Sunday, 05 November 2017 00:00

ፎርብስ የዓመቱን የአለማችን 100 ኃያላን ሴቶች ይፋ አደረገ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

- አንጌላ መርኬል ለ7 ተከታታይ አመታት 1ኛ ደረጃን ይዘዋል
          - አምና 2ኛ የነበሩት ሄላሪ ክሊንተን፤ ዘንድሮ 65ኛ ደረጃን ይዘዋል
          - ግማሽ ያህሉ ሴቶች አሜሪካውያን ናቸው

     ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2017 የአለማችን 100 ኃያላን ሴቶችን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን ላለፉት ስድስት አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የዘለቁት የጀርመን መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬል ዘንድሮም ቀዳሚነታቸውን አስከብረዋል፡፡
በቅርቡ በተካሄደ ምርጫ ለአራተኛ የስልጣን ዘመን የአገሪቱ መራሄ መንግስት መሆናቸውን ያረጋገጡት መርኬል፤ በአመታዊው የፎርብስ መጽሄት የአለማችን ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ሲካተቱ የዘንድሮው ለ12ኛ ጊዜያቸው መሆኑን ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የአንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ በዘንድሮው ዝርዝር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የማይክሮሶፍቱ መስራች ባለቤት የሆኑትና ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ የተባለውን የበጎ ምግባር ተቋም ከባለቤታቸው ጋር አቋቁመው በመምራት ላይ የሚገኙት ሚሊንዳ ጌትስ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ የፌስቡኳ ሼሪል ሳንበርግ በአራተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ የጄኔራል ሞተርስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ሜሪ ባራ አምስተኛነቱን ይዛለች፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ኃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት 100 ሴቶች በቢዝነስ፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በፖለቲካ፣ በበጎ ምግባር፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች መስኮች ስኬትን የተጎናጸፉ፣ ሃብት ያካበቱ፣ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉና ተሰሚነትን ያተረፉ ናቸው ተብሏል፡፡ ከአመቱ 100 ኃያላን የአለማችን ሴቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት አሜሪካውያን መሆናቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ ሚሼል ኦባማ ዘንድሮ ከዝርዝሩ ሲወጡ፣ በምርጫ የተሸነፉት ሄላሪ ክሊንተን አምና ከነበሩበት የ2ኛነት ደረጃ በሚገርም ሁኔታ አሽቆልቁለው፣65ኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
ዘንድሮ 23 የአለማችን ሴቶች በአዲስ ገቢነት የኃያላኑን ዝርዝር መቀላቀላቸው የተነገረ ሲሆን፣ 19ኛ ደረጃን የያዘቺው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ከእነዚህ ሴቶች አንዷ መሆኗም ታውቋል፡፡

Read 5926 times