Monday, 13 November 2017 09:38

በጣሊያን ለግራዚያኒ መታሰቢያ ያሰሩ የሀገሪቱ ባለስልጣናት በእስራት ተቀጡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   ግራዚኒ ከ 1ሚ. በላይ ኢትዮጵያውያንን አስጨፍጭፏል

    በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጭፍጨፋ ተጠያቂ ለሆነው የፋሺስት ጣሊያን የጦር አዝማች ሩዶልፍ ግራዚያኒ የመታሰቢያ ፓርክና ሃውልት ያሰሩ የጣሊያን ባለስልጣናትን የሀገሪቱ ፍ/ቤት በእስርና በገንዘብ ቀጣ፡፡
እ.ኤ.አ በነሐሴ 2012 ዓ.ም በጣሊያን ላዚዮ ግዛት አፊል ከተማ ላይ የተገነባው የፋሽስት የጦር አዝማቹ ሩዶልፍ ግራዚያኒ የመታሰቢያ ሃውልትና ፓርክ በኢትዮጵያውያንና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲወገዝ የከረመ መሆኑ ይታወሳል፡፡
“አለማቀፉ ህብረት ለፍትህ - የኢትዮጵያ ጉዳይ” የተሰኘ ማህበርም ጉዳዩን እዚያው ጣሊያን አፊሌ ከተማ ወደሚገኝ ፍ/ቤት ወስዶ ሲሟገት የከረመ ሲሆን ፍ/ቤቱ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ፣ የሃውልቱን መታሰቢያና ሙዚየሙን እንዲሰራ ያደረጉት የአፊል ከተማ ከንቲባ ኤልኮል ቪሪን በ8 ወር እስራትና በ120 ዩሮ ገንዘብ መቀጮ ሲቀጣ፣ አማካሪዎቹን ደግሞ በ6 ወር እስራትና በ80 ዩሮ ገንዘብ መቀጮ ቀጥቷል፡፡ የእስራት ጊዜያቸውን ከጨረሱም በኋላ ለ5 ዓመት ከማንኛውም ህዝባዊ አገልግሎት መብቶች እንዲገደቡ ፍ/ቤቱ ወስኗል፡፡
የፋሺስት ተቃዋሚ ለሆነው ድርጅት የ8 ሺህ ዩሮ ካሳ እንዲሁም ክሱን ለመሰረቱ አካላት 1800 ዩሮ እንዲከፈላቸውም ተወስኗል፡፡
በቀጣይም በአፊል ከተማ የሚገኘው የግራዚያኒ ሃውልትና መታሰቢያ ፓርክ እንዲፈርስ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ማህበሩ ለአዲስ አድማስ የላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ይጠቁማል፡፡
በዚህ የፍርድ ሂደት በጣሊያን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ የላዚዮ ግዛት አስተዳዳሪ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ማህበሩ አስታውቋል፡፡ በ5 ዓመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት የፋሺስት መንግስቱ የኢትዮጵያ አስተዳዳሪ ተወካይ የነበረው ሩዶልፍ ግራዚያኒ፤ ከ1 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መግደሉን፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ (525 ሺህ) ቤቶችን ማፍረሱን፣ 14 ሚሊዮን እንስሳትን መጨፍጨፉንና ከ2 ሺህ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ማውደሙን መግለጫው ያትታል፡፡

Read 2636 times