Monday, 13 November 2017 09:40

መንግስት የሼህ መሃመድ አላሙዲንን ጉዳይ እየተከታተልኩ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

 በሳኡዲ የሚገኙ ንብረቶቻቸውና የባንክ ሂሳባቸው ታግዷል

    ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር ሼክ መሃመድ አሊ አላሙዲ፣በሳኡዲ በተጠረጠሩበት ሁለት የሙስና ጉዳዮች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ዘገባዎች የጠቆሙ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ጉዳዩን ከሳኡዲ ባለስልጣናት ጋር እንደተወያየበትና ሂደቱንም በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፡፡  
የሳኡዲ መንግስት በሙስና ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ከ30 የማያንሱ  የአገሪቱ ልኡላን ቤተሰቦችና ኢንቨስተሮች መካከል አንዱ የሆኑት ሼህ መሃመድ አላሙዲ፤ በቢሊዮን ዶላር በሚገመቱ ሁለት ጉዳዮች መጠርጠራቸውን የመረጃ ምንጮቼ አረጋግጠውልኛል ሲል የጀርመን ድምፅ ዘግቧል፡፡
ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የገለፀው የሀገሪቱ መንግስት፤ 1500 የሚደርሱ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በማደን ላይ እንደሆነ  አስታውቋል፡፡
የሳኡዲ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ የሼህ መሃመድ አላሙዲን ጉዳይ ጨምሮ የሁሉም ተጠርጣሪዎች የፍርድ ሂደት በተፋጠነና ለሁሉም ግልፅ በሆነ ችሎት እንደሚታይ መግለጻቸው የተዘገበ ቢሆንም ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል ተብሏል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ቢሊየነር፤ በሳኡዲ የሚገኘው የድርጅታቸው ንብረትና የባንክ ሂሳባቸው መታገዱ የተገለፀ ሲሆን ከሳኡዲ ውጪ ያሉ ኩባንያዎቻቸው ግን ሥራቸውን እንደማይስተጓጎሉ፣በለንደን የሚገኙት ተወካያቸው ሰሞኑን ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤”የባለሀብቱን መታሰር በሚዲያ ከሰማን በኋላ ከሳኡዲ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ለማጣራት ሙከራ እያደረግን ነው፤ሂደቱን በቅርበት እንከታተለዋለን “ ብለዋል -ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡  
በሳኡዲ በሙስና ተጠርጠረው ከታሰሩት ከልኡል አልዋሊድ ቢን ታላል ቀጥሎ ሁለተኛ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት 3ኛው ቢሊየነር የሆኑት ሼህ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ መታሰር፤ በርካታ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃንን እያነጋገረ ሲሆን በአረብ ሀገራት ታዋቂ የሆነው “The Middle East Monitor” ጋዜጣ በበኩሉ፤ባለሀብቱ ለኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ 88 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መለገሳቸውን በመጥቀስ፤ “የግድቡ ደጋፊ የነበረው ባለሃብት፤ በሳኡዲ አረቢያ ታስሯል” ሲል ዘግቧል፡፡
የሳኡዲው አልጋ ወራሽ የጀመሩት የፀረ ሙስና ዘመቻ፣ ከበርካታ የዓለም መንግስታት ድጋፍ እየተቸረው ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ፣ለዘመቻው ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ሰሞኑን አስታውቀዋል፡፡ ሼህ መሃመድ አሊ አላሙዲንን ጨምሮ 30 የሚደርሱት የሙስና ተጠርጣሪዎቹ፤ሪያድ በሚገኘው ባለ አምስት ኮከቡ ሪትዝ ካርልተን ሆቴል በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ሲዘገብ ሰንብቷል፡፡  

Read 10996 times