Sunday, 05 November 2017 00:00

የአቶ በቀለ የዋስትና እግድ ጉዳይ ላይ ለመከራከር ጠበቆች አልወሰኑም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

የህግ ባለሙያዎች እግዱ “ህግን የተከተለ አይደለም” አሉ

    በጠቅላይ ፍ/ቤት የተፈቀደላቸው የዋስትና መብት፣ የአቃቤ ህግን አቤቱታ ተከትሎ በሰበር ሰሚ የታገደባቸው የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ በቀለ ገርባ፤ በዋስትና እግዱ ላይ መከራከሪያ እንዲያቀርቡ ለህዳር 14 ቀን 2010 ተቀጥሯል፡፡
የዋስትና መብታቸው የታገደው አቶ በቀለ ገርባ ምላሻቸውን እንዲያቀርቡ የተጠየቀ ቢሆንም ጠበቆቻቸው “በክርክሩ መሣተፍ ይጠቅማል አይጠቅምም” በሚለው ላይ ተመካክረው ውሳኔያቸውን ለመገናኛ ብዙሃን እንደሚያሳውቁ ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ አመሃ መኮንን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አንጋፋው የህግ ባለሙያና የተከሣሹ ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን፤ የጠቅላይ ፍ/ቤቱ የዋስትና መብት ወዲያው ተፈፃሚ ሆኖ፣ አቶ በቀለ ከእስር ሊለቀቁ ይገባ ነበር ብለዋል- “ይግባኝ ስለተጠየቀባቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል” የሚለው ህጋዊና አጥጋቢ ምክንያት አለመሆኑን በመግለፅ፡፡
ሌላው የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳም የአቶ አመሃን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ይጋራሉ፡፡ “አቶ በቀለ ዋስትና እንደተፈቀደላቸው ወዲያውኑ ከእስር መለቀቅ ነበረባቸው፤ አካሄዱ ህግን የተከተለ አይደለም” ብለዋል፡፡
በፍ/ቤት ዋስትና የተሰጠው ግለሰብ ወዲያው ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁመው ፍ/ቤቱም እንደተለቀቀ ነው የሚቆጥረው ያሉት ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ፤ አቃቤ ህግ ለተከሳሽ የተሰጠን ዋስትና የሚያሳግድበት የህግ አግባብ በሀገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫም ሆነ የሥነ ስርአት ህግ እንደሌለ ይከራከራሉ፡፡ “በአቶ በቀለ ገርባ ላይ የተፈፀመውም ከህግ አግባብ ውጪ የሆነ እገታ እንደሆነ ነው የምረዳው” ይላሉ - አቶ ተማም፡፡

Read 878 times