Monday, 13 November 2017 11:08

የትምህርት ጥራት ችግር - የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

  • በትምህርት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ መበረታታት አለባቸው
       • አድማስ ዩኒቨርሲቲ፤ 11ኛውን የጥናትና ምርምር ጉባኤ አካሄደ
       • ዕድገትም ሆነ ውድቀት በትምህርት ጥራት ላይ የተመሰረተ ነው
       • የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ዋናው፣ ተማሪዎችን ማብቃት ነው

    በየዓመቱ ችግር ፈቺ የሆኑ ጉዳዮችን በመምረጥ፣ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ሲያካሂድ የቆየው አድማስ ዩኒቨርሲቲ፤ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ፣ 11ኛ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን “Quality of Education and University-industry Linkage” በሚል ርዕስ፣ በፍሬንድሺፕ ሆቴል አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ ወደ ሰባት የሚጠጉ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ስለ ዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ጉዞና የደረሰበት ደረጃ፣ ለ11 ዓመት ስለዘለቀው የጥናትና ምርምር ጉባኤ፣ ስለ አገሪቱ የትምህርት ጥራት ችግር፣ በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሃብቶች ስለሚገጥሟቸው ፈተናዎች ----እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሞላ ፀጋዬ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡-

   አድማስ ዩኒቨርሲቲ፤ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዴት እንደረሰ በአጭሩ ያብራሩልን?
አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ሂደቶችን አልፏል፡፡ በ1990 ዓ.ም “አድማስ የስልጠና ማዕከል” በሚል ነበር የተቋቋመው፡፡ ከዚያም ከ1 ዓመት በኋላ በ1991 ዓ.ም ማሟላት የሚገባውን ሁሉ አሟልቶ ወደ ኮሌጅነት አደገ፡፡ በኮሌጅነት በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናዎችን እየሰጠና ራሱን በማቴሪያል፣ በሰለጠነ የሰው ሀይል፣ በሌሎችም እያሳደገ ከቆየ በኋላ፣ በ1999 ዓ.ም ደግሞ በወቅቱ ከባድና ፈታኝ የነበሩትንና የትምህርት ስልጠና ህጉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች አሟልቶ፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ራሱን አሳደገ፡፡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የሚፈለገውን አሟልቶ፣ ወደ ሙሉ ዩኒቨርሲቲነት በማደግ አገልግሎቱን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው 10 ካምፓሶችና 50 ያህል የርቀት ትምህርት ማዕከላት አሉት። 10ኛው ካምፓስ ሱማሌ ላንድ፣ ሀርጌሳ ይገኛል። ሀርጌሳ ያለው ካምፓስም የራሱ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን አስመርቆ ወደሚፈለጉበት ኢንዱስትሪ (የስራ ዘርፍ) አሰማርቷል፡፡ አሁንም በዲግሪ፣ በቴክኒክና ሙያ፣ በመደበኛና በርቀት ከአገር ውስጥም ከውጭም ወደ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች አሉን፡፡
በጥናትና ምርምር ጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተገለጸው፤ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ ማካሄዱ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የቀረቡት የጥናትና ምርምር ውጤቶች ምን ይመስሉ ነበር? ዘንድሮ የተመረጡትስ በምን ርዕስ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ናቸው?
እንዳልሺው የዘንድሮው ለ11ኛ ጊዜ የቀረበ ነው። የጥናትና ምርምር ጉባኤ ማዘጋጀት ስንጀምር፣ ርዕሰ ጉዳዮቹ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም የወቅቱ አንገብጋቢ ችግር ኤችአይቪ/ኤድስ ስለነበረ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት የምርምር ውጤቶቹን በማቅረብ፣ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ ስለነበረብን ነው፣ ያኔ ርዕሰ ጉዳዩን የመረጥነው፡፡ እስካሁንም ለዚህ ጉባኤ የሚቀርቡ የጥናትና የምርምር ውጤቶች መስፈርት፤ “ወቅቱን ያገናዘበና ከወቅቱ ጋር የሚሄድ” የሚል ነው፡፡
እስካሁንም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ (GTP1 እና 2)፣ ለምሳሌ ከጂቲፒ 1 የሚወሰደው ትምህርት፣ ጂቲፒ ሁለትን እንዴት ይደግፈዋል? በጂቲፒ1 የነበሩ ክፍተቶች በጂቲፒ2 እንዳይደገሙ ምን  ጥንቃቄዎች መደረግ አለባቸው? በሚሉት ላይ ወቅቱን ተከትለው የተሰሩ የምርምር ውጤቶች፣ በጉባኤው ቀርበው፣ ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ምሁራን ተወያይተውባቸዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ የሆኑ፣ ሁሉንም ወቅታዊ ችግሮች የሚዳስሱ ጥናትና ምርምሮች ይቀርባሉ፡፡ ወደ ዘንድሮው ጉባኤ ስንመጣ ትኩረት ያደረግነው፣ በትምህርት ጥራት ላይ እና  በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር ላይ ነው፡፡ ይሄ ርዕሰ ጉዳይ ምናልባትም ከዘንድሮ ጋር ለሶስተኛ ጊዜ ነው ትኩረት ተሰጥቶት የቀረበው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የትምህርት ጥራት ጉዳይ አስጊና ሁሉንም እያነጋገረ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ እንደመሆኑ ጥራት ጎደለው ማለት ሁሉም ነገር ያለዚህ ቁልፍ አይከፈትም ማለት ነው፡፡ የሁሉም ዘርፎች እንቀስቃሴ እድገትም ሆነ ውድቀት በዚህ የትምህርት ጥራት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ መንግስትም ትኩረት የሰጠው ለዚህ ይመስለኛል፤ ትክክልም ነው፡፡ እኛም በበኩላችን፤በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየቱም ሆነ መነጋገሩ አስፈላጊ መሆኑን ስለምናምን፣ ለጉባኤው የመረጥነው ጉዳይ ሆኗል፡፡
የ”ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ” ትስስር ሲባል ምን ማለት ነው? እስቲ ያብራሩልን?
ዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስር፣ በአገራችን በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ዩኒቨርሲቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር ስንል፣ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ተማሪዎችን አስመርቀው ያወጣሉ፡፡ ከዚያ እነዚህ ምሩቃን ወዴት ይሄዳሉ? ነው - ጥያቄው፡፡ አንድም የራሳቸውን ትንንሽ ኢንዱስትሪ አሊያም ትንንሽ ስራዎች ይፈጥራሉ እንበል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ወደ ኢንዱስትሪው በመሄድ ተቀጣሪ ነው የሚሆኑት፡፡ በመምህርነትም ይሁን በማኑፋክቸር ኢንዱስትሪው፣ በሁሉም ዘርፍ ይቀጠራሉ። ሁሉም ቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ራሳቸውን ችለው ኢንዱስትሪ ናቸው፡፡ ይህንን ስንመለከት በዋናነት የምናነሳቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ አንደኛ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስመርቁት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን አይነት ሰልጣኝ ነው? ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ይዞ ነው ከዩኒቨርሲቲዎች የሚወጣው? ለምሳሌ ኢንዱስትሪው “ብቁ የሆኑ ዜጎች አላገኘሁም” ብሎ እያማረረ ከሆነ፣ብቁ የሚላቸው ዜጎች ምን መሆን አለባቸው? የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው የብቁ ባለሙያዎች እጥረት እንዳለ ይሰማል ---
ይሄ’ኮ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ችግር ባይኖር ጥናትና ምርምሩን ትኩረት አይሰጠውም ነበር። ስለዚህ ኢንዱስትሪው ብቁ የሚለውን ሰልጣኝ፣ ዩኒቨርሲቲው ያውቀዋል ወይ? የሚለውን ጭምር ይዳሰሳሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ፕሮግራሞች በርካታ ተማሪ  ይመረቅባቸዋል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪው ገብተው ግን አይቀጠሩም፡፡ ምናልባት ዩኒቨርሲቲውና ኢንዱስትሪው ተናበው ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ይሰምር ነበር፡፡ የሚፈልጉት የምሩቅ ፕሮፋይል ተጠንቶ ኢንዱስትሪው፣ ለዩኒቨርሲቲው ማቅረብ አለበት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደግሞ ከኢንዱስትሪው ጋር ተቀናጅቶ መስራት አለበት፡፡
ለምሳሌ ባንክን እንደ አንድ ኢንዱስትሪ እንውሰድና፣ በአሁኑ ሰዓት ስንት ምሩቃን ነው የሚፈልገው? ሁለትም በምን አይነት ስኬልና አመለካከት ነው ምሩቆችን የሚፈልገው? ባንኩ የሚፈልገውን ያህል ቁጥር ዩኒቨርሲቲው ላያመርት ይችላል፡፡ በዚህም የተነሳ ባንኩ እጥረት ይገጥመዋል። ተናበው ተሳስረው ቢሰሩ ግን ሁለቱም ተቋማትም ሆኑ ምሩቃን ውጤታማ ይሆናሉ፤ ነው ሀሳቡ፡፡ ሌላው ጥቅሙ፣ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እያሉ፣ በኢንዱስትሪው ገብተው፣ የተግባር ስልጠና የማግኘት ዕድል ይገጥማቸዋል። ትምህርት ላይ ሳሉ በተግባር ስራውን ካወቁት፣ ተመርቀው ሲወጡ፣ አዲስ ስለማይሆንባቸው ፈጥነው ወደ ስራ ለመግባትና ውጤታማ ለመሆን ይረዳቸዋል፡፡ ከመደናገርና ከእንግድነት በራቀ ስሜት፣ ሥራቸውን አቀላጥፈው መስራት ይችላሉ። ለዚህ ግን መጀመርያ ሁለቱ አካላት ትስስር ፈጥረው መስራት አለባቸው፡፡ ይሄ የተለመደው ማስመረቅ፣ ውጤት እያመጣ አይደለም፡፡ አንዳንድ ፕሮግራም ላይ ምሩቅ ይበዛል፤ አንዳንድ ፕሮግራም ላይ የምሩቃን እጥረት አለ፡፡ ኢንዱስትሪው በብዛት የማይፈልገው መስክ ላይ ምሩቅ ከበዛና የሚፈልገው ላይ እጥረት ከተፈጠረ፣ ውጤቱ ኪሳራ ብቻ ነው። የሁለቱ አካላት ትስስር ይህንን አለመጣጠም ያስተካክላል፡፡ ተምሮ ሥራ ማጣትንም ያስወግዳል፡፡ ኢንዱስትሪው “ብቃት” የሚለውን ደረጃም ተገንዝቦ፣ ተማሪዎችን ለማምረት ይረዳል፡፡
የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ወደ ንግዱና ገንዘብ መሰብሰብ ስለሚያመዝኑ፣ የትምህርት ጥራት ላይ ክፍተት ይታይባቸዋል የሚል አመለካከት ይንጸባረቃል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል? በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ይኖራሉ?
በአብዛኛው ከላይ የገለፅሽው አመለካከት አለ፡፡ በዛሬው ጉባኤ ላይ የቀረቡ ጥናቶች የሚያመለክቱት ግን በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት ላይ የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩን ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን የትምህርት ጥራት ችግር፣ ትልቅ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በግል ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎችም ከታች ባሉ ት/ቤቶችም እንዲሁም በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ታች ባሉ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችም ነው የሚታየው፡፡ እንደ ግል የትምህርት ተቋም ሰራተኛነቴ፣ የግል ዘርፉን ብናገር ይሻላል፡፡ በግሉ ዘርፍ ያለ የትምህርት ተቋም፣ ዝም ብሎ ተነስቶ፣ ፕሮግራም አይከፍትም፤ ዩኒቨርሲቲ አይከፍትም፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ አድማስ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለመድረስ፣ ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ብዙ ሂደቶችን አልፏል፡፡ መስፈርቶችን በሙሉ በሚገባ አሟልቶ ነው ፈቃድ ያገኘው። ተይው ዩኒቨርሲቲውን፣ አንዲት ፕሮግራም ያለፈቃድና እውቅና በትምህርት አይነቶች ላይ አትጨምርም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኤጀንሲ የተባለው አካል ፈቃድ መስጠት አለበት፡፡ ኤጀንሲው ፈቃድ ሲሰጥ፣ አነስተኛ የጥራት መስፈርቶች (Minimum requirements) አስቀምጦ፣ ፈቃድ ጠያቂው፣ እነዚያን ማሟላት አለበት፡፡ ሲሟሉ ፈቃድ ያገኝና፣ በዚያች ፕሮግራም ላይ እድሳት ማድረግ አለበት፡፡
ከመጀመሪያው ይልቅ ሁለተኛው እድሳት ከበድ እያለና መስፈርቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ሶስተኛና አራተኛው እድሳት ደግሞ የበለጠ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ ስለ ጥራት ስናወራ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ማስመር አለብን፡፡ ቀስ በቀስ እያሳደግን፣ ሂደት የሆነውን የጥራት ጉዳይ ማሳደግ እንችላለን። ስለ ትምህርት ጥራት ጉድለት ሲነሳ፣ችግሩን ወደ ግሉ የትምህርት ተቋማት ብቻ መወርወር ስህተት ነው፡፡ በመንግስትም በግልም የጥራት ችግር አለ። ቅድም እንዳልሺው፣ የግል ተቋማት ላይ ችግሩ የሚወረወረው ከተማሪ የተወሰነ ክፍያ ስለሚጠይቁ ነው፡፡ መጠየቅ አለባቸው፤ ምክንያቱም ለፅድቅ አይደለም የሚሰሩት፡፡ ትርፉ ግን ብዙ አይደለም፡፡ በትምህርት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች፣ መመስገንና መበረታታት አለባቸው፡፡ በሌሎች የንግድ ስራዎች ላይ ቢሰማሩ ብዙ ያተርፋሉ፡፡ ነገር ግን ትምህርት እንደ ሌላው ሸቀጥ አይደለም፤ ብቁ ዜጎች ተቀርፀው የሚወጡበትና አገር የማስቀጠል ጉዳይም ነው፡፡
የሆነ ሆኖ አንዳንድ የግል ተቋማት፤ከትምህርቱ ይልቅ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ሊያመዝኑ ይችላሉ። እንደነዚህ አይነት ተቋማት ጨርሶ የሉም ለማለት አልችልም፡፡ ህግና ሰርዓትን መጣስ፣ የመግቢያ መስፈርት ያላሟሉ ተማሪዎችን ስለከፈሉ ብቻ ማስተማር እና የመሳሰሉትን ህጎች የሚጥሱ ይኖራሉ፡፡ ግን ብዙ ትርፍ ሳይፈልጉ፣ ዜጋን የሚቀርፁና ለብዙዎች ተስፋን የፈነጠቁ የግል ተቋማት ባለቤቶች፤ ከነዚህኞቹ ጋር ተደምረው መፈረጅ የለባቸውም፡፡ በዚህ ላይ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ ሀላፊነት ተሰምቷቸው የሚሰሩ የግል ተቋማት ባለቤቶችን በግሌ አደንቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል ስትመለከቺው፣ ሁሉም የመንግስት ተቋማትስ፣ በአንድ አይነት ጥራትና ትጋት ይሰራሉ ማለት ይቻላል? አይቻልም፡፡ አንድ የሚያግባባው ጉዳይ ግን የግልም ሆኑ የመንግስት የትምህርት ተቋማት ላይ የጥራት ችግር አለ፡፡ ይህን የጥራት ችግር ለመቅረፍ የግልም የመንግስትም ተቋማት፣ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች----- ብዙ የሚጠብቃቸው የቤት ስራ አለ፡፡
በዘንድሮ  ጉባኤ ላይ ከቀረቡት ጥናቶች ውስጥ የትምህርት ጥራት ችግር በአገር ላይ ያመጣውን ተጽዕኖ የዳሰሰ ይኖር ይሆን?
በእርግጥ በአገር ላይ ያመጣው ተፅዕኖ ይኖራል፤ ግልፅ ነው፤ ተፅዕኖው ግን መጠኑ ምን ያህል ነው የሚለውን ለማጥናት ከባድ ነው፡፡ ይህን ያመለከቱ ጥናቶችም በጉባኤው ላይ የሉም፡፡ ነገር ግን በግሉም በመንግስትም የትምህርት ተቋማት በኩል፣ የጥራት ችግር መኖሩን ጥናቶቹ ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ብቻም ሳይሆን የዩኒቨርሲቲ- ኢንዱስትሪ ትስስሩን በተመለከተ፣ እንኳን ደካማ ነው፣ ጠንካራ ነው ለማለት ቀርቶ፣ ጭራሽ የለም፡፡ ጥናቶቹ ይህንንም ነው ያመላከቱት፡፡
ለትምህርት ጥራት መጓደል አንዳንድ መንግስት ያስቀመጣቸው ፖሊሲዎች ክፍተትም እንደ ምክንያት ይነሳል?
ለምሳሌ?
ለምሳሌ አንድ ተማሪ ብቁ ዜጋ ሆኖ በትምህርቱ እንዲቀጥል መሰራት ያለበት ገና ከመሰረቱ ነው፤ ነገር ግን አሁን ያለው ፖሊሲ፣ አንድ ተማሪ እስከ 4ኛ ክፍል እንዳይወድቅና እንዲያልፍ ብቻ ይደነግጋል። ይሄን እንደ ከፍተት የሚያዩ አሉ፡፡ ሌላው በግል የትምህርት ተቋማት፣ ኮሌጅም ይሁን ዩኒቨርሲቲ ሲከፈቱ መጀመሪያ የሚያወጡት የንግድ ፈቃድ ነውና፣ ከትምህርቱ ይልቅ ንግዱ ላይ ማተኮራቸው አንዱ የትምህርት ፖሊሲው ችግር ነው ሲሉ የሚተቹ ባለሙያዎች አሉ፡፡----
እዚህ ላይ ስህተት አለ፡፡ 30 ገፅ የሚሆነውን የትምህርት ፖሊሲ (በ1994 የተነደፈውን ማለት ነው)፣ ከዚያም በኋላ የወጡ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን እዚሁ ዘርፍ ውስጥ ስላለሁ በደንብ አውቃቸዋለሁ፡፡ ጥራት እንዲጠበቅ፣ ፍትሀዊነትና የትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም አግባብነት እንዲኖር  አቅጣጫ ያስቀምጣሉ፡፡ ይሄ አንደኛው ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ 30 ዓመት፣ በአገራችን ስንት ዩኒቨርሲቲዎች፣  ስንት ምሁራን ነበሩ? ብዙ ተቋማትና ምሁራን ባልነበሩበት ወቅት ስለ ጥራት ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡
ብዙ ምሩቅ ብዙ ዩኒቨርሲቲ በሌለበት፣ ትንሽ ተስፋ ብቻ ይዘን በምንጓዝበትና ከሁሉም አገራት ኋላ ቀርተን ጭራ በነበርንበት በዛን ጊዜ፣ ስለ ትምህርት ጥራት ማውራት አግባብም ትክክልም አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግስት ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ፣ ፍትሀዊነት እኩልነት ማስፈንና ፖሊሲ ማስቀመጥ ነበረበት። ይሄ አግባብ ነው፤ ትክክልም ነው፡፡ በሌለ ነገር ላይ ስለ ጥራት አናወራማ! አሁንም እኮ በአፍሪካ - ከሰሀራ በታች ካሉ አገራትም አንፃር ብንታይ፣ ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ከተደራሽነት ፍትሀዊነትና እኩልነት አንፃር ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን የጥራት ችግር ፈተና ሲሆን እንዲህ አንነጋገራለን፡፡ የግድም ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ተማሪ በተቀበልን ቁጥር ብዙ ቤተ-ሙከራዎች፣ ጥሩ አቅም የታጠቁ ብዙ መምህራን ---- ከየት ይመጣል? ይሄም አንዱ መሻሻልና መለወጥ ያለበት ነው፡፡ ፖሊሲ መኖሩ የግድ ነው፤ ስለ ጥራት እያወራን ስለሆነ፡፡
በፖሊሲው ላይ ሌላው እንደ ስኬት የምወስደው፣ ትምህርት ለግሉ ዘርፍ መፈቀዱ ነው፡፡ (የግሉ የትምህርት ተቋማት ያሉበት ቁመና ይቆየንና) ሰው ገንዘብ ሲኖረው ልጆቹን ማስተማር የሚፈልገው የት ነው? በዚህ ላይ ለምን እውነት አንነጋገርም፤ ምክንያቱም ሁላችንም እናውቀዋለን። ሰው የገንዘብ አቅሙ እያደገ በመጣ ቁጥር ከፍሎ ነው ማስተማር የሚፈልገው፡፡ በተለይ የግል የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ፣ የፖሊሲ ክፍተት አለ በሚለው የማልስማማውም ለዚህ ነው፡፡ እነ ሀርቫርድ እነ ዬልና ሌላም ጠንካራ የሚባሉ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ ከኮሌጅ ተነስተው እያደጉ ነው ጠንካራና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት፡፡ ይሄ ግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ደረጃ ስትደርስ፣ እነዚህ የግል ተቋማት ተጠቃሚያቸውና ፈላጊያቸው በጣም ይበዛል፡፡ ምክንያቱም መንግስት ለትምህርትም ለጤናም እየደጎመ አይቀጥልም፡፡ አቅም ያላቸው ሰዎች፣ ልጆቻቸውን በእነዚህ ተቋማት  በማስተማር፣ የመንግስት ጫና መቀነስ አለባቸው፡፡
ቀደም ብዬ ከ1-4ኛ ክፍልን በተመለከተ ያነሳሁትን ጥያቄ አልመለሱልኝም ዶ/ር?
እዚህ ላይ ያነሳሽው ጥያቄ አከራካሪ ነው፡፡ አከራካሪ ነው ስል፣ በምሁራዊ ቋንቋ ነው መነጋገር ያለብን፡፡ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ፣ ከጥናት ውጤቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በማገናዘብ እንጂ ያነሳሽውን ጥያቄ እኔ የምነግርሽ ከግል አመለካከቴ ነው፡፡
አሁን ያለው አስተሳሰብ ልጁ፣ መሰረታዊ ነገሮችን እስከያዘ ድረስ ለምሳሌ ማንበብ መፃፍ ከቻለ፣ የሂሳብ ስሌቶችን ከሰራ --- መጨረሻ ስለወጣ ለምን ይወድቃል? ለምንስ ያንን ክፍል መልሶ ይደግማል? የሚል ነው፡፡ መጨረሻ የወጣው እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ሳያውቅ ከሆነ፣ ያንን ልጅ ማብቃት ነው፡፡ እያበቁ እንዲዛወር ማድረግ። ምክንያቱም በተለይ ወደ ገጠሩ ክፍል ስትሄጂ፣ ከዚያም የሴቶችን የትምህርት ሁኔታ ስትመለከቺ---ከፍተኛ የመውደቅ ሂደት አለ፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችም አሉበት፡፡ አካዳሚክ ባክግራውንድም አለው፡፡ በአጠቃላይ ጉዳዩ አከራካሪ ነው፡፡ “የለም እስከ አራተኛ ክፍልም ቢሆን ተማሪዎች መውደቅ ካለባቸው፣ መውደቅ አለባቸው” እያልን መከራከር እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት፣ የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ዋናው፣ ተማሪዎችን ማብቃት ነው፡፡
በጉባኤው ላይ የሚቀርቡትን የጥናትና ምርምር ውጤቶች፣ መንግስት በግብአትነት ይጠቀምባቸዋል?
ይሄንን እንዲህ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ለምን ያልሽ እንደሆነ፣ የእኛ ስራ በዋናነት ይሄንን መድረክ ማዘጋጀትና ባለድርሻ አካላትን በጉባኤው ላይ መጋበዝ ነው፡፡ ለምሳሌ በዘንድሮው ጉባኤ ላይ ያተኮርነው፣ ስለ ትምህርት ጥራትና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ላይ በተሰሩ ጥናትና ምርምሮች ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ባለድርሻ ያልናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰዎች፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የቴክኒክና ሙያ ሃላፊዎች ጠርተናል፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው መ/ቤቶች ተወካዮችንም ጋብዘናል፡፡ እነዚህ ተቋማት በጉባኤው ላይ ተገኝተው መውሰድ የሚገባቸውን መውሰድ የእነሱ ፋንታ ይሆናል፤ ከጥናቱ ማለት ነው፡፡ እኛ በዚህ ሳናበቃ እነዚህን የጥናትና ምርምር ውጤቶች፣ በፕሮሲዲንግ መልክ አሳትመን፣ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እናሰራጫለን፡፡ ከዚህ አልፎ እነዚህ የጥናት ውጤቶች፣ ምን ላይ ነው ያሉት? ሼልፍ ላይ ቀርተዋል? ብለን ውይይት አድርገን እናውቃለን፡፡ ፈፃሚው አካል ሌላ ነው፡፡ የእኛ ስራ ጥናቶች ማቅረብ፣ መድረኮችንና ውይይቶችን ማመቻቸት ነው፡፡
በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሃብቶች የሚገጥማቸው ዋና ዋና ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
እኔ እንደውም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ሳስብ ቅር የሚለኝን ነገር ልናገር። መንግስት ለእርሻው ዘርፍ፣ ለግንባታውና ለሌላውም ኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሲያደርግ፣ ለግሉ የትምህርት ተቋማት ግን ማበረታቻ አያደርግም፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የራሳቸውን የዩኒቨርሲቲ ህንፃ መገንባት ይፈልጋሉ፡፡ ቦታ የመፍቀድና መሰል ማበረታቻዎች በመንግስት አይደረግላቸውም፡፡ አብዛኞቹ ማለት ይቻላል ህንጻ ተከራይተው ነው የሚሰሩት፡፡ በተከራዩት ህንፃ ላይ ቤተ-ሙከራ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ሌሎችም መሟላት ያለባቸውን ለመሟላት መከራ ነው፡፡
ምክንያቱም በአብዛኛው ህንፃዎች የሚገነቡት በባለቤቶቹ ዲዛይንና ፍላጎት ነው። ቦታ ቢፈቀድላቸው ግን ለመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ የሆኑ ህንፃዎችን ገንብተው፣ ያለ ችግር መስራት ይችሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ ወደ ግል የትምህርት ተቋማቱ የሚመጡ ተማሪዎች፤ መንግስት የሚፈልገውን ያህል፣ በሚፈልገው ነጥብ ከወሰደ በኋላ የሚተርፉት ናቸው፤ ዝቅ ያለ ውጤት ያላቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህን ተማሪዎች ማብቃት በራሱ ሌላው የግል  ተቋማት ፈተና ነው። ይህንን መሰል ችግሮችና ፈተናዎች ተቋቁመው ነው የሚሰሩት። ስለዚህ መንግስት እነዚህን የግል ተቋማት ማበረታታትና ማመስገን አለበት፡፡ የምር ሊመሰገኑ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 4258 times