Monday, 13 November 2017 10:38

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(8 votes)

  “--ዛዴሞስ የታሰረበት ብልቃጥ ወደ ሰማየ ሰማያት ሲወረወር፣ ነፋስ ያመጣው ሀይለኛ ዝናብ አግኝቶት ኢትዮጵያ ምድር
አደረሰው፡፡ … ደብረዘይት ሆራ ዳርቻ ላይም ወረወረውና ተሰበረ፡፡ … ንጉሥ ሰለሞን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ያላስታወሰው አንድ
ነገር ቢኖር፣ ድግምቱ ውሃ ከነካው እንደሚረክስ አለማስተዋሉ ነበር፡፡--”
      

   “ጭስ ባለበት እሳት ነበር፣ ውሃ ባለበት ህይወት አለ፣ ያልተፈሳ አይሸትም” እንደሚባለው፣ “ያልተወራም አይሰማም” … የሚሏት አባባል የዋዛ አይደለችም፡፡
ወዳጄ፤ አንዳንድ የእምነት ተቋማት “የዚህ ዓለም ገዢ ሳጥናኤል ነው” … እያሉ ይሰብካሉ። … እንደ ምሳሌም ኢየሱስን ወደ ተራራው ጫፍ ይዞት ወጣ፡፡ … ምድርንም ሁሉ እያሳየው፤ “አንዴ ስገድልኝና … ይሄ ሁሉ ያንተ ይሆናል” … አለው። ተብሎ የተፃፈውንና ሌሎች መሰል ታሪኮችን ከቅዱስ መጽሐፍ ይጠቅሳሉ፡፡ … እስኪ ይቺን አንብቡ፡-
የዳዊት ልጅ ንጉሥ ሰለሞን (ጠቢቡ ሰለሞን)፤ በየጊዜው የተነሱበትን ጠላቶች እየመከተ፣ በጥበቡ ደግሞ ህዝቡን ሰጥ ለጥ አድርጎ በማስተዳደር ለረዥም ዘመን በአባቱ ዙፋን ተቀምጧል፡፡ … ሰለሞን ብዙ ሚስቶችና ዕቁባቶች በቤተ መንግሥቱ እንደነበሩትም ተፅፏል፡፡ የኛይቱን ‹ቱሪስት› ንግሥት ሳይጨምር፡፡
ንጉሥ ሰለሞን ዕውቀትና ብልሃትን የተማረው በእጅጉ ጠቢብና አስተዋይ ከነበረው ጓደኛው ‹ዛዴሞስ› መሆኑ ይተረካል፡፡ ዛዴሞስ በጥበብ የረቀቀ፣ በፍልስፍና የመጠቀ ነበር፡፡ … ብረት አንጥሮ ወርቅ የማድረግ ጥበብን (Alchemy) ጨምሮ የሚያውቀውንና የሰለጠነበትን ነገር በሙሉ ለጓደኛው ለሰለሞን አስጠንቶታል፡፡
ዛዴሞስ የሚኖረው ከጓደኛው ከንጉሥ ሰለሞን ጋር በቤተ መንግስቱ አንደኛው ጎን ውስጥ ነበር። … ይኸ ጠቢብ ቀንና ሌሊት በምርምር ስራው ላይ ስለሚጠመድ የአገሬው ሰዎች አይተውት አያውቁም፡፡ እንደውም በንጉሳቸው አስተዋይነትና ብልህነት በተገረሙ ቁጥር “ሳጥናኤልን ቤተ መንግሥቱ ውስጥ አስሮታል … ጥበብን የሚገልፅለት እሱ ነው፡፡” …. እያሉ ያሙታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ንጉሡ፣ ጓደኛው ዛዴሞስ ዘንድ ቀረበና፡-
“ከፀሐይ በታች የማናውቀው ነገር ይኖራልን?” … ሲል ጠየቀው፡፡
 ዛዴሞስም፡- “ንጉሥ ሆይ፤ ዕውቀት እንደ ሌላው ህዋስ በያንዳንዱ ቅጽበት የምትፈጠር፣ የምታድግ፣ የምትረሳ፣ የምትለወጥ፣ የምትሞት … እየበዛችና እየረቀቀች በሄደች ቁጥር የምትደበቅ፣ ቀላልና አስደሳች ግን ደግሞ አስሸፋች መንፈስ አይደለችምን?” … በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት፡፡
“መጨረሻዋስ ምን ይሆን?”
“መጨረሻዋና መጀመሪያዋ አንድ አይነት ይመስላል፡፡ … በያንዳንዱ ፍጡር ህይወትና ኑሮ ልክ ተመዝና እየተሰፈረች፣ ከሚያልፉት እየቀረች፣ ከመጪዎቹ እየተዋደደች… ትቀጥላለች፡፡”
“ስለ ሰው ዕውቀት ለይተህ ንገረኝ?”
“…የሰውም እንደዛ ይመስለኛል፡፡ … ኑሮውን የሚመራበት፣ ክፉና ደጉን ‘ሚለይበት፣ ሌሎችን ሰዎችና አካባቢውን መርምሮ ‘ሚረዳበት፣ በተለይ ደግሞ የእውነተኛ ደስታ ምንጭ የሆኑትን እንደ ንባብና ሙዚቃ የመሳሰሉትን የጥበብ መንገዶች ሲከተል፣ ፍቅር ርህራሄና ደግነትን ሲኖር፣ ቴክኖሎጂ፣ ሃይማኖትና ሳይንስን ለሰው ልጆች ጥቅም ሲያውላቸው፣ ራሱን በትክክል ከሌሎች ለይቶ ሲያውቅና በአለም ላይ የሚገባውን ቦታ በመረዳት በመንፈሳዊ ብፅዕትና (wisdom) ሲባረክ፣ ከአንድ ነገር መሆን … ሁሉንም ነገር ወደመሆን መቀየርና ‹ምስጢር› ራሱን ወይም በሌላ አነጋገር እግዜር ራሱን መሆን ሲችል ነው --- አወቀ እሚባለው፡፡ … ወደ መጀመሪያ ንፅህና መመለስ ያልኩህም እሱን ነው፡፡ …”
ንጉሥ ሰለሞን ጓደኛውን ከተሰናበተ በኋላ ብዙ ነገሮችን በሃሳቡ ሲያወጣና ሲያወርድ ቆይቶ … ‹ጥበብ›ን የተማረው ከጓደኛው መሆኑን፣የሚገዛው ህዝብ ባወቀ ጊዜ፣ ክብሩን የሚያሳንስበት፣ ሃሜቱም እውነት እንደሆነ የሚያረጋግጥበት መሰለው። … ውሎ አድሮም ልቡ ተንኮልን ተመኘ፤ ሸፍጥ በነፍሱ ላይ አደረችበት፡፡ … “ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደደው” … የሚለውን የአባቶቹን ቃል ዘነጋ፡፡ …
ንጉሱ፤ ባደረበት ቅናት ግፊት ተንኮሉን እንዴት እንደሚያሳካ ሲያስብና ሲያሰላስል ሰነበተ፡፡ … ወደ ጓደኛውም ተመልሶ በመሄድ፡- “ዛዴሞስ ጓዴ … ቀረ የምትለው፣ የምትነግረኝ ነገር የለምን?” … በማለት ጠየቀው፡፡
“ኧረ በፍፁም! … ምንም የለም” አለውና፤ ትንሽ አሰብ አድርጎ፣ “ከእንግዲህ የቀረህ ‹ራስህን የመሰወር› ጥበብና ‹የዘላለማዊነት› … ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ እሱ ደግሞ ፍፁም መሆን ላይ በሚደረስበት ጊዜ የሚቻል ‹ብቃት› ወይም ‹መሆን› እንጂ አንዱ ከሌላው የሚማረው ነገር አይደለም፡፡ … ሊገለፅበት የሚችል ቃል እንኳ አልተፈጠረለትም። … እንደው በልማድ ወደ ‹ምስጢርነት› መቀየር እንለዋን፡፡” ሲል አስረዳው፡፡  
ንጉሥ ሰለሞን፤ በጓደኛው ዓይን ራሱን ሲመለከት ገና ብዙ እንደሚቀረው ተገነዘበ፡፡ … ይህ ደግሞ በአእምሮው ውስጥ የጠነሰሰውን ተንኮል ይበልጥ እንዲያፋፋም ገፋፋው፡፡ ወደ መኖርያው ተመልሶም ለብዙ ቀናት ሲያስብና ሲጨነቅ ከረመ። ...ከብዙ ማሰላሰል በኋላም አንድ ዘዴ ብልጭ አለለት፡፡
እንደ ሌላው ጊዜ ወደ ጓደኛው ጋ በመሄድ፣ ስለተለያዩ ነገሮች እያወሩ ሳለ፣ በጨዋታ አስታኮ ጓደኛውን፡-
“እስቲ ‹መሰወር› እንዴት እንደሆነ አሳየኝ?” አለው፡፡
 ዛዴሞስም ምስጢሩን ሊገልፅ ብድግ አለ። … ሰምቷቸው ‘ማያቃቸውን እንግዳ ቃላቶች እያጉመተመተ፣ መጀመሪያ እንደ ባዘቶ ጥጥ ቡፍ ካለ በኋላ፣ ቀስ በቀስ ወደ እንፋሎት መሳይነት ተቀይሮ፣ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ ከነበረው ትንሽ ብልቃጥ ውስጥ እየገባ መታመቅ ጀመረ፡፡ … በንቃት ሲመለከተው የነበረው ጓደኛውም፤ ጨርሶ መከተቱን እንዳየ፣ በፍጥነት ብልቃጡን ግጥም አድርጎ ከደነው፡፡ … ጥቂት ቀናትም በየሄደበት ቦታ ሁሉ እየያዘው ቢጓዝም፣ ብልቃጡን ባየ ቁጥር ተንኮሉን እያስታወሰው ዕረፍት የሚነሳና ምቾት የሚያሳጣ ሆነበት፡፡ በዚህም የተነሳ ላንዴና ለዘላለሙ ሊገላገለው ፈለገ፡፡ በተማረው የአስማት ሃይልም በመታገዝ፣ ብልቃጡን እንዳይመለስ አድርጎ፣ ወደ ሰማየ ሰማያት ወረወረው፡፡ … እፎይም አለ፡፡ …
ንጉሡ፤ ዕኩይ ድርጊቱን ለመርሳት በእቁባቶቹ መሃል እየተመላለሰ፣ ራሱን ለማስደሰት በፅኑ ተጋ፡፡ … ነገር ግን የፈፀመው ክህደት ሰርክ ከፊቱ እየተደቀነ፣ ህሊናውን አቆሰለው፤ ፀፀት ውስጡን እየሰረሰረ ያፈራርሰው ጀመር፡፡ ይቅርታ ጠይቆ የሚነፃበት ጉዳይ ባለመሆኑም በእጅጉ አዘነ፡፡ … እየደከመ በሄደበት ጊዜም ሸክሙን ይቀንስለት እንደሆን በማሰብ፤ “…ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም! ሁሉም ነገር ከንቱ .. የከንቱ ከንቱ ነው!” በማለት ተናዘዘ፡፡ … ይህ ኑዛዜ እስከ ዛሬ ድረስ ከተፃፉት ኑዛዜዎች፤ ‹ድንቅ› የሚባል ሲሆን በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥም የተካተተ ነው፡፡
ዛዴሞስ የታሰረበት ብልቃጥ ወደ ሰማየ ሰማያት ሲወረወር፣ ነፋስ ያመጣው ሀይለኛ ዝናብ አግኝቶት ኢትዮጵያ ምድር አደረሰው፡፡ … ደብረዘይት ሆራ ዳርቻ ላይም ወረወረውና ተሰበረ፡፡ … ንጉሥ ሰለሞን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ያላስታወሰው አንድ ነገር ቢኖር፣ ድግምቱ ውሃ ከነካው እንደሚረክስ አለማስተዋሉ ነበር፡፡ አዛዴሞስ ለረዥም ዘመናት በስደት ሆራ ሀይቅ ውስጥ ኖረ፡፡ … መንፈሱ የማረካቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም ‹ቆሪጥ› እያሉ ይጠሩት ጀመር፡፡ … ንጉሥ ሰለሞን ከሞተ ከሶስት ሺ ዓመታት በኋላ ቆሪጥ በኢትዮጵያ እንደሚኖር በመረጋገጡ፣ አንዳንድ የአፍሪካ ነገሥታትና መሪዎች፣ በአሳቻ ሰዓት እየሄዱ እንደሚጎበኙት፣ ለወዳጅነታቸውም ምክር እንደሚለግሳቸው ይነገር ነበር፡፡
ዛዴሞስ (ቆሪጥ) የዛሬ አርባና ሃምሳ ዓመታት ገደማ ራሱን ወደ ሌላ ሰውነት ቀይሮ በአንድ የአውሮፓ ከተማ ሲዘዋወር ሲከታተሉት በነበሩት የአሜሪካ የፀጥታ ሰራተኞች ተጠለፈ፡፡ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ተወስዶ በካፒቶል ሂል ምድር ቤት፤ የምርምር ስራ እየሰራ እስከ አሁን ድረስ በከፍተኛ እንክብካቤ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ በየጊዜው የምናያቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችም የሱ ፍሬዎች ናቸው ይባላል፡፡
አዛዴሞስ፤ አንዳንዴ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ማለቱ አልቀረም፡፡ አንድ ጊዜ ታዲያ መልኩን ቀይሮ፣ በፒያሳ ጎዳናዎች ሲንሸራሸር፣ ሚስጥሩ እንዴት እንዳፈተለከ ሳይታወቅ ብዙ ሰዎች ከበው እየተከተሉት፤ “ነቢዩ ኤልያስ መጣ! … ነቢዩ ኤልያስ ይኸውና!” እያሉ ሲጮሁ እንደተለመደው በጥበቡ ራሱን ሰውሯል እየተባለም ይወራል፡፡
ወዳጄ ፡- ቀድሞ “ይቺን አንብባት” ብዬህ ነበር። … እስካሁን ያነበብከውን ማለት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ያነበብከውን እንድትረሳው እመክርሃለሁ። … ምክንያቱም ‹ተረት› ነው፡፡ … ግን በቀላሉ እንዳነበብከው በቀላሉ የምትረሳው ይመስልሃል? … መልሱን እኔ እነግርሃለሁ … ‹አትችልም!› … ‹ልማድ› የምንለው ነገር ልክ ግድግዳ ላይ በሙቅ እንደምናጣብቀው ወረቀት በቀላሉ ይለጠፋል። … ለማላቀቅ ግን አስቸጋሪና አድካሚ ነው፡፡ … አእምሮአችንም እንደዛ ነው፡፡ .. መጀመሪያ ‹እውነት› መስሎት የተቀበለውን ነገር እንዲተውና እንዲረሳ ብንነግረው በቀላሉ ‹በጄ› አይለንም፡፡ … በራሱ መንገድ መርምሮና አጣርቶ ያስወግደዋል እንጂ ‹እኛ› ስለፈለግን ብቻ አይሆንም፡፡  እውነትንም እንደዛ ነው እሚፈልገው፡፡ … ራሳችንን በራሳችን ስንዋሽ፣ ‹እንቢ› እያለ ‘ሚያስቸግረን ለዚህ ነው፡፡
ሂንዱኢዝም፣ ቡድሂዝምና ጄኒዝም ለሚባሉት እምነቶች central and powerful experience የሚባለው mysticism (ሚስቲሲዝም) መገለጫው፣ የእያንዳንዳችን አእምሮ ‹የራሴና የራሴ ብቻ ዕውነት› ብሎ በሚቀበለው ነገር ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው “ሞቼ ተነሳሁ”፣ “እግዚአብሔር አነጋገረኝ”፣ “የሞተ ዘመዴን አገኘሁት” ቢል ሌላው አያምነውም፡፡ … ለባለቤቱ ግን ዕውነት ከሆነ ‹የሱ ብቻ እውነት!› ሆኖ ይቀራል ማለት ነው፡፡
ወዳጄ፤ ወደ ተረታችን ስንመለስ፣ዛዴሞስ ምስጢሩን ለቅርብ ጓደኛውና ወዳጁ በመናገሩ ወዳጁ እንዳጠመደውና ሊያጠፋው እንደሞከረ አይተናል፡፡ ነገሩ የሆነው ከሶቅራጥስ በፊት መሆኑ እንጂ ከሶቅራጥስ በኋላ ቢሆን ኖሮ ዛዴሞስ ይጠነቀቅ ነበር፡፡
 ሶቅራጥስ፡- “ምስጢርህን ለማንም አትናገር። ከተናገርክ በተናገርከው ነገር በራሱ ትታሰራለህ። … ምነው በቀረብኝ ኖሮ፣ብለህም ታቃትታለህ፡፡ … የመከነ ሀሳብ፣ አንዴ የተወረወረ ጦርና ያለፈ ጊዜ እንደማይመለስ ሁሉ ---- ከአፍ የወጣም አፋፍ መሆኑን አትርሳ” … ይልሃል!!
ሠላም!!!

Read 4406 times