Sunday, 05 November 2017 00:00

ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ሰኞ ክስ እንደሚመሰርት አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

ህገ መንግስቱን የመጣስ ክስ ነው ተብሏል

    በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ በተደጋጋሚ እውቅና ብጠይቅም አስተዳደሩ ቀና ምላሽ አልሰጠኝም ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ በከተማ አስተዳደሩ ላይ ህገ መንግስቱን የመጣስ ክስ ሰኞ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እንደሚመሰረት በተለይ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ስለ ጉዳዩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ ፓርቲው መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለያደርግ ያቀደው ሰላማዊ ሠልፍ አስተዳደሩ እውቅና በመንፈጉ የተነሳ አለመሳካቱን አስታውሰው፤በድጋሚ ነገ እሁድ ጥቅምት 26 ሊያካሂድ ያሰበው ተመሳሳይ ሰላማዊ ሠልፍም እውቅና ባለማግኘቱ፣ፓርቲው ህገ መንግስታዊ መብቱን ለማስክበር ወደ ፍርድ ቤት ለማምራት መገደዱን ተናግረዋል፡፡
በነገው ዕለት ፓርቲው ከፒያሳ ሚኒልክ አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ የሚጓዝ ሰልፍ ለማካሄድ አቅዶ ለመስተዳደሩ የእውቅና ጥያቄ ቢያቀርብም፣ “በቂ የፖሊስ ሃይል የለንም” በሚል እውቅና መነፈጉን አቶ አበበ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ክልከላውን ተከትሎም ፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በማድረግ፣በአስተዳደሩ ላይ ህገ መንግስቱን የመጣስ ክስ እንዲመሰረት በሙሉ ድምፅ  መስማማታቸውንና ክሱም መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ የፓርቲው የህግ ክፍል ያዘጋጀውን ክስ ከነገ ወዲያ ሰኞ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እንደሚያቀርብ አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

Read 4203 times