Print this page
Saturday, 04 November 2017 12:44

የኦሮሞ - አማራ የአንድነት ኮንፈረንስ ዛሬ በባህር ዳር ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 “አንድ ነን አንለያይም!”

    በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ እና በአማራ ክልል አቻቸው ገዱ አንዳርጋቸው የመድረክ አጋፋሪነት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች የወንድማማችነትና የአንድነት ኮንፈረንስ ይካሄዳል፡፡
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የሁለቱ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ኮንፈረንስ ላይ ከ20 የኦሮሚያ ዞኖችና ከ18 ከተሞች የተውጣጡ ከ250 በላይ የኦሮሞ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ የኦሮሞ ምሁራንና አርቲስት አሊ ቢራን ጨምሮ የኦሮሞ አርቲስቶች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አንድነት፣ ሁለቱ ህዝቦች በጋራ ለሀገር ሉአላዊነት ስለፈፀሙት ተጋድሎ እንዲሁም የሁለቱን ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የሚያሳዩ የውይይት መነሻ ፅሁፎች በምሁራን ቀርበው ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“የኦሮሞ ህዝብ አንድነት ያለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ የኦሮሞ ህዝብ እድገትና ብልፅግና ያለ ኢትዮጵያ እድገትና ብልፅግና ዘላቂ ሆኖ ብቻውን ሊቆም አይችልም” ያሉት አቶ አዲሱ፤ ይህን ሃሣብ መነሻ በማድረግ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ወንድማማችነት ማጠናከር የሚያስችሉ ኮንፈረንሶች በቀጣይም ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በባህር ዳር የሚካሄደውን ይህን ኮንፈረንስ፤  የሁለቱ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች በጋራ ይመሩታል ተብሏል፡፡
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ትናንት (አርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም) ወደ ባህር ዳር ሲያመሩ (Nuti tokko Addaan hinbaanu!) “አንድ ነን አንለያይም!” የሚል መፈክር አንግበው መሆኑ ታውቋል፡፡
በቅርቡ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢ የተወጣጡ ከ200 በላይ ወጣቶች፣ በጣና ሃይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመንቀል ወደ ባህርዳር መጓዛቸው የሚታወስ ነው፡፡

Read 3526 times