Print this page
Sunday, 05 November 2017 00:00

ሽቶው

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(4 votes)

 ያሬድ ሲበዛ የሲጋራ ሱሰኛ ነው፡፡ በቀን ወደ ሁለት ባኮ ሲጋራ ያጨሳል፡፡ ድራፍትም ሲጠጣ እንደ ስፖንጅ ነው የሚመጠው፡፡ የሲጋራ ነገር ግን አይነሳ፡፡ በላይ በላዩ ነው፡፡ አንዱን ሲጋራ ሳይጨርስ ሌላውን ይለኩሳል፡፡ ደመወዙ ታድያ አንድም ጊዜ በቅቶት አያውቅም፡፡ ጠይም ፊቱ የተለበለበ ግንድ መስሎዋል፡፡ እድሜው ወደ ሰላሳዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ያሬድ፤ ቁመቱ አጠር ያለ ሲሆን ሰውነቱ ግን ለክፉ አይሰጥም፡፡
አንድ አራት በአራት የሆነች ክፍል ሃያ ሁለት አካባቢ ተከራይቶ ይኖራል፡፡ አንድ ባለ ሜትር ከሃያ ፋሚሊ አልጋ፣ አንድ ቁምሳጥንና በደህና ጊዜ ሦስት ሺህ ብር የገዛው የሲዲ መጫወቻ ያለው ቴፕ ሪከርደር--- የሚኮራባቸው ንብረቶቹ ናቸው፡፡ በተለይ ቴፕ ሪከርደሩ እንደ ነፍሱ የሚያየው ውድ ንብረቱ ነው። ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ከመጠን ያለፈ የኦልዲስ ሙዚቃ አድናቂ ስለሆነ ነው፡፡
ያሬድ ሙዚቃ አድናቂ ብቻ አይደለም። አዋቂም እንጂ፡፡ እሱ ቤት የሌለ የድሮ አልበም የለም። ህይወቱ በሙሉ ከሲጋራውና ከሙዚቃው ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ሞቅ ያለና የደስ ደስ ያለው ስሜት ሲሰማው የቢጅሶችን «ስቴይንግ አላይቭ» እና «ሳተርዴይ ናይት ፊቨር» ወይም የቢትልሶችን «ማኒ ኬንት ባይ ሚ ላቭ»ን ወይም የኤልቪስ ፕሪስሊን «ዶንት ቢ ኤፉል» ያዳምጣል፡፡ የኩል ኤንድ ዘጋንጐችን፣ የቴምፕቴሽኖችን፣ የሮሊንግ ስቶኖችን፣ የአባሞችን፣ የቦንይምስን . . . ስፍር ቁጥር የለውም። ማይክል ጃክሰን፣ ስቲቭ ወንደር፣ ኬኒ ቼስኒ፣ ዶሊ ፓርተን . . . እንደ ሲጋራው ሱስ የመንፈሱ ሱስ ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ ደግሞ ጥላሁን ገሰሰን፣ ሙሉቀን መለሰን፣ አስቴር አወቀን፣ ግርማ በየነን፣ ሚኒሊክ ወስናቸውን ሲኮመኩም ያመሻል፡፡ የዛን ያህል ደግሞ ሂፕ ሆፕና ራፕን ሲጠላ ለጉድ ነው። ፌፍቲ ሴንትና ፒዲዲ የሚባሉ ስሞችን ሲሰማ ያመዋል፡፡ የምዕራቡን ሙዚቃ ድምፅ በሌለው ሽጉጥ የገደሉ አድርጐ ነው የሚያስባቸው፡፡
ያሬድ መምህር ነው፡፡ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ የእንግሊዝኛ አስተማሪ፡፡ ታድያ እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ ኬሚስትሪ ከምታስተምር  ዴሚኒ ከምትባል ወጣት ሸንቃጣ አስተማሪ ጋር በድንገት ተዋወቀ፡፡ መንገድ ላይ ዝናብ ደብድቦት፣ ወደ ትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲገባ ነው ከአንድ ከሚያውቃት ሌላ አስተማሪ ጋር ቆማ ያያት፡፡ አስተማሪዋ አስተዋወቀቻቸው፡፡ እጁን ስትጨብጠው ልክ ብዙ አመት እንደምታውቀው ፍቅረኛው፣ በሞቀ ለስላሳ እጅዋ፣ እጁን እያሻሸች፤ «ወይኔ እንዴት በርዶሃል» አለችው፡፡
ያኔ ነው የተለከፈው፡፡ እንደ ጥቁር የወይን ዘለላ ፍሬ የሚያንፀባርቁ አይኖችዋን እያየ ፈዞ ቀረ፡፡ ምንም የማይቀራት ቆንጆ ነች፡፡ የሚያምር መልክና የሰውነት ቅርፅ ያላት፡፡ ያሬድ እንደዚህ አይነት የሚያፈዝ ውበት አይቶ አያውቅም፡፡ ልክ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ እንደተነከረ፣ ትንፋሽ ሲያጥረው ታወቀው። ልክ ሊያያል ሪች እንዳለው፤ «ስሪ ታይምስ ኤ ሌዲ ነች» ሲል አሰበ፡፡ ያን ቀን ማታ እቤቱ ገብቶ «ስሪ ታይምስ ኤ ሌዲ» የሚለውን ዘፈን በጀርባው ተኝቶ፣ ሲጋራውን እያጨሰ፣ ለስምንት ጊዜ ያህል ሰማው። ያን ቀን የለበሰችውን ውሃ አረንጓዴ ቀሚስ ለብሳ አየር ላይ እየተንሳፈፈች ትታየው ነበር፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ የአስተማሪዎች ካፌ ውስጥ እንደገና አያት፤ ነጭ ጋዋንዋን ለብሳ ነበር፡፡ ገና እንዳያት ተስፋ ቆረጠ፡፡ እቺ ለኔ አትሆንም፡፡ ከአቅሜ በላይ ነች ሲል አሰበ። ሲጋራውን እያጨሰ አንድ ጥግ ተቀመጠ፡፡ ከሁለት አስተማሪዎች ጋር ቆማ እያወራች፣ ሰረቅ አድርጋ ስትመለከተው አስተዋለ፡፡ «አሃ! ይህቺ የኬሚስትሪ አስተማሪ፤ ከኔ ጋር የሚያዋህድ አንድ ኬምስትሪ አላት ማለት ነው» አለ በልቡ፡፡
አስተማሪዎቹ ተለይተዋት ብቻዋን ስትቀር፣ በድፍረት ሄደና ሰላም አላት፡፡ ሞቅ ያለ ፈገግታ ነበር የሰጠችው፡፡ በልቡ፤ «አይ ጥርስ!» እያለ «እንዴት ነሽ» አላት፡፡
«ሰላም ነኝ፡፡ አንተስ?»
«ደህና ነኝ» አለና ድንገት ደጋግሞ ለሦስት ጊዜ ሳለ፡፡
«የእንግሊዝኛ አስተማሪ ነህ አይደል?»
«አዎ»
«ጐበዝ አስተማሪ እንደሆንክ ሰምቻለሁ» ሳቅ አለች፡፡
«ማን ነገረሽ?»
«ይባላል!»
ስለኔ ታውቃለች ማለት ነው ሲል አሰበና ኩራት ቢጤ ተሰማው፡፡ ጋዋንዋን አውልቃ ወንበር ላይ ስትሰቅል ልትወጣ እንደሆነ ገመተ፡፡ ተከትሏት ለመሄድ አሰበ፡፡ በርግጥ አንድ የሚያስተምረው ቀሪ ፔሬድ አለው፡፡ ነገር ግን ከክፍል ቀርቶ ስለማያውቅ ዛሬ ቢተወው ብዙም ችግር እንደማይፈጠር ገመተ፡፡
«እየወጣሽ ነው» አላት ፈገግ ብሎ፡፡
«አዎ አንተስ?»
«እኔም ወጪ ነኝ» አላት፡፡
ተያይዘው ከግቢው ወጡ፡፡ በቁመት ትንሽ ሳትበልጠው አትቀርም፡፡ አብሯት በመሄዱ ኩራት ተሰማው፡፡
«ቡና ለምን አልጋብዝሽም?»
«አይ እቸኩላለሁ፡፡ የምሄድበት አለኝ» አለችው።
ለምን እቅጩን አልነግራትም ሲል አሰበ፡፡ እርግጥ ልጅቷ የወደደችው ትመስላለች፡፡ ግን ሌላ ያስተዋለው ነገር ተግባቢነትዋና ሞቅ ያለ ፈገግታዋ ለሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እንደሆነ ነው፡፡ ታድያ ይሁን አይሁን ለማይታወቀ ነገር ጊዜውን በጭንቀት የሚያጠፋበት ምክንያት ምንድንው? የእግረኛውን መንገድ ይዘው ቀስ ብለው እየተራመዱ፣ ወደ ታክሲ መያዣው ሲያመሩ፣ እንደምንም ደፍሮ እንደወደዳትና ጓደኛው እንድትሆን እንደሚፈልግ ነገራት፡፡ በመገረም ትኩር ብላ ተመለከተችው፡፡
«አዝናለሁ፡፡ ሊሆን አይችልም» አለችው፡፡
«ለምን?» አለ ምራቁን ዋጥ አድርጐ፡፡ ሲጋራውን ከኪሱ አውጥቶ እየለኮሰ፡፡
«ብዙ ምክንያት አለ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ይሄ የምታጨሰው ሲጋራ ነው»
«ሲጋራ?»
«አዎን፡፡ ሱሰኛ ነህ፤ እኔ ደግሞ ሱሰኛ ሰው…» አንጠልጥላ ተወችው፡፡
«ብተውስ?» አለ ልቡ እየመታ
«እስኪ ተወውና» ሳቅ አለች፡፡
አንድ ፎቅ ስር ያሉ ብዙ ሱቆች አካባቢ ደርሰዋል። ውድ ዕቃዎች የተደረደሩበት ቡቲክ ስታይ ወደዚያ ጠጋ አለችና መመልከት ጀመረች፡፡ ያልተደረደሩ የሴቶች መዋቢያ ዕቃዎች የሉም፡፡ ጐንበስ ብላ ስትመለከት እንደ ሐረግ የተመዘዘ ሽንጧን በመቋመጥ እያየ፣ እግረ መንገዱን ቀልቧ የተሳበበትን እቃ ተመለከተ፡፡ አንድ በሴት ቅርፅ በተሰራ ጠርሙስ የተቀመጠ ያለ ሽቶ ነው የምትመለከተው፡፡
«የተለየ ሽቶ ነው» አለ አብሮዋት ሽቶውን እየተመለከተ፡፡
«በህይወቴ በጣም የምመኘው ሽቶ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ ያደለው ነው ይሄን ሽቶ የሚቀባው» አለችውና ቀና አለች፡፡ ቀስ ብለው እየተራመዱ፣ ወደ ታክሲው መቆምያ ደረሱና «በል እሺ» አለችና ልትለየው ለሰላምታ እጅዋን ዘረጋች፡፡
«ነገ እንገናኛለን» አላት የተዘረጋ እጅዋን እየጨበጠ፡፡ ታክሲ ውስጥ ገባች፡፡ ታክሲው ይዟት ሄደ፡፡ የሱም ልብ አብሮዋት ከነፈ፡፡
ተመልሶ ወደዚያ ቡቲክ ሄደና ስታየው የነበረውን ሽቶ ተመለከተ፡፡ ዠን ፖል ይላል፡፡ ወደ ሱቁ ገባና ባንኮኒው በስተጀርባ ቆማ ሞባይል የምታወራውን፣ የፊትዋ ወዘና የሚያለጠልጠውን የሱቅዋን ባለቤት አየ፡፡ «ምን ልታዘዝ?» አለችው ፊትዋ ላይ ምንም ፈገግታ ሳይታይ፡፡
«ይሄ ሽቶ ስንት ነው ዋጋው?» ሽቶውን በእጁ እየጠቆመ «ሁለት ሺህ ብር» ወሬዋን ቀጠለች፡፡ በሁለት ነገሮች ደሙ ፈልቶዋል፡፡ አንደኛው በሽቶው ወድነት፤ ሁለተኛው በሻጭዋ ንቀት፡፡ እንደ ሰው አልቆጠረችውም፡፡ ይሄን ሽቶ መግዛት እንደማይችል አሳምራ ታውቃለች፡፡ በሚቀጥለው ቀን ዴሚኒን አገኛት፡፡ ሲጋራ ለማቆም እንደወሰነ ነገራት፡፡ ከልቡ ነበር፡፡ ፈገግ ብላ ካየችው በኋላ «በርታ» አለችው፡፡
«ላንቺ ስል ነው» አላት፡፡ ሳቅ ብላ አየችውና ወደምታስተምርበት ክፍል ገባች፡፡ ማታ ወደሚያመሽበት ቡና ቤት ሄዶ ድራፍቱን ሲጠጣ አንድም ሲጋራ አላጨሰም፡፡ አብሮት የሚጠጣው ጓደኛው በመገረም ያየዋል፡፡ ስለ ኬምስትሪ አስተማሪዋ አጫውቶት ነበር፡፡
«እንዴት ብትወዳት ነው ባክህ የምትወደውን ሲጋራ ያቆምከው?» አለው
«ምን ላድርግ ሁለት ወዶ አይሆንም» መለሰ «ለእስዋ ብለህ ካቆምክ እንደገና ትጀምራለህ፡፡ ለራስህ ብለህ ነው ማቆም ያለብህ» አለው ድራፍቱን እየተጐነጨ፡፡ የሚበቃውን ያህል ጠጥቶ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቅዳሜ ቀን ልደትዋ መሆኑን ነግራው ነበር። ያንነ የወደደችውን ሽቶ ገዝቶ ሊሰጣት ወስኗል፡፡ ገንዘብ ግን የለውም፡፡ ተሟሙቶ ከየትም ማምጣት አለበት፡፡ ኪሱ ውስጥ የቀረው ገንዘብ ከሁለት መቶ ብር አይበልጥም፡፡ የሚያበድረው ሰው ደግሞ የለም። ያን ሌሊት ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድና ቀዳዳ ሁሉ ሲያስብ አደረ፡፡ ምንም ፍንጭ ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ያለው እድል አንድ ዕቃ መሸጥ ነው። ቴፕ ሪከርደሩን ዞር ብሎ ተመለከተው። ሆዱን ባር ባር አለው፡፡ጠዋት ያን ብቸኛ ቅርሱ የሆነውን ቴፕ ሪከርደር ይዞ ወጣ፡፡ ብዙ ቦታዎችን ካጠያየቀ በኋላ ተሳካለትና አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ብር ሸጠው። እውነት ለመናገር ግን አገሩን የሸጠ መስሎ ነው የተሰማው፡፡ ከሰአት በኋላ ወደዚያ ቱቢክ ሄደና በተራው ሻጭዋ ላይ ተዘባነነባት፡፡ ሁለት ሺህ ብር ባንኮኒው ላይ ሲያስቀምጥ፣ ፊትዋ ላይ ከበሬታ ተመለከተ፡፡ ሽቶውን በስጦታ ዕቃ አስጠቀለለና ይዞት ወደ ትምህርት ቤት ሄደ፡፡
ዴሚኒን ያገኛት ከክፍል አስተምራ ስትወጣ ነበር። ጥቁር ሰማያዊ ጂንስ ሱሪ ከነጭ ቢትልስ ሹራብ ጋር ለብሳ፣ ላዩ ላይ ነጭ ጋዋንዋን ደርባ ነበር። ጥቅሉን ሰጣት፡፡
«ምንድነው?» አለችው በመገረም እያየችው፡፡
«ስጦታ ነው፡፡ እቤትሽ ስትገቢ እይው» አላት፡፡
ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ሽክ ብሎ ለበሰና ወደ ዴሚኒ ቤት ሄደ፡፡ ቤትዋን በጥቆማ ነግራው ነበር። ከካሜሩን ኤምባሲ አጠገብ በስተግራ፡፡ እቤትዋ ውስጥ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ነበር፡፡ አንዳንድ የሚያውቃቸው አስተማሪዎችም ነበሩ፡፡ ቤቱ በሰው ሞልቶ ስለነበር የሚቀመጥበትን ወንበር ፍለጋ አይኑን አማተረ፡፡ ከአንድ ወፍራም በደንብ የዘነጠ ሰውዬ ጐን፣ አንድ ባዶ ወንበር እንዳለ አስተዋለ። ሄዶ ተቀመጠ፡፡ አጠገቡ የተቀመጠው ወፍራም ሰውዬ፤ አዱኛ የተትረፈረፈለት ቱጃር እንደሆነ ያስታውቃል። ቡናማ ህብር ያለው የጣልያን ሱፍ ለብሷል፡፡ ሃያ አራት ካራት ወርቅ የሆነ ሮሌክስ ሰአት አድርጓል፡፡ ከአዞ ቆዳ የተሰራ ጫማው፣ መልክ እስኪያሳይ ድረስ ተወልውሏል፡፡ ኪንግ ኤድዋርድ የሚባል ሲጋራ እያጨሰ ነበር፡፡ያሬድን በፈገግታ ተመለከተና ሲጋራ ጋበዘው፡፡
«አላጨስም አቁምያለሁ» አለ ያሬድ
«ሲጋራ ማቆም ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ እራሴ ለመቶ ጊዜ አድርጌዋለሁ» አለውና ከት ብሎ ሳቀ፡፡
ሰውየው ለማለት የፈለገው ያሬድ ገብቶታል፡፡
«ደስ አትልም!?» አለው ሰውየው፤ ወደ ዴሚኒ እየተመለከተ፡፡ ዴሚኒ ከቼኮላቱ ቶርታ ጋር የሚመሳሰል ቡናማ፣ ቢጫ ጠቃጠቆ ያለበት ቀሚስ ለብሳለች፡፡ ፀጉርዋን ወደ ኋላ ለቃዋለች፡፡ ኬኩ ላይ የተሰካውን በሃያ ሰባት ቁጥር ቅርፅ የተሰራውን ሻማ እፍ ብላ ስታጠፋ ሰው ሁሉ አጨበጨበ፡፡
«ፍቅረኛዬ ነች» አለ ሰውየው በኩራት እያያት
«ምን?» አለ ያሬድ፤ የገዛ ምራቁ እያነቀው፡፡ «ፍቅረኛ እንደሌላት ነበር የማውቀው» አለ ያሬድ እየተንተባተበ፡፡ «በቅርቡ ነው የተዋወቅነው፡፡ በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ፡፡ በምንዋ እንደወደድኳት ታውቃለህ?» አለው ሰውየው፤ ፈገግ ብሎ ያሬድን እያየ
«እ?»
«በተቀባችው ሽቶ፡፡ ዠን ፖል ነው የተቀባችው። ውድ ነገር የሚወዱ ሴቶች አከብራለሁ» አለው ሰውየው ፈገግ ብሎ፡፡
ያሬድ ምንም አላለም፡፡ እጁን ወደ ሰውየው ዘረጋ፤ ሰውየው በመገረም ያሬድን እየተመለከተ «ምነው?» አለው «ሲጋራ ስጠኝ» አለ ያሬድ
«እንዳቆምክ ነግረኸኝ ነበር»
«ሲጋራ ማቆም በጣም ቀላል ነው፡፡ ወደፊት መቶ ጊዜ ላደርገው እችላለሁ» አለ ያሬድ፤ ኪንግ ኤድዋርዱን ሲጋራ እየለኮሰ፡፡ ሁለቱም ሲጋራቸውን እያቦነኑ፣ ኬኩን የምትቆርሰውን ዴሚኒ ተመለከትዋት፡፡
ከአዘጋጁ፡-(ውድ አንባቢያን፤ከላይ የቀረበው አጭር ልብወለድ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣነው ቢሆንም አልፎ አልፎ እንደምናደርገው ለየት ያለና አስደማሚ እንዲሁም ግሩምና ያልተጠበቀ አጨራረስ ያለው ሆኖ ስላገኘነው ነው የመረጥነው፡፡ እንደወደዳችሁት እርግጠኞች ነን)

Read 3073 times