Print this page
Monday, 13 November 2017 09:54

የባህሪ ‘ታስክ ፎርስ’!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  “--ታዲያላችሁ…አንድ ወዳጃችን በአንድ ወቅት አንድ ብጣሽ ወረቀት፣ የተሰባበረ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ይጥላል፡፡ ለዛ አይደለም እንዴ የተቀመጡት! እናማ…የቆሻሻው መጣያ ለመድረስ አንድ ሀያ ሜትር ተራምዷል፡፡ ሲመለስ አብሮት የነበረው ጓደኛው ምን ይለዋል… “ፈረንጅ መሆንህ ነው!” እንዲህ ያለው ሰው ደግሞ ቀለም ያልገባው፣ ምናምን አይደለም፡፡ ኮሌጁን በጣጥሶ ጥሩ ሥራ ላይ ያለ ነው-”


   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ ..አንዳንድ ነገሮች ሁልጊዜ እናወራቸዋለን፣ ግን ሲብስባቸው እንጂ ሲሻሻሉ አይታዩም፡፡ ለምሳሌ መሀል ጣት…አለ አይደል… የራሷን እድል በራሷ የወሰነች ነው የሚመስለው፤ በመኪና መስኮቶች የሚቀሰረው የመሀል ጣት ቢቆጠር --- ብናጣ፣ ብናጣ ከአፍሪካ አንደኝነት፣ ከዓለም ሁለተኝነትን አናጣም ነበር፡፡ ሁልጊዜ ይነሳል፣ ግን እየባሰበት ነው የሚሄደው፡፡
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዳንድ ሸላይ ባለመኪና እሀቶቻችን፣ ጥፍራችሁን ጎራዴ የምታሳከሉት ለዚህ አገልገሎት ነው እንዴ! መአቶቹ እንዲህ ሲያደርጉ እናያለና፡፡ እዚህ ጋ መሀል ጣት ሲቀሰር ከጎኑ ያለው የጋብቻ ቀለበት የተሰካበት ጣት ይታዘባል እኮ! ባለቤትየዋ ቢያይ ኖሮ እኮ፣ በማግስቱ ሽማግሌዎች ሰብስቦ “አፋቱኝ!” ይል ነበር፡፡ አሀ… የሰዉ ሚስት፤ “እንዴት አይነት ደርባባ፣ የሰው መውደድ ያላት ናት!” ምናምን ስትባል የእሱን ግን “በመኪና መስኮት መሀል ጣቷን ከመቀሰር ሌላ ምን ሥራ አላት!” ልትባልበት ነው።
ይቺን ስሙኝማ…ጓደኛሞቹ እያወሩ ነው፡፡
“በእናትህ፣ ያቺ እዛ’ጋ ያለች አስጠሊታ ማናት? ሰው እንዴት እንዲህ አስቀያሚ ይሆናል!  ታውቃታለህ?”
“አዎ፣”
“አንተ የምታውቃቸው ሴቶች ሁሉ ደባሪዎች ናቸው፡፡ ይቺን ደግሞ የት ነው ያወቅሀት!”
“ሚስቴ ነች፡፡”
ከዚህ በኋላ የት ይደረሳል! (ከዚህ የሚገኘው ‘የሞራል ትምህርት፤ የእሷዬዋን ሚስትነት ሳታረጋግጡ አስተያየት አትስጡ የሚለ ነው፡፡)
በቀደም በከተማችን አንዱ ክፍል የሆነ ነው። እንዲሁ አንዱ…አለ አይደል… “እኔ ላስ ቬጋስ ባልሄድ፣ ላስ ቬጋስን እዚሁ አመጣታለሁ፣” የሚል አይነት፣ ‘ከተሜ’ የሆነ ሰው እግር ስር ይተፋል፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ ከርቀት ነው ‘የወረወረው።’ ልቅ ሙቀቱ እያነፈነፈ እንደሚሄድ ተምዘግዛጊ ሚሳይል፣ እዛ ሰው እግር ስር ሄዶ ዘጭ ማለቱ ራሱ ለገጠር ሰዎች የሚሆን ትእይንት ነበር…ያውም እንዲህ፤ “ዛሬስ መንገዱ ላይ ብዙ ሰው የለም” በሚባልበት ቀን እንኳን ሳንገፋፋ በማንሄደባት ከተማ! ያኛውም ሰው በጣም ተናዶ ትንሽ አቧራው መጫጫስ ጀምሮ ነበር፡፡ ሚሳይል ወረዋሪው ምንም አልመሰለው። እንኳን ይቅርታ ሊጠይቅ ፈገግ  ነው ያለው፡፡ በሆዱ፤ “ማታ ቺቺንያን በዚህ ወሬ ነው የምቀውጣት፣” እያለም ሊሆን ይችላል፡፡ በሆዱ ምንም ይበል ምንም፣ የሚገርመው አፍ አውጥቶ የተናገረው ነው፡፡ “መብቴ ነው!” ነበር ያለው፡፡ መብት! በአደባባይ ሰው እግር ስር መትፋት ነው መብት!
ይቺ ከተማ በጣም አስቸጋሪ እየሆነች ነው፡፡
እግረ መንገዴን…በየቦታው ቆሻሻ መጣያ ተብለው የተቀመጡትን የብረት ሳጥን ነገሮች ልብ ብላችሁልኛል! ብዙዎቹ እኮ ተነቃቀለው፣ ተነቃቅለው እነሱ ራሳቸው ‘የሚነሳ ቆሻሻ’ ሆነዋል፡፡ ከወራት በፊት ምንም ያልሆኑት ሳጥኖች እየተነቀሉ በሌሎች ሲተኩ፣ ‘የጥራት ጉዳይ’ ምናምን መስሎን ነበር፡፡ (በሆዳችን ያልነው ሆዳችን ውስጥ ይቅርና ማለት ነው፡፡) ሌላው ደግሞ ብዙ ቦታዎች እነኚሁ ‘ብረታ ብረቶች’ መሀል መንገድ ላይ ነው የተደነቀሩት፡፡ እንኳን ተሰባብረው እንዲሁም ለሰዉ ዝውውር እንቅፋት ነገሮች ሆነዋል፡ እኔ የምለው…ለዚች እንኳን እግረኞችን የማይረብሽ ዘዴ የሚያመጣ ሰው አጥተን ነው!
ታዲያላችሁ…አንድ ወዳጃችን በአንድ ወቅት አንድ ብጣሽ ወረቀት፣ የተሰባበረ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ይጥላል። ለዛ አይደለም እንዴ የተቀመጡት!  እናማ…የቆሻሻው መጣያ ለመድረስ አንድ ሀያ ሜትር ተራምዷል። ሲመለስ አብሮት የነበረው ጓደኛው ምን ይለዋል… “ፈረንጅ መሆንህ ነው!”  እንዲህ ያለው ሰው ደግሞ ቀለም ያልገባው፣ ምናምን አይደለም፡፡ ኮሌጁን በጣጥሶ ጥሩ ሥራ ላይ ያለ ነው፡፡ የትኛው ‘ኮርስ’ ላይ ነው፣ ቆሻሻ በስርአት መጣል የፈረንጅ ብቻ ነው ብለው ያስተማሩት!
የምር አኮ የሚገርም ነገር ነው፣ አልለቅ ያለን አባዜ። …አንድ መልካም ነገር ስትሠሩ “ፈረንጅ ለመሆን ነው!” የሚሏት ነገር የተለመደች ነች፡፡
አሁን ለምሳሌ ሁልጊዜ የምናነሳው ሰዓት የማክበር ነገር አለ፡፡ እናማ ሰዓት አክብረን ስንገኝ እንኳን “እሱ ፈረንጅ ነው፣” ይባላል፡፡
ከወራት በፊት ነው፡ መኪናዋ እነኚህ ለመጓጓዣ ሳይሆን ሰፊው ህዝብ ላይ፤ “እናንተ የምድር ጎስቋሎች፣ ስታሳዝኑ!” ለማለት የተያዘች የምትመስል መኪና ውስጥ የሆኑ ጎረምሶች ነበሩ…ሸላይ የሚመስሉ ወጣቶች።  እየተሳሳቁ የሙዝ ልጣጮች ወደ መሀል መንገዱ ሲወረውሩ፣ መንገድ ላይ ይተለላፍ የነበረውን ያንን ሁሉ ሰው ከመጤፍ አልቆጠሩትም፡፡ እነኚህ እንግዲህ ‘ዘመናዊ’ ሆነው፣ “ትዊተርና ፌስቡክ እያለልኝ፣ ለምን ብዬ ነው ወረቀት የማገላበጠው!” የሚሉ አይነት ናቸው።
ችግሩ ደግሞ ራሳቸውን በ‘ስልጣኔ ማማ’ ላይ ያደረሱ ሰዎች… አለ አይደል…ከሰው ለየት ለማለት ብለው የሚያደርጉት ነገር፣ የባህርይ ብልሹነት ነው፡፡ መንገድ ላይ ገፍቷችሁ፣ ወይም ደህና አድርጎ ‘ገፍትሮ አንገዳግዷችሁ’… አለ አይደል… “ይቅርታ” የሚል ሰው ማግኘት ብርቅ ሆኗል። ይቅርታ የሚጠይቁ ቢኖሩም ከሚጠይቁት አብዛኞቹ፣ በወጣትነት እድሜ ያሉ ናቸው። አቅመ አዳምን በ‘ደብል’ና በ‘ትሪፕል’ ያለፈው ወገኔ ሁሉ ምን ነካው! እንዴ እንቁጣጣሽ እየበረከተ ሲሄድ፣ ጭራሹኑ የባሰ እየፈነዱ ይሄዳሉ እንዴ!
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…የሆነ ልደት ላይ ነው …ሳህኑ ላይ የቀሩት ሁለት ኬኮች ብቻ ናቸው፡፡ አንደኛው ትልቅ ሲሆን ሌላኛዋ ሚጢጢ ነች፡፡ አንደኛው ልጅ፤ በመልካም ምግባር ሳህኑን ወደ ጓደኛው ይዘረጋል። ጓደኝየውም ትልቁን ኬክ አነሳ፤ ይሄኔ አቀባዩ…
“እንደው ትንሽ እንኳን መልካም ባህሪይ የለህም! አንተ ለእኔ በሳህን ብታቀርብልኝ ኖሮ፣ ትንሹን ኬክ ነበር የማነሳው፣” ሲለው፣ ያኛውም ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ታዲያ ምን ያነጫንጭሀል፤ የምትፈልግውን ትንሹን ወሰድክ አይደል እንዴ!” ብሎት እርፍ!
እናላችሁ… የባህሪይ ነገር በኋላ ማርሽ እየተንደረደረ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የታክሲ ተራ ጥበቃ አሪፍ ነገር ነው። ከብዙ እንግልት፣ ከብዙ እንካ ስላንትያ አትርፎናል፡፡ ግን አሁንም አንዳንድ ጉልምስናውን ያለፉ ሰዎች ሳይቀሩ ሰልፍ ሰብረው ሲገቡ ታያላችሁ፡፡ ወይ ሳያስፈቅድ፣ ወይ “ግዴለም፣ ግባ!” ምናምን ሳይባል ዘው ይልና ከመሰለው ብቻ… “ስለቸኮልኩ ነው፣” ይላል፡፡ ዘንድሮ…ማን የማይቸኩል አለና ነው! ለሁሉም ነገር ችኮላ ላይ አይደለን እንዴ!
በዛ ሰሞን የሆኑ የደረትና የክንድ ጡንቻቸው ተወጥሮ፣ ልብሳቸውን ሊበጫጭቅ ዳር የደረሰ ሁለት ጎረምሶች፤ መአት ሰው ተሰልፎ እያለ፣ እንደመጡ ሰተት ብለው ታክሲ ውስጥ ይገባሉ፡፡ (ዘንድሮ፣ አይደለም እንዲህ ጡንቸኛው፣ የእኔ ቢጤ ሲምቢሮው ሁሉ ‘ሳምሶን ጸጉሩን ሳይሸለት’ አይነት ነገር እያሰመሰለ ነው፡፡) ከዛ ሁሉ ከተሰለፈው ሰው፤ አንዱም ጥያቄ አላነሳም፡፡ ምናልባት አስራ ሦስት፣ አስራ አራት ዓመት የማይበልጠው የታክሲው ረዳት ግን “ውረዱ!” አላቸው። እነሱም በአፋቸው በመነጋገር ሳይሆን ጡንቻቸውን በመደባበስ፤ “እዚህ የተከመረው ገንፎ መሰለህ!” አይነት መልእክት ለማስተላለፍ ሞከሩ፡፡ ትንሹ ልጅ ግን ጭራሽ ባሰበት፡፡
“ውረዱ! ሥራችንን እንሥራበት!” ሲል አፈጠጠባቸው፡፡ ወረዱ፡፡ ይሄኔ ከተሰለፉት ብዙዎቹ፣
“ጎበዝ!”
“እንዲህ ነው ወንድ ማለት!”
“የዋዛ ጩጬ አይደለችም!” ምናምን ተባባሉ። ዘንድሮ ብዙ ሰው ጎል የሚገባው፣እኛ ልንሠራው የማንሞክረውን፣ እኛ ጎመን በጤና ብለን የተውነውን፣ እኛ “ደግሞ እዚህ ነገር ውስጥ እጄን ከትቼ ልከረቸምልሀ!” እያልን ሌላው ሲሠራው ግን…
“ጎበዝ! ልብ ማለት እንዲህ ነው!”
“እናቷ የወለደቻት ጀግና ማለት እሷ ነች!” እያልን መዳፋችን እስኪያሞቀሙቅ እያጨበጨብን ነው። እንዲህ አይነት ‘ጭብጨባዎች’ን እየሰሙ፣ ስንቶች በማይሆን መንገድ ሄደዋል!
መንገድ ላይ ፊት ለፊታችሁ እንደ ጅብራ ይገተራል፤ (ጅብራ ምንድነው?)
“ስንት ሰዓት ነው!” አጠያየቁ የትብብር ጥያቄ ሳይሆን የኤፍአይቢ. ምርመራ ነገር ይመስላል፡፡ (ፊልሞች ላይ እንደምናየው ለማለት ነው)፡፡
“ለሦስት አስር ጉዳይ፡፡”
 “አመሰግናለሁ፣” የለ፣ “እግዜር ይስጥልኝ፣” የለ…ብቻ የሆነ ቂም ይዞ በሆዱ፣ “ቆይ ብቻ፣ አመቺ ቦታ እንገናኝና!” ብሎ ይዝት ይመስል፣ ተኮሳትሮባችሁ ይሄዳል፡፡
እኔ የምለው…‘’የባህሪ ታስክ ፎርስ ምናምን የሚባል ነገር” እናቋቁም እንዴ! ባይሳካስ ምን ችግር አለው? ትንሽ ወራት ቆይተን ‘ታስክ ፎርሱ’ ለምን ውጤታማ እንዳልሆነ የሚያጠና ሌላ ታስክ ፎርስ እናቋቁማለን!
ደሀና ሰንብቱልኝማ!

Read 2925 times