Sunday, 05 November 2017 00:00

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በስጋት ጭጋግ ስር!

Written by  ገለታ ገ/ወልድ
Rate this item
(8 votes)


           በእኛ ሀገር ልማድ እንደ አይን ብሌን የምንመለከተውን ነገር እንኳን ክፉውን ለጥንቃቄ የሚረዳውን ስጋት መተንፈስም ቢሆን በጨለምተኝነት ያስፈርጃል፡፡ ሆኖም ስለ ትልቁ ሀገራዊ እሴታችንና የትውልድ ቅርሳችን ስንል ግን ወቅታዊ ስጋቶችን ለመሰንዘር እንገደዳለን፡፡ ሌሎችም ሃሳባቸውንና ስጋታቸውን ከመተንፈስ ወደ ኋላ እንዳይሉ እናሳስባለን፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው። እንደ ዕቅዱ ግን በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ በከፊል ሃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቅ ነበር፡፡ ይሁንና አሁንም የግድቡ ግንባታ ሂደት ከ63 በመቶ ያላለፈ ሲሆን በአሁኑ ፍጥነት መጓዝ ከተቻለና ሀገሪቱ በጀመረችው የእድገት ጉዞ ከቀጠለች ብቻ  ተጨማሪ አምስት ዓመታት ገደማ ሊወስድ እንደሚችል የመስኩ ምሁራን ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደውና ባልተቋጨው የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ፖለቲከኞች ምክክር ወቅትም ይሄው ጉዳይ ተጠቁሟል፡፡  
በዚህ ላይ የተሟላ መግባባት ያልተፈጠረበት የአባይ ዲፕሎማሲ፣ በሀገራችን እየተመላለሰ የሚጎበኘን ፖለቲካዊ  አለመረጋጋት፤ የኢኮኖሚው ዕድገት በሚፈለገው ደረጃ አለመቀጠልና በተለይ  እንደ ውጭ ምንዛሬ  አይነት  ወሳኝ  ግብአቶች እጥረት መፈጠሩ እንዲሁም  የህዝቡ ተሳትፎ በፍጥነት እያሽቆለቆለ መምጣቱ (በታላቁ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ መረጃ ላይ መጠቀሱን ልብ ይሏል) ታላቁን ፕሮጀክት እንዳያጓትተው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል፡፡
በእርግጥ ባለፉት ዓመታት የማይደፈረውን ደፍሮ ወደ ስራ በመግባት መንግስት ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛ እርብርብ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ግንባታ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተፋጠነ ነው ባይባልም፤ ሁለቱ የግንባታ ምዕራፎቹ ተጠናቅቀው በሦስተኛው ምዕራፍ ላይ  እንደደረሰ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ግንባታው ግዙፍ ከመሆኑ አንጻር መጓተቱ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ  የህዝብ ተሳትፎና የመንግስት ብርቱ ትኩረት ሊነፈገው አይገባም የሚባልበት ግልፅ ምክንያቶች ግን አሉ፡፡ አንደኛው ከተፋሰሱ ሀገሮችም ሆነ ከሌላ ወገን  ግድቡን በመልካም ጎኑ የሚመለከቱት እንዳሉ ሁሉ፤ በመጥፎ ገፅታው  የሚመለከቱት ባለመጥፋታቸው ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው የሌሎች ሀገሮች ድጋፍ እንደሚኖርበት ቢታመንም በኤርትራው መንግስት አስታጣቂነት ፕሮጀክቱ በሚካሄድበት ስፍራ ላይ ከአንዴም ሁለት፣ ሶስት  ጊዜ የጥቃት ሙከራ መደረጉ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ የተቃራኒው ወገን ውጤት ያመጣበት ባይሆንም ተደጋጋሚ ውዝግብ ተነስቶበትም ታይቷል፡፡
የዓለም ሚዲያዎች እንኳን የግድቡን ግዝፈትና ፋይዳ ደጋግመው ሲዘግቡ፣ ገፅታችን መገንባቱና ሥራው ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ ቢያስደስትም አዘጋገባቸው ገና ሳይጠናቀቅ ፕሮጀክቱን የሚጠራጠሩ ተፃራሪዎችን የሚያበረክት  አካሄድ እንዳለው የሚናገሩ ነበሩ፡፡ ከሁለት ዓመት  በፊት  ሮይተርስ  ያወጣው ዘገባ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በግብጽ ለረዥም ዓመታት ተይዞ የነበረውን ወንዙን የመጠቀም የበላይነት የሚያስቀርና ሀገሪቱን የቀጣናው የኤሌክትሪክ ማማ እንደሚያደርጋት ጥርጥር እንደሌለው የሚያትት ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ ሌሎች ምሁራን የተናገሩት ቢሆንም በትንታኔው የቀረቡት በውሃ ቴክኖሎጂ ምርምር እውቅ የሆኑ ግብፃውያን ምሁራን ግን በአንድ ጊዜ ከ27 ሺ ሜጋዋት ሃይል በላይ ( አሁን ላይ ከ5ሺ እንደማይበልጥ ልብ ይሏል) አመንጭታ የምትጠቀመውን ሀገራቸውን ወደ ጎን ብለው ይህን ማለታቸው  ትዝብት ላይ  የሚጥልና “ዶሮን ሲያታልሏት …” የሚያሰኝ ነበር፡፡
በእርግጥም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑ ይታወቃል። ምክንያቱም ግድቡ የሀገራዊ የፀረ -ድህነት ትግሉ አንድ አካል ከመሆኑም በተጨማሪ ለዚህ ትግል ከዳር መድረስ ወሳኝ ሚና ያለው  እንደሆነ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ በተለይም በሀገራችን በፍጥነት እየተስፋፋ ላለው ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር፣ ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ቀጣይነትም ጉልህ ድርሻ የሚጫወት ስለመሆኑ አያጠራጥርም። ሀገራችን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለምታደርገው ሽግግር በሃይል አቅርቦት ብቻ ሳይሆን በቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፉ  በኩልም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ  ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህ የሚሳካው ግን ህዝቡ እውነታውን በግልፅ ተገንዝቦና በፕሮጀክቱ ላይ ተመላልሶ ከሚነዛው ውዥንብር ተላቆ፣ ተሳትፎውን በጀመረው መንገድ ማስቀጠል ሲችል ብቻ ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሃምሳ  ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ሀገራዊ የሃይል አቅርቦትን የሚያሳድግ ከመሆኑ ባሻገር፤ የቀጣናው ሀገሮች የሃይል እጥረትን ለሟሟላት ያለው ድርሻም ከፍተኛ  መሆኑ ይታመናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ድረስ በታችኛው የወንዙ ተፋሰስ ሀገሮች በተለይም በግብፅ በኩል ያደረው ስጋትና መጠራጠር ቀላል አይመስልም፡፡ እስካሁንም ድረስ መለስ ቀለስ በሚለው የድርድር ሙከራቸዉ በአንድ በኩል በእኛ ሀገር በኩል እምብዛም እንደ ስምምነት የማይቆጠረዉን የ1959 አጀንዳን የማንሳት፣ በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የመራመድ ብሎም ከምክንያታዊና ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ያፈነገጠ ድርድር የማድረግ ሙከራ  እየታየ ነው፡፡
በወቅቱ ሮይተርስ የግድቡ ጠቀሜታን አስመልክቶ እንደዘገበው፣ ግድቡ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል እንደ ኒውዮርክ የመሰሉ በአደጉ ሀገራት የሚገኙ ታላላቅ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ፍጆታ የሚሸፍን ከመሆኑም በላይ  የኤሌክትሪክ ሃይል ለተራቡ የቀጣናው ሀገራት መፍትሄ ሊሆን ይችላል ሲል ለግብፅም  ሆነ ለሱዳን ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእርግጥም የምንገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ያለበት መሆኑ አይካድም፡፡ የሃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታትም የኢፌዲሪ መንግስት በሚያራምደው የጋራ ተጠቃሚነት መርህ አኳያ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም ሌሎች ሀገሮች በሚፈለገው ደረጃ  ሀሳቡን ተቀብለው እየተንቀሳቀሱ ናቸው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡
ሌላው ቀርቶ ብዙዎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች በኢንቴቤው የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት ፊርማቸውን ቢያኖሩም በየምክር ቤታቸዉ ያለፀደቁት ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ለግድቡ ያላቸውን አጋርነት ከሱዳን በስተቀር ሌሎች ሲገልፁም አይሰማም፣ በይፋም አልታየም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በውስጥ ችግርና በድህነት ጭምር ለግብፅ ዲፕሎማሲ ጫና የተጋለጡ ሀገሮችም አሰላለፋቸው በግልጽ  አይታወቅም፡፡   
በእርግጥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ባላት አቅምና በውስን ደረጃም ቢሆን  ለአጎራባች ሀገሮች በተለይም ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ኬንያን ለመሳሰሉ ሀገሮች የኤሌትሪክ ሃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ትርጉም  ደግሞ ከዚህም በላይ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በአንድ በኩል የእነ ግብፅን  ለብቻ የመጠቀም አሮጌ አስተሳሰብ በማስወገድ አዲስ አስተሳሰብን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ያሰፈነ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጋራ የማደግና በሀገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ ያንን ለማድረግ ግን ግድቡ በሁላችንም ትብብር ሥራው ከዳር መድረስ ይኖርበታል፡፡ ለፖለቲካ ሴራም ሆነ ለውዝግባችን ምልክት ሆኖ ሊታይ አይገባም፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በውሃ ሀብታቸው የመጠቀም መብታቸው ተገድቦ መቆየቱን ማንም የሚያውቀው ሃቅ ነው። እነዚህ ሀገራት የበይ ተመልካች ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል፡፡ በዚህም ህዝቦቻቸው በድህነት ማጥ ተዘፍቀው እጃቸውን ለምፅዋትና ለልመና ሲዘረጉ ቆይተዋል፡፡ በውሃ ሀብታቸው ተጠቅመው የማደግና ከድህነት ቀንበር የመላቀቅ መብታቸውን  እንደ ህልም ሊቆጥሩትም ተገደዋል፡፡
ይሁንና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይህንን አሮጌ አስተሳሰብ በመስበር፣ በግብጽ ለረጅም ዓመታት ተይዞ የነበረውን ወንዙን የመጠቀም የበላይነት ማስቀረት የቻለ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር፤ የተፋሰሱ ሀገራትን ተስፋ ያለመለመ ስለመሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ግድቡ አዲስ አመለካከትን የፈጠረና ግለኝነትን አሽቀንጥሮ የጋራ ተጠቃሚነትን ያሰፈነ” እንደሆነ የሚነገርለት። እውነታው ይህ ይሁን እንጂ በሁሉም ዘንድ የጋራ ስሜት መፍጠር ተችሏል ለማለት የማይስደፍሩ የተለያዩ መደናቆሮችና እግር መጎተቶች ይታያሉ፡፡
በአንድ ወቅት ሀገሪቱ ለሃይል አቅርቦት የሰጠችውን ትኩረት ተከትሎ ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ ከምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል በተጨማሪ፤ ለሩዋንዳ አራት መቶ፣ ለየመን ደግሞ ዘጠኝ መቶ ሜጋ ዋት ለማቅረብ በድርድር ላይ እንደምትገኝ ሲገለፅ፣ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን አጭሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ሃሳብ እውን መሆን የሚችለው ግን ታላቁ ፕሮጀክት ተጠናቆ ሃይል ሲያመነጭ ብቻ  እንደሆነ  ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ከዚህ ቀደምም በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችን እንዳይከበር ካስገደዱን ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ድህነታችን  ነበር። ይህ ትናንት ነው። ዛሬም ቢሆን ግን አይፈጠርም ብሎ መደምደም  አይቻልም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየታያ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋትና የብሄረሰቦች ግጭት፣ የህዝቡንና ባለሀብቱን ተማምኖ ወደ ስራ መግባት ሊያውክ የሚችል ነው። የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትንም ያባብሳል። ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የአሜሪካ መንግስት በኤምባሲው በኩል፣ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረትም በተደጋጋሚ በልኡካኖቻቸው አማካኝነት የሚገልፁት ስጋት ብቻ አይደለም። ራሳቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ እየተፈጠረ ያለው መንግስታዊ ቅሬታና የመንግስትም  የማያረካና መንቻካ ምላሽ  ወደ ኋላ እንዳይመልሰን ስለሚያሰጋ ነዉ፡፡ ስለዚህ ቀድሞ እዚህ  ላይ ያለውን ትብትብ መፍታት ያስፈልጋል፡፡
በአንድ ወቅት የግብጹ አል ሃራም የአረብኛ ድረ ገጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግርን አስመልክቶ፤ “ኢትዮጵያ ከበርካታ ሀገሮች ጋር ህብረት የፈጠረች ሀገር በመሆኗ ግብጽ በምታካሂደው ዘመቻ በቀላሉ የምትጎዳ፣ ተፅዕኖ የሚደርስባትና ስትራቴጂካዊ ልማቷ የሚቀለበስ ሀገር አይደለችም” ሲሉ መናገራቸውን በስጋት ዘግቦ ነበር፡፡ ይህ የአል ሃራም ስጋትና የሀገራችን በራስ መተማመን እውን መሆን የሚችለው ግን እንደ ወትሮው ሁሉ ሀገራችን ሰላሟን ጠብቃ፣ ለቀጠናው ሰላምም ዘብ ስትቆም፣ ልማቱና ዕድገቱም ሳይስተጓጎል ሲቀጥል፣ እንዲሁም በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ የዜጎች መብት አጠባባቅ ሀገሪቱ ከወቀሳ ስትድን ብቻ ነው፡፡  አሁን ባለው የዓለም ተጨባጭ ሁኔታ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ዜጎች እየሞቱ፣ ሀብት እየወደመና ሀገሬው ዋስትና እያጣ  ሁነኛ አጋር ማግኘት ጨርሶ የማይታለም ነው፡፡  
እንደሚታወቀው ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ነበር፡፡ አሁንም የዲፕሎማሲ ድርድሩ እንደቀጠለ ቢሆንም በቀደመው ተግባሯ ስላለመቀጠሏ ማረጋጋጫ ማግኘት ያስቸግራል። እስከ አሁንም ድረስ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከምትላቸው ሃይሎች በተጨማሪ ድጋፍ ያበረክታሉ ብላ በምትጠረጥራቸው ሀገሮች ሁሉ ልዑካኗን በማሰማራት፣ ለዓላማዋ ስኬታማነት የሚቻለውን ሁሉ አንደምታደርግም ግልፅ ነው፡፡  በኢትዮጵያ  የውስጥ ጉዳይ በእጅ አዙር በመግባት ወይም ቅሬታዎችና ግጭቶች እንዲነሱ በማድረግ ስራ ላይ መጠመዷንም የኢትዮጵያ  መንግስት ደጋግሞ ይከስ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ ነባራዊ ሀቅ ነው በግድቡ ተፋጥኖ ማለቅ ላይ ተጨባጭ ስጋት አለብን የሚያሰኘው፡፡  
በቅርቡ ጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ለ16ኛ ጊዜ ምክክር ማድረጋቸዉ ተደምጧል። ውይይቱም አሁንም ድረስ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በታችኛዉ የተፋሰሱ ሀገሮች ላይ ስለሚያደርሰው  ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢዊ ተፅዕኖ፤ እንዲሁም የውሃ ሙሊትና አለቃቀቅ ተፅዕኖ ላይ ጥናት በማስጠናት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ለዚህም የጥናት አማካሪ ቡድኑ የሥራ መመሪያ ላይ ከስምምነት ቢደረስም አሁንም ግብፅ የተጽዕኖ ግምገማዉ ሲጠና የ1959 የግብጽ ውሃ “ስምምነት” ውስጥ ይካተት ማለቷ ኢትዮጵያን አስቆጥቷል። ይሄ በሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ከስምምነት ላይ የተደረሰውን የኢንቴቤ ስምምነትንም ወደ ኋላ የሚመልስ ነው፡፡
ይህ አካሄድ ደግሞ ከዚህ ቀደምም የተንፀባረቀ ሲሆን ተቀማጭነቱን አውሮፓ ያደረገው የውሃ ኢንስቲትዩት ባለሥልጣን፣ የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት ኤክስፐርት የሆኑት ዶክተር ኢና ካስካ፤ ግብጽ የህዳሴውን ግድብ በሚመለከት የወጣውን ዓለም አቀፋዊ ሪፖርት በምስጢር መያዟ አግባብነት እንደሌለው ከገለፁበት ክስተት ጋር ይዛመዳል፡፡  በመሆኑም አሁንም  ሀገሪቱ በታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅና ለጋራ ጥቅም መዋል ላይ የያዘችው ትክክለኛ አቋም ምን እንደሆነም ማረጋገጥ የሚያስችል ነገር አልተጨበጠም፡፡ በአጠቃላይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ተጋግሎ የተጀመረው ኢትዮጵያዊ ህብረታችን በሰመረ መንገድ እንዲቀጥል፣ የተወለካከፈው ፖለቲካ ተስተካክሎ፣ ሁሉን አሳታፊነትን መላበስ አለበት። ህዝቡም ከጥላቻና መጠራጠር ወጥቶ የተባበረ ክንዱን በፀረ ድህነት ላይ ማንሳት ይገባዋል፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው በግድቡ ሥራ ላይ ሊያጋጥም የሚችለው ማንኛውም የውስጥና የውጭ ስጋት ሊመከት የሚችለው፡፡ ያለበለዚያ ግን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በስጋት ጭጋግ ሥር መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

Read 7493 times