Sunday, 05 November 2017 00:00

ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚያስብ የአዲሱ ትውልድ አመራር ለማፍራት አቅጣጫ ተቀምጧል - ኦህዴድ

Written by 
Rate this item
(72 votes)

• *ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸውን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመቀየር ተስማምተናል
• *የህዝቡ ፍላጎት የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ያስፈልጋል
• *የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም የሚል መግባባት ላይ ደርሰናል

    ኦህዴድ፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ስለ ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም የሚያስቡ የቀጣይ ትውልድ አመራሮችን በስፋት ለማፍራት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወቀ፡፡ 2 ሺህ ያህል ተሳታፊዎች በታደሙበት የአዳማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ፣ ከጥቅምት 19 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በተደረገው የኦህዴድ 7ኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ላይ፤ ስለ ክልሉ የፀጥታ ጉዳይ፣ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል
ጋር ስላጋጠመው ችግር፣ ስለ ፌደራሊዝምና ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ በስፋት ውይይት መካሄዱን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊና የኮንፈረንሱ ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡  ከህብረ ብሄራዊ ፌደራል ሥርአት ግንባታ ጋር በተያያዘ  ሰፋ ያለ ሃሳብ መንሸራሸሩንና ለሀገሪቱ ከህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርአት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በመተማመን፣ ኦህዴድና የክልሉ ህዝብ ፌደራሊዝምን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው መግባባት ላይ መደረሱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡ በፌደራል ሥርአቱ ግንባታ ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆኑን የገመገመው ኮንፈረንሱ፤ ይህንንም ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች ጋር በመሆን በትዕግስትና በዲሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል - አቶ አዲሱ፡፡ የኢትዮጵያ አንድነትንና የህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝምን ከማጠናከር አኳያም “የተሃድሶው የኦህዴድ አመራሮች” ትልቅ ድርሻ አለን ያሉት ቃል አቀባዩ፤ “የሀገራችንን የኢትዮጵያን አንድነት ከማጠናከር አንፃር ሚናችን ጉልህ ስለሆነ፣ያንን ሚናችንን መወጣት አለብን የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል” ብለዋል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ህብረ ብሄራዊ ፌደራል ሥርአት፣ ስለ ህዝቦች ወንድማማችነት የሚያስብና ከምንም በላይ ለሀገርና ለዜጎች የሚቆም የቀጣይ ትውልድ አመራር በኦህዴድ በኩል የመፍጠር ስራ እንዲሰራም መታቀዱን አቶ አዲሱ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡ “ኦሮሞ ሲጠቀም አማራው፣ ትግሬው ወላይታው -- ይጠቀማል” የሚል አስተሳሰብ በመያዝ፣ ለህዝቦች መቀራረብና የሀገር አንድነትን ለማምጣት ግልፅ መግባባት ላይ መደረሱንም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት፣ የህዝቡ ፍላጎት የደረሰበትን ደረጃ የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ያስፈልጋል በሚል መግባባትም፤ በቀጣይ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ላይኛው የኦህዴድ ድርጅታዊ መዋቅር ድረስ እንደገና የማጠናከር ሥራ እንዲሰራም ታቅዷል ተብሏል፡፡  “በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶች ሳይሸራረፉ፣ ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበሩ ሚናችንን ለመወጣትም ተስማምተናል” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የፍትሃዊ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተም በክልሉ ነዋሪ የሆኑ ሁሉም ዜጎች፣ የኢኮኖሚ አብዮቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑም አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ “ከመልካም አስተዳደር አኳያ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከፍትህ ሥርአቱና ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር ተያይዞ ብዙ ያልተሻገርናቸው ችግሮች እንዳሉ ተገምግሟል፤ በአጠቃላይ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸውን ፖለቲካል ኢኮኖሚ
ለመቀየርም መግባባት ላይ ተደርሷል” ብለዋል፤አቶ አዲሱ፡፡ ሌላው የኮንፈረንሱ አጀንዳ  ከፀጥታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ እንደነበር ጠቁመው፤ አሁን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ግርግር፣ በኪራይ ሰብሳቢዎች ሴራ የተወጠነ መሆኑን መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡ “እኛ የክልሉ አመራሮች፤ ከእንግዲህ የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም የሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ”የተፈፀሙ ግድያዎችና የደረሱ ጉዳቶችም በፅኑ ተወግዘዋል” ብለዋል፡፡
በሶማሌ - ኦሮሚያ ግጭት ምክንያት ስለተፈናቀሉ ወገኖች አጥብቆ የተወያየው ኮንፈረንሱ፤ በግጭቱ ምክንያት ፌደራሊዝሙ አደጋ ውስጥ ገብቷል ሊባል እንደማይችልና ችግሩን በሰከነ መንገድ መፍታት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ መቀመጡን አቶ አዲሱ አብራርተዋል፡፡    

Read 14874 times