Monday, 13 November 2017 10:13

በኮሎምቢያ 12 ሺህ ኪ.ግ አደንዛዥ ዕጽ ተያዘ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኮሎምቢያ ፖሊስ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ሊላክ ተዘጋጅቶ የነበረ 12 ሺህ ኪሎ ግራም ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ ዕጽ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወቀ ሲሆን ግምቱ 360 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ይህን ያህል ክብደት ያለው አደንዛዥ ዕጽ በአንድ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ይህ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ነው ያለው ቢቢሲ፤ የአደንዛዥ ዕጹ ባለቤትም ገልፍ ክላን የተባለው እጅግ አደገኛ የወንጀለኞች ቡድን ፊታውራሪ ዳሪዮ ኡሳጋ የተባለ ግለሰብ መሆኑን  ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ቀንደኛውን ወንጀለኛ ዳሪዮ ኡሳግን ለመያዝ ለአመታት ደፋ ቀና ቢልም አሁንም ድረስ እንዳልተሳካለት የጠቆመው ዘገባው፤ ፖሊስ ይህንኑ ቡድን ለመቆጣጠር በጀመረው ዘመቻ፣ ዕጹ በአገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት በአንድ የሙዝ እርሻ ውስጥ ተደብቆ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላት የሆኑ ከ1 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአገሪቱ ፖሊስ፤ ከአደንዛዥ ዕጹ ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን የቡድኑ ግብረአበሮች የሆኑ አራት ግለሰቦችን መያዙን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች 20 ቶን ያህል አደንዛዥ ዕጽ መያዙንም አስታውሷል፡፡

Read 1421 times