Sunday, 05 November 2017 00:00

በኢትዮጵያ ሩጫ ያልተዘመረለት ጀግና ስለሺ ስህን፤ THE SILVERMAN

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

ይህ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ በየጊዜው የሚቀርበው፤ ‹ታላላቅ ስፖርተኞችን አስደናቂ ብቃታቸውንና የህይወት ዘመን ታሪካቸውን ባስታወስን ቁጥር ለዛሬም ለወደፊትም የመንፈስ ብርታት ይሆነናል› በሚል ነው
               
     አትሌት  ስለሺ ስህን ባለፉት  ሶስት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ የራቀ ቢሆንም  የሩጫ ዘመኑን አላቆመም፡፡  ከእነአበበ ቢቂላ፤ ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር   በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ፍፁም የበላይነት የነበረው የአረንጓዴው ጎርፍ  ትውልድ በእነ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስህን እንደተገነባ ይታወቃል፡፡ 3ቱ አትሌቶች በኢትዮጵያ የሩጫ ታሪክ በረጅም ርቀት ከፍተኛ ውጤቶችን አስመዝግበዋል፡፡
አትሌት ስለሺ በመካከለኛ ርቀት 3ሺ ሜትር፤ በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር፤ በ10 ፣ 15 እና 20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች ፤በአገር   አቋራጭ  ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች ከ15 ዓመታት በላይ ተወዳድሯል፡፡ በዓለማችን ታላላቅ የአትሌቲክስ መድረኮች ላይ በረጅም ርቀት በተደጋጋሚ  የብር ሜዳልያዎችን  በመሰብሰቡ  ‹‹ዘ ሲልቨር ማን›› የሚል ስም ወጥቶለታል፡፡   ኢትዮጵያ ውስጥ በአትሌቲክስ ስኬት ልዩ ክብር የሚሰጠው የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎች መጎናፀፍ ከ4-10 ባለው ደረጃ ሩጫን መጨረስ ክፉ ልማድ ሆኖ ያን ያህል አይደነቅም፡፡ በታላላቆቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች የዓለም ሻምፒዮና፣ የኦሎምፒክ እና የዓለም አገር አቋራጭ ሌሎች ግዙፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በጠንካራ የልምምድ ዲስፕሊኑ፤ ቡድን በመልካም መንፈስ በሚያስተባብርበት ተግባሩ፣ ለውጤታማነት የሚያግዙ ልምምዶችን በጋራና በትጋት መስራቱ፤ በውድድር ላይ ለተቀናቃኝ አትሌቶች ዙርን በሚያከርበት አሯሯጡ፤ ተፎካካሪዎችን ከሜዳልያ ውጭ ለማድረግ በሚከተለው ታክቲክ ግን ስለሺ ስህን በኢትዮጵያ ሩጫ ያልተዘመረለት ጀግና ሆኖ ሊደነቅ ይገባል፡፡ አትሌት ስለሺ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በረጅም ርቀት የወርቃማው ትውልድ አባል ብቻ አይደለም፡፡ ከ2004 - 2007 ባሉት የውድድር ዘመናት ከዓለማችን አምስት ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች አንዱ ነበር፡፡ በሩጫ ዘመኑ ከነበሩት የሌላው ዓለም አትሌቶች ቢነፃፀር ይበልጣቸዋል፡፡ ከአውስትራሊያው ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጭ ክሬግ ሞትራም ፤ ከአሜሪካው ጋልን ሩፕ ከሌሎች የኬንያና የኤርትራ ምርጥ አትሌቶች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ከምንግዜም የረጅም ርቀት  ሯጮች ተርታ ሊሰለፍ የበቃ ነው፡፡
በኦሎምፒክ፤ በዓለም ሻምፒዮና፤ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሊዘነጋ የማይችል ምርጥ የስፖርት ስብዕና አለው፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት የኢትዮጵያ አትሌቶች በነገሱበት የውድድር ዘመናት የቡድን ስራ ዋና ተዋናይና ተምሳሌት ሆኖ በማገልገል ተደንቋል፡፡ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የአረንጓዴ ጎርፍ ባህል ብዙ መስዕዋትነቶችን በመክፈልና ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የሜዳልያ ክብሮችን በመጎናፀፍ ከወርቃማው ዘመን ምርጥ አትሌቶች ተርታ የሚያሰልፈው ታሪክን አስመዝግቧል፡፡ በተለይ በትልልቅ የዓለም አትሌቲክስ መድረኮች ከኢትዮጵያ ምርጥና ወርቃማ አትሌቶች ስኬት ጀርባ ዱካው አይጠፋም፡፡   
*   *   *
ይህ የስፖርት አድማስ ልዩ የታሪክ ማስታወሻ የአትሌት ስለሺ ስህንን የሩጫ ዘመን ይመለከታል፡፡ ስለ ቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቶች የተሟሉ የሩጫ ዘመን ታሪኮች በአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ድረገፅ ላይ የሚገኙት ናቸው፡፡ በተለይም‹‹ፎከስ ኦን አትሌትስ›› በሚል አምዱ ስር  ከ2000 እኤአ ጀምሮ የብዙ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሩጫ ታሪክ ተፅፏል፡፡ በኦሎምፒክ ሪፈራንስ፤ በኦል አትሌቲክስ፤ ራነርስ ዎርልድ እና ሌትስ ራን እና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን በማጣቀስ የተዘጋጀ ነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የሩጫ ዘመኑ አጀማመር
የትውልድ ስፍራው በቅቤ ምርቷ በምትታወቀው ሸኖ  ነው፡፡ ሸኖ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 130ኪሜ ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የአትሌት ስለሺ ወላጆች ሰፊ የእርሻ ማሳ ያላቸውና በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ገበሬዎች ቢሆኑም እንደቤተሰቡ በግብርና ሙያ ለመሰማራት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ቀዳሚ ምኞቱ በትምህርቱ ውጤታማ ለመሆን ነበር፡፡ ይሁንና በየጊዜው የኃይሌን የአትሌቲክስ ውጤቶች እና አስደናቂ ጀብዱዎች ይሰማበት በነበረበት የታዳጊነት እድሜው ለአትሌቲክስ ስፖርት ያለው ፍቅርን እያደላ ሄዷል፡፡
የኃይሌ ገብረስላሴ የሩጫ ጀግንነት መነሻ ሆኖት ወደ ሩጫ ስፖርት አተኮረና አትሌት ለመሆን ሲወስን በትምህርት ቤቱ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች በመሳተፍ እና ከሌሎች አትሌቶች ጋር በየእለቱ የሚሰሩ መደበኛ የሩጫ ልምምዶች መስራት ጀመረ፡፡ ብዙም  ሳይቆይ በሚማርበት ትምህርት ቤት በ800 እና በ1500 ሜትር ሻምፒዮን ሊሆን በመብቃቱ የኦሮሚያ ክልልን በመወከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፍበት እድል ተፈጥሮለታል፡፡
በታዳጊነቱ ትምህርቱን በማቋረጥ ወደ ስፖርቱ ሙሉ ለሙሉ ለመግባት መወሰኑን ለቤተሰቡ ሲናገር ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡በሁለተኛ ደረጃ የመልቀቂያ ፈተና ጥሩ ውጤት አምጥቶ ትምህርቱን በዩኒቨርስቲ እንዲከታተል ነበር የሚፈልጉት፡፡ በመጨረሻም የቤተሰቡን መልካም ፈቃድ አግኝቶ በሩጫው ስፖርት ለመስራት በመወሰን ከጓደኞቹ ጋር ከትውልድ ከተማ ሸኖ ተነስቶ አዲስ አበባ ገባ፡፡  በሩጫ ስፖርት ስኬታማ ለመሆን አብረውት የነበሩት ጓደኞቹ በአዲስ አበባ ብዙ አልቆዩም ወደ ሸኖ ተመለሱ፡፡ ስለሺ ግን ምንም እንኳን  ብቸኛ ሆኖ በከተማ ህይወት ቢቸገርም በስፖርቱ ስኬታማ ለመሆን እንደሚችል ፅኑ እምነት ስለነበረው አዲስ አበባ ቆይቶ በጥረቱ ገፋበት፡፡ በ12 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ለመሳተፍ በቻለበት የመጀመርያ የአዲስ አበባ ውድድሩ የሮጠው የ12ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና በሚሰጥበት ሰሞን ነበር፡፡ ጥናት እና ልምምዱን በትኩረት ለመስራት ቢቸገርም፤በጎዳና ላይ ሩጫ ተሳትፎ ሁለተኛ ደረጃ አገኘ፡፡ ከውድድሩ ማግስት በወሰደው የማትሪክ ፈተናም ሊሳካለት ችሏል፡፡
ከክልል ወደ ብሄራዊ ቡድን ከዚያም ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ
በ2001 እ.ኤ.አ ላይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኦሮሚያን ክልል ወክሎ  በ10 ሺ ሜትር ተወዳደረ፡፡ ከ1-10 ባለው ደረጃ ውስጥ በመግባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የተቀላቀለ ሲሆን፤ በ2002 እ.ኤ.አ ላይ ወደ የዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ገብቷል፡፡  የውድድር ዘመኑ ለአትሌት ስለሺ ስህን የሩጫ ዘመን ተስፋ ሰጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት ብቻ አልነበረም፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት በሆነው ገ/እግዚአብሔር ገብረማርያም 3 ጊዜ የተሸነፈባቸው ውድድሮች የሚታወሱ ናቸው፡፡   
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የወጣቶች ውድድር፣ በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እና በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ልዩ ሩጫ ውድድሮች  ነበር፡፡  በመጀመርያ በአየርላንድ ደብሊን በተደረገ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በወጣቶች ቡድን በመካተት በታሪክ የመጀመሪያውን የዓለም አቀፍ ውድድር አደረገና በወጣቶች ምድብ የ8 ኪ.ሜ ውድድር ላይ ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ሲያሸንፍ እሱ 6ኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ይሄው የውድድር ዘመን ሳይጠናቀቅ በጃማይካ ኪንግስተን በተካሄደ የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ደግሞ በ10 ሺ ሜትር ለኢትዮጵያ ቡድን  ቢሰለፍም በድጋሚ በዚህ ውድድር ላይ አሸናፊ ሆኖ የወርቅ ሜዳልያውን  ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም ሲያጠናቅቅ በሁለተኛ ደረጃ ተከትሎት በመግባት  በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ የመጀመሪያውን የብር ሜዳልያ ክብር ተጎናፅፏል፡፡ በመጨረሻም በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ የጎዳና  ሩጫ ላይ ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም በአንደኛ ደረጃ ሲጨርስ  ቀነኒሳን  ቀድሞ በመግባት ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት ችሏል፡፡  
በ2002 እ.ኤ.አ ላይ በጃማይካ ኪንግስተን ከተማ የተካሄደው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለአትሌት ስለሺ ዓለም አቀፍ የውድድር ደረጃ በተለይ በረጅም ርቀት 5 ሺ እና 10 ሺ ሜትር ውድድሮች ከኢትዮጵያ የወቅቱ ምርጥ አትሌቶች ተርታ የሚሰለፍበትን ብቃት ያመለከተበት ነበር፡፡ በቀጣይ 4 የውድድር ዘመናት በሁለቱም የረጅም ርቀት ሩጫዎች የምንግዜም ውጤት እና የፈጣን ሰዓቶች ደረጃ  እስከ 4ኛ ደረጃ በሚጠቀስበት ስኬት አድርሶታል፡፡ 2003 እኤአ የሩጫ ዘመኑን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት የውድድር ዘመን ሆኖለታል፡፡ በመጀመርያ በስዊዘርላንድ ሉዛን በተደረገ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  በአዋቂዎች የ12 ኪ.ሜ ውድድር ተሳትፎ ቀነኒሳ በቀለን ተከትሎ በመግባት በ2ኛ ደረጃ የጨረሰ ሲሆን በአዋቂዎች ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ ያስመዘገበው የሜዳልያ ውጤቱ ነበር፡፡
በዚሁ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ከአንድ የውድድር ዘመን በፊት በብዙ ውድድሮች ያሸነፈው ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያም በ3ኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያ ወስዶ ነበረ፡፡ በተመሳሳይ የውድድር ዘመን በተካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ደግሞ የቅርብ ተፎካካሪዎቹን ቀነኒሳ በቀለና ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያምን በማሸነፍ ብዙዎችን በአድናቆት አስደመመ፡፡  በኢትዮጵያ ሻምፒዮናው በ5 ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለን በ10 ሺ ሜትር ደግሞ ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያምን ቀድሟቸው በመግባት ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን የተጎናፀፈ ሲሆን  በሁለቱም ርቀቶች የሻምፒዮናውን ሪከርዶችም ሊያስመዘግብ በቅቷል፡፡ ይህ አስደናቂ ውጤቱም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመካተት  የመጀመሪያውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎውን ወደ የሚያረጋገጥበት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡
የኢትዮጵያን የዓለም ሻምፒዮና ቡድን ለመምረጥ በሆላንድ ሄንግሎ በተካሄደ የ10 ሺ ሜትር ውድድር ላይ ከተሳተፈ በኋላም ቀነኒሳ በቀለ እና  ኃይሌ ገ/ሥላሴን በከፍተኛ ብቃት በመፎካከከር በ3ኛ ደረጃ  ውድድሩን በመጨረስ የዓለም ሻምፒዮና ትኬቱን ለመቁረጥ በቅቷል፡፡  በፈረንሳይ ፓሪስ ተዘጋጅቶ ለነበረው 9ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመጀመርያ ጊዜ በመሳተፍ የሩጫ ዘመኑን አብይ ምዕራፍ ከፈተ፡፡
*   *   *
በሁለት ኦሎምፒኮች
በ10ሺ ሜትር 2 የብር ሜዳልያዎችን በኦሎምፒክ መድረክ የተጎናፀፈ አትሌት ሲሆን ማሳካት የቻሉት የዓለማችን አትሌቶች 50 ያህል ናቸው፡፡ በ2004 እኤአ በግሪክ አቴንስ  በተካሄደው 28ኛው ኦሎምፒያድ የመጀመርያ ኦሎምፒኩን በመሳተፍ የብር ሜዳልያ የወሰደው በ21 ዓመቱ ነበር፡፡ በ2008 እኤአ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ደግሞ በ25 ዓመቱ ሁለተኛውን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ሊያገኝ በቅቷል፡፡
በ4 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች
በሩጫ ዘመኑ አራት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን በረጅም ርቀት በመካፈል ከፍተኛ ልምድ ያለው ሲሆንከኢትዮጵያ በወንዶች ምድብ በ3ኛ ደረጃ የሚቀመጥ የምንግዜም ከፍተኛ ውጤትን አስመዝግቧል፡፡ በ4 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 3 የብር እና 1 የነሐስ በድምሩ 4 ሜዳልያዎች በመሰብሰቡም በአይኤኤኤፍ ከ1 በላይ ሜዳልያ ያገኙ 60 ምርጥ አትሌቶች ተርታ ይሰለፋል፡፡ በ10 ሺ ሜትር ሁለት የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን በማግኘት  በሻምፒዮናው ታሪክ ከፖል ቴርጋት ጋር 3ኛ ደረጃን በመጋራት ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበ ነው፡፡ በ2005 እኤአ በፊንላንድ ሄልሲንኪ እና በ2007 እኤአ በጃፓን ኦሳካ እንዲሁም ተጨማሪ የነሐስ ሜዳልያ በ2003 እኤአ በፓሪስ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አግኝቷል፡፡ በ5ሺ ሜትር ደግሞ  በ2005 እኤአ በፊንላንድ ሄልሲንኪ የብር ሜዳልያ አሸንፏል፡፡
በአገር አቋራጭ  በጎዳና ላይ ሩጫዎች
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ባለው ልምድ በ12 ኪሜ በ2004 እ.ኤ.አ ላይ በ3ኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያ በ2006 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በ2ኛ ደረጃ የብር ሜዳልያ ማግኘቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ በአውሮፓ የተለያዩ አገራት በተካካሄዱ አገር አቋራጭ ውድድሮችም የተሳተፈ ሲሆን፤  በተለይ በ2002 እና በ2003 እ.ኤ.አ ላይ በስፔን በተካሄዱት የክሮስ ኢንተርናሽናል ዴቫንታ ዴባኖስ የአገር አቋራጭ ውድድሮች አከታትሎ ያሸነፈ ነበር፡፡
የአገር አቋራጭ እና የትራክ ላይ የረጅም ርቀት ውድድሮችን ካቆመ በኋላ በ2005 እኤአ በዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በኤድመንተን ካናዳ 4ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ በማራቶን የመጀመርያ ውድድሩን በ2011 እኤአ በአምስተርዳም ማራቶን አድርጎ ነበር፡፡ በ36ኛው ኪ ሎሜትር ላይ አቋርጦ በመውጣት አልተሳካላትም፡፡
የወርቅ ሜዳልያዎቹ
በሩጫ ዘመኑ ከፍተኛ ውጤትና የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገባበቸው ውድድሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺ ሜትር ለ3 ጊዜያት በ5 ሺ ሜትር 1 ጊዜ  በድምሩ 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ማግኘቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በ2003 እኤአ  በናይጄርያ አቡጃ በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እንዲሁም በህንድ አይድራባድ በተደረገው አፍሮ ኤሽያ ጨዋታዎች በ10ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን አግኝቷል፡፡ በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር ፍፃሜ ለ2 ጊዜያት በ10ሺ ሜትር አፍሪካን ወክሎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ወስዷል፡፡
የቡድን ስራ ያሳየባቸው ውድድሮች
በ2004 እኤአ ላይ በአቴንስ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ውድድር ቀነኒሳ የወርቅ ሜዳልያውን ሲጎናፀፍ በቡድን ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በወቅቱ የዓለማችን ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ቀነኒሳና ኃይሌ  ጋር ተከታትለው ለመግባት ያሳዩት የትራክ ላይ ድራማ በቴዲ አፍሮ አንበሳ የተባለውን ታዋቂ ሙዚቃ እንዲሰራ ምክንያት ነበር፡፡ በ2003 እኤአ ላይ በፓሪሱ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ቀነኒሳ በቀለና ኃይሌ ገብረስላሴን ተከታትለው የገቡበት ውድድርም ከማይረሱ ገድሎቹ ይጠቀሳሉ፡፡
ከቀነኒሳ ጋር
በተለያዩ የዓለም አቀፍ ውድድሮች  በተደጋጋሚ የወርቅ ሜዳልያውን የሚነጥቀው ቀነኒሳ በቀለ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃዎች በመጨረስ በ5 ትልልቅ ውድድሮች 5 የብር ሜዳልያዎችን አግኝቷል፡፡ በቀነኒሳ በቀለ ተቀድሞ የብር ሜዳልያ ያገኘባቸው በ2003 እ.ኤ.አ ላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በ2004 እ.ኤ.አ በኦሎምፒክ፣ በ2007 እ.ኤ.አ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በጃፓን አሳካ እንዲሁም በ2008 እ.ኤ.አ   በቤጂንግ ኦሎምፒክ ናቸው፡፡
ያሸነፋቸው ታላላቅ አትሌቶች
ታላላቅ የዓለም አትሌቶችን በተለያዩ የውድድር መድረኮች አሸንፏል፡፡ በ2004 እ.ኤ.አ ላይ በአውሮፓ በተካሄደ የአገር አቋራጭ ውድድር ሲያሸንፍ የኬንያዎቹን ፖል ቴርጋት እና ኤሊውድ ኪፕቾጌ አስከትሎ በመግባት ነበር፡፡
*   *   *
የአትሌቶች ማህበር ፤የዲባባ ቤተሰብና ኢንቨስትመንት
አትሌት  ስለሺ ስህን በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የአትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ነው፡፡ ማህበሩ የተመሰረተው ከ2 ዓመት በፊት ሲሆን  ለፕሬዝዳንትነት የተመረጠው  የኦሮሚያ ክልልን ወክሎ በመወዳደር ነበር፡፡ ማህበሩ የተቋቋመው ለአትሌቶች ጥቅም እንዲሰራ ፤መብታቸውን እንዲያስከብር፤ ለተሻለ ውጤት የሚመቹ አቅጣጫዎችን እንዲዘረጋ  ነው፡፡ አትሌቶች በቂ ውድድር እንዳያገኙ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይከላከላል፡፡ ከስልጠና፤ ከአሰልጣኞችና ከሌሎች የክለብና የብሄራዊ ቡድን መብትና ግዴታዎች የሚነሱ ችግሮችን በመፍትሄ ለማስቀረትም ይንቀሳቀሳል፡፡ አትሌቶች በተለይ ከማኔጀሮቻቸው በሚፈፅሟቸው የክፍያ፤ እና የኮሚሽን ውሎች ያሉ መጭበርበሮችን የሚታገል ነው፡፡
 በብሔራዊ ቡድን ደረጃም አትሌቶች በተደጋጋሚ ቅሬታ ከሚያነሱባቸው ችግሮች ዋንኛው ከስልጠና ጋር የተያያዘ መሆኑን በመታዘብ የስለሺ ስህን ጅምር እንቅስቃሴዎችም አሉ፡፡ አትሌቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻለና ቀጣይነት ያለው ሥልጠና በማግኘት ለውጤታማነት የሚረዳ ድጋፍ እንዲያገኙ ይፈልጋል፡፡ አትሌቶች በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለስፖርቱ ልማትና ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረከቱም ማህበሩ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ጥረት ያደርጋል፡፡
ለስለሺ ስህን ረጅም ጊዜ ያሳለፈበት ክቡር የሩጫ ሙያው ብዙ ልምዶችን እና እውቀቶችን ፈጥሮለታል፡፡ ከውድድር የራቀ ቢሆንም ከአትሌቲክስ ስፖርት ግን ሙሉ በሙሉ አልተለያየም። በየእለቱ መደበኛ የሩጫ ልምምዱን የሚሰራ ሲሆን የሩጫ ዘመኑን በማራቶን  ውጤታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ አሁንም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ነው፡፡ ከአትሌቶች ስልጠና የማናጀር ስራዎች ጋር ግንኙነቶችም አለው፡፡ ጎን ለጎን በአትሌቶች ማናጀርነት እየተንቀሳቀሰም ሲሆን በረጅም ርቀትና በማራቶን አሰልጣኝነት የሚንቀሳቀስበትን ሁኔታ በማጠናከር ላይ ይገኛል፡፡
ከታዋቂዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የሚሊኒዬሙ ጋብቻ ተብሎ በተሰየመ ሰርግ በ2008 እኤአ ትዳር እንደፈፀመ ይታወቃል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት ናታን የተባለውን የመጀመርያ ልጃቸውን አፍርተዋል፡፡
ታላላቅ ሴት አትሌቶች በሚገኙበት የዲባባ ቤተሰብ አባወራ እንደመሆኑ ኃላፊነቱ በስፖርቱም በኢንቨንስትመንቱም ነው፡፡ ከባለቤቱ ጥሩነሽ ዲባባ ፤ ከሌሎች እህትና ወንድሞቿ ጋር በቅርበት በመሆን  በስልጠናው፤በስነልቦናው እና ሌሎች ሁኔታዎች ይሰራል፡፡  ከአትሌቲክስ ባሻገር በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራቱ እነሱን በማስተዳደር ጊዜው የተጣበበ ነው፡፡ የተሰማሩባቸው የሪል እስቴት እና የሆቴል ኢንቨስትመንቶች ናቸው፡፡  ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ያደረጉባቸው ሲሆን ከ300 በላይ ሰራተኞችን የቀጠሩ ናቸው፡፡ በቦሌ ካራ ማራ አካባቢ የሚገኘው ባለ4 ኮከብ ሆቴል እና መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ስለሺ ቢዝነስ ሴንተር ህንፃ ናቸው፡፡

Read 4103 times