Print this page
Monday, 13 November 2017 10:31

‹‹…ካንሰር ተከሰተ ማለት…የመጨረሻ… ››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(1 Vote)

  ‹‹….እኔ የመጣሁት ከደብረዘይት ነው፡፡ የአምስት ልጆች እናት ነኝ፡፡ ለረጅም ጊዜያት ታምሜ ቆይቻለሁ። ከፊት ለፊት ከእንብርቴ በታች የተድበለበለ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ መንገድ መሄድ ያቅተኛል፡፡ መንገድ ሄጄ ስመለስ የግድ አልጋ መያዝ ነበረብኝ፡፡ በቃ መንቀሳቀስ አልችልም፡፡ ሆድሽን ወደላይ ደግፈሽ ያዥው ያዥው ይለኝ ነበር፡፡ ከአንድ አመት ወዲህ ግን ነጭ ፈሳሽ ይፈሰኝ ጀመር። እሱን ዝም ብዬ ስከታተል ጭራሹንም ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ፈሰኝ ጀመር፡፡ በአለሁበት አካባቢ ወዳለው ሐኪም ቤት ስሔድ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ወዳለበት መሔድ አለብሽ ስለአሉኝ ወደጥቁር አንበሳ ተላልፌ ነበር። ከጥቁር አንበሳ ነው ወደዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የመጣሁት። እግዚአብሔርን የማመሰግነው ይህ ሆስፒታል ባልጠ በቅሁት መንገድ በፍጥነት ከሕመሜ ገላግሎኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት ማህጸኔም ጭምር እንደወጣ ተነግሮኝ በጸጋ ተቀብዬዋለሁ፡፡››
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ታካሚ
ባለፈው እትም የሴቶች የመራቢያ አካል ካንሰር ሕመም ሕክምናን በሚመለከት ከዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የ Gynecology oncologist ነት ትምህርት ተማሪ (ለመመረቅ ጥቂት ወራት የቀራቸው) የሰጡትን ማብራሪያ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ የ Gynecology oncologist ነት ትምህርት በአሁኑ ወቅት የቅዱስፓውሎስ ሚሊኒ የም ሜዲካል ኮሌጅ ካሪኩለም ቀርጾ በውጭ አገር ከሚገኙ ተቋማት ጋር ስምምነት በማድረግ በመስጠት ላይ እንደሚገኝና  ትምህርቱም የሚሰጠው በትምህርት ክፍል ተቀምጦ ሳይሆን በስራ የተደገፈ ወይንም ስራውን እየሰሩ መሆኑን ባለፈው እትም አስነብበናል፡፡ ከአሁን ቀደም  የካንሰር ህክምና በአጠቃላይ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረ ሲሆን ትምህርቱም ከአሁን ቀደምም በሰፊውና ቀጣይነት ባለው መንገድ ሲሰጥ ነበር ሊባል እንደማይችል ባለሙያው ባለፈው ማብራሪያቸው አውስተዋል፡፡ እንደሚታወቀው አሁንም የጨረር ሕክምና የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡
ሆስፒታሎችን ከመገንባትና የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶችን ከማሟላት እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎችን ብዛት እና እውቀታቸውን ወይንም ችሎታቸውን ከማጠናከር ባሻገር የህመም ተኞች ቁጥርንስ እንዴት መቀነስ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ ማብራሪ ያቸውን ሰጥተዋል፡፡
የካንሰርን ሕክምናን በሚመለከት አስቀድሞ መከላከሉ  አንዱ የስራው አካል መሆን የሚገባው ነው። ካንሰር ከመከሰቱ በፊት መከላከል ቢቻል እጅግ ተመራጩ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የሴቶች የመራቢያ አካላት ካንሰሮች ሊከላከሉአቸው የሚቻሉ አለመሆናቸው አስቸጋ ሪው ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ልንከላከለው የምንችለው የካንሰር አይነትም አለ፡፡ እሱም የማህ ጸን በር ወይንም ጫፍ ካንሰር ነው፡፡ ይህ በአገራችን እጅግ ብዙ ሴቶችን የሚያሰቃይ የካንሰር ህመም አይነት ነው፡፡ በሀገራችን ተንሰራፍቶ ያለውን የማህጸን በር ካንሰር ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ካንሰር ምርመራ በማድረግ እና አጋላጭ ሁኔታዎችን በማስወገድ መከላከል ይቻላል። ይህን የካንሰር ሕመም ተከላከልን ማለት በኢትዮጵያ ያለውን የመራቢያ አካላት ካንሰር ቁጥር በከፍተና ሁኔታ መቀነስ ቻልን ማለት ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰርን መከላከል ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ አጋላጭ ነገሮችን ማስወገድ በመሆኑ እነዚህም፡-
በልጅነት የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግን፣
በግብረ ስጋ ግንኙነት አማካኝነት ለሚተላለፉ በሽታዎች መጋለጥን፣
ከአንድ ሰው በላይ የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግን?
ሲጋራ ማጤስ እና የተለያዩ እጾች ተጠቃሚ መሆንን፣
የሰውነት የመከላከል አቅምን ለሚቀንሱ በሽታዎች መጋለጥን…ወዘተ ያካትታል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትንና መሰል አጋጣሚዎችን በማስወገድ የማህጸን በር (ጫፍ) ካንሰርን ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል ይቻላል፡፡
ይህ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ በሽታ እንደመሆኑ ሌላው የመከላከያው መንገድ ክትባት መውሰድ ነው፡፡ ይህ የማህጸን በር ካንሰር ከማንኛውም አይነት የካንሰር ሕመም ለየት የሚያደርገው ካንሰሩ ከመከሰቱ በፊት የሚከሰት ለውጥ መኖሩ ነው። እነዚህ ለውጦች ወደካንሰርነት ከመቀየራቸው በፊት አመታትን ያስቆጥራሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህን የሚከሰቱ ለውጦችን አስቀድሞ በምርመራ ማወቅ ካንሰሩ እንዳይከሰትና እንዳይራባ መንገድ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህም በአጠቃላይ እድሜአቸው ከ30-49/ አመት የሆናቸው ሴቶች ምርመራ እያደረጉ አስቀድሞ የጤናቸውን ሁኔታ እንዲያረጋግጡ በአገር ደረጃ እየተሰራበት ነው፡፡
ሌላው የካንሰር አይነት ከማህጸን ዘርፍ የሚነሳው ኦቫሪያን ካንሰር የሚባለው ነው፡፡ ይህን የካንሰር ሕመም አስቀድሞ ማወቅ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ እድሎች የሉትም፡፡ ኦቫሪያን ካንሰር አጋላጭ መንገዶች አሉት፡፡
ልጅ አለመውለድ፣
ልጅ ወልዶ ጡት አለማጥባት ፣
በዘር የሚተላለፍ የጤና ችግር…ወዘተ
ከላይ የተጠቀሱትን ለኦቫሪያን ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶች  አስቀድሞ መከላከል አይቻልም፡፡ ነገር ግን ማንኛዋም ሴት ስለጤንነትዋ አስቀድማ ምርመራ የምታደርግ ከሆነ ችግሩን ለከፋ ደረጃ ሳይደርስ ማስወገድ ታካሚዋንም ሙሉ በሙሉ ከህመምዋ መፈወስ ይቻላል፡፡
በካንሰር ሕክምና ዙሪያ እንደችግር የሚታዩ አንዳንድ የታካሚዎች ባህርይ ሊጠቀስ ይቻላል ዶ/ር ታደሰ እንደገለጹት፡፡ ለምሳሌም፡-
በጨረር ሕክምናው ዙሪያ ከሚስተዋሉት ነገሮች በጨረር ሕክምናው ወቅት ጨረሩ ዝም ብሎ በሰው ላይ የሚረጭና ሌላ ጉዳት የሚያደርስ ተደርጎ መወሰዱ አንዱ ስህተት ነው፡፡ የጨረር ሕክምናው በተለያዩ መሳሪያዎች እገዛ ሕመሙ በተከሰተበት ወይንም አስፈላጊ በሆነው ቦታ ላይ የሚሰጥ እንጂ ጨረሩ የታካሚውን ሌላ አካል ቀውስ ውስጥ የሚከት አይደለም፡፡ ጨረር በአይን የሚታይ ነገር ሳይሆን ጨረርን ሊያፈልቁ የሚችሉ ትናንሽ መድሀኒት ነገሮች ወደሰ ውነት ውስጥ የሚገቡበት ሕክምና ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ታካሚዎች የጨረር ሕክምና ሲታዘዝላቸው ሁሉ ነገር ያበቃለት ነው ብለው ስለሚያስቡ ህክምናውን ትተው ወደቤታቸው የሚመለሱ አሉ፡፡ ይህ ግን ስህተት መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት፡፡
የመራቢያ አካላት ካንሰር ሕመም ተከስቶ ወደሕክምናው ከመጡ በሁዋላ ኦፕራሲዮን እንደሚያስፈልጋቸው ሲገለጽላቸው …ኦፕራሲዮን አልደረግም….ቢላዋ ከሚነካኝ ከነሙሉ ሰውነቴ ልሙት ብለው ወደቤታቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይም ከገጠር አካባቢ የሚመጡ ታካሚዎች ማንንም ሳያማክሩ በቀጠሮአቸው ቀን ከሐኪም ዘንድ ከመቅረብ ይልቅ ወደቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡
ሌላው ሐኪሙ ለታካሚው በቀጥታ የህመሙን ደረጃ ገልጾ በሚደረገው ሕክምና በዚህ ደረጃ ልትድን ትችላለህ…ካልተሳካ ደግሞ የሚከተለው ነገር ይህ ነው…ብሎ ማስረዳት የግድ ይጠበቅበታል፡፡ ታካሚውም ስላለበት ደረጃ ማወቅ መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን የሕመሙ ደረጃ እና ከህመሙ የመፈወስ ወይንም ይብሱንም ሊከሰት የሚችል ነገር መኖሩ ሲነገር…አሃ… ይሄማ ከሆነ ይቅርብኝ …የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
 ሁሉም ታካሚ ማለት ይቻላል ከሕክምና በሁዋላ ሙሉ በሙሉ መዳንን ብቻ ጠብቆ ስለሚመጣ ቅንጣት ታክል ችግር ሊከሰት ይችላል ተብሎ ሲነገር ሕክምናውን መቀበል ያቅታቸዋል፡፡ ነገር ግን በሕክምናው አሰራር አስቀድሞ ሊከሰት የሚችለውን አጋጣሚ በትክክል ለታካሚው ማስረዳት ግዴታ ነው፡፡
በስተመጨረሻ ዶ/ር ታደሰ የገለጹት በሴቶች የመራቢያ አካላት የካንሰር ሕክምና እየተስፋፋ በመሆኑና በተለይም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምናው አገልግሎት በመሰጠት ላይ ስለሆነ ሆስፒታሎች ታካሚዎቻቸውን ወደሆስፒታሉ መላክ ይችላለሉ። ህብረተሰቡን በሚመ ለከት በተለይም የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በትክክል መከላከል የሚቻል መሆኑ ባደጉት አገሮች የተረጋገጠ ሲሆን ባለፉት 50/ አመታትም ከ70-50/ በመቶ ያህል ቀንሶአል፡፡ ስለዚህም በኢትዮ ጵያም የቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ ቀላል ሰለሆነና ብዙ ቦታም አገልግሎቱ የሚሰጥ በመ ሆኑ ሴቶች ምርመራውን ቢያደርጉ በማህጸን  በር ካንሰር ከመያዝ ይድናሉ። ባጠቃላይም ካን ሰር ተከሰተ ማለት  የመጨረሻ ነው ማለት አይደለም፡፡ አስቀድሞ ከታወቀና ከመሰራጨቱ በፊት ሕክምናው ከተደረገ መዳን እንደሚቻል ሁሉም ሰው ሊያውቅ ይገባል፡፡

Read 3741 times