Print this page
Sunday, 05 November 2017 00:00

ለኢትዮጵያ ኋላ ቀርነት ተጠያቂው ላሊበላ?

Written by  በዓለሙ ኃይሌ
Rate this item
(3 votes)

“በዚህ ሕንጻችሁ ብቻ ዓለምን አሸንፋችሁታል” (የሶቭየት ሕብረት ፓትርያርክ)
         
   ስለ ኢትዮጵያ የተነገሩና የተጻፉ አያሌ ሥራዎችን ስንመረምር፣ ሀገሪቱ በአብዛኛው በጐ ነገር ሲተረክላት የኖረች መሆኗን እንገነዘባለን፤ ከፍተኛ ስፍራም ተሰጥቷት እንደነበር እንረዳለን። ተዘግኖ ከማያልቀው አኩሪ ታሪኳ አንዳንዱን ብንጠቅስ፣ የሰው ዘር መፀነሻ ማሕፀን፣ የሥልጣኔ መነሻ ማዕከል፣ ሀገረ እግዚአብሔር፣ የሐቀኞች ምድር፣ የክርስቲያን ደሴት (እኔ አይደለሁም ያልኩት፤ ኢንሳይክሎፒዲያን ይመልከቱ)፣ የነፃነት ባለቤት፣ የግዮን /ዐባይ/ ምንጭ፣ የታሪክ መዝገብ፣ የቱሪስት መስህብ፣ የቅርስ መደብር፣ የውርስ መዘክር ፣ የባሕል ዕምብርት፣ የፊደል እትብት ወዘተ ተብላለች፡፡
ገና ዓለም ጨለማ ውስጥ በነበረበት ወቅትና አብዛኛው  ባሸለበበትና እስከ መኖሩም ባልታወቀበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ አግራሞትና አድናቆት የተቸራቸው፣ ምስጋናና አክብሮት የተሰጣቸው  የጥበብ ሥራዎች ሠርታ፣  የዘመን ማከማቻ የሆኑ ቅርሶች አበርክታ እንደነበር ዛሬም ድረስ በምስክርነት ቆመው የሚናገሩ ማስረጃዎች ዋቢ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬ የሕዝቧ ቁሳዊ ፍላጐት ተሟልቷል፣ ፋብሪካ ተበራክቷል፣ ዘመናዊ ሥልጣኔ ተስፋፍቷል፣ ብልጽግና ተገኝቷል ተብሎ አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡ ችግር ዐይኑን አፍጥጦ፣ ድህነት ጥርሱን አግጥጦ፣ ኋላ ቀርነት ተንሰራፍቶ፣ ጉስቁልና ቤቱን ሠርቶ ወዘተ--- ይገኛልና፡፡  ይህ ለምን ሆነ? ጥንታዊ ሥልጣኔያችንስ ለምን ሳይስፋፋና ሳይቀጥል ቀረ? ለምንስ የሁሉ ጭራ ሆነን ቀረን? እንዴት “ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” ሆንን?  “ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞች ፊተኞች” የተባለው የክርስቶስ አባባልስ እንዴት ደረሰብን? የዳቦ ቅርጫት የተባለች አገር፤ በምን ምከንያት የረሀብ ቅርጫት ልትባል በቃች? የሚለውን ዕንቆቅልሽ ለመፍታት አያሌ ምሁራን ሲጠይቁ፣ መንስኤውንም ለማወቅ ሲጨነቁ እናያለን፡፡ አንዳንዱ ከስንፍና ጋር፣ ሌሎች ከገዥዎቻችን እኩይ ተግባር ጋር፣ ሌላው ከጦርነት  ጋር፣ ጥቂቶች ደግሞ ከበዓላት ብዛት ጋር፣ ሌሎች ዘወትር ከማይተኙልን ከውጭ ጠላቶች ጋር፣ አንዳንዶች ደግሞ ከባሕር በሮቻችን በባዕድ ዜጐች መዘጋት ጋርና ከውስጥ የሥልጣን ፉክክር፣ እርሱንም ተከትሎ ከሚነሣው ግርግር ጋር ያያይዙታል። በተለይ ሰላም ለኢትዮጵያ ቅንጦት እንደነበርና በዚህም ምክንያት ከመፋጀት በስተቀር ለመሥራት፣ ለመሻሻል፣ ለመማር፣ ለመመራመር፣ ለማሰብ፣ ለማብሰልሰል፣ ለመጠየቅ፣ ለማወቅ፣ ለመፈልሰፍ፣ ለመፈላሰፍ ዕድል እንዳልነበረ የጻፉ አሉ፡፡
አሁን በቅርቡ ደግሞ ከፈላስፋዎቹ ከዘርዓ ያዕቆብና ወልደ ሕይወት አንፍራዛዊ አተያይ በመነሣት፣ የኋላ ቀርነታችንና የድህነታችን ምከንያቶች፣ ከምንኩስናና ብሕትውና ኑሯችን ጋር የተያያዘ ነው ማለት ተጀምሯል፡፡
ለዚህም ሐሳብ ዋና አቀንቃኙ የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡ በሳቸው ሐሳብ ተስማምተው፤ “የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ አሁን ዘመን ድረስ ያሳለፈውን የእሴት ሽግግር እንዲሁም አሁን ባለንበት ኋላ ቀር የማኅበረሰብ ሁኔታ ወደ ኋላ ሄደው፣ መነሻ ምክንያቶችን በታሪክ ውስጥ በርብረው ያሳዩን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ናቸው፡፡  ቀድመን ጀምረን ለምን መጨረሻ እንደቀረን፣ የታሪክ ዱካዎችን ተከትለው ሄደው፣ የኋልዮሽ ጉዞ መቼና እንዴት እንደተጀመረ የነገሩን ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው” የሚሉን ደግሞ ሌላው የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መጽሐፍ ደራሲ ብሩህ ዓለምነህ ናቸው። ብሩህ በነሐሴ 2ዐዐ9 ዓ.ም ባሳተሙት በዚህ መጽሐፍና በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ደጋግመው ጽፈዋል፡፡  ዋናው ሐሳብና አዲስ ግንዛቤም፤ “አክሱማዊነትና ላሊበላዊነት” የሚለው ፍልስፍና ሲሆን አክሱማዊነት የሰውን ልጅ ምድራዊ የበላይነት የሚያንጸባርቅ ሲሆን ላሊበላዊነት ደግሞ የሰውን ልጅ ምድራዊ ዝቅተኛነት ያመለክታል። ጥንታዊ የአክሱም ሐውልት በራሱ የተማመነ፣ ወደ ሰማያት በድፍረት አንጋጦ አማልክቱንና ከዋክብቱን፣ ጨረቃንም ወደ ላይ አፍጥጦ “እኔ እንዲህ ነኝ፤ ይሄንንና ያንን ማድረግ ችያለሁ” ብሎ የሰውን ልጅ ምድራዊ የበላይነት ኩራት የሚያበስር ነው፤ ላሊበላ ድንጋይ ፈልፍሎ ወደ ምድር አጎንብሶ፣ ራሱን ዝቅ በማድረግ፣ እላዩ ላይ የመስቀል ምልክት ጭኖ ፈጣሪን “አንተ የሁሉም በላይ ነህ” የሚል ሲሆን ይሄም የመለኮትን ሃያልነትና የሰውን ልጅ ዝቅተኛነት የሚያስተጋባ ነው፡፡” ሲሉ የዶ/ር ዳኛቸውን ሐሳብ ደጋግመው አንስተውተል፡፡
ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምም ይሄንን ዘመን “የብሕትውና ዘመን ጅማሮ ይሉታል” ሲሉም ያክሉበትና ደራሲው፤ “የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተሠሩበት ዘመን የብሕትውና ዘመን መጀመሪያ ሳይሆን እንዲያውም ብሕትውናው በጣም አድጎ፣ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ነው” ይሉታል (የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ 2ዐዐ9 ገጽ 2ዐዐ)፡፡
“ከ11ኛው ከ/ዘመን በኋላ መንፈሳዊ ሕይወት የበላይነት ማዕከል በሆነችው ላሊበላ ተተካች፤ ላሊበላውያን የአክሱማዊነትን መንፈስና እሴት እርግፍ አድርገው ትተው፣ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ብቻ ተጠመዱ . . . ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት ያደረግነው ሽግግር በስተመጨረሻ በምድራዊ ሕይወቱ የደኽየና በቁሳዊ ሐብቱም የተራቆተ ማኀበረሰብን በመፍጠር ተደመደመ” /ገጽ 214/፡፡
እንዲህ እንዲህ እያሉ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያን ኋላ ቀርነት፣ ድህነት፣ ድንቁርና በጠቅላላው የችግር ማጥ ውስጥ መዘፈቅና የጨለማ አዘቅት ውስጥ መውደቅ፣ በማያልቅ መከራ ውስጥ መስመጥ፣ ለልመና መዳረግና የዓለም ጭራ ሆና መቅረት ምክንያትን በላሊበላ ላይ የደፈደፉት፡፡ ይኽንንም ሲያጠናክሩት፤ “በአክሱም ጊዜ መከበሪያ የነበሩ ሥራዎች በላሊበላ ዘመን መሰደቢያ መሆናቸውንና በፊት ብረት የማቅለጥ፣ መርከብ የመሥራት፣ ሕንፃ የመሥራት እንደ ትልቅ የእጅ ሙያ ሲቆጠሩ የነበሩት፣ በላሊበላ ዘመን ግን የትልቅነት መገለጫው የማይሠሩ እጆች ሆኑ፤ በሃይማኖት ትምህርት መላቅ፣ በፊት ትልልቅ ቴክኖሎጂዎችን ሲሠሩ የነበሩት ባለሙያኞች፣ በላሊበላ ዘመን ቀጥቃጭና አንጥረኛ እየተባሉ ተገፈተሩ” /ዝኒ ከማሁ/ ይሉናል።
ፀረ ምንኩስና አመለካከት የነበራቸው ኢትዮጵያዊያኑ ፈላስፎች፣ ዘርዓያዕቆብና ወልደ ሕይወት፣ ምንኩስናን፤ የሰውን ፍጥረትና የፈጣሪን ጥበብ የሚያጠፋ፣ ከጠወለገና ከደረቀ እንጨት ጋር በማመሳሰልም፤ “ምዑት” ሲሉት፣ መነኩሴዎችን የሾዎች፣ በክፉ በሽታና ተፈጥሯቸው ባልሆነ በሌላም የፍትወት አበሳ /በግብረ ሰዶማዊነት/ ዝሙት ወጥመድ የሚጠመዱ፣ የሞቱ፣ ከንቱዎች፣ ዋሾዎች፣ በሚዛን የቀለሉ፣ የፈጣሪ ከሃዲዎች፣ ሥርዓት አፍራሾች፣ እንስሳትን የመሰሉ… ኧረ እንዲያውም ከእንስሳም የባሱ” በማለት ምንኩስናን የሚያስበልጠውን የሰው አመለካከት ደግሞ “ወስላታ የሰው ሚዛን” /ገጽ 36/ ብለው መወረፋቸውንና ማዋረዳቸውን ይነግሩንና፣ “በምንኩስና ባህል የተነሣ የኅብረተሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት የተመሰቃቀለ ሆነ፤ ምንኩስና ኅብረተሰቡ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ምስቅልቅል ሕይወት ፈጠረ” ይላሉ፡፡
በመነኮሳትና በካህናት ላይ የወረደው ቃለ ጽርፈት በቀላሉ የሚያልቅ አይደለም፡፡ አለቃ ዐፅመ፤ የላሊበላ ዘመን፤ የኋላ ቀርነታችን፣ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የመሄዳችንና ለዘመናት በድህነትና በበሽታ፣ በረኀብ፣ በርዛት፣ በምፅዋት የመኖራችን ዋነኛው ምክንያትና ምንጭ መሆኑን ባይጠቅሱም፣ ለጥንታዊ ሥልጣኔ መውደቅና የእርስ በርስ የጦርነት አውድማ መሆን፣ ካህናቶችን ተጠያቂ ማድረጋቸውን አሁንም “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል፡-
“ከ15ዐዐ እስከ 19ዐዐ የተለወጠ ነገር የለም፤ በኢትዮጵያ በየወንዟ የፈሰሰው ደም፣ የተደረገው ሥራ ጥፋቷም ምንጩ አንድ ነው፤ ይህችን የከበረችና የኖረች መንግሥት አስረጅተው ያደነቆሯት ካህናት ናቸው፡፡ የክፋት ምንጮች፣ የድንቁርና መሥራቾች፣ በካህናት ክፋት የተነሣ የሸፈቱትን በኢትዮጵያ ስንቱን እንጽፋለን? ሀገሪቱም ጥቂት ቀን ከጦርነት አርፋለሁ ስትል፣ ካህናት የሃይማኖትን ነገር ያነሳሉ፤ መርዝና ቂም ያለበት ስብከታቸውን ይዘው በየመኳንንቱ ይዞራሉ፤ ከቤተ ክርስቲያን ሳይሄዱ በማለዳ ወደ ቤተ ነገሥታት ይሄዳሉ” /ዝኒ .ከ/። እግዚኦ ያንት ያለህ?! ጉድ ነው ከማለት በቀር ምን ማለት ይቻላል!?  ታዲያ እስካሁን ድረስ ያልተባለ ነገር ቢኖር፣ ለዛሬው የዘረኝነት፣ የጐሰኝነት፣ የመከፋፈል፣ የመፈናቀል፣ አገር የመገነጣጠል እንዲሁም  እያንዣበበ ላለው የመከራ ደመና፣ የመሰደድና የዓሣ ነባሪ ቀለብ መሆን፣ ለዛሬው የሐገሪቱ ውርደት፣ ለወረደባት መቅሰፍትና ወደብ አልባነት፣ ፍጅት ወዘተ --- ምክንያቱ “ላሊበላዊነትና ካህናት” ናቸው የሚለው ብቻ ነው፤ ዳርዳርታው ከዚያ ባይርቅም፡፡
ሮማውያኑ ነገሥታትና ገዥዎች፤ ትልቅነታቸው ጨርሶ ጠፍቶ ለድሎትና ለጌጥ፣ ለግልሙትናና ለጭካኔ ሥራ ለቆ፣ ጠባያቸው ተበላሽቶ፣ ዝሙትና ስካር፣ ሌብነትና ክህደት ወዘተ ተንሠራፍቶ፣ ፍቅርና አንድነት፣ ሰላምና ትእግስት፣ ምክርና ውይይት ጠፍቶ፣ ሌሎች ኃይለኞች አይረቤነታቸውን አጢነው ሲመጡ፣ መንግሥታቸው እንደ አሮጌ ሕንፃ ተንዶ ወደቀ፤ ሮም በተራዋ የተገዥነት ቀንበር ተሸከመች፡፡ ግሪክ በጥበብ፣ ሮም በአስተዳዳር ናላ ሆነው ኖረው፣ ኋላ ሲወድቁ ያልሠለጠኑ ኃይላቸው ሲገን፣ ዓለም ወደ ኋላ ቀርና፣ ጦርነት፣ የጨለማ ዘመን ሲመጣ፣ የሮማ መንግሥትም ታላቅ አወዳደቅ ሲወድቅ፣ “ክርስትና ነው ይህን ያመጣብን” ብለው ከሰሱ። ምክንያቱም ክርስትና የጣኦት አማልክቶቻችንን በማዋረዱና “በአንድ አምላክ እመኑ፣ የክርስቶስን አዳኝነት ተቀበሉ” በማለታቸው ነው ሲሉ ምክንያት ደረደሩ፡፡ በጠባያቸው መበላሸት መውደቃቸውን ረስተው፣ ሮምን ባጠፉት ልዩ ልዩ ሕዝቦች አውሮፓ ተበጠበጠች፤ ጥበብ ጠፋች፤ አቲላ ጨካኙ ከእስያ ተነሣ፤ “ፈረሴ ባለፈበት ቦታ ሁሉ ሣር አይበቅልም” ይል ነበር፡፡ በጭካኔው “የእግዚአብሔር መቅሰፍት” ተባለ፡፡ በ57ዐ መሐመድ በሰይፍ ለማስለም ተነሣ፤ በጦር ዓለም ተበጠበጠች፤ ኋላ እስላሞች ጌጥ፣ ደስታ፣ ምቾት ፣ ስንፍና ስላደረባቸው ተዳከሙ፡፡ ግሪክ ስትፈርስ ተንሰቅስቆ ያለቅስ ለነበረው ሰው፤ “በወንድነት ተከራክረህ ለማዳን ያልቻልከውን አገር፤ እንደ ሴት አልቅስላት” እስከ መባል ደረሰ /ከበደ ሚካኤል/፡፡
እኛም መስማማት፣ መነጋገር፣ መወያየት ጠንክሮ መሥራት፣ መፋቀር፣ መተባበር፣ ጊዜያችንን በቁም ነገር ላይ ማዋል፣ ካለፉት የዓለም ጥፋቶችና ውደመቶች፣ ጦርነቶችና ድርጊቶች ተምረን ያንን ጥፋት ላለመድገም መትጋት ተስኖን ብንጠፋ ምክንያታችንን፣ ከክርስትና እርሱንም ተከትሎ በመጣው ምንኩስናና /ብሕትውና/ ብቻ እያመካኘን ብንፈላሰፍ፣ ለችግራችን መፍትሄ እምናመጣ አይመስለኝም፡፡ ኢመርስን የተባለው አሜሪካዊ ምሁር፤ “ከታሪክ የምንማረው ነገር ቢኖር ሰዎች ከታሪክ ለመማር አለመቻላችንን ነው” ያለው ጥልቅ ብሂል፣ በኛም ላይ እንዳይፈጸም ያሰጋል፡፡  ካለፈው በዓለምና በኛም ከደረሰው ጥፋት እየተማርን አይደለምና፡፡
“አሳብህን ባልቀበልም እንድትገልጸው ያለህን መብት ግን እስክሞት ድረስ አከብርልሃለሁ” እንዳለው ታላቁ ፈላስፋና ደራሲ /ቮልቴር/፣ የአክሱማዊነትና የላሊበላዊነትን ሐሳብ ቀርቶ ሌላ የፈለገውን ቢል እኔም ሐሳቡን አከብራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ለመቀበል ግን እቸገራለሁ፡፡ ምከንያቱም “ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳልና።
ላሊበላ የመጠቀና የረቀቀ የግዙፍ ፕሮጀክት ሥራ ውጤት ነው፡፡ ምጡቅ የሆነ አእምሮ በነበራቸው የጥበብ መሐንዲሶች የታነጸ መሆኑን እንመለከታለንና፤ የተለያየ ረቂቅ ጥበባት ፈሶበት እንደታነጸ እናያለንና፤ የብልሆቹን ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ችሎታ /ክሂሎት/ እንገነዘብበታለንና፤ የታታሪዎቹንና የጠንካሮቹን፣ የዐዋቂዎቹን፣ የቆራጦቹንና የሥራ መሐንዲሶቹን፣ ያባቶቻችንን ማንነት፣ የቀደምት ኢትዮጵያዊያንን ትጉህነት፣ሥራ ወዳድነት፡ አዳዲስ የፈጠራ ሐሳብ አፍላቂነት፣ ያፈለቁትን ሐሳብ በንድፈ ሐሳብ /ቲዎሪ/ ብቻ ሳያስቀሩ፣ የተወሩትን በተግባር አዋይነት እናስታውልበታለንና፡፡ እንደነ ገጣሚ ሰሎሞን ደሬሳና ሠዓሊ ወቀራፂ በቀለ መኮንን የመሳሰሉት በሳል ምሁራን፣ የገረማቸውም ከሥራው ይልቅ መጀመሪያ ሐሳቡ እንዴት እንደመጣላቸው ነበር። እውነትም ይገርማል፤ ይደንቃል፡፡ ድንጋይ እኮ በዓለም ሁሉ ሞልቷል ግን ድሮም ሆነ ዛሬ ድንጋይን አይቶ ማለፍ፣ ቢበዛ ካብ መካብ እንጂ ሌላ ቁም ነገር ላይ ሲውል አልታየም፡፡ እነ ቅዱስ ላሊበላ ግን ይህን ግዑዝ ነገር “ሕይወት” ሊዘሩበት አሰቡ፣ አብሰለሰሉ፣ አወጡ፣ አወረዱ፣ ተፈላሰፉ፣ አውጠነጠኑ፣ በሐሳባቸው ከመሬት ልብ ውስጥ ድንጋይን ቆፍረው አውጥተው፣ ለክተው፣ መትረው፣ ውሃ ልክ አውጥተው፣ ከታች ከመሠረቱ ሳይሆን ከላይ ከአናቱ አንስተው ወደ ታች በመውረድ ጠርበው፣ ፈልፍለው፣ ሞርደው፣ አለስልሰው፣ በሐረግ፣ በሥዕል፣ በቅርፃ ቅርፅ፣ በዲዛይን አስጊጠው፣ በመልክ አስውበው፣ ከአንድ ድንጋይ የተለያዩ በርካታ ሕንጻዎችን አንጸው፣ ዐለምን ዕፁብ ድንቅ ሊያሰኙትና ሊያስደንቁት፣ ሊያስገርሙትና “ዕፁብ ያንተ ሥራ” ሊያስብሉት፣ ከአራቱም ማዕዘናተ ዓለም ቱሪስቱን ወደ ኢትዮጵያ ሊያጐርፉት፣ ሰው “ማሰብ ባይችል እንኳ ማሰብ እንደሚችል ሊያሳውቁት”፣ መኖር ማለት መተንፈስ ፣ መብላትና መተኛት ብቻ ሳይሆን፣ ማሰብና መሥራት መሆኑን ሊያስተምሩት ቆርጠው ተነሡ፡፡  የአሜሪካው ሊቅ ኢመርሰን፤ “እያንዳንዱ ሐሳብ፣ ለእያንዳንዱ ሥራ እናቱ መሆኑን እናውቃለን” እንዳለው፣ ይህ በእነ ቅዱስ ላሊበላ አእምሮ የተፀነሰው ትልቅ ሐሳብ፣ እውን ሆኖ በተግባር ውሎ፣ እነ ሕንፃ ላሊበላን፣ ይምርሃነ ክርስቶስንና ነአኩቶለአብን የመሳሰሉ የጥበብ ልጆች አሰገኘ፡፡
ኧረ እንደምን አርጎ ሠራው
ኧረ እንደምን አርጎ አነጸው
የመጥረቢያው እንኳ እጀታ የለው
ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
ዐይኔ ዓለም አየ እግሬ ደርሶ
የድንጋይ ወጋግራ የድንጋይ ምሰሶ
--እያለ በጥዑም ዜማ፣ በሠናይ ቃና ኢትዮጵያዊው ሳሚ /ተሰላሚ/ ሲያዜም፣ የቅኔው ሊቅ ደግሞ ሥራው አልጠገብ፣ ሁልጊዜ አዲስ ቢሆንበት “ሞት ሕንጻ ላሊበላ ኩለሄ እንግዳ” አለና ተቀኘ፡፡  “ሞትና የላሊበላ ሕንጻ ሁልጊዜ አዲስ፣ ሁልጊዜ እንግዳ ነው አይለመድም” ማለቱ  ነው።  ይበል ያሰኛል፡፡ ፈረንጆችም፤ “Incredible (የማይታመን) Spectacular, Astonishing, Amazing, surprising እያሉ ያሞግሳሉ (ግሩም ድንቅ እጹብ ለማለት ነው)፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ፣ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ እንደ ላሊበላ ሕንፃ ያለ በዚች ኘላኔት እንዳልተሠራ፣ ወደፊትም እንደማይሠራ የጻፉ በርካታ ናቸው፡፡
የፍራንሲስኮ አልባሬዝን አባባል፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ያነበበ ሁሉ የሚያስታውሰው ነው። ይህ በ152ዐ እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፖርቹጋላዊው አሳሽ፤ 6 ዓመት ሙሉ በሀገሪቱ ቆይቶ፣ ሕንጻ ላሊበላን ከጫፍ እስከ ጫፍ ጐብኝቶ፣ አጥንቶ ብዙ ካደነቀ በኋላ፤
“ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሥራ ብዙ ብጽፍም  የሚያምነኝ ሰው መኖሩ በጣም ያስጨንቀኛል፤ ያሳስበኛልም፣ እስካሁን ያልኩትም እንኳ ቢሆን ውሸት ነው የሚሉኝ፤ ነገር ግን የጻፍኩት በሙሉ እውነት ለመሆኑ በኃያሉ እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ በላይ ማለት ይቻል ነበር፤ ሆኖም ስሜ በቀጣፊነት እንዳይነሣ እሰጋለሁ . . . ይህን የሚመስል በዓለም እንደማይገኝም እገልፃለሁ”
--- በማለት “እባካችሁ እመኑኝ እውነት ነው” ሲል ለማያምኑ ለማሳመን፣ እየማለና እየተገዘተ ለዓለም አስተዋውቆታል፡፡ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ብዛት ያላቸው የሀገራት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ደራሲዎች ፣ መሐንዲሶችና፣ ሠዓሊዎች፣ ቀራፂዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተጓዦች፣ አሳሾች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ ቱሪስቶች ወዘተ ጐብኝተውታል፡፡ አንድ ስማቸውን የዘነጋኋቸው የሶቭየት ኅብረት ፓትርያርክ ግን በአድናቆትና በተመስጦ ለአቀባበል ለተሰበሰበው የላስታ ላሊበላ ሕዝብ፤“በዚህ ሕንጻችሁ ብቻ ዓለምን አሸንፋችሁታል” ያሉት አይረሳኝም፡፡
ይህ ከድንጋይ ማሕፀን በላስታ ላሊበላ ምድር ተፀንሶ የተወለደ ጥበብ፤ የቅዱስ ላሊበላ 1ኛ ደረጃ ተማሪዎች እያለን፣ ገጣሚ በነበረው መምህራችን፣ ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረ/ኘሮፌስር በሆነውና በምርምር ሥራው በታወቀው በአያሌው ሺበሺ የተደረሰውን መዝሙር እንዲህ እያልን እናዜመው ነበር፤
ባቢሎንም በሉት ኢየሩሳሌም
ቅዱስ ላሊበላ ወደር የለህም
ከሰባት ነገሮች ባለም ከሚገኙት
በጣም አስደናቂ ግሩም ከተባሉት
ከግብጾች ፒራሚድ ከሮም ካቴድራል
ከአትክልቱ ሥፍራ ከህንዶች ታጅመሃል
ቢበልጥ ነው እንጂ ህንጻችን መች ያንሳል፡፡
ስለዚህ ውቅር ሕንጻ በአድናቆት የጻፉትን ሁሉ ብንጠቅስ ዘርዝረን አንጨርሰውም፡፡   UNESCO, Windmuller-luna, david, w-philipson, alvares, sihabaddinahmed, pankhurst, david buxton, mark jarzombek, silvia pankhrust paul b.henze, ወዘተ፡፡ ኢትዮጵያውያኑንማ ስንቱን ዘርዝረን እንዘልቀዋለን፡፡ እነዚህ ሁሉ አደነቁ፤ አወደሱ፡፡ ለኢትዮጵያ ውድቀትና ጥፋት፣ ለዚህም ምስቅልቅል ሕይወት ያደረሰ የላሊበላ የብሕትውና ዘመን ነው ያሉ ግን አልገጠሙኝም፤ ለሥልጣኔዋ፣ ለዕድገቷ፣ ለዕውቅናዋ፣ ለብዙዎች ብልጽግና፣ ለኢኮኖሚዋ ዕድገት፣ ለባህሏ ልማት ምከንያት ሆነ ከማለት በስተቀር።    
እኔማ ድፍረቱን አጥቼ ነው እንጂ “ዓለም በድንቁርና ተኮንኖ ሲኖር ግሪክ ብቻዋን በሥልጣኔ ጸድቃ ትኖር ነበር” እንደተባለው፣ ዓለም ባብዛኛው በጨለማና በኋላ ቀር አስተሳሰብ ሲኖር ፣ ኢትዮጵያ /በእነ ላሊበላ/ በሥልጣኔ ተራምዳ ትኖር የነበረች ሀገር ናት ለማለት ይዳዳኛል፡፡  ደግሞ እውነትም ነው፡፡ ዛሬ ሠልጥነናል፣ በጥበብና በብልጽግና አድገናል፣ እግዚአብሔርንም አውቀናል፣ መጥቀን ሄደናል የሚሉ ብዙ ሐገራት ኋላቀር በነበሩበት ጊዜ፣ እነ አሜሪካም ሊሰለጥኑ ቀርቶ መኖራቸው እንኳ ገና ባልታወቀበትና ብዙዎቹ በዛፍና በጐጆ ይኖሩ፣ በዋሻ ይጠለሉ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን እነ አክሱምንና ላሊበላን ፣ ጐንደርና ሐረርን በመሳሰሉ ሰማይ ጠቀስ ሐውልቶችና ሕንፃዎች ያጌጡ እንደነበር በርካታ ምሁራን የመሰከሩት ሀቅ ነው፡፡
በዚህና በመሳሰለው ምከንያት ተነሥቼ ነው ከአክሱማዊነት ወደ ላሊበላዊነት ያደረግነው ሽግግር በምድራዊ ሕይወት የደኽየ፣ በቁሳዊ ሐብቱም የተራቆተ ማኀበረሰብን በመፍጠር ተደመደመና በአክሱም ጊዜ መከበሪያ የነበሩ ሥራዎች፤ በላሊበላ ዘመን ግን የትልቅነት መገለጫው የማይሠሩ እጆች ሆኑ፤ ትልልቅ ቴክኖሎጂዎችን ሲሠሩ የነበሩት ባለሙያዎች በላሊበላ ዘመን ቀጥቃጭና አንጥረኛ እየተባሉ ተገፈተሩ፤ የላሊበላ ዘመንም የብሕትውና መኖሪያ እንዲያውም አድጐ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት . . . ድንጋይ እየፈለፈሉ አብያተ ክርስቲያናትን ከመሥራት ውጭ …. ወዘተ የሚለውን አባባል ለመቀበል ያዳገተኝና ይህን የዶለዶመ ብዕር ለማንሳት የደፈርኩት፡፡
መልካም ሥራ ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ እርስ በርሱ “የተደበደበና” የተቃረነ ሐሳብ የያዘ የሚመስለው ይህ የፍልስፍና መጽሐፍ፤ “ምንኩስና የተጀመረው በዳግማዊ እለ አሜዳ /46ዐ-472/ ዘመን በመጡት 9ኙ ቅዱሳን መነኮሳት፣ የተስፋፋውና የሕዝቡ ባህል ሆኖ የወጣው ግን በ6ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ መሆኑን ይገልጽና፣ ከ9ኙ መነኮሳት አንዱ የሆኑት አባ ጰንጠሌዎን አፄ ካሌብን ጨምሮ 15ዐዐ ሰዎችን አመንኩሰዋል” ሲል ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስን ዋቢ በማድረግ ያትታል፡፡  ይህ እንግዲህ ከላሊበላ ዘመን 6ዐዐ ዓመት ያህል ቀድሞ መሆኑ ነው፡፡  ይህ ሁሉ ሰው በአክሱም ዘመን ባንድ ሰው ብቻ የመነኮሰ፣ ስምንቱ ምን ያህል አመንኩሰው፣ ሀገሩን መነኩሴ በመነኩሴ አድርገውት እንደነበር መገመት አያዳግትም። ከሀገራዊ ሥልጣንና ዝና ይልቅ የግል ነፍሳቸውን ለማዳን፣ ዓለማዊውንና ምድራዊውን ሕይወት እርግፍ አርገው ወደ ብህትውናና ምንኩስና፣ ወደ ምነናም በመሄድ እንዲመሩት የተሰጣቸውን ሀገርና ሕዝብ፣ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በትነው በመመንኮስ፣ ወደ ብሕትውና ኑሮ የሄዱበት መሆኑንን ይዘረዝራል፤ ለምሳሌም ዳግማዊ አፄ እለአሜዳ፣ አፄ ካሌብ፣ አፄ ገብረ መስቀልንና አፄ እለ ገበዝን ይጠቅሳል። ይህ የሚያሳየው በ13ዐ ዓመታት ውስጥ አምስት ነገሥታተ አክሱም ሥልጣናቸውንና ሕዝባቸውን እርግፍ አድርገው ትተው፣ መመንኮሳቸውንና ይህም የሚያሳየው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በአክሱምና በአካባቢዋ ላይ የምንኩስና ሕይወት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትና ተቀባይነት ያገኘበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡  
ቅዱስ ያሬድም “የመንግሥቱን እኩሌታ ልስጥህ” ቢባል እንቢ ማለቱና መመነኑ፣ የአፄ ገ/መስቀል ልጅ የዙፋን የወራሽነት ጊዜውን በናፍቆት መጠባበቁን ትቶ ምንኩስናን መምረጡ፣ አፄ ካሌብም በዓለም ላይ ገናና ከሆነበት ሥልጣኑ ወርዶ የብሕትውና ሕይወትን መምረጡ፣ በወቅቱ የምንኩስና ሕይወት በሀገራችን የደረሰበትን ከፍተኛ ደረጃና ተቀባይነት ያሳያል” ይላል /ገጽ 211/፡፡
በገጽ 29 ላይ ደግሞ “6ኛው ክ/ዘ ላይ የታየው አዲስ ባህል መወለድና የነባሩ አክሱማዊ ባህል መውደቅ በዋናነት ከ9ኙ ቅዱሳን መነኮሳት መምጣት ጋር የተያያዘ ነው” ይለናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የዓለማዊ ጥበብ ቀርቶ መንፈሳዊ ዕውቀት የተነሣውና የቀጠለው በአክሱም መሆኑን ነግሮን ሲያበቃ፣ ለምድራዊው ሕይወት መኮሰስና ጥበበ ዕድ መኮስመን፣ የብሕትውና መግነንና የሥራ መብነን ምክንያት የሆነው የላሊበላ ዘመን መምጣቱን ይነግረናል፡፡
ዶ/ር ላጲሶ ጌዴ ሌቦ፤ “ከአክሱም ወደ ዘጉየ ሥርወ መንግሥት የተደረገ ሽግግር ለኢትዮጵያ መንግሥትና ኅብረተሰብ ዕድገትና የደቡብ መስፋፋት ጠንካራ መሠረት ፈጥሯል” ሲሉ “የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግስት ታሪክ” በሚለው (1982፣ ገጽ 89) መጽሐፋቸው የገለጹት አባባልም፣ ዶ/ር ዳኛቸውን አበሳጭቷቸው፤ “ይሄን ሽግግር በእንደዚህ ዓይነት ሙገሳ ብቻ አድበስበሰን ማለፍ የለብንም” በማለት “ከላሊበላዊነት ዘመን የተጀመረው የብሕትውና ሕይወት ግን የእጅ ሙያዎችን የተናቁና የተዋረዱ አደረጋቸው፡፡ ሌላው ይቅርና ሕዝቡ የቁም ጽሕፈትን ሙያ ከአስማት ጋር ስላያያዙት በርካታ መምህራን ከጽሕፈት ሥራ እንዲገለሉ ተደርገዋል” ይላሉ፡፡
እግዚኦ ያንት ያለህ አሉ፤ አበባ ገብረ ኢየሱስ። እንዲህ ላሊበላዊነትን “ድንጋይ ከመፈልፈል በስተቀር” እያሉ የሚያናንቁት፣ የዛሬ 9ዐዐ ዓመት መኪና እና አውሮፕላን ባለመሥራቱ ነውን? ወይስ ምናልባት ፍልስፍና ተምሮ፣ አዳኙንና አምላኩን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመካዱ ይሆን? መቸስ ያኔ የዶ/ር መምህራን የነበሩት  ኢ-አማንያኑ፤ “እግዚአብሔርን ገድለነዋል፤ ሞቷል፣ የለም” ያሉት እነ ኒችና ማርክስ አልተፈጠሩ፣ ከነማን ተምሮ ይካድ? እነሱ ቢያስተምሩትስ በሕይወቱ ታላላቅ ተአምራትና ድንቅ ነገር እያደረገ ያየውን፣ ከብዙ ፈተናም ያዳነውን፣ እነዚያን የመሳሰሉ ረቂቅ የሕንጻ ትንግርቶች ይሠራ ዘንድ እንዲያስብና እንዲተገብር የሚያደርግ የረቀቀ አእምሮ የፈጠረለትን መድኃኔዓለም ክርስቶስን እንዴት ይካደው? ክርስትና እኮ ያኔ ዓለምን እንደ ጨው ያጣፈጠበትና ብርሃኑን ያበራበት ዘመን ነበረ፡፡

Read 1425 times