት ዕድል አግኝተው የነበሩት ኢቦዎች ያገኙት በየመስሪያ ቤቱ የመቀጠር እድል ሀውሳዎችን ያስቆጣቸው ነበር፡፡ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ 250 ግድም የሚጠጋ ጎሳ ያቀፈችው ናይጄሪያ፣ ታላቅ ቀውስ ውስጥ ተዘፈቀች። በመጨረሻ በ1967 የኢቦ ጎሳዎች ያቀረቡት የመገንጠል ጥያቄ ናይጄሪያን የከፋ ጦርነት ውስጥ ከቷታል፡፡ በ1970 ጦርነቱ በኢቦዎች ሽንፈት ሲደመደም፣ ሀገሪቱ በጎሳ ላይ የተመሰረተውን ፌደራሊዝም ‹‹አይንህን ላፈር›› ብላ አሸቀንጥራ ብትጥለውም፣ አንጎበሩ ግን ለተደጋጋሚ የስልጣን ሽኩቻና መፈንቅለ መንግስት ዳርጓታል፡፡
ናይጄሪያ በጎሳ ፌደራሊዝም የተነሳ የታመሰችው፣ ኢትዮጵያም የሚታየው ችግር ውስጥ የገባቸው የጎሳ ፌደራሊዝም የቀውስ መንገድ በመሆኑ አይደለም፤ ከላይ እንደጠቀስኩት በዚህ አስተዳደራዊ ስርአት በልጽገው በሰላም የሚኖሩ ሀገሮች አሉ፡፡ ‹‹የጎሳ ፌደራሊዝም አይሰራም፣ ወይም ይሰራል›› ለማለት የአስተዳደር ስርአቱን በትክክል ተግብሮ ማየት ያሻል። ‹‹በናይጄሪያና በኢትዮጵያ አልሰራም›› ከሚለው መደምደሚያ፣ ‹‹በትክክል ተተግብሯል ወይ?›› የሚለው ጥያቄ ይቀድማል፡፡
ሁለቱ ሀገሮች የጎሳ ፌደራሊዝምን ለመከተል ሲወስኑ የነበሩበት ሁኔታ በተለያየ ጽንፍ ሊቀመጥ የሚችል ነበር፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ናይጄሪያ የጎሳ ፌደራሊዝምን የተቀበለችው፣ በእንግሊዝ የቅኝ አገዛዝ የተነሳ በጎሳ ተከፋፍላ ነው፡፡ ሀገሪቱ በነጻነት ማግስት የተከተለችው የጎሳ ፌደራሊዝም የተከፋፈለችውን ሀገር፣ በልዩነት ውስጥ አንድ አድርጎ ማስቀጠል አልቻለም፡፡ ይልቁንም ሀገሪቱ በጎሳ ጦርነት ለመታመስ የወሰደባት ስድስት አመት ብቻ ነው፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጵያ የጎሳ ፌደራሊዝም አስተዳደራዊ አወቃቀርን ስትቀበል እንደ ናይጄሪያ በጎሳ የተከፋፈለች ሀገር አልነበረችም፡፡ ምንም እንኳን በሀገሪቱ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩል መብትና ነጻነት የነበራቸው ባይሆኑም፣ በንጉሱም ይሁን በደርግ አስተዳደር ጠንካራ ብሄራዊ ስሜትና የአንድነት መንፈስ ነበር፡፡ በርግጥ ይህ ብሄራዊ አንድነት ከፍቅር ይልቅ ሀይልን፣ ከመብት ይልቅ ግዴታን ያስቀደመ ጨካኝና ጨቋኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግ ፌደራሊዝምን ሲቀበል ዋና ግቡ ይህን ግዴታን ያስቀደመ ጨካኝና ጨቋኝ ብሄራዊ የአንድነት ስሜት፣ የዜጎችን መብት ባረጋገጠ  - ፍቅርንና መተሳሰብን መሰረት ባደረገ፣ ብሄራዊ የአንድነት ስሜት ለመተካት ወጥኖ ነው፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ የተጨቆነ ካለ ጨቋኝ አለ፤ የተበደለ ካለ በዳይ አለ፡፡ በዳይና ተበዳይ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ በጉልበት - በሀይል ካልሆነ በስተቀር በፍቅርና በመፈቃቀድ ሊተቃቀፉ አይችሉም። በመሆኑም የእያንዳንዱን ዜጋ (በጎሳ ቅንብብ ውስጥም ቢሆን) መብት ማስከበር የፌደራሊዝሙ መሰረት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሲሆን ነው የቀደመው ብሄራዊ አንድነት የተቸነከረበትን ሚስማር በፍቅር እቅፍ የሚተካው።  እዚህ ላይ የኢህአዴግ ፊደራሊዝም ዋናው ግብ ብሄራዊ አንድነቱ የተቀበቀበበትን ሚስማር ነቅሎ፣ በምትኩ በፍቅር በተዘረጉ ክንዶች እቅፍ ማጽናት እንጂ፣ ሚስማሩን ነቅሎ በሚስማሩ በግዴታ የተያያዙትን አካላት እንዲበተኑ መፍቀድ አይመስለኝም፡፡ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ስመለከት ግን ከዚህ የሰመረ አይደለም።
የፌደራል ስርአቱ ለ26 አመታት ተተግብሮ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመፈላለግ የተቃቀፈ፣ በልዩነት ያጌጠ ሀገርን አላመጣም፡፡ ኢህአዴግ አንድነታችን በጉልበት የተቸነከረበትን ሚስማር ነቀለው እንጂ፣ በፍቅር እቅፍ አልተካውም፡፡ ከመሰረቱ የተዛባውን ፌደራሊዝም፤ ችግሮቹን በሂደት እያረመ፣ የጎበጠውን እያረቀ በልዩነቷ ህብረት ያጌጠች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት አላስቻለም፡፡ ይልቁንም ልዩነትን እያጠነከረ፣ የተከፋፈለች ደካማ ሀገርን የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ሁለት ማሳያዎች ላስጨብጥ፡፡
አንድ፤ ክልሎች እራስን በራስ የማስተዳደርና ሌሎች መብቶቻቸው በህግ የተደነገገላቸው የአንድ ሉአላዊ ሀገር ክፍሎች ወይም አካላት ሳይሆኑ፣ እራሳቸውን ሉአላዊ አድርገው መቁጠርን አደርጅተዋል፡፡ በመሆኑም በክልሎች ወሰንና በመሬት ይገባኛል ውዝግብና ግጭት የዜጎች ህይወት ይጠፋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ይፈናቀላሉ፡፡ ዘርማንዘሮቻቸው ቀድመው ከሰፈሩባቸው ክልሎች ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን እንደ ‹‹መጤ - የሌላ ሀገር ዜጋ›› እድርጎ የማየት አዝማሚያ ከማቆጥቆጥ አልፎ ለማበብ እንቡጥ እየጣለ ነው፡፡ አንዱ ክልል ሌላውን ‹‹የዘር ማጥፋት›› አውጆብኛል ብሎ በይፋ ይከሳል፡፡ ይህ ልዩነትን ሲኮተኩት የኖረው ፌደራሊዝም ፍሬ ነው፡፡ የክልልም ሆነ የፌደራል መንግስታት፣ የዜጎችን ደህንነት ዋስትና መስጠት ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ ዜጎችን ተቀብሎ በሚያቋቁምበትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከሱማሊያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎቹን ተቀብሎ በሚያቋቁምበት አሰራር መካከል እምብዛም ልዩነት ያለ አይመስለኝም፤ ይመጣሉ፤ ጊዜያዊ መጠለያ ይገባሉ፤ መልሶ ለማቋቋም እርዳታ ይሰበሰባል፡፡
ሁለት፤ የክልሎች እራሳቸውን የአንድ ሉአላዊ ሀገር አካል አድርጎ ያለማሰብ፣ በሌላ አገላለጽ ሌሎች ክልሎችን የራስ አድርጎ ተቆርቋሪነትን ያለማሳየት የፌደራል መንግስቱን ብሄራዊና አለማቀፋዊ አቅም እጅጉን የቀነሰው ይመስለኛል፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግስት ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው በጋንቤላ በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ ያደረሱትን ጥቃት የኢህአዴግ መንግስት የፈታበት መንገድ ሉአላዊ ክብራችንን ያስጠበቀ አይመስለኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ደቡብ ሱዳንን እንደ ሀገር ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ፣ ታጣቂዎቹን እንደ ቡድን ተጠያቂ አድርጎ እርምጃ መውሰዱ ለጥቃቱ ተገቢ ምላሽ አይመስለኝም፡፡ (በርግጥ የተወሰዱትን ህጻናት ለማስመለስ አስችሏል፤ ይህ ባይሆን ምንአልባት የህጻናቱ ደብዛ ሊጠፋ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆን ነበር፡፡) ኢህአዴግ እንደ አንድ ሉአላዊ መንግስት፣ ለተዘረፉት ከብቶች፣ ለተገደሉት ዜጎችና ያለወላጅ ለቀሩት ህጻናት፣ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ካሳ መጠየቅ ነበረበት፡፡ ይህን በተመለከተ መንግስት በይፋ ለህዝብ የገለጸው ነገር ካለ አልሰማሁም፤ ኖሮ ያልሰማሁ ከሆነ እንደ ስህተት ይቆጠር፡፡ ሀገሮች በሌላ ሀገር የሚቃጠባቸውን ጥቃት የሚፈቱበት መንገድ፣ ለሀገራዊ ሉአላዊነታቸው ያላቸው አመለካከት ነጸብራቅ ነው። ለጥቃት ካሳ መጠየቅ የሚያሳየው ድህነትን ሳይሆን፣ ሀገራዊ ክብርንና ኩራትን ነው። አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1988  በሎከርቢ ሰማይ ላይ ለፈነዳውና የ270 ዜጎቿን ህይወት ለቀጠፈው ፓን. አሜ. 103 አይሮፕላን፣ ሊቢያን ተጠያቂ አድርጋ፣ ከአመታት ማእቀብ በኋላ 2.7 ቢልየን ዶላር ካሳ ተቀብላለች፡፡ ለእያንዳንዱ ሟችም 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ተከፍሏል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ህጻናቱን በቤተ መንግስት ሰብስቦ የገቢ ማሰባሰቢያ ከማዘጋጀት ባለፈ፣ ህጻናቱን ለዚህ ያበቃውን የደቡብ ሱዳን ጥቃት በሉአላዊነታችን ላይ እንደተቃጣ ጥቃት አልተመለከተውም፡፡ ይህ ሲታይ የኢህአዴግ መንግስት ክልሎችን በፌደራሊዝም ጥላ አስተቃቅፎ,፣ ጠንካራ ብሄራዊ አንድነትን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን የታፈረችና የተከበረች ሉአላዊ ሀገር ማድረግ እንደተሳነው መገመት አያዳግትም፡፡
ይህ አሁን በሀገሪቱ የሚታየው ችግር፣ ማለትም የአንድ ክልል ነዋሪዎች በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ ለመኖር፣ ለመዘዋወርና ለመማር የሚገጥማቸው ችግር በጊዜ ካልተፈታ ሀገሪቱን ወደ ከፋ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ሊከታት ይችላል። አሁን በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ከነበሩ ችግሮች የሚለየው ዋና ጉዳይ የየክልሉ አመራሮች፣ የህዝብን ችግር ከህዝብ ጋር ሆነው ለመፍታት መነሳታቸውን በግልጽ ለመናገር መድፈራቸውና በተግባር ለማሳየት መሞከራቸው ነው (ጥቂት ቢሆኑም)፡፡ ይህ ሁኔታ ለሰላማዊ ሰልፎች የሚከፈለው የህይወትና የደም ግብር በእጅጉ እንዲቀንስ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ከአመት በፊት እንኳን የነበረውን ሁኔታ ብናጤን ልዩነቱ በግልጥ ይታያል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ወቅት የክልላዊ መስተዳድሮች ለ26 አመታት ለመጥራት ሲጸየፉት የነበረውን ‹‹ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት›› መስበክ የጀመሩበት ነው፡፡ ይህ ‹‹እሰየው›› እንጂ፣ ‹‹ለምን ሆነ›› አያስብልም፡፡ በ26 አመት መንቃት፣ በ27 አመት ከመንቃት ወይም ጭራሽ ካለመንቃት የተሻለ ነው፡፡
በተለይ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ ሲናገሩት የሚሰማው፤ ‹‹የአንድ ኢትዮጵያ›› ጥሪ በሌሎች ክልሎች ነዋሪዎችም ሳይቀር እንደ ጥቅስ እየተወሰደ ነው፡፡ ይህ የሆነው የተናገሩት ተአምር ሆና አይደለም፤ አንድም ህዝቡ ከእነሱ ያልጠበቀው ቅድስና፣ አንድም የሀገሪቱ ህዝቦች የልብ መሻት በመሆኑ ይመስለኛል፡፡
በብዙ ሀገሮች ለብሄር ብሄረሰቦች እኩል መብትን ለማጎናጸፍና በመካከላቸው የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማክሰም፣ ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ ጎሳንና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም፣ ከተጠበቀው በተቃራኒ፣ በጎሳዎች መካከል ግጭት የማስነሳቱ እድል ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በበርካታ ሀገሮች ታይቷል። ይህ የሚሆነው ግጭት የጎሳ ፌደራሊዝም ተፈጥሯዊ ባህርይ ሆኖ አይደለም፡፡ በአብዛኞቹ የአለም ሀገራት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች እንደሚኖሩበት አካባቢ (ከተማ ወይ ገጠር)፣ የተፈጥሮ ሀብት (በተፈጥሮ ሀብት መበልጸግና መደህየት)፣ የዝመና ደረጃ (መማር ያለመማር)፣ ከፖለቲካዊ ስልጣን ባላቸው ርቀት ... ወዘተ. መመዘኛዎች ሲታዩ ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ የአማራን፣ የኦሮሞን፣ የጋምቤላንና የአፋርን ብሄረሰቦች መስደን ከነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ብንገመግም የጉዳዩን እውነትነት ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ይህ ዋናው የጎሳ ፌደራሊዝም የግጭት ምንጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፊደራል ስርአቱ እነዚህን አይቀሬ የሚመስሉ ግጭቶች ሊቀንስ፣ ብሎም ከነጭራሹ ሊያስወግድ ይችላል፡፡ Horowitz D. የተባለ ጸኀፊ በ1985 እ.ኤ.አ. Ethnic groups in conflict በተባለ መጽሀፉ ውስጥ፣ በጎሳ ፌደራሊዝም የአስተዳደር ስርአት በጎሳዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶችን ለመቀነስ የሚረዱ ብሎ አምስት ነጥቦችን ይዘረዝራል፡፡
ዛሬ ሀገራችን ከሩብ ምእተአመት የፌደራሊዝም ትግበራ በኋላ ግጭቶች በመቀነስ ፋንታ እየበረከቱ የመጡት ጸሀፊው የጠቀሳቸው ነጥቦች ባለመተግበራቸው ይመስለኛል፡፡ እስቲ ከአምስቱ ነጥቦች መካከል ሁለቱን ብቻ (በቦታ ጥበት የተነሳ) ጠቅሰን እንገምግም። Horowitz ከጠቀሳቸው ነጥቦች አንዱ፣ በብሄር ብሄረሰቦች (ክልሎች) መካከል ለሚደረግ ትብብር ማበረታቻ የሚሰጡ (የሚያበረታቱ) ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ (promoting policies that create incentives for inter- ethnic cooperation) የሚል ነው፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር የሀገራችንን ፌደራላዊ አስተዳደር ስንገመግም የምናገኘው ውጤት አመርቂ አይደለም፡፡ አብዛኛዎቹ ክልሎች ስራ ለመቅጠር ቋንቋቸውን ያስቀድማሉ፡፡ የብዙሀን መገናኛዎቻቸው አብዛኞቹ ፕሮግራሞች ክልል አይሻገሩም፤ የትምህርት ስርአቱ መናበብ ይጎድለዋል፡፡ የፌደራል ብዙሀን መገናኛዎችም፣ ‹‹በዚህ ክልል እንዲህ ተሰራ፤ እንዲህ ተኖረ›› በሚል የተከታተፉ ዜናዎችና ፕሮግራሞች የተሞሉ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ነው፣ ሰሞኑን በአማራና በኦሮሞ ክልሎች መካከል የተደረገው የሰላም ፍለጋ ምክክር፣ እንደ ባድሜና ጾረና ድል ያስፈነጠዙት፡፡
በጎሳ ፌደራሊዝም አስተዳደር ስርአት ግጭትን ለመቀነስ ከሚያግዙ ነጥቦች መካከል ሁለተኛው በፌደራሊዝም ስርአቱ ውስጥ ከጎሳዊ ፍላጎት የተለዩ ማህበረሰባዊ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን መንደፍ (promoting policies that encourage alignment based on interests other than ethnicity) ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የሀገራችንን ፌደራሊዝም ስንገመግም አሁንም ከግምት የሚገባ አዎንታዊ ምላሽ አናገኝም፡፡ የፌደራሊዝሙ ፖሊሲዎች በአብዛኛው ጎሳዊ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ ናቸው። በዚህም የተነሳ ፉክክርንና ውድድርን አምጥተዋል። ለምሳሌ ያህል እንኳን የዩኒቨርሲቲዎችን ስርጭት ብንመለከት አብዛኞቹ በማዳረስ አይነት በየቦታው የተበተኑ ናቸው፡፡ በሚገባ የተደራጁ ቤተ-ሙከራዎችና ቤተ-መጻኅፍት የተሟሉላቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሌሏቸው አካባቢዎች፣ ዩኒቨርሲቲ ቆሞላቸዋል። በዚህም የተነሳ ‹‹የዚህ አካባቢ ነዋሪዎች . . . የዚህ አካባቢ ብሄርብሄረሰቦች በአካባቢያቸው ዩኒቨርሲቲ እንዲገነባላቸው ጠየቁ፡፡›› የሚል ዜና መስማት ብርቅ ያልሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ተቋማትን መገንባት ሀገራዊ የልማት እቅድን መተግበር ሳይሆን፣ አካባቢያዊ ጥያቄን መመለስ እየሆነ ነው፡፡ ሁለቱን አቀናጅቶ እንዲያሳካ የተቀረጸ የልማት ፖሊሲ የለንም፡፡
በአጠቃላይ ሀገሪቱ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ ላይ የደረሰችው ጎሳና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም በመከተሏ ብቻ ሳይሆን፣ ስርአቱን ግጭቶችን ሊያስቀር እንኳን ባይችል ሊቀንስ በሚችል ጥንቃቄና እውቀት ላይ የተመሰረተ መንገድ ባለመተግበሯ ነው፡፡ አሁን ኢህአዴግ ሀገሪቱን የገጠማት ችግር ከዚህ ፖለቲካዊ አስተዳደር፣ ምርጫና ትግበራ የመነጨ መሆኑን መቀበል ያሻዋል፡፡
ፖለቲካዊ ችግር ደግሞ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያሻዋል። በመሆኑም አሁን እንደሚታየው የየክልል አመራሮች እየተቧደኑና እየተመራረጡ በሚያደርጉት መመካከርና እርቀ - ሰላም፣ ሀገራዊ እርቅና ሰላም ሊወርድ አይችልም፡፡ በርግጥ ጊዜያዊ ግጭቶች በማብረድ በከንቱ የሚጠፋ ህይወትንና የሚጎድል አካልን ሊያስቆሙ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ዘላቂና ሀገራዊ ሰላምና እርቅ ሊያመጡ ግን አይችሉም፡፡ ብሄራዊ እርቅ አውርዶ ሀገራዊ ሰላም ለማምጣት የሚቻለው ስር ነቀል ፖለቲካዊ እርምጃ ከተወሰደ ብቻ ነወ፡፡ ለሀያ ስድስት አመታት ኮትኩተን ያሳደግነው ጎሳዊ ፌደራሊዝም፣ ያንዠረገገውን እንቡጥ እያየን ነው - ጥላቻና ግጭት፡፡ ይህ እንቡጥ ከማበብም አልፎ ፍሬ እየጣለ ነው፡፡ በወጉ አፍርቶ ዘሩን እየበተነ እንዲራባ መፍቀድ የለብንም፡፡ ገበሬ የጓሮው ብርቱካን መኮምጠጥ ሲጀምር አንድ ሁለቴ ይገርዘዋል፤ ካልሆነም ነቅሎ ይጥለዋል፡፡
ብልህ ገበሬ የኮመጠጠው ብርቱካን ማሳው ላይ አርጅቶ እስኪወድቅ አይጠብቅም፡፡ የፖለቲካችን ገበሬ ደግሞ ኢህአዴግ ነው። የኮመጠጠውን የፖለቲካውን ዛፍ መግረዝ ወይም ነቅሎ መጣል አለበት፡፡ ወድቆ መበስበስ ምርጫው መሆን የለበትም፡፡   

Read 3555 times