Monday, 13 November 2017 10:43

ሀገርሽማ የኔ ልጅ…!?

Written by  ገዛኸኝ ፀ. ጸጋው
Rate this item
(17 votes)

  እውነት ማለት የኔ ልጅ?” ብዬ ግጥም ልጽፍልሽ ስነሳ፣
“እንቢዬው!” ብለሽ ሞግቺኝ፣ ጫጩት ሐሳቤን ሳልኮሳ፤
ጥሬዬን ብቻ እያለምኩ፣ አንቺንም በሆዴ እንዳልረሳ!
የእኔ ዕውነት ገንዘብ ነው ልጄ? ብቻ የምሸጠው አልጣ፣
“የተጻፈበትን የቀለም ዋጋ” ባስር እጥፍ እስኪያወጣ፣
መጻሕፍቴን አዳቅዬ፣
ሁለቱን ባንድ አብቅዬ፣
ዋጋ እንዲፋቅ ተባብዬ፣ ወደ ገበያ ብወጣ፣
እንዴት አዋጪ መሰለሽ ልጄ? ብዙ ገንዘብ እኮ አመጣ…
የሚል ሠርክ ሳንቲም ቆጣሪ፣ ቀሽም አባት ከምሆንብሽ፣
“ዋጋ ለምን ይፋቃል ባቢ!? ለማታለልማ አትረብሽ!”
እያልሽ ገስጪኝ የኔ ልጅ፣ ሂስሽ ነው ነፍሴን የሚበጃት፣
ዕውነትሽን ሸቅጬባት፣ በእሳት ምላሴ ከምፈጃት፣
ተማሪዎቼም ከሚታዘቡኝ፣ ነገዬን በቂም ከሚፈርጇት፣
እባክሽ ልጄ ተለመኚኝ! ቃሌን ከግብሬ አወዳጃት፡፡
አየሽ የኔ ልጅ …
“ሀገር ማለት… ?” እያልኩ፣ ካቅራራሁማ ጠርጥሪ፣
ግጥሟንም ከ’ነ ሐሳቧ፣ መስመር በመስመር ቁጠሪ!
መሽቶ እስኪነጋም ሩቅ ነው፤ “እውነትን” ለማወቅ ስ’ጥሪ፡፡
እንዳሻኝ እየቸረፈስኩ፣ ስንኞቿን አንቀራቅቤ፣
ውኃ ከሚጠብስ ጠቢብ ጋር፣ “የግጥም ክትፎዬን በቅቤ”
ማወራረጃውን ካቲካላ፣ እኛ እንዳንጠጣውም አቅቤ፣
አሟሙቄ እያጫረትኩ፣ ብርር ብዬም “ብር!” ከምል፣
የመንፈስ ሕብስትሽን ሸጬው፣ ቃሌ ኅሊናሽ ውስጥ ከሚያምል፣
“‹ሀገር…?› ማለቱን ተወውና፣ እስኪ ‹እኔ ማለት…?› ብለህ ጀምር፣
ራስን ማወቅ ነው የሚበጅ አባ! ቅድሚያ እስኪ ራስህን መርምር!”
እያልሽ ምከሪኝ የኔ ልጅ፣ ሂስሽ ነው ነፍሴን የሚበጃት፣
ሀገርሽን አስቸርችሬ፣ በቋያ እሳቴ ከማስፈጃት፣
የመንፈስ ልጆቼም ከሚታዘቡኝ፣ ነገዬን በጠፍ ከሚፈርጇት፣
እባክሽ የኔ ልጅ ማልጂኝ፣ ቃሌን ከግብሬ አወዳጃት!
አየሽ! እምቦቅቅላዬ … አየሽ
የጠላሽውን “ለማስወንጀል”፣ መዋሸትሽ ብቻ አይበቃም፣
“ደራሲ” እንዲሉሽ ሞክሪ! ነገርሽ በጥሬው እንዲቃም…
“ምሁር” ካልተባልሽማ ይከብዳል፤ ባዶ ውሸትሽ አያመረቃም፡፡
“ታዋቂ ናት” እንድትባይም፣ “አዋቂዎቹን” ቀድመሽ አዋርጂ፣
ባደባባይ ትሳደቢና፣ በ’የ ጓዳቸው ገብተሽ ስገጂ!
እንደ ምንም “ታዋቂ” ከሆንሽ፣ ከዚያ በኋላማ ተይው፣
ያሻሽን ብትይ ማን ሊጠይቅ? ሰውን ሁሉ “ጉድ!” አስብይው፤
አበሻ እኮ ትንፍስ አይልም፤ የፈለገ ብትበድይው፡፡
ዕውነቴን እኮ ነው የኔ ልጅ
ያ የደራሲ ማኅበር፣ ያንቺን ስም እንዲያወሳት፣
ምንም ቢሆን እንዳያቅትሽ፤ በውሸት አቧራ ማንሳት!
የፈለገ ሙያ ይኑረው፣ ላንቺ ብቻ እስካልደረጀ!
ማኅበር ይሉት ጽሕፈት ቤት፣ መኖሩስ ለምን በጀ!?
ይልቅ እንዳያሳጣሽ፣ ባዶነትሽን እያወጀ…
“አንድም ጽሑፍ ያልጻፈ ሰው፣ የሚመራው ማኅበር” ብለሽ፣
ቀድመሽ “መወንጀል” ትቺያለሽ፣
ብቻ “መድፈር ነው!” የኔ ልጅ? ዱክትርናሽን ከያዝሽ …
እያልኩ ከምሰብክሽ፣ ድንቁርናዬን እያጣባሁ
        ነገሽን ከማበላሸው፣
በምላስ ማደርን ልቄ፣ መብለጥለጥን አውርሼሽ
        ዘመንሽ ከሚያቀረሸው፣
“ሰከን በል!” በይኝ ልጄ! ራሴን ከራሴው አስታርቂናም
        ኅሊናዬን አስፈውሽው፡፡
አዎ! … ይልቅ! አንድ ነገር ልንገርሽ፣
ስለ ዕውነተኛዋ ሀገርሽ …
አዬሽ፣ ሀገርሽማ የኔ ልጅ… !? ኢትዮጵያሽማ የኔ ውድ!
ዕውቀትንና ዕብለትን ሳይለይ፣ ጋዜጣ ሙሉ
ክሽፈቱን ቀድቶ፣
በሕይወት ያለን ታላቅ ደራሲ፣ “በሙቷል” ሙሾው
ሀገር አርድቶ!
እሱ ራሱ ሴራውን ሠርቶ፣ እሱ ራሱ ሕግ አውጥቶ፣
እሱ ራሱ ዳኛ አምጥቶ፣ እሱ ራሱ ቢጤውን ጠርቶ…
በኮረኮንች ተዳፋት ላይ፣ እንደሚንከባለል ባዶ በርሜል፣
በጩኸቱ አደንቁሮሽ፣ “ጩኸቴን ተቀማሁ” የሚል፤
የዘመን ኩርፊያሽ የማይገባው፣ ለዕውቀት የከፈልሽውን የሚቀማ፣
ንቀሽ መተውሽ የሚያጀግነው፣ ሠርክ ሰው መዝለፍን የተጠማ፣
እንዲህ ዓይነት ዕውቀት አርካሽ፣ እንዲህ ዓይነት ልበ ጠማማ…
የሚፏልልባት ምድር ናት፤ ሀገርሽ ይሏት አውድማ፡፡
ኢትዮጵያ ማለት ይህቺ ነች፤ “የደፋር ምሁር” ባድማ!
እንዲያ ነው የኔ ልጅ ዕውነቱ! ይኸው ነው የሀገርሽ “አርማ፡፡”
 
(ለዕውነትና ለኪነ ጥበብ፣ ሸፍጠኞችና ቸርቻሪዎች ሁሉ!
ጥቅምት 21፣ 2010ዓ.ም)

Read 6521 times