Monday, 13 November 2017 10:35

ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና - ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ‹የጥንታዊ ኢትዮጵያን ጥበብ› የሚዳስሱ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ስውተረተር፤ ‹Encarta 2009›ን ስለ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደያዘ ጠየቅኩት:: የአውሮፓ ነው ያለውን ከጥንታዊት ግሪክ ጀምሮ እስከ ዘመናዊ አሜሪካ ድረስ ያሉ የፍልስፍና ዓይነቶችን ዘርዝሮ አቀረበልኝ፤ ወደ ህንድና ቻይናም ሔዶ አማረጠኝ፤ ወደ መካከለኛው የእስልምና ዓለም ፍልስፍናም ወስዶ አስጎበኘኝ። ምንም እንኳን በዚህ መልክ ቢያማርጠኝም፤ እኔ ግን ‹ጥያቄዬ አልተመለሰም› አልኩት፡፡ ሐቀኛው Encarta እንኳን በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአፍሪካ፣ ፍልስፍና መኖሩን እንዳማያውቅ እቅጩን አረዳኝ፡፡ ይህም የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የተናገሩትን አስታወሰኝ፡፡
ዶ/ር አክሊሉ፣ ለአሜሪካን ኮንግረስ የአፍሪካ ክፍል በአቀረቡት የመወያያ ሐሣብ፤በእ.ኤ.አ.1958 በካይሮ ላይ ‹Mutual appreciation of western & Eastern cultural values› በሚል ርዕስ በተካሔደ ጉባኤ፤ የአፍሪካ አስተምህሮ አለመነሳቱ አስገርሟቸው ‹አፍሪካ የት ናት?› የሚል ጥያቄ ለመጠየቅ መገደዳቸውን አንስተው፣ የተሰጣቸው መልስም ‹አፍሪካ ያላት ማሐይም ማኅብረሰብ ነው› የሚል ዓይነት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እኔም Encarta ሐቀኛ መልሱን ከነገረኝ በኋላ ብዙ ጥያቄዎች ተግተለተሉብኝ፡፡
ከጥያቄዎቹ መካከል አንዱ፤ ‹ለምን የእኛ ዕውቀት ሳይመዘገብ ቀረ?› የሚል ነው፡፡ Encyclopedia of Philosophy የሚለውን ባለ አሥር መድበል የዕውቀት መዝገብ አገላበጥኩት፡- ‹ከየት ላምጣልህ?› የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት፡፡ ጉድ! ብላችሁ ሃዘን እንዳትቀመጡ፤ ሰጋሁ፡፡ ቢያንስ እነ ዘርዓ ያእቆብን አለማወቁ አይገርማችሁም? እውን ኢትዮጵያ፤ የእኔ የምትለው የራሷ ጥበብ የላትም? ነው እንዳይታወቅ የተፈለገበት ምክንያት አለው? ግን ለምን? ኢትዮጵያ አሁን እንዳለችበት ሳትሆን በፊት በተለይም በጥንት ዘመናት የሥልጣኔዎች ምንጭ የነበረች ሀገር ናት። በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱ ጉድፈቶችን ለመዛግብተ ቃሎቻቸው ማብራሪያ እንደ ምሳሌ ለማስቀመጥ የፈጠኑ አውሮፓውያን፤ ለምን በአጠቃላይ የአፍሪካን በተለይም የኢትዮጵያን ፍልስፍና መዝግበው ለማሳወቅ ሳይችሉ ቀሩ? ከእነ ደካርትና ካንት ፍልስፍና ጋር ይመሳሰላል የሚባለውን የዘርዓ ያዕቆብን ፍልስፍና ያላካተቱበት ምሥጢሩ ምንድነው? አለማወቅ? ዘረኝነት? ወይስ ሌላ ጉዳይ?
 የኢትዮጵያ ፍልስፍና ማጠንጠኛ
ከላይ የጠቀስኳቸውን ጥያቄዎች እያብሰለሰልኩም፤ ‹ራሱ ፍልስፍና ምንድን ነው?› የሚል ጥያቄ መጣብኝ፡፡ በጣም የከነከናችሁን ጥያቄ ስትጠይቁ፣ መልሱን ቶሎ ካላገኛችሁ የበለጠ ጥያቄ ይጎለጎልባችሁ የለ? ስለዚህ የፍልስፍና ምንነትን ማብሰልሰል ጀመርኩ፡፡ ፍልስፍና በነጠላ ትርጉሙ፤ ‹ጥበብን ማፍቀር› ማለት እንደኾነ  መጀመሪያ ቃሉን ተናገረው ከተባለው ከፊጣጎረስ (Pythagoras) መረዳት ችያለሁ፡፡ ሶቅራጥስም የፍልስፍና መሠረቱ መደነቅ መቻል መኾኑን ነግሮኛል፡፡ በጥበብ ፍቅር ተነድፎ በመደነቅ ምርምር የሚደረገውም ትክክለኛው እውነት ጋር ለመድረስ መሆኑንም ተረድቻለሁ፡፡ እና ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው የዚህ ዓይነት ጥበብ አልነበራቸው? ይህንን ለማረጋገጥም የኢትዮጵያውያንን የጥንታዊ የትምህርት መስኮች (ጉባኤያት) መዳሰስ አስፈላጊ ኾኖ አገኘሁት፡፡ በዚህም ‹የኢትያጵያ ፍልስፍና ምን ዓይነት ነው?› ለሚለው ጥያቄ መልሱን ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ ከዚያም የሚከተሉት ነጥቦች የኢትዮጵያውያን ጥበብ ዋና ዋና ማጠንጠኛዎች መስለው ታዩኝ፡፡
 ሃይማኖት የጥበብ መነሻና ማዕቀፍ
የኢትዮጵያ ጥበብ መሠረቱ ዕውቀት ሳይሆን ሃይማኖት (እምነት) መሆኑን ተረዳሁ፤ ስለሆነም ‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።› ይላል፡- በኢትዮጵያ የተመለከትኩት ፍልስፍና። በዚህም የተነሳ፤ ‹በእግዚአብሔር መኖር ላይ ተማምኖ መፈላሰፍ ይቻላል? ወይስ አይቻልም?› የሚለው ጥያቄ መጥቶ ድንቅር አለብኝ፡፡ ለዚህ የሚሆን መልስ ሳፈላልግም፣ አብዛኞቹ የጥንታዊት ግሪክ ፈላስፎች፣ የአንድ አምላክ መኖርን የሚደግፉ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ እነ ኤራቅሊጠስ፣ ዜኖፎን፣ ሶቅራጥስ፣ ፕሌቶ፣ አርስጣጣሊስና ሌሎችም አጠራራቸው ቢለያይም፣ በእግዚአብሔር መኖር ግን እንደሚስማሙ ሳያብሉ መሰከሩልኝ። ለማጠናከር ብዬ ወደ ሮማያውያን ተሸጋገርኩ። እነ አውግስቲን ኋላም እነ ቶማስ አኳይነስ “የፍልስፍናችን መሠረትና ጉልላት የእግዚአብሔር መኖር ነው” ብለው መለሱልኝ፡፡ ምስክር በሦስት ይፀናል ብዬ ወደ ዘመናዊያን ፈላስፎች ተጠጋሁ፤ እነ ደካርት፣ በርክሌይ፣ ካንትና መሰሎቻቸው የፍልፍናችን መሠረት እግዚአብሔር ነው አሉኝ። ከዚህ በኋላ እንግዲያውስ፣ የኢትዮጵያውያንም ጥበብ መሠረቱን ‹እግዚአብሔርን መፍራት› ማድረጉ ከፍልስፍና ውጭ አያስወጣውም አልኩኝ። በእምነት ላይ የተመሠረተ ፍልስፍና አይኖርም ያለው ማን ነው?
 እንደውም ፍልስፍና በእምነት ላይ ሲመሰረት አሳማኝነት ይኖረዋል ብዬ ገመትኩ፤ እምነት አልባ ፍልስፍና ግን መሠረቱ አጨቃጫቂ ነውና፤ አጨቃጫቂ ነገርም ተቀባይነት አይኖረውም፡- የሚል እምነት ሰረፀኝ፡፡ ምክንያቱም የፍልስፍና መሠረት እምነት ነው ካልን፤ የእምነት ዋናው መሠረትም፣ የእግዚአብሔር መኖር ነው፤ እግዚአብሔር ደግሞ በባሕርዩ ፍጹም ስለሆነ ሌላ አያስፈልገውም፤ የአስተሳሰብ ሁሉ መደምደሚያ ነው፡፡ ነገር ግን ፍልስፍና የእምነት መሠረት ከሌለው በምን መነሻ መስማማት ይቻላል? ስለዚህ የኢትዮጵያውያንም ፍልስፍና በእምነት ላይ መመሥረቱ አስተውሎታዊ ነው እንጂ አለማወቅ አይደለም፤ ብዬ ወሰድኩት፡፡
 የጥበብ በሥነ ምግባር መቃኘት
ሁሉም ጥበባቸው በሥነ-ምግባር የተቃኘ መሆኑን ዐየሁ፤ ለዚህም የተረጎሟቸው የታዋቂ ፈላስፎች ጽሑፎች ሳይቀሩ በምስክርነት አረጋገጡልኝ፡፡ አንጋረ ፈላስፋን (የፈላስፎች አነጋገር) አገላብጬ ተመለከትኩት፤ የብዙ ፈላስፎች ሥነ ምግባራዊ ንግግር ወይም መልካም ምክር በኢትዮጵያውያን መንፈስ ተቃኝቶ ተሰብስቦበታል፡፡ እንደውም አብዛኞቹ የመጽሐፉ ጥቅሶች፤ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የራሳቸውን ፍልስፍና ደብቀው በሌሎች ፈላስፎች ስምና ባልታወቁ ፈላስፎች መልክ የሰገሰጉባቸው መሆናቸውን ጠረጠርኩ፡፡ ጥርጣሬዬ ያለምክንያት አይደለም፤ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትህትና ስለሚያጠቃቸው ዐዋቂ ሰው መስለው መታየት እንደማይፈልጉ ከጻፏቸው የሃይማኖት መጻህፍት   ተገንዝቤአለሁ፡፡ ስለዚህ ይህም ጥርጣሬ የኢትዮጵያውያንን የትህትና ልምድ በማየት የመጣ ነው፡፡ በተጨማሪም የዘርአያዕቆብንና የወልደሕይወትን ፍልስፍናዊ መጣፎች ተመለከትኩ፤ በዋናነት በሥነምግባር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ወይም በሥነ ምግባር ፍልስፍና የተቃኙ ናቸው፡፡ ሥነ-ምግባር ደግሞ አንዱና ዋናው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መሆኑን ዐውቃለሁ። እንደውም ሥነ-ምግባር አልባ ፍልስፍና ሰብዕና አልባ ዕውቀት እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ስለዚህ የጥንት ኢትዮጵያውያን ፍልስፍና በሥነ ምግባር ገመድ መሸበቡ፣ መልካምና ጥሩ ፍልስፍናዊ ዕይታ መሆኑን አጤንኩኝ፡፡
  የጥበብ ዕምቅነት፣ ኅብራዊነትና አመሥጥሯዊ ትርጓሜ
ፍልስፍናቸው በዋናነት በኅብር ትርጓሜያት የሚፈታ መሆኑንም የተመለከትኩት መለያው ነው፡፡ በመጀመሪያ ቅኔዎቻቸውን ተመለካከትኩ፤ የሚደንቁ ዕይታዎችንና ልዩ አቀራረቦችን ሳገኝ ‹ይህማ የትም የማይገኝ የኢትዮጵያውያን ብቸኛ ፍልስፍና ነው!› እስከማለት ደረስኩ፤ ተደንቄ፡- መፈላሰፍ ልጀምር! ቅኔያቸው ሥጋና ነፍስ የተዋሐዱበት እንጂ በአጥንትና ሥጋ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ሰው ሕይወት ዘርቶ የሚንቀሳቀሰው ነፍስ ያለው ከሆነ ነውና፡፡ ይህ ደግሞ የሚገለፀው በኅብርነት ነው፡፡ ተፈጥሮ የተሠራችው ታምቃ በኅብርነት ስለሆነ የኢትዮጵያም ጥበብ ኅብርነት ማጠንጠኛው መሆኑን ታዘብኩኝ፡፡ ይህንን በሚመለከት የኔታ ዓለማየሁ ሞገስ፤ “መልክዐ-ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሐፋቸው፡-
‹የኅብር አገር ጎጆ መግቢያና መውጫው፣
ሊቃውንት የሠሩት ኹለት በር አለው፤
ምንም ኹለት ቢኾን ሦስት አራትም፣
ጠባብ ስለኾነ ደንቁር አይገባም፡፡› ብለዋል፡፡
የትርጓሜ መጻሕፍታቸውን ቃኘሁ፤ እያጋጩና እያነጻጸሩ ሲያብራሩና ትክክለኛውን አንድምታ አንጥረው ሲያወጡ ዐይቼም፤ ‹እና ከዚህ በላይ ፍልስፍና ምን ዓይነት ነው!?› ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፤ ለምንስ ትርጉም አስፈለገ? አልኳቸው በጨዋነቴ፡፡ ‹ፊደል ይገላል፤ ምሥጢር ግን ሕይወትን ይሠጣል› ብለው የተሸፈነውን፣ ነፍስ የሆነውን መልዕክት ለመረዳት፣ መተርጎም እንዳለበት አስረዱኝ፡- “አዬ! የልጅ ነገር፤ አሁን ይኼ ይጠየቃል!” ብለው እኮ ነው፡፡
እንዲሁም አባባሎቻቸውን፣ ምሳሌያዊና ፈሊጣያዊ ንግግሮቻቸውን፤ እለታዊ ጨዋታቸውን በማየት ድንቅ ለዛቸውንና ዐስተውሎታዊ ንግግራቸውን፣ በዐጭሩ እነሱ ‹እንደ ወርቅ አንከብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ› እንደሚሉት ሆኖ አገኘሁት። በዚህ ላይ ወሬ አምሮኝ፣ በልጅነት ጠጋ ጠጋ ብላቸው እኮ፣ ለልጅ በሚገባ መልኩ ‹ዕንቆቅልህ!› ማለታቸው አይቀርም! እኔማ ምን እመልሳለሁ ‹ምን ዐውቅልዎት!› ከማለት ውጭ፡፡ ጉድ! ምሥጢር እየሣበኝ እኮ ብዙ ወሸከትኩ፡፡ በጥቅል ላውራ፤ አዎ በጥቅሉ በኢትዮጵያውያን ፍልስፍና፤ መንፈሳዊነት የሌለው አስተያየት የለም፤ መንፈሳዊነቱም ያለ ሥጋዊ ግዙፍ ነገር አይገለጽም፡፡ ስለዚህ ኅብረ-ነገር (ኅብረ-ፍልሰፍና) የኢትዮጵያውያን ዕውቀት ድረ-ማግ ነው፡፡
  አስማትም ጥበብ ነው!
ከዚህ ሌላ ስለ ደብተራዎች ድንቅ ግብር (አስማተ-መተት) አንስቼ አላውራ እንጂ እነሱን እኮ ጠላት አይደፍራቸውም! አልተወራላቸውም እንጂ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቷን ጠብቃ የኖረችው በእነሱ የመተት ጥበብ ጭምር ነው! … ካላመናችሁ ባለ ቅኔ ‹ገሞራው›ን ምስክር ልጥራ፡- የደብተራውን ግብር ያውቃልና እንዲህ አለ፡-
‹…በሩቅ አነጣጥሮ- በራዳር አስማቱ፣
ቶርቦዶ የሚያደርግ- ባንደርቢ ድግምቱ፣
ካድማስ የሚያወርድ- ሳተላይት ምትሃቱ፣
ድባቅ የሚመታ- ባዙቃ አንደበቱ፣
ድምጥማጥ አብንኖ- ጠላት አርጊ ከንቱ፣
ታላቅ ግብር(Role) ነበረው- ደብቴ ታጋይ ብርቱ፣…..›
(አቢሲኒያ መጽሔት ቅጽ 1፣ ቁጥር 16 ጥር 1993)
በሞቴ ስለ ደብተሮች አንድ ታሪክ ላውራ! የልጅ ወሬም ቢሆን ያዳምጡኝ፡፡ ወሎ ውስጥ ነው አሉ፡- ላስታ አካባቢ፡፡ አንድ መሪጌታ ናቸው፡- ድብትርናቸው ያልታወቀባቸው ሊቅ፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን የቀለም ቀንድ ያደርጉታል፤ አጅሬው ከሳቸውም አልፎ ጠቢብነትን ይዞ እቤቱ ‹ከች!›። አንድ ቀን ታዲያ እናቱ ክሽን ያለች ዶሮ ወጥ ለአባወራዋ ትሠራለች፤ አባት ግን ከልጅ ጋር መሻማት አልፈለጉም፡፡ ስለዚህ ልጃቸው ከቤት የሚወጣበትን ዘዴ ቀይሰው ዘመድ ጋር መልዕክት ይልኩታል፤ ይች ዘዴ የገባችው ልጅ ደግሞ በድግምቱ ድስቲቷን ቆልፏት ይሔዳል፤ ማን ወንድ ይክፈታት! አባት ተናደዱ፤ ልጁም መልዕክቱን አድርሶ መጣ፡፡ የተናደዱት አባት ግን ልጃቸው ገና በሩ ላይ ሲገባ ዐሠሩት፡- መውጣት አይችል መግባት አይሆንለት፤ የበር መዝጊያ መስሎ ቆመ፡- እንሞካከር ማለት እኮ ነው - በደብተራኛ፡፡
እሱስ ቢሆን ያስመሰከረ ሊቅ አይደለ? አባቱን ዐያቸው፤ ፊት ለፊቱ በአንድ እግራቸው መሬት እረግጠው በሌላው ደግሞ ካልጋው ጠርዝ ላይ አንፈራጠው ይመለከቱታል፡፡ ሊቁ ልጅም ጦርነቱን ዝም ብሎ አልተሸነፈም፤ አባቱን ከመሬትና ካልጋ ጋር ጠፈራቸው፡- መዘዋወር የለ! መንቀሳቀስ። አሁን ተግባቡ፤ “በል ልጄ ፍታ! ልፍታ!” አሉ አባት፤ ተፈታተው አብረው በሏታ! ክሽንዋን የዶሮ ወጥ። ጎበዝ ለጎበዝ ከተገናኘ ይከባበራል፡፡ አዩልኝ፤ ይህንን ጥበብ! የመስተፋቅር ጥበባቸውንማ ሁሉም የሚያውቀው ነው! ምን አወራዋለሁ!፡- ካስነኩ በቃ! በፍቅር ክንፍ ነው፡- እንቅልፍ የለ! ምግብ አያሰኝ! ዝም ብሎ በፍቅር መንፏቀቅ!
ከፊደል እስከ ሰዋሰው ሥርዓት ያለው ጥበብስ?
በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዕውቀት መዋቅራዊ ጥበብ ተገረምኩ፡፡ ከፊደል ገበታ ጀምሮ እስከ ሰዋሰዋዊና አጠቃላይ የቋንቋ መዋቅር ስልታቸውን ሳይ መልሴ ምን ሆነ? ‹ዕፁብ! ዕፁብ! ውእቱ!› የፊደል ገበታ እኮ የኢትዮጵያ ማንነት የተጻፈበት ካርታ ነው፡- የሚያነበው ቢገኝ:: ስለሆነም ነው ሊቁ አስረስ የኔሰው፤ ‹“ፊደል ሐውልት ነው … ፊደል መልክ ነው … ፊደል አባት ነው … ፊደል ልጅ ነው … ፊደል ወሰን ነው … ፊደል ዓላማ ነው … ዓላማም የኩራት ምልክት ነው፡፡ ኩራትም ነፃነት ነው፡፡ … የማንኛው ነገር መጠቅለያ ፊደል ነው፡፡” ብለው የመሰከሩት፡፡ (አስረስ የኔሰው፤ “የካም መታሰቢያ የኢትዮጵያ ፊደል መሠረትነት መታወቂያ” 1951 ዓ.ም)፡፡ አረ ለመሆኑ! የእኛን ፊደል የሚያስንቅና የሚቀድም የዓለም ፊደል (አልፋ ቤት) ይምጣና እስቲ ይወዳደር ብዬ ልፎክር እንዴ? ይኸው ፎከርኩ!
የሰዋሰው መዋቅሩም እኮ የተፈጥሮ ግልባጭ ነው፤ ምን ልበል!:- ሰማይና መሬት በዕውቀት የተገናኙበት መሰላል ማለት እንጂ፡፡ በአዕማዳት ቆሞ፣ በአለቃ ተደራጅቶ፣ በሠራዊት የሚጠበቅ፣ በመራሂያን የሚፍታታ፣ በዓቢይና በንዑስ አግባባት እየተዋሐደና እየተበተነ የሚታሠር አስደናቂ የዕውቀት ድርጅት ነው እኮ ሰዋሰዋችን! ስለዚህ የዕውቀት ድርጅት እኔማ ምን እላለሁ? ሊቃውንቱ ቢያወሩት ይሻላል እንጂ! የእኔ ግብር ‹አባ በሌሉበት…› ዓይነት ነው፡፡
በአጠቃላይ ስለ ባህላችን ልናገር እንዴ? ስለ ትውፊታችን ልመስክር እንዴ? ስለ ገዳ ሥርዓት፣ ስለ ሥነ መንግሥት፣ ስለ ዘመን አቆጣጠራችን፣ … ስለተጠየቅ ልጠየቅ፣ ስለ በልሃ ልበለሃ--- ክርክር ላውራ እንዴ? ጊዜ አይበቃማ! ባላዋቂነት ይበላሻላ! አቅም የለማ!... በዐጭሩ የኢትዮጵያውያንን አስደናቂ ፍልስፍና ተመልክቼ፣ ጥበበኛነታቸውን ማረጋገጥ ቻልኩ፡፡ ከዚያም እንዲህ አልኩ፤ ‹እኔ የዚህን ያህል ዐይቼ፣ ፍልስፍናቸው ከማረከኝ፣ ዐስተዋይ የፍልስፍና ሊቅ ቢፈትሸውማ! ምን ሊል ነው?› ግን እስከዛሬ በአግባቡ ያልተፈተሸው ለምንድን ነው? መልሱን በአግባቡ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በወፍ በረር የሞካከሩት እንዳሉ ግን መመልከቴን አልሸሸግም፡፡
ማሳረጊያ
ሐሣቤን ልቋጭና ልሰናበት፡፡ በእኔ አቅም የኢትዮጵያውያንን አስገራሚ አስተውሎቶች፣ የጥበብ ፍቅር፣ እውነት ለማግኘትና ለማረጋገጥ የሚሔዱበትን እርቀት ዐይቼ ተደንቄያለሁ፡፡ እኔ እንደተረዳሁት ኢትዮጵያውያን የሥልጣኔው ምንጭ ነበሩ፡፡ የሥልጣኔ ምንጭ ለመሆን የቻሉት ደግሞ የራሳቸው ዐተያይ፣ አስተምህሮና የዕውቀት ክምችት ስለነበራቸው ነው፡- ገና ጥንት፡፡ ሊኖራቸው ከሚችለው ዕውቀት ውስጥ ደግሞ ፍልስፍና ቅድሚያውን ይይዛል፡፡ ስለዚህ ‹ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ፍልስፍና ያዳበሩ ሕዝቦች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው› ብዬ ደመደምኩ፡፡
 ሆኖም በውስጤ ለተፈጠረብኝ ‹ለምን?› የሚል ጥያቄ፣ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ የእኛን ፍልስፍና፤ ዓለም አቀፍ መዝገበ ቃላትና ዕውቀተ መዝገብ የማያውቁት፣ በእኛ ስንፍና ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወይስ የእኛ ፍልስፍና እንዳይታወቅ  ማዕቀብ ተደርጎብናል? ችግሩ ከእኛ ከሆነስ፣ ለምን ፍልስፍናችንን ለቀረው ዓለም ለማሳወቅ ዳተኛ ሆንን? እስቲ መልስ አምጡ!

Read 1901 times