Sunday, 05 November 2017 00:00

ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ የኢሊባቡሩን ግጭት ማጣራታቸውን አስታወቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 · “አሰቃቂ ግድያዎች በህፃናት ላይ ሳይቀር ተፈፅመዋል”
           · “በግጭቱ 35 ሰዎች ሞተዋል፤24 በጽኑ ቆስለዋል”
           · “ለተጎጂዎች ያሰባሰብነውን 700ሺ ብር እንዳናደርስ ተከለከልን”

    በቅርቡ የተከሰተውን የኢሊባቡር ግጭት ለማጣራት ወደ ሥፍራው አጣሪ ቡድን መላካቸውን የጠቆሙት ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ፤በግጭቱ 35 ሰዎች መሞታቸውንና የደረሰው ሰብአዊ ጉዳትም በመንግስት ከተገለፀው በላይ ከባድ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በመኢአድ ዋና ፀሀፊና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳነ ጥላሁን የሚመራውና ከሁለቱ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሶስት አባላትን የያዘው አጣሪ ቡድን፣ ወደ ስፍራው ተጉዞ ባደረገው ምልከታ፣ የደረሰባቸውን ግኝቶች በተለይ ለአዲስ አድማስ የገለፀ ሲሆን ለተጎጂዎች ከበጎ አድራጊዎች ያሰባሰቡትን 7 መቶ ሺህ ብር እርዳታ ለማድረስ አለመቻሉን ጠቁሟል፡፡  
አጣሪ ቡድኑ፤ ግጭቱ ከተከሰተባቸው አምስት ወረዳዎች መካከል በተለይ በጮራ ወረዳና በጌጂ የደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በአሰቃቂ መረጃዎች የተሞላ ከባድ ጉዳት ነው ብሏል፡፡
የአጣሪ ቡድኑ መሪ አቶ አዳነ ጥላሁን ስለ ጉዳዩ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤”በጮራ ወረዳ የ3 ወር ህፃን በገጀራ ስለመቀላቷና የ6 ወር ህፃን ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ እንዲሞት ስለመደረጉ ማስረጃ አሰባስበናል” ብለዋል፡፡ በወረዳው ሌሎች አሰቃቂ ጉዳቶችም መፈጸማቸውን ተጎጂዎችን በማነጋገር ለማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በህፃናቱ ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ጉዳት የዞኑን አመራሮች ለማነጋገር ያደረጉት ጥረትም “በዚህ ጉዳይ ልናነጋግራቸው አንችልም” በመባላቸው እንዳልተሳካላቸው አቶ አዳነ ገልጸዋል፡፡
ከተጎጂዎችና ከአካባቢው ህብረተሰብ ባሰባሰቡት መረጃም፤ በግጭቱ መንግስት እንደሚለው 20 ሳይሆን 35 ሰዎች መሞታቸውን፣ 24 ሰዎች በፅኑ መቁሰላቸውን፣ አንድ ሴትን ጨምሮ 4 ሰዎች ደግሞ ደብዛቸው መጥፋቱን በሪፖርታቸው አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም 405 ቤቶች ከእነ ሙሉ ንብረታቸው መቃጠላቸውን፣ 190 ቤቶች ላይ በከፊል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ት/ቤቶች መውደማቸውን በምልከታ አረጋግጠናል ብለዋል - የአጣሪ ቡድኑ መሪ፡፡ “በግጭቱ ላይ አንዳንድ የመንግስት አመራሮች ጭምር እንደተሳተፉ መረጃ አጠናቅረናል” በማለትም አቶ አዳነ ጠቁመዋል፡፡  
ሰማያዊ ፓርቲና መኢአድ፤ግጭቱን ከማጣራት ጎን ለጎን፣ በጋራ ከለጋሾች ያሰባሰቡትን 7 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ እርዳታ በጥሬም ሆነ በዓይነት ለተጎጂዎች ለማድረስ ቢሞክሩም “ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፈቃድ ያስፈልጋል” በሚል መከልከላቸውን ጠቁመው፤በቀጣይም ፈቃዱን አግኝተው እርዳታውን ለማድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ የቡድኑ መሪ ገልጸዋል፡፡

Read 3357 times