Sunday, 05 November 2017 00:00

በቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን የምዕመናን ገንዘብ እየተመዘበረ ነው ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(10 votes)

- በሁለት ወር ብቻ 1.9 ሚሊዮን ብር ተዘርፏል - (ምዕመናን)
         - ቼኩ ከምክትሉ ጋር በጋራ የተፈረመ ስለሆነ የተመዘበረ ገንዘብ የለም
         - አጣሪ ቡድኑ ምዝበራ መፈፀሙን አላረጋገጠም - (የደብሩ ዋና አስተዳደሪ)
             
   በደብረ ፅጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ግምት ያለው የምዕመናን ገንዘብ በአስተዳደር ሰራተኞች ያለ አግባብ መመዝበሩን፣ የደብሩ ምክትል አስተዳዳሪና ምዕመናን ገለፁ፡፡ በሁለት ወር ብቻ ከ1.9 ሚ. ብር በላይ ያላግባብ መዘረፉን በደብሩ የምዕመናን ተወካይና የደብሩ ምክትል አስተዳዳሪ መምህር ሃ/ማሪያም ገ/ስላሴ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ መላዕከ ገነት ተስፋ ፍስሀ በበኩላቸው፤ ተመዘበረ የተባለው ገንዘብ የወጣው ከምክትል አስተዳዳሪው ጋር በጋራ በፈረምነው ቼክ ሲሉ ገልፀው፤ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን አጣርቶ መመለሱንና የፊታችን ሰኞ ወይም ማክሰኞ ኮሚቴው ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ጉዳዩን እንዲያጣሩ ከመደባቸው ሁለት ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ገብሬ መስቀል ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው ሲመልሱ፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ጉዳዩን አጣርተው ከተመለሱ ሁለት ወር እንደማይሞላቸው ጠቁመው ምላሽ ለመስጠት ትንሽ የዘገዩት፣ አገር አቀፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እየተካሄደ በመሆኑ ነው ብለዋል። የማጣራት ሂደት ባደረጉበት ጊዜ አንዳንድ ክፍተቶችና ሊታረሙ የሚገቡ ስህተቶች እንደተመለከቱና ይህንንም ለማስተካከል በደብሩና በአዲስ አበባ ሀገረ-ስብከት ፅ/ቤት በኩል በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በማጣራት ሂደቱ ተዘረፈ ስለ ተባለው ገንዘብ ያገኙት ማስረጃ መኖሩን የተጠየቁት አቶ ገብሬ መስቀል፤ ገንዘቡ ተመዝብሯል ለማለት በሁለቱም ወገን የሚቀርቡ የሰነድ ማስረጃዎችን ማገናዘብ እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ “ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በዘፈቀደ ይሄ ወጥቷል፤ ያኛው ተዘርፏል” ማለት እንደማያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ካላጣራችሁ እስካሁን ምን ነበር የምትሰሩት በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ “ይሄኛውን ምላሽ በደንብ በሰነድ አስደግፈን ቅሬታ ላቀረበው አካል እናቀርባለን” ብለዋል፡፡ የምዕመናን ተወካይና የደብሩ ምክትል አስተዳዳሪ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የተመዘበረው፣ ሰበካ ጉባኤው በዕቅድ የያዛቸውን የካህናት ማረፊያ ደጀ ሰላም እንዲሁም የአብነትና የሰንበት ት/ቤቶች ህንፃ ቅየሳ ለማስጀመር የአፈር ጠረጋ የተካሄደ ሲሆን 49 ጭነት መኪና አፈር መጓጓዙንና ለአንድ ጭነት 500 ብር፣ ለ49 ጭነት ደግሞ 24 ሺህ 500 ብር ፀድቆ፣ ቼክ በደብሩ አስተዳዳሪና በምክትሉ ቢፈረምም ባልታወቀ ሁኔታ “800 ጭነት አፈር ተጓጉዟል” በሚል የአፈር ማጓጓዙን ስራ በሰሩት ግለሰብ ስም 424 ሺህ 500 ብር ከባንክ ያለ አግባብ መውጣቱን፣ ጉዳዩን ተወክላ ስትከታተል የነበረችው  የምዕመናን ተወካይ ወ/ሪት ሐይማኖት እርቅይሁን ተናግራለች፡፡
በተጨማሪም ብዛታቸው አራት የሆነ ሶስት በሶስት ሜትር  ድንኳኖችን፣ እያንዳንዳቸውን በ11 ሺህ ብር ከመድን ዲኮር እንዲገዙ ሰበካ ጉባኤው ቢወስንም፣ ጉባኤው ውሳኔ ባልሰጠበት ቦታና ሂሳብ፣ ለአራቱ ድንኳኖች 374 ሺህ ብር፣ በማይመለከተው የደብሩ ሰራተኛ ስም ወጥቶ መገኘቱ፣ የህዝብ ገንዘብ ያለ አግባብ እየተመዘበረ እንደሆነ ማሳያ ነው ስትል ወ/ሪት ሐይማኖት አክላ ገልፃለች፡፡
በ2009 ዓ.ም ለቅዱስ ኡራኤልና ለማሪያም በዓል ሲያገለግሉ ያደሩትን ማህበረ ካህናት ለመመገብ፣ ሰበካ ጉባኤው፣ 60 ሺህ ብር እንዲወጣ በቃለ ጉባኤ ወስኖ፣ የደብሩ አለቃና ምክትሉ ቼክ ቢፈርሙም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ሂሳቡ 260 ሺህ ብር ሆኖ ከባንክ መውጣቱን የገለፁት የደብሩ ም/አስተዳዳሪ መምህር ሃ/ማሪያም፤ “እያንዳንዱን የባንክ ስቴትመንት ከባንክ አስወጥቼ ሳመሳክረው ባላወቅኩት መንገድ ገንዘብ እየተመዘበረ መሆኑን ተረድቼአለሁ፤ ስለዚህ የሚመለከተው የፍትህ አካል እልባት ይሰጠው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ በቤተክርስቲያኑ ለንብረት ማከማቻ ተብሎ የተሰራው ብረት ቤት፤ ሰበካ ጉባኤው ሳይፈቅድና በመሀንዲስ ከሚገመተው በላይ 240 ሺህ ብር እንደተሰራ ተደርጎ ግልፅ ባልሆነ መንገድ በደብሩ ሰራተኛ ስም ከባንክ መውጣቱ፣ የሊፍት ሞተር የተቀመጠበት ቦታ ክፍተት ያለው በመሆኑ አደጋ እንዳያደርስ በማሰብ፣ ቤተ ክርስቲያኑ እቃ አቅርቦ፣ ለእጅና ለጉልበት ዋጋ 5 ሺህ ብር እንዲከፈል ጉባኤው ቢወስንም፣ 295 ሺህ ብር ከባንክ በቼክ መውጣቱ፣ የኤሌክትሪክ ኬብል ግዢ እንዲፈፀም በተወሰነው መሰረት በወቅቱ በነበረው የግዢ ክፍል ተገዝቶ የነበረ ቢሆንም በዚሁ የኬብል ግዢ ስም በድጋሚ 155 ሺህ ብር በተጭበረበረ መንገድ መውጣቱ፣ በንብረት ክፍል ሀላፊው በሁለት ቼክ ምክንያቱ ሳይጠቀስ 529 ሺህ ብር ከባንክ ወጥቶ መወሰዱንና ሌሎችም ምዝበራዎች በህዝብ ንብረት ላይ እየተፈፀሙ መገኘታቸው ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ብላለች- ወ/ሪት ሐይማኖት፡፡
ቀደም ሲል እያንዳንዱ ወጪ ሲደረግና ቃለ ጉባኤ ሲያዝ፣ የባንክ ስሊፕና የቃለ ጉባኤው ግልባጭ ለምዕመናን ተወካዩ ምክትል አስተዳዳሪው ይሰጥ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወክሎ ወደ ደብሩ የመጣው የሂሳብ ሹም፤ “ተጠሪነቴ ለሀገረ ስብከቱ ነው” በሚል እነዚህን ሰነዶች መከልከላቸውንና በዚህም የተነሳ ዘረፋው መመቻቸቱን የምዕመናን ተወካዮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ለአዲስ አበባ አገረ ስብከት ፅ/ቤት፣ ዝርዝር መረጃው የቀረበ ሲሆን ጽ/ቤቱ የመደባቸው አጣሪዎች ጉዳዩን በፍጥነት አጣርተው፣ አስቸኳይ ምላሽ ባለመስጠታቸው የምዕመኑ ተወካይ ባለፈው እሁድ ማለዳ፣ ለምዕመኑ ዝርዝር ሪፖርት ሊያቀርቡ ቢዘጋጁም፤ የካራማራ ፖሊስ፡- “ወቅቱ ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆነ ሁከት እንዳይፈጠር ሪፖርቱ ይዘግይ” በማለቱ ሳይቀርብ መቅረቱን የምዕመናን ተወካዮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ “በሁለት ወር ውስጥ፡- ከግንቦት አጋማሽ እስከ ሀምሌ አጋማሽ፣ ወደ 2 ሚ. ብር ገደማ ከተመዘበረ፣ ከነሀሴ እስካሁን ያለው ምዝበራ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ስናስብ በእጅጉ ስጋት ላይ ወድቀናል” ያለችው ወ/ሪት ሐይማኖት፤ “ፖሊስም ሆነ ሌሎች የፍትህ አካላት ይህን ዝርፊያ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ እንጠይቃለን” ብላለች፡፡

Read 6071 times