Print this page
Saturday, 04 November 2017 11:50

12ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 · ከጃፓን፣ ኢራቅና አፍሪካ አገራት የመጡ 70 ፊልሞች ተመዝግበዋል
            · ባንኮችና የፊልሙ ዘርፍ በአጋርነት የሚሰሩበት ምክክር ተዘጋጅቷል

     በ”ሊንኬጅ አርትስ ሪሶርስ ሴንተር” ላለፉት 11 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል፤ ዘንድሮም ከታህሳስ 16-23 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በ12 የፊልም  የውድድር ዘርፎች ለአሸናፊዎች ሽልማት እንደሚሰጥ ታውቋል።
“Sankofa the Art of Storytelling” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው 12ኛው የፊልም ፌስቲቫል፤ መሪ ቃሉን የወሰደው “ሳንኮፋ” ከተሰኘው የፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ፊልም ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ወደ ኋላ ወደ ምንጫቸው ተመልሰው፤ ታሪካቸውንና ማንነታቸውን ካወቁ በኋላ በዚህ መነሻነት ወደፊት እንዲራመዱ የሚያስተምር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍ ከመላው ዓለም 70 ያህል የሲኒማ ቤት ፊልሞች፣ ዘጋቢ አኒሜሽን፣ ኤክስፐርመንታል፣ ክላሲክና ዘመናዊ ፊልሞች የተመዘገቡ ሲሆን በቀጣይም መረጣው እንደሚካሄድ አዘጋጁ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ወርክሾፖች፣ ሴሚናሮችና የፓናል ውይይቶች እንደሚያካትትም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በ12 የፊልም ሥራ ዘርፎች ተወዳድረው ያሸነፉ የሚሸለሙ ሲሆን ዘርፎቹም፡- ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ ምርጥ ዳይሬክተር፣ ምርጥ ፅሁፍ፣ ምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ ምርጥ ሴት ተዋናይት፣ ምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ፣ ምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት፣ ምርጥ አጭር ፊልም፣ ምርጥ ተስፋ የተጣለበት (የተጣለባት) ተዋናይ (ተዋናይት) እና የህይወት ዘመን የፊልም ስራ የሚሉ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተመልካች ምርጫ ሽልማት (Audience Choice Award) በሚል ዘርፍ ያሸነፉም ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
በ12ኛው የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ከተካተቱ አዳዲስ ሀሳቦች መካከል ለታላቋ ኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ኩራትና ታሪክ ይመጥናሉ የተባሉትን ስሞች ለሽልማት ስያሜ ማድረግ ሲሆን ዘንድሮ ስያሜ የሚሰጣቸው ስድስት የሽልማት ዘርፎች ይኖራሉ ተብሏል። ስድስቱ ሽልማቶችና ስሞቻቸውም ለምርጥ ፊልም- “Black Lion” ለምርጥ ዳይሬክተር -“Saba (Ethiopian Eye) ለምርጥ ፀሐፊ-“Geezopia”፣ ለምርጥ ሲኒማቶግራፊ “Rainbow” ለምርጥ ሴት ተዋናይት -  “Dinkinesh” እና ለምርጥ ወንድ ተዋናይ -  “Dinkinoh” መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡   
ሌላው አዲሱ ሀሳብ ከፊልም ሰሪ ውጭ የሆነ ማንኛውም ሰው በሞባይል ስልኩ የቀረፀው የትኛውም የሶስት የአራት ወይም የሁለት ደቂቃ ፊልም በዚህ ዓመት ለውድድር እንደሚቀርብና አሸናፊው እንደሚሸለም የጠቆመው የ“ሊንኬጅ አርት ሪሶርስ ሴንተር” እና የፌስቲቫሉ ዳይሬክተር አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ፤ ድንገት በተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረፁ አሳዛኝ፣ አዝናኝና አስተማሪ ሊሆኑ ስለሚችሉ ታዳሚው እንዲያያቸው እንደሚደረጉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ሌላው የዚህ ዓመት ፌስቲቫል ያካተተው አዲስ ሀሳብ፤ “Bank and Film Sector conference” የተሰኘ ሲሆን ይህም ሁለቱም ዘርፎች በአጋርነት ሊሰሩ በሚችሉበት መንገድ ላይ በመወያየት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መድረክ መቅረፅ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡ ባንኮች ለፊልሙ ዘርፍ ብድር የሚሰጡበትና የፊልም ኢንዱስትሪውም በበጀት እጥረት ከሚሰራው ደረጃውን ያልጠበቀ ስራ ወጥቶ የተሻለና ደረጃውን የጠበቀ ፊልም ለተመልካቹ ለማቅረብ የሚያስችለው መንገድ ላይ ሁለቱ አካላት ሰፊ ውይይትና ምክክር አድርገው ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ምክክር ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ከጃፓን፣ ከኢራቅ፣ ከአፍሪካና ከሌሎች አገራት የመጡ 70 ያህል ዘጋቢ፣ አጭር፣ የሲኒማ ቤት፣ ኤክስፐርመንታል፣ ክላሲክና ዘመናዊ ፊልሞች መመዝገባቸውንና መረጣው በቀጣይ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡ ከታህሳስ 16-23 ቀን 2010 ዓ.ም ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ፌስቲቫል ላይ በቫድማስ ሲኒማ፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝና በሩሲያ የባህል ተቋም (ፑሽኪን) የፊልም መረጣው፣ የፊልሞች እይታ፣ የፓናል ውይይት፣ ሴሚናርና ወርክሾፖች ሲካሄዱ ቆይተው፣ የመጨረሻው የሽልማት ስነ - ስርዓት ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

Read 1995 times