Print this page
Monday, 13 November 2017 10:40

ሰለሞን

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(12 votes)

አይደለህም ያንድ ሰሞን!
የማንም ያልሆንክ ህመም
የራስህ የብቻ ቀለም
የራስህ የብቻ ግጥም
አንተኮ ነህ!
ዕንባ ምን ይበጃል ላንተ፣ ራስህ የፊደል ዕንባ
ራስህ የቃላት ቆባ!
ሰለሞን፤
አደለህም ያንድ ዘመን!
የሁሌ ፋና ነህና- የሁልጊዜ ፍልስፍና
የዘላለም ግጥምኮ ነህ
የዘለዓለምም ፊደል፤
አንብበን የማንጨርስህ
ደርሰን የማንጠግብህ
የራስህ ወለሎታት ነህ!
የሁሌ ግጥም ነህ አንተ
የሁሉ ዓለም የሁሉ ጭንቅ
የፈረሰኛ አባትህ ልጅ
የትም የምትታሰር፣ የትም የምትፈታ
ከማንም የማትወግን፣ በማንም የማትረታ፤
ሆኖም ቤት የማትመታ
የዘለዓለም ግጥም ነህ!
የሁሉ ቤት፣ ሆሄ ጌታ!!
ሰለሞን፤
አይደለህም ያንድ ሰሞን!
አይደለህም ያንድ ዘመን!
የሁሌ ፍልስፍና ነህ
የማትደረስ ድርሰት
የማትደፈር ድፍረት
የማትገጠም ግጥም
ተለየህ ሳንገጣጠም!
ሰለሞን፤
አይደለህም ያንድ ሰሞን!!
ጥቅምት 2010
   ለወዳጄ ለሰለሞን ደሬሣ

Read 5993 times