Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 14 April 2012 11:40

ከምንም ተነስቶ የ1ሚ.ዶላር ቢዝነስ የፈጠረው ስደተኛ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የላይቤሪያው ተወላጅ ፎምባ ትራዋሊ በትምህርቱ ለመዝለቅ አልታደለም፡፡ በታዳጊነቱ የቤተሰቡን ጉሮሮ ለመሙላት ሲል ትምህርት አቋርጦ ወደ ሥራ ለመግባት ተገደደ፡፡ ትራዋሊ በብዙ ውጣ ውረዶች ቢያልፍም የማታ ማታ የተለያዩ ምርቶችን ከውጭ የሚያስመጣ ኩባንያ በመመስረት ወደ ቢዝነስ ገብቷል፡፡ ኩባንያው ዛሬ በላይቤሪያ አሉ ከተባሉ ትላልቅ ኩባንያዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ የትራዋሊ አስመጪ ኩባንያ “ኩምባ ቤይንዱ” ይባላል - በእናቱ ስም፡፡ ለኩባንያው የእናቱን ስም የሰጠው  ያለምክንያት አይደለም፡፡ አንዳችም የቀለም ትምህርት ያልጐበኛቸው እናቱ፤ ልጆቻቸውን ያሳደጉት ቁንዶበርበሬና ኦበርጂን ቸርችረው ነው፡፡

ለዚህ ነው ስማቸውን ማስታወሻ ያደረገው፡፡ የቤተሰቡ የበኸር ልጅ የሆነው ትራዋሊ ኩባንያውን ከማቋቋሙ በፊት ብዙ አቀበትና ቁልቁለት ወጥቷል ወርዷል፡፡ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ እናቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ የቤተሰቡ ሃላፊነት ጫንቃው ላይ ያረፈበት ትራዋሊ፤ በጋሪ ላይ ነጠላ ጫማዎችን ደርድሮ በላይቤሪያ መዲና ይሸጥ ነበር፡፡

በ1989 (እ.ኤ.አ) በላይቤርያ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ወደ ጋምቢያ ተሰደደ፡፡ በ1991 ጦርነቱ ጋብ ሲል ወደ ትውልድ አገሩ ተመለሰ - በግሉ የቆጠባትን 15 ዶላርና የማሊ ጓደኛው የሰጠውን 120 ዶላር ቋጥሮ፡፡ ይህችን ገንዘብ ይዞ ነበር ንግድ የጀመረው - “ኩምባ ቤይንዱ ኤንድ ሰንስ” የሚል ኩባንያ በመክፈት፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ካፒታላችን ወደ 3ሺ ዶላር አደገ ያለው ትራዋሊ፤ “አሁን በመላው አገሪቱ ቢዝነሳችንን አስፋፍተናል” ብሏል - “African dream” ለተሰኘው የቢቢሲ ተከታታይ የስኬት ፕሮግራም፡፡

ኩባንያው የፕላስቲክ ምርቶች፣ ጫማዎች እና የመዋቢያ እቃዎችን ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከቱርክና ከአጐራባች አገሯ አይቮሪኮስት ያስመጣል፡፡

በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቭያ እና በበርካታ የክ/አገር ከተሞች ለሚገኙ ትናንሽ ሱቆችም ምርቶቹን እንደሚያከፋፍል ይናገራል፡፡ ኩባንያው ከሃያ የማያንሱ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ነዋሪዎች ዘወትር በመዲናዋ ወደሚገኘው የኩምባ ቤይንዱ ኤንድ ሰንስ የገበያ ማዕከል ይጐርፋሉ - በትራዋሊ መደብር ብቻ የሚገኙ እቃዎችን ለመሸመት፡፡

በእርግጥ ሚ/ር ትራዋሊ ወደ ቢዝነስ ሲገባ ይህን ያህል አድጌ እመነደጋለሁ የሚል ህልምም ሆነ ምኞት አልነበረውም፡፡

“ፈጽሞ አልሜውም አስቤውም አላውቅም፡፡ እኔ ያለምኩት 500 ዶላር ብቻ ለማግኘት ነበር” ብሏል ለቢቢሲ አፍሪካ ሪፖርተር፡፡

“ስለ 1ሺ ወይም 10ሺ ዶላር ለማውራት እና 1ሚ.ዶላር ላይ ለመድረስ እበቃለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ 500 ዶላር ካገኘሁ ወደ ናይጀሪያ ገበያ ሄጄ የናይጀሪያን እቃዎች እገዛለሁ የሚል ነበር ሃሳቤ” ይላል፡፡

በላይቤሪያ የሰፈነው ሠላም አስር ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ የዚያኑ ያህል እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል - ሚ/ር ትራዋሊ፡፡

“በላይቤሪያ ቢዝነስ መስራት በጣም ቀላል ነው፡፡ አሁን ቢዝነስ የሚሰሩ ብዙ ላይቤሪያውያን ታያላችሁ” የሚለው ትራዋሊ፤ ከየትኛውም አገር የበለጠ በላይቤሪያ ቢዝነስ መስራት አበረታች እየሆነ መምጣቱን ይገልፃል፡፡ መጀመሪያ ግን እኛ ዜጐች በአገሪቱ ባለው ዕድል ተጠቃሚ መሆን አለብን፤ ከዚያ በኋላ ሌሎች ይከተላሉ ብሏል፡፡

ቢዝነሱን በአርአያነት የመምራት ፍላጐት እንዳለው የሚናገረው ሥራ ፈጣሪው፤ ቀጣይ ህልሙ ወደ አምራችነት መግባት እንደሆነ ይገልፃል፡፡

“አገሬ አሁን ምርቶችን ወደ ውጭ መላክ አለባት፡፡ እነዚህን አልባሳት እንደገና በቻይና ትገዙታላችሁ፤ በላይቤሪያ የተሰራ (Made in Liberya) የሚሉ አልባሳትን እዚሁ ትሸምታላችሁ” ይላል - ትራዋሊ፡፡ የ41 ዓመቱ ሚ/ር ትራዋሊ በራሱ ጥረት ራሱን መፍጠር በመቻሉ ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማው ይናገራል፡፡ “የሂሳብ አያያዝ (accounting) በት/ቤት ተምራችሁ ዶክትሬት ድግሪ ልታገኙ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሃሳብ ከሌላችሁ ቢዝነስ መስራት አስቸጋሪ ነው” ብሏል፡፡

ገንዘባችሁን ማሳደግ የምትፈልጉ ከሆነ ቁጠባንም መማር አለባችሁ የሚለው ሥራ ፈጣሪው፤ ገንዘቡን ያለአግባብ እንደማያባክን ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡ ህይወቱን የሚመራው በከፍተኛ የቁጠባ አኗኗር እንደሆነ በመግለፅም፤ ለስምንት ዓመት አንድ ጂንስ ሱሪ መልበሱን ጠቅሷል፡፡

ሚ/ር ትራዋሊ እንደሚለው፤ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ቢዝነስ ለመጀመር የግድ ብዙ የገንዘብ ካፒታል አያስፈልጋቸውም፡፡

“ቢዝነስ ለመጀመር 1ሚ ዶላር አያስፈልጋችሁም” ይላል - ትራዋሊ፡፡

ላይቤሪያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሌሎች ጓደኞቼ የምለግሳቸው ምክር አለ የሚለው ሥራ ፈጣሪ፤ “ማንኛውንም ቢዝነስ በ100 ወይም በ500 ዶላር ለመጀመር ማመንና መደፋፈር አለባችሁ፡፡

እናቴ በዛሬ ዘመን እዚህ ግባ በማትባል 5 ወይም 10 የአሜሪካ ሳንቲም ነበር ሥራ የጀመረችው” ብሏል - ሚሊዬነሩ የላይቤሪያ ሥራ ፈጣሪ፡፡ የቱንም ያህል መነሻ ገንዘባችን አነስተኛ ቢሆንም በፅናትና በቁርጠኝነት ተግተን ከሰራን ያለምነው ስኬት ላይ መድረሳችን አይቀሬ ነው እያለን መሰለኝ - የዛሬው ሚሊዬነር፤ የትላንቱ ሥራ ፈጣሪ! ጐበዝ ታዲያ ምን አሰባችሁ? 1ሚ. ዶላር ለካ ያን ያህልም ሩቅ አይደለም - ግን ልበሙሉነትን ይጠይቃል!!

 

 

 

Read 3475 times Last modified on Saturday, 14 April 2012 11:44