Saturday, 18 November 2017 12:32

የአማራና የትግራይ ህዝብ የአንድነት ጉባኤ ዛሬና ነገ በጎንደር ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


    “አንድነታችን ለሰላማችን፣ ሰላማችን ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ቃል፣ ሁለተኛው ዙር የአማራና የትግራይ ህዝቦች የአብሮነትና የአንድነት ጉባኤ ዛሬ እና ነገ በጎንደር ይካሄዳል፡፡
የህዝብ ለህዝብ የአንድነት ጉባኤውን መድረኩን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ከትግራይ ክልል 500 ገደማ ከሃገር ሽማግሌዎች፤ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከምሁራንና ከክልሉ አመራሮች የተውጣጡ የጉባኤው ተሳታፊዎች ትናንት አርብ ጎንደር ከተማ የገቡ ሲሆን ከአማራ ክልል ደግሞ  800 ያህል  ተሳታፊዎች በጉባኤው ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ 1300 ተሳታፊዎችን ያካተተው የአብሮነትና የአንድነት ጉባኤው፤ የሁለቱ ክልል ህዝቦች አንድነትና ታሪካዊ አብሮነት  እንዲሁም ቀጣይ ግንኙነት ላይ ያተኮረ ጥናት በምሁራን  ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል - አቶ ንጉሱ፡፡
በተጨማሪም የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑት “ፀገዴ” እና “ጠገዴ” የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ በነሐሴ ወር በመቀሌ በተደረገው ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፤ የሁለቱ ክልል መንግስታት የደረሱበት መፍትሄ በጉባኤው ላይ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከትግራይ ክልል ለጉባኤው የመጡ ተሳታፊዎች  በሰሮቃ፣ በሳንጃ፣ በትክል ድንጋይና በጎንደር ከተሞች ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸውም አቶ ንጉሱ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡

Read 2148 times