Saturday, 28 October 2017 10:40

በ72ኛው የተመድ በዓል፣ የኢራን ኤምባሲ ዝግጅት ተደነቀ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

    የተባበሩት መንግሥታትን የተመሠረተበት 72ኛ ዓመት በዓል ከትናንት በስቲያ በኢሲኤ የተከበረ ሲሆን የተለያየ አገር ኤምባሲዎች፣ ባህላዊ ምግቦቻቸውንና ባህላዊ አልባሳታቸውን እንዳቀረቡ ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ 20  ኤምባሲዎች የየአገሮቻቸውን ባህላዊ ምግብ ባቀረቡበትና ባህላዊ አለባበሳቸውን ባሳዩበት ዝግጅት፤ የኢራን ኤምባሲ ያቀረባቸው ባህላዊ ምግቦች፣መጠጦችና ባህላዊ አለባበስ በጣም የተወደደ እንደነበር የኤምባሲው የባህል ክፍል ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
 ኃላፊው ሚ/ር ሰዒድ ሐሰን ሃይድሪ በተለይ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ብቻ ሳይሆኑ የየአገሮቻቸውን ባህላዊ ምግቦችና አለባበስ ያቀርቡ የነበሩ ተሳታፊዎች የኢራን ኤምባሲን ምግቦችና መጠጦች ለማየትና ለመቅመስ ድንኳኖችን ሲያጨናንቁ ነበር ብለዋል፡፡
የተለያዩ አገር ሕዝቦች እንዲተዋወቁና እንዲቀራረቡ ከሚያደርጉ ነገሮች ዋናው ምግብና መጠጥ ነው ያሉት ሚ/ር ሃይድሪ፤ በኢራን የተለያዩ ከተሞች ከተመሳሳይ ነገር የተለያየ ጣዕም ያላቸው ምግቦች ይሠራሉ፡፡ በዝግጅቱም ላይ የኢራን ኤምባሲ አባላት ለአንድ ሳምንት ያዘጋጁትና የተለያዩ የኢራን ባህላዊ ምግቦችን፣ ከምግብ በኋላ የሚበሉ ጣፋጭ ኬኮች (ዲዘርት) ጊሚሽ ሳባሚኒ፣ ዓለም አቀፉ የኢራን ምግብ “ካባብ ከባድ፣ ታችን፣ ደርሼክ ፖሎ” እንዲሁም ከእርጎ የሚሰራው ዲቅ የተባለ ባህላዊ መጠጥ ቀርቦ ወዲያው ማለቁን ገልጸዋል፡፡ የኢራን ባህላዊ አልባሳትን ለብሰው የቀረቡት ልጃገረዶችም ውብ ነበሩ ብለዋል፡፡

Read 1814 times