Sunday, 05 November 2017 00:00

ከፌስ ቡክ ገፅ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 
             የምሁራን ሚና ምንድን ነው?

        እንደ ጣና ተለቅ እና ጠለቅ፣ እንደ ዓባይም ረዘም ያለ ዓላማ/አጀንዳ የሚኖረው ጉዞ......

   ኦቦ ለማ መገርሳ ከነገ ወዲያ ቅዳሜ ከፊንፊኔ ይነሱና ወደ ዓባይና ጣና መገኛ... ወደ አማራ ክልል... ወደ ባሕር ዳር ይሄዳሉ። ጉዞው የፍቅርና የምክር ነው። የሰላም ጉዞ !
የኦሮሚያው ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ የብቻቸውን አይደለም ወደ አማራ የሚያቀኑት። ከ 300 በላይ የኦሮሚያ ባለሥልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች እና የዲያስፖራ አባላትም አብረዋቸው ይጓዛሉ። ከአማራ ክልል አቻዎቻቸው ጋርም በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ። እግረ መግዳቸውንም የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ። ከጣና የገነትን ንጹህ አየር እየሳቡ በባሕር ዳር ዘንባባዎች ሰልፍ ታጅበው ይዝናናሉ። በባሕር ዳር ውበት ሐሴትን ተላብሰው ጣናን በጥልቀት እያዩ እምቦጭን ይረግሙታል።
የጣናን አፍንጫ ተጠግታ በግዮን እግር ስር ከተቆረቆረችው ውቢቱ ባሕር ዳር ከመድረሳቸው በፊት... ገና ሰላሌን አልፈው ዓባይን ሲሻገሩና የአማራ ክልልን ሲረግጡ... ከደጀን ጀምሮ ልዩ አቀባበል ይጠብቃቸዋል። አቀባበሉ በሰዎች ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም ይታጀባል። አሁን ጥቅምት እያለቀ ነው። የጎጃም ምድር ሰብልን አዝሎ አሽቷል። የደጀን ለጥ ያለ ሜዳ በንፋስ አቅጣጫ በሚዘናፈል ማኛ ጤፍ ተሸፍኖ የመንገዱን ግራና ቀኝ አስውቦታል። በየማሳው ድንበር አደይ አበባ ፈክቷል። ተምጫ ወንዝን ተሻግሮ ምዕራብ ጎጃም ለም መሬት ባሸተ በቆሎ ተሸልሟል። ሳይበሉት ያጠግባል። ለዓይን ይማርካል፤ መንፈስን ያረካል።
የአዊ ሜዳዎች አረንጓዴ ናቸው። በድንች፣ በስንዴና በጤፍ አዝርእት ተሸፍነዋል። ሌላ ውበት.... ሌላ ሐሴት። ይህ የተፈጥሮ ቅኔ ብዙ ጥሪን ያስተላልፋል። በልዩነት ተውቦ አንድ የመሆንን ጥሪ።
የማኛ ጤፍ እንጀራ ምን በባለሙያ ተውቦ ቢጋገር፣ በጋራ መዓድ ካልበሉት አያምርም። መሶብ ሞልቶ በተዘናፈለው የለምለም እንጀራ መዓድ ዙሪያ የበቆሎ ጠላ ተቀድቶ ካልተቀመጠ ስሜትን ምሉዕ አያደርግም። አብሮ መብላት ባህላችን ነው። የሩቅ ወዳጅ ዘመድ ሲኖር ቤት ይደምቃል። አብሮነት ውበታችን ነው። አንድነት የሚያምረው ልዩነት ሲኖር ነው። ልዩነት ከሌለ ስለ አንድነት ማን ያወራል? አንድ የመሆን መንፈስ የሚመነጨው ከልዩነት ነው።
እሁድ ኦቦ ለማና የአማራው አቻቸው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመሩት የጋራ መድረክ ይጠበቃል። ከመድረኩም ብዙ አጀንዳዎች። ከአጀንዳዎችም ብዙ ተስፋዎች።
ከመድረኩ የለማ መገርሳ የአንድነትና የፍቅር ስብከት ይጠበቃል። ሰውዬው ሲናገር ያምርበታል። አንደበቱ ይጣፍጣል። ለነገሩ ፍቅርና አንድነትን የሚሰብክ አንደበት ላይጣፍጥ አይችልም።
የአማራ እና የኦሮሞ የበለጠ መግባባትና መተሳሰር ለሀገራችን ብዙ ማለት ነው። በጣም ብዙ። የሁለቱ ክልሎች ግንኙነት መጠናከር ማለት ከ80 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ አብሮነት ማለት ነው። የሕዝቦች አብሮነት ሀገርን ከፍ ያደርጋታል።
ሁሉንም የኢትዮጵያን ሕዝቦች በፍቅር አንድ ያድርግልን!!
ሰርገኛ ጤፍ ማን ነው?
(Andualem Y)
አንድ ወቅት ላይ የኦሮሞ ባላባቶች አንዲት የኦሮሞ መንግስት ለመመስረት አቅደው እንደነበር ይነገራል፡፡ የሀሳቡ አመንጪና ዋና አቀንቃኝ ደግሞ የጅማው አባ ጅፋር ልጅ ሱልጣን አባ ጆቢር ነበር። አባ ጆቢር ይሄንን እቅዳቸውን ለአካባቢ ባላባቶች ባማከሩ ጊዜ፣ ከባላባቶቹ መካከል ከአንዱ፣ የሜጫና ጅባት ባላባት ከሆኑት ከአባ ዶዮ ከባድ ፈተና ገጠማቸው፡፡
አባ ዶዮ፣ ቀይና ነጭ ጤፍ ደባልቀው “እስክመለስ ድረስ ለዩና ጠብቁኝ” ብለው ሄዱ። ሲመለሱ ጤፉን መለየቱ የማይቻል መሆኑ ሲነገራቸው፣ “በሉ አማራንና ኦሮሞን ለመለያየት ስለሚያስቸግር አገራችንን በህብረት እንገንባ እንጂ መለያየቱ ይቅር” አሉና ዕቅዱ ሥራ ላይ ሳይውል ቀረ፣ እየተባለ በሰፊው ይወሳል፡፡ (የ20ኛው ክ/ዘ/ን ኢትዮጵያ መፅሀፍ ላይ የተወሰደ)
የወቅቱ የኦሮሚያ አስተዳደር፣ እኒያን ብልህ የኦሮሞ መሪ አባ ዶዮን ያስታውሱናል፡፡ አገር ግንባታ ላይ የብቻ ጉዞ እንደማያዋጣ ፅኑ እምነት ይዘው ሲንቀሳቀሱ ማየት ከጀመርን እነሆ አመት ሊሞላን ነው፡፡ በኦቦ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር አብይ አህመድ፣ በእኒህ ሁለቱ መሪዎች አንደበት “ኢትዮጵያ” ስትጠራ መስማት ልብን በሀሴት ይሞላል፡፡ በየመድረኩ፣ “ስለ ጠባብነትና ስለ ትምክህት” እየተናገሩ ጆሯችንን አያደሙትም… ይልቁኑ “ስለ አንድነትና ስለ ፍቅር” ደጋግመው ሲናገሩ፣ ስለ ነገ ተስፋ እንድንሰንቅ ያደርጉናል፡፡
አቶ ለማ፣ “የኢትዮጵያ ህዝቦችን ያስተሳሰረው የደም ሐረግ ብርቱ ነው። ድልድያችን ሻማ፣ ከዘራችን ቄጤማ አይደለም፤ ዘመን ባስቆጠረ አብሮነታችን ወደላቀ ደረጃ እንደምንሸጋገር እናምናለን” ይሉናል። በተመሳሳይ፣ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢህአዴግ ለፖለቲካ ትርፋ ሲል እርስ በራሱ እንዲጠራጠርና በአይነቁራኛ እንዲተያይ ያደረጉትን የአማራና የኦሮሞ ህዝብ “ላይለያዩ በደም የተገመዱ ህዝቦች ናቸው” ሲሉ ዶክተሩ አብይ አህመድ አስረግጠው ይነግሩናል፡፡
ስለ ልዩነት ሳይሆን ስለ አንድነት፣ ስለ ጥላቻ ሳይሆን ስለ ፍቅር ሲነገር የሚጠላ እሱ ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ እኝህ ሁለት የወቅቱ መሪዎች ስለ ፍቅር ሲናገሩ፣ በሚመሩት የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ህዝቦች ልብ ውስጥም እንዲነግሱ አድርጓል፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተፈጠረውና ለግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ መፈናቀል ምክንያት በሆነው ቀውስ ዙሪያ፣ ዶ/ር አብይ ሃረርጌን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ስለ ፍቅር ሲናገሩ፡
“ሐረርጌ የፍቅር ሀገር ናት። ፍቅር ከዚህ ኤክስፖርት ሊደረግ ይገባል። ዓለምና ኢትዮጵያ በፍቅር እጦት በሚሰቃዩበት በዚህ ጊዜ እናንተ ፍቅርን የማታካፍሉን ከሆነ እየበላን እንራባለን…” ነበር ያሉን።
ስለ ኢትዮጵያና ስለ ልጆቿ በአንደበታቸው መልካም የሚናገሩ የፍቅር ሰባኪዎችን ሁሉ የኢትዮጵያ አምላክ ይከተላቸው!!”
ምንጭ//Andualem Y.//
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሕዝብ ተቃውሞና አመፅ እየታየ ነው። በሕዝቡ የተቃውሞ እንቅስቃሴና መንግስት እየወሰደ ካለው እርምጃ አንፃር የሀገሪቱ ምሁራን አቋምና ተግባር ምን መሆን አለበት? በዚህ ረገድ ምሁራኑ ሁለት አማራጮች አሏቸው። አንደኛ፡- የመንግስትን አቋምና እርምጃ በመደገፍ የህዝቡን እንቅስቃሴ ማውገዝ፣ ሁለተኛ፡- ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመንግስትን አቋምና እርምጃ መቃወምና መተቸት። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የሀገራችን ምሁራን፣ አንዱን ወገን በመደገፍ ወይም በመቃወም ሃሳብና አስተያየት ሲሰጡ አይስተዋልም። በእርግጥ ምሁራኑ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደረጋቸው ፍርሃት ነው። ይህ ግን የሚሸሹትን ነገር ከቤታቸው ድረስ መልሶ ያመጣዋል። ከራሳቸው አልፎ፣ በማህበረሰባቸውና በሀገራቸው ላይ ውድቀትና ጭቆና እንዲነግስ ያደርጋል።
በዘንድሮ አመት የተነሳውን የተቃውሞ አንቅስቃሴ ለመግለፅ በስፋት ጥቅም ላይ ከዋሉ ቃላት ውስጥ፤ “ሰላም – ፀረ-ሰላም፥ ሽብር – ፀረ-ሽብር፥ ልማት – ፀረ-ልማት፥ ሕዝብ – ፀረ-ሕዝብ፥ ሕጋዊ – ሕገ-ወጥ፣..” የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ ደግሞ በመንግስት ሚዲያዎች፤ “የፀረ-ሰላም ኃይሎች፥ የነውጥና ብጥብጥ ቀስቃሾች፥ የሽብር ኃይሎች፥…” የሚሉ ለዛ-ቢስ አባባሎች (Cliches)፣ “ሣይቃጠል በቅጠል፥ ፀጉረ-ልውጥ፥…” የመሳሰሉ አሰልቺ ዘይቤዎች (tired metaphors)፣ እንዲሁም “ጥቂት፥ የተወሰኑ፥ አንዳንድ፥…” የሚሉ የግብር-ይውጣ አገላለፆች (lazy writing) በስፋት ይደመጣሉ። እንግሊዛዊው ፀኃፊ ጆርጅ ኦርዌል፤ ይሄን “የፖለቲካ ቋንቋ” በማለት ይገልፀዋል። የሀገራችን ምሁራን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደረጋቸው ፍርሃት ዋና ምንጩ ደግሞ የፖለቲካ ቋንቋ ነው።
የፖለቲካ ቋንቋ በስፋት በሚዘወተርበት ሁኔታ አብዛኞቹ ምሁራን “ደጋፊ” ወይም “ተቃዋሚ” ተብለው በጅምላ እንዳይፈረጁ በመስጋት አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ፣ ከትችትና ነቀፌታ አልፎ ለእስራትና ሞት ሊዳርግ ይችላል። ስለዚህ ምሁራን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየት በነፃነት መግለፅ ይፈራሉ። ነገር ግን፣ ጆርጅ ኦርዌል፤ የመንግስትን አቋምና እርምጃ በይፋ ለመቃወም የሚፈሩ ምሁራንን “un-political’ imaginative writers” በማለት ይገልፃቸዋል። እነዚህ ምሁራን ለዛ-ቢስ፥ አሰልቺና የግብር-ይውጣ የሆኑ የፖለቲካ ቃላትና አባባሎችን ከሚፅፉትና ከሚያነቡት የመንግስት ጋዜጠኞች ብዙም የተለዩ እንዳልሆኑ እንደሚከተለው ይገልፃል፡-
“And so far as freedom of expression is concerned, there is not much difference between a mere journalist and the most ‘un-political’ imaginative writer. The journalist is unfree, and is conscious of un-freedom, when he is forced to write lies or suppress what seems to him important news: the imaginative writer is un-free when he has to falsify his subjective feelings, which from his point of view are facts. …If he is forced to do so, the only result is that his creative faculties dry up. Nor can he solve the problem by keeping away from controversial topics. There is no such thing as genuinely non-political literature.” (George Orwell, Politics And The English Language, 1946)
በፍርሃት ምክንያት ሃሳብና ተቃውሞን በይፋ አለመግለፅ፣ መንግስት በህዝቡ ላይ እያደረሰ ላለው ጭቆናና በደል፣ ድጋፍና ትብብር እንደማድረግ ነው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ምሁር ለበደልና ጭቆና ድጋፉን ከመስጠት ይልቅ ፍርሃቱን መጋፈጥ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ የፍርሃቱ ምንጭ የሆነው የፖለቲካ ቋንቋ፤ መሰረታዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ከመረዳት ይጀምራል። እንደ ጆርጅ ኦርዌል አገላለፅ፣ የፖለቲካ ቋንቋ ውሸትን እውነት፣ ግድያን ክብር በማድረግና ከነጭ-ውሸት ጋር ህብረት እንዳለን ለማስመሰል የተቀረፀ ነው “Political language is designed to make lies sound truthful and murder respectable, and to give an appearance of solidity to pure wind”.
በዚህ ላይ ኢድዋርድ ሳይድ የተባለው ምሁር ደግሞ ምሁራን ከእንዲህ ያለ ቋንቋና ተግባር ጋር ምንም ዓይነት ሕብረት ሊኖራቸው እንደማይገባ ይጠቅሳል። እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም “Representations of an Intellectual – Holding Nations and Traditions at Bay” በሚል ርዕስ በሰጠው ትንታኔ፣ ምሁራን ከተጨቆኑ ወገኖች ጎን በመቆም ትችትና ተቃውሟቸውን የማሰማት ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-  “Never solidarity before criticism” is the short answer. …This does not mean opposition for opposition’s sake. But it does mean asking questions, making distinctions, restoring to memory all those things that tend to be overlooked or walked past in the rush to collective judgment and action.”
እንደ ኢድዋርድ ሳይድ አገላለፅ፣ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት መንግስትን በግልፅ መተቸት ነው። ከምሁራን የሚጠበቀው፣ ሁሉንም ነገር በጭፍን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መለየትና መፍትሄ የሚሹ ነገሮችን መጠቆም፣ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ችግሮችን በማስታወስ ዳግም እንዳይከሰቱ ማሳሰብና የመሳሰሉትን በማድረግ፣ ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ነገር ግን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ብሔሮች፣ ሃይማኖቶችና ቋንቋዎች ባላቸው ሀገራት ነገሮች ቀላልና ቀጥተኛ አይደሉም። አሁን በኢትዮጵያ እንደሚታየው ዓይነት፣ ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲኖር ምሁራን በተዓማኒነታቸው ላይ ምህረት-የለሽ አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃሉ።
እንደ ማንኛውም ሰው፤ ምሁራን የራሳቸው ሀገር፥ ብሔር፣ ማህበረሰብና ቤተሰብ አላቸው። ምንም ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ቢኖራቸው፣ ምሁራኑን ከቤተሰቦቻቸው፥ ማህበረሰባቸው፣ ብሔርና ሀገራቸው ጋር ከሚያስተሳስረው ተፈጥሯዊ ገመድ በላይ ጠንካራ ሊሆን አይችልም። በዚህ ምክንያት፣ ለምሳሌ በራሳቸው ብሔር ተወላጆች ወይም በቤተሰቦቻቸው ላይ ጭቆና ሲደርስ ከሌሎች ብሔር ተወላጆች በላይ ሊሰማቸው፣ ከወትሮው በተለየ ትችትና ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስታት ከአንዱ ወይም ከሌላው ብሔር የቋንቋ፣ ባህልና ሥልጣን የበላይነት ጋር ተያያዥነት አለው። ስለዚህ፣ የመንግስት አስተዳደራዊ ችግሮች በብሔሮች ላይ የተፈፀሙ በደሎችና ጭቆናዎች ተደርገው የመወሰድ እድላቸው የሰፋ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሕዝቦች መካከል ያለው ልዩነት ሰው-ሰራሽ እንጂ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ማሳመን ይጠበቅባቸዋል። በአንድ ሕዝብ ላይ የተለየ ጥቃትና ጭቆና ሲደርስ ግን ሕዝቡን በመወከል መተቸትና መቃወም፣ በሕዝባቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ወይም ከዚህ በፊት የደረሰውን በደል፣ ጭቆና እና ግድያ በይፋ በመቃወም ለህዝባቸው ያላቸው ድጋፍና አጋርነት መግለፅ ይጠበቅባቸዋል።
ከላይ እንደተገለፀው፣ የምሁራን ኃላፊነት በሀገራቸው፥ ብሔር፥ ማህበረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና ከመናገር ባለፈ ተመሣሣይ በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መናገር፣ ማሳወቅ፣ መተቸትና መቃወም ነው። በቀድሞ ስርዓት በእኛ ብሔር፥ ማህበረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ ስለደረሰው ድብደባ፥ እስርና ግድያ መናገርና ማስታወስ እንዳለ ሆኖ፣ የምሁራን መለያ ባህሪ በእነሱ ብሔር፥ ማህበረሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ የደረሰው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ እንዳይደገም፣ በእነሱ ላይ ሲደርስ የተቃወሙትን ነገር በሌሎች ላይ እንዳይደርስ መቃወም ነው።
(ከስዩም… ፌስቡክ ተቀንጭቦ የተወሰደ)

Read 1177 times