Print this page
Sunday, 05 November 2017 00:00

ለተፈጠሩ አለመረጋጋቶች ምክንያቱ የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው - ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(23 votes)

“የመንግስት ቃል አቀባይ ሆኜ የግሌን ሀሳብ የምናገርበት ምክንያት የለም”
    በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ተቃውሞና አለመረጋጋቶች ዋነኛው ምክንያት የወጣቶች ሥራ አጥነት መሆኑን የመንግስት  ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ሰሞኑን ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡  በየዓመቱ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ወጣቶች የሥራ ዕድል አለማግኘታቸው ለአለመረጋጋቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ለቢቢሲ የገለጹት ዶ/ር ነገሪ፤ ሀገሪቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከፍተኛ የተማረ ሀይል ማፍራቷን ጠቁመው፣የተማረው ኃይልና የሥራ እድሎች አለመጣጣማቸውን አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቃንን የሚያፈሩ 40 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ሀገሪቱ እንዳላት የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ መንግስት ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ ልዩ በጀት ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡   ከዓመት በፊት ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በአምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ለቢቢሲ የገለፁት ዶ/ር ነገሪ፤ ይሁን እንጂ አሁንም በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ሥራ ፈላጊዎች ናቸው ብለዋል፡፡ “የተቃውሞ መነሻው በክልሎች መካከል ፍትኃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖሩና የአድሎአዊነት ጉዳይ ነው የሚባለው መሰረተ ቢስ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ሁሉም ክልሎች እኩል ስልጣን ያላቸውና በእኩል የፌደራል መንግስቱን የመሠረቱ ናቸው” ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ በእንግሊዝ ለንደን፣ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ባለፈው ሳምንት ሚዲያዎችን አስመልክቶ የሰጡት መግለጫ፤ “የግል አስተያየት ሊሆን ይችላል” መባሉን በተመለከተም፤”እኔ የመንግስት ቃል አቀባይ ሆኜ የግሌን ሀሳብ የምናገርበት ምክንያት የለም፤የመንግስትን አቋም ነው ያንፀባረቅኩት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም፤ ”የግልም ይሁን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ ከህግ አግባብ ውጪ ከተንቀሳቀሱ በህግ ተጠያቂ የማይሆኑበት ምክንያት የለም” ብለዋል፤ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፡፡





Read 5451 times