Saturday, 18 November 2017 12:49

የእነ አቶ ለማ መገርሳ ስኬቶችና ቀጣይ ፈተናዎች!

Written by  ታምራት መርጊያ utdtaman@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

      ባለፋት ሁለት ዐመታት በኢትዮጵያ በቆዳ ስፋትም ይሁን በሕዝብ ቁጥር ትልቁ ብሄር በሆነው የኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ (domino effect) ሕዝባዊ ተቃውሞች ሲናጥ መክረሙ የሚታወስ ነዉ፡፡ አሳዛኙ እውነት ደግሞ ይኽንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የበርካታ ዜጎች መተኪያ የሌለው ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ አልፏል፤ የአያሌ ምስኪን ወገኖች አካል ለጉዳት ተደርጓል፣ ዜጎች ለፍተው ጥረው ያፈሩት ንብረት ወድሟል እንዲሁም በርካታ ወገኖቻችን ከቀያቸው ለመፈናቀልና ለስደት ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ይህ መራር ሀቅ በመንግሥትም ይሁን በተቃዉሞ ጎራ በቆሙ ሀይሎች የተገለፀና የታመነ ጉዳይ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ይሁንና የዚህ ሁሉ የፖለቲካና ማሕበራዊ ትራጀዲ ውጥንቅጥ ማክተሚያ ሁነኛ መፍትሄ ግን ቢያንስ እስካሁን ድረስ ሊገኝ አለመቻሉ ደግሞ ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን በሀገሪቱ ዉስጥ እየተከሠቱ የሚገኙት ዜጎችን  ለህልፈትና ለአካል መጉደል የሚዳርጉ፤ እንዲሁም ዜጎች ለፍተው ደክመው ያፈሩትን ጥሪት በቅፅበት ወደ ትቢያነት የሚቀይሩ ክስተቶች መቼት ፍፁም ተገማች (Predictable) ያልሆነበት ሁኔታ መስፈኑ ነው፡፡ በመሆኑም ዛሬ በሀገራችን በፖለቲካው ረገድ የት፣ መቼና ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት በእጅጉ አዳጋች እየሆነ ይገኛል፡፡ አስቀድሞ የነገሮችን መነሻ፣ ሂደትና ዑደት በአግባቡ ያለመረዳት፣ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ጥበብ ጉድለት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ እዚህ ላይ በአረብ ሀገራት ተከስቶ የነበረውን የአረብ ፀደይ (Arab spring) ተብሎ የሚጠራውን ሕዝባዊ አመፅ በምሳሌነት መጥቀስ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡
እንደሚታወሰው ይኽ በአረብ ሀገሮች ውስጥ ተቀጣጥሎ የቆየውና አይነኬውን የሊቢያ ፕሬዚደንት ኮሎኔል ሞሀመድ ጋዳፊን ከመንበረ ስልጣናቸዉ አንስቶ፣ በፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ እንደ ቆሻሻ ተጥለው እንዲገኙ ብሎም ለህልፈት የዳረጋቸው፣ የግብፁን ሆስኒ ሙባረክ ከተደላደለው የስልጣን መንበራቸው ወደ ዘብጥያ ለመወርወር ያበቃቸው፣ የቱኒዚያውን ኘሬዚዳንት ቤን አሊ አገር ጥለው ለባዕድ ሀገር ስደት የዳረጋቸው፣ በሶርያና በየመን እስካሁን ድረስ ማብቂያ ያልተገኘለትን የእርስ በርስ እልቂት አማጪ የሆነዉ ጉዳይ፥ በቀላሉ ሊፈታ ይችል የነበረ፥ መንስኤው እጅግ አነስተኛ የሆነ፤ መዘዘ ብዙ የአመራር ጥበብ ጉድለት የወለደው፣ የግለሰብ ምሬት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
የሆነውም እንዲህ ነበር፦ አንድ ሞሀመድ ቦአዚ የተባለ ምስኪንና ጎስቋላ ቱኒዚያዊ የመንገድ ዳር ድንች ጠባሽ፤ የጠበሰውን ድንች ሸጦ የእለት ጉርሱን እንዳያገኝ  የቱኒዚያ ፖሊሶች ከግራ ወደ ቀኝ እያላጉ ቢያስቸግሩት ጊዜ ድንች ለመጥበስ ያዘጋጀውን ጋዝ እላዩ ላይ አርከፍክፎ ሲያበቃ፣ ክብሪት ጭሮ፣ ማአሰላማ (አበቃ) ብሎ እራሱን አቃጥሎ ገደለ። ከዚያም ያቺ ቅፅበት ለቦአዚ ህልፈትን፣ ለአረብ ሀገራት ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች ምስቅልቅሎችን ወለደች፡፡ ተያይዞም ታፍኖ የቆየው ሕዝባዊ ብሶትና የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ታላላቅ እጆች (Big hands) ሕዝባዊ አመፁ በሰፊው እንዲቀጣጠል ነዳጅ በማርከፍከፍ ረገድ የነበራቸው ሚናና ተፅእኖ ቀላል ግምት እንደማይሰጠው ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህኞቹ (የሕዝብ ብሶትና የምዕራባውያን ተፅዕኖ) የሞሐመድ ቡአዚ ድርጊት በከፈተው ቀዳዳ መሰስ ብለው የገቡ የቀላሉ መነሻ ተከታዮች (Secondary) እንጂ የችግሩ ዋናና መሠረታዊ መነሻዎች አልነበሩም፡፡
በተመሣሣይ መልኩ በሀገራችን ውስጥም የተከሰተውና እስካሁንም ሁነኛ መፍትሔ ያልተገኘለት ችግር ከቀላል መነሻ  የተነሳ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለማስታወስ ያህል ይኽን መነሻው ትንሽ፣ መዘዙ ደግሞ ከባድ የሆነና በኦሮሚያ ክልል ተጀምሮ በኋላም ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የተዛመተውን ህዝባዊ ተቃውሞ የቀሰቀሱት፣ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው የኦሮሚያዋ ጊንጪ ከተማ የሚገኙ ለአካለ መጠን እንኳን ያልደረሱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ መነሻም “ጭልሞ የተባለውን ጫካ አትንኩብን፣ ኳስ መጫወቻ ሜዳችንን አትውሰዱብን” የሚል ቀላል ተቃውሞ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይኽ አነስተኛ መነሻ የነበረው ተቃውሞ ታዲያ በወቅቱ በተገቢ መንገድ እልባት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ አገራችን ያለችበት ሁኔታ ውስጥ ባልተገኘን ነበር የሚለዉ ሀሳብ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡
ጆን ማክስዌል የተባለ ፀሀፊ እንደተናገረው፤ “መሪ ማለት የመፍትሔ መንገድን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ መፍትሔን በተግባር ላይ የሚያዉልና ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫን የሚያመለክት ወይም የሚያሳይ ነዉ፡፡ እንዳለመታደል ሆነና ይኽንን የተገነዘቡ መሪዎች ስላልነበሩ (ቢያንስ በዚያን ወቅት) አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት ሁኔታ ለመዳረግ በቃች፡፡ በዚህም ሳቢያ በመላው ሀገሪቱ የተከሰተው ችግር  ከባድ የፖለቲካ ጫናና ግፊት ውስጥ የከተተው መንግሥት፣ ቀዉሱን ለመፍታት እንደሚያስችለው ተስፋ በማድረግ፤ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ከስልጣን እስከ ማንሳትና በአዳዲስ ተሿሚዎች እስከመቀየር፣ በሙስና ጠረጠርኳቸዉ ያላቸዉን ባለስልጣናትም ወደ ወህኒ እንዲወርዱ እስከ ማድረግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅም እስከመገደድ፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን እስከ መሰረዝ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጥ ወዘተ.... ደረጃ ደረሰ፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት የተወሰዱት እነዚህ ሁሉ እርምጃዎች ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔ ለማምጣት ተስኗቸው መቅረቱን በቅርብ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ሁኔታዎች አስረጂ ናቸው፡፡ ይኽም በመንግሥት ደረጃ የችግሩ አንጓና መሰረታዊ መንስኤዎች እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ እስከ አሁን እንዳልተገኘ አመላካች ነው፡፡
ወደተነሳንበት አቢይ ጉዳይ ስንመለስ፤ ይኽንኑ የመንግሥት እርምጃ ተከትሎ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ በመንግሥት ላይ የፈጠረው ጫናና ግፊት የወለዳቸው እነ አቶ ለማ መገርሳና አዲሶቹ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ወደ ስልጣን መጡ። አቶ ለማ መገርሣም ይሁኑ አዳዲሶቹ የርሳቸው ባልደረቦች፣ ከዚህ ቀደም አብዛኞቻችን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ አይተናቸዉ የማናውቅ  አዳዲስ ገፆችና ክስተቶች (fresh blood coming-out from nowhere) ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ ስልጣን ላይ ከወጡ አንስቶ እስከ አሁን የሄዱበትን መንገድ፣ የሚወስዷቸዉን እርምጃዎች ስንመለከት ደግሞ ቀጣይነቱና ተዓማኒነቱ ላይ ጥርጣሬ ያላቸዉ ወገኖች ሀሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአመዛኙ በአዎንታዊ ጎኑ የሚታይና ይበል የሚያሰኝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እዚህ ላይ እስካሁን ለሰሩት በጎ ስራም እውቅና  መስጠት ተገቢ ጉዳይም ይመስለናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያዊያን መጥፎ የሰራን ከመውቀስ ባሻገር በጎ ለሰራም እውቅና የመስጠት ባህልም ማዳበር ስለሚገባን ነው፡፡ እነ አቶ ለማ መገርሳ ከአምናው ጥቁር ታሪክ በመማር የዘንድሮው እሬቻ በዐል በሰላም እንዲጠናቀቅ የተከተሉት የብልህ እስትራቴጂ፤ እያሣዩ ያለው ሕዝባዊ ወገንተኝነት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ወንድም ሕዝብ ጋር ተቀራርቦ በሠላምና በመከባበር ለመኖር ይችል ዘንድ ሀሣብ በማመንጨት ረገድም ሆነ ለመተግበር የሚያደርጉት ጥረትና በተለያዩ ብሔሮች መካከል ያለዉን አለመግባባት ለማስወገድ የሚከተሉት የኢትዮጵያ አንድነት መርህ፣ በበጎ ጎኑ የሚነሱላቸው ጠቃሚ ተግባራት ናቸው፡፡ ይሁንና አሁን የጀመሩት ጥረት በዘላቂነት ግቡን እንዲመታ የማድረግ ከባድ ፈተናም ከፊታቸው ተጋርጦ ይጠብቃቸዋል፡፡
ይህን ፈተና ለመወጣት ካልቻሉ አሁን የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ አንዳንዶች እንደሚጠረጥሩት፣ የይስሙላና ጊዜ ለመግዛት ብቻ የታለመ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ይህን የጥርጣሬ አመለካከት ለማስወገድ የጀመሩትን መልካም ጅማሮ በዘላቂነት አጠናክረው የመሄድ ትልቅ የቤት ሥራና ብርቱ ፈተና በሚገባ ሊወጡት የሚገባ ጉዳይ ይሆናል፡፡ በመሆኑም የእነ አቶ ለማ መገርሳ አስተዳደር በቀጣይ የሚከተሉት ነጥቦች ላይ አበክሮ የመስራት ፈተና ይጠብቀዋል፦
አሁን የጀመሩትን የኢትዮጵያን አንድነት መልሶ የሚያጠናክር ተግባር በመቀጠል፣ የሕዝብ ለሕዝብ አብሮነትን በማጠናከር፣ የኦሮሞን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ብሔረሰቦች ጋር በሠላም፣ በመከባበር፣ ያለምንም ቁርሾ እንዲኖር ማድረግ (Peacefull coexistance)
በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ መንግሥት መሐከል የሚኖረው ግንኙነት፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሠመረ እንዲሆን መስራት፣
ከዚህ ቀደም አሮሚያን ካስተዳደሩ አካላት  በላቀ መልኩ በአንጻራዊነት በሕዝቡ ያገኙትን ተቀባይነትና የሕዝብ አመኔታ ሣይሸረሸር አስጠብቀውና የበለጠ እንዲጠናከር  መስራት፣
የህዝቡን ስሜትና ህመም በቅርበት ማዳመጥና ለህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝና የተቀላጠፈ መፍትሔ መስጠት፣
በክልሉ የሚገኙ የወረዳ፣ የዞንና የክልሉ አስተዳደር ድረስ የሚገኙ ክልላዊ የመንግሥት መዋቅሮች፣ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተቀላጠፈ መንገድ ደረጃ በደረጃ እንዲወገዱ በማድረግ፡ ግልፅ፡፣ ተጠያቂነትና አሣታፊ የሆነ ስርዐት እንዲሰፍን መትጋት፣
የመልካም አስተዳደር አደጋ የሆነውና የክልሉን ህዝብ ሲያማርር የኖረውን የሙስና ወንጀል በፅኑ በመታገል፣ ሙሰኞችን በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ፣
ላለፉት አመታት የኦሮሞ ሕዝብ በክልሉ ከሚኖሩም ይሁን በሌላ የሀገሪቱ ክፍል ከሚገኙ የሌላ ብሔር ተወላጆች ጋር በባላንጣነት ስሜት እንዲተያይ ብሎም ወደ አላስፈላጊ ግጭት ዉስጥ እንዲገባ ሲያደርገው የነበረዉን ከፋፋይ አስተሳሰብ ለማጥፋት ማሕበራዊ ስነልቦና (Social Psychology) ላይ አበክሮ መስራት፣
እነዚህንና ሌሎች የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው የሐገሪቱ ብሔሮች ጋር በእኩልነት፣ ፍትሐዊ የሆነ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ አንድነት፣ በመከባበርና በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲሰፍን የሚያደርጉ ተግባራትን አጠናክረው ከቀጠሉ፤ ለሁሉም ምቹ የሆነች፣ ብዝሐነትን የምታስተናግድና የምታከብር፥ በተለያዩ ብሔሮች መሀከል በመፈቃቀር ቃል ኪዳን የተገነባች አንዲት ኢትዮጵያን ጠብቆ ለማቆየት ከክልሉ የሚጠበቁ ፈተናዎችን አርዓያነት ባለው ሁኔታ ማለፍ የሚችል ከሆነ፣ የእነ አቶ ለማ መገርሳ አስተዳደር በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ሊፃፍ የሚችል አዲስ ታሪክ ይሠራል ማለት ነው፡፡

Read 3643 times