Print this page
Saturday, 28 October 2017 10:30

‹‹…ጥራቱን የጠበቀ የስነተዋልዶ ጤና…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የጥራት ማሻሻያ በሚል ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ለመስራት የሚያስችል ፕሮጀክት እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ እዮብ መሐመድ ይባላሉ፡፡ አቶ እዮብ የጥራት ማሻሻያ ሲባል ምን ለማለት ነው? የሚለውን ማብራሪያቸውን ለአንባቢ ይድረስ ብለናል፡፡
እንደ አቶ እዮብ አገላለጽ የጥራት ማሻሻያ ሲባል በአጠቃላይ አንድ ሰው ለሕክምና አገልግሎት ወደሕክምና ተቋም ሲቀርብ ማግኘት የሚፈልገው ጥራቱን የጠበቀ የህክምና እርዳታ ነው ማለት ነው፡፡ ጥራት የሚለው ቃል ሲተነተንም፡-
ጥራት ሲባል… በህክምና አሰጣጥ ወቅት ሰአቱን የጠበቀ መሆኑ፣
ጥራት ሲባል… የኢኮኖሚው ሁኔታ ተጠቃሚን ያማከለ እንዲሆን፣
ጥራት ሲባል… የህክምና ባለሙያው ተገቢ የሆነ እውቀትና ዝግጁነት፣
ጥራት ሲባል… የህክምና ተቋሙ አደረጃጀት በተቻለ መጠን ለአገልግሎት ብቁ መሆን፣...ወዘተ
የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ጥራት ሲባል የራሱ የሆኑ መለኪያዎች ያሉት ሲሆን ተገልጋዩ ማለትም ታካሚው ጤናውን ለመጠበቅ የሚያስችለው አሰራር እንዲኖር ለማድረግ የሚረዱ መንገዶችን ፕሮጀክቱ ይከተላል። በእርግጥ ጥራቱ የተሟላ አገልግሎት የሚባለው ተመሳሳይ የሆነ አለምአቀፍ መስፈርት ባይኖረውም ግን ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በሁሉም ዘንድ ከስምምነት የሚደረስባቸው ግልጽ የሆኑ መስፈርቶች ናቸው፡፡
በህብረተሰቡ የስነተዋልዶ ጤና ላይ የጥራት ማሻሻያ ሲባል የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2015-2020/ በአገር አቀፍ ደረጃ Health sector transformation በሚል ተግባራዊ ከሚያደርገው የሁለተኛው ዙር የጤና አገልግሎት ማሻሻያ የመጀመሪያው ክፍል ማለትም equity and quality service የሚለው አካል ነው፡፡ ይህም ማለት ፍትሀዊና ጥራት ያለው የጤና ተደራሽነት ወይንም አገልግሎቱን ለሁሉም በእኩልነት ማዳረስ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሮጀjክት በዚህ ላይ በመመስረት የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው፡፡
አቶ እዮብ እንደሚሉት የስነተዋልዶ ጤና ሲባል ብዙ የጤና ሁኔታዎችን የሚዳስስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የሚያተኩርበት ፕሮጀክት ግን በተለይም በቤተሰብ እቅድ አገልግሎትና ጥንቃቄ የተሞላበት ወይንም ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ላይ ነው፡፡ ስለዚህም የፕሮጀክቱ ዋና አላማ፡-
የቤተሰብ ምጣኔን አገልግሎት ጥራቱን በጠበቀ መንገድ ተደራሽ ማድረግ፣
የቤተሰብ ምጣኔ ሳይጠቀሙ ወይንም በአጋጣሚ በሚፈጠር ግንኙነት ምክንያት ልጅ ለመውለድ እቅድ ሳይኖራቸው እርግዝና ቢከሰት በሕግ በተፈቀደው መሰረት ለሕክምና ባለሙያው በተገቢው አስረድቶ ጥንቃቄ የተሞላበት ያልተፈለገ እርግዝናን ማስወገድ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡  
በእነዚህ አሰራሮች ጥራት ሲባል የምክር አገልግሎት ከመስጠት ይጀምራል፡፡ እነዚህን አገልግ ሎቶች ፈልጋ ሐኪም ዘንድ የምትቀርብ እናት ተገቢውን ምክር ማግኘት አለባት፡፡ ይህች እናት ሳትገደድ ምርጫዋ መጠበቅ አለበት። የምትወስደው መከላከያ መድሀኒት እራስዋ አምናበት በፍላጎትዋ እንዲሆን ማድረግ ከባለሙያው ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት የሚያተኩረው ይህን አገልግሎት ባለሙያዎች በጥራት ለተገልጋዩ እንዲያደርሱ ማስቻል ነው፡፡ ስለዚህም ፕሮጀክቱ የሚያተኩርባቸው ሁለት ዋና ነጥቦች አሉ፡፡
ፍትሀዊና ጥራት ያለው የጤና ሽፋን፣
የህክምና ባለሙያው ሩህሩህ ፣ቸርና ሰውን አክባሪ የሆነ ባለሙያ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡
ስለዚህ ባለሙያው በዚህ በጥራት ፕሮጀክት አማካኝነት ስልጠና እንዲያገኝ እና ክህሎቱን እንዲያሻሽልና የተሟላ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በተመረጡ እና ፕሮጀክቱ በሚሰራባቸው የጤና ተቋማት በአመት ሁለት ጊዜ ባለሙያዎች እንዲጎበኙ እና አሰራሩን እንዲፈትሹ ይደረጋል፡፡ ይህ ስራ በጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ብቻም ሳይሆን የተለያዩ አጋር ድርጅቶች በተለ ይም ደግሞ መንግስት የሚሰራው ስራ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም መንግስት በሚሰራበት መዋቅር ውስጥ ድጋፍ ማድረግ ወይንም ማገዝ ዋነኛ አቅጣጫው ነው፡፡
የጥራት ማሻሻያው ፕሮጀክት የህክምና ባለሙያዎችን ክህሎት ለማሻሻል በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከነበሩ ባለሙያዎች መካከል ሁለቱን ለዚህ እትም ጋብዘናል፡፡
ሲስተር ዘነቡ በሰሜን ሸዋ ጤና መምሪያ የእናቶችና ወጣቶች ባለሙያ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG   ፕሮጀክት በተለይም የእናቶች ሞትን ለመቀነስ የሚረዳውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ላይ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ምን ያህል ስራው በጥራት ይሰራል አይሰራም የሚለውን ለመመልከትና በሚፈለገው ደረጃ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስለሆነ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ሀሳባቸውን የሰጡን አቶ ተስፋዬ አበበ የአርሲ ዞን ጤና መምሪያ የጤና ተቋማት ጥንካሬ አቀናጅ ወይንም አስተባባሪ ናቸው፡፡ እሳቸውም ሲስተር ዘነቡ የተናገሩትን በመደገፍ ዋናው ነገር ግን በተለይም ባልተፈለገ እርግዝና ምክንያት እና ጽንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ በአርሲ ዞን ብዙ ሴት ወጣቶች እራሳቸውን እሚያጠፉበት እንዲሁም የተለያዩ መርዞችን እየወሰዱ የሚሞቱበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እፍረት ነው፡፡ ለምሳሌም በዞኑ ባህል መሰረት አንዲት ልጅ ከመዳርዋ በፊት ብታረግዝ እጅግ የምትወገዝ እና ቤተሰብዋም በእስዋ ምክንያት ስለሚያፍርባት ይህንን አጋጣሚ ለማንም ሳያሳውቁ እራሳቸውን ለህልፈት የሚዳርጉ ብዙ ናቸው። ከዚህም ባለፈ የራሳቸውን እርምጃ ከወሰዱ በሁዋላ እና ብዙ ችግር ከተፈጠረ በሁዋላ ወደ ሆስፒታል ቢደርሱም እንኩዋን በሚፈጠረው የደም መፍሰስ እና በኢንፌክሽን መመረዝ ምክንያት መሞታቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡን ከማን ቃት ባሻገር አገልግሎቱንም በጥራት ተደራሽ ማድረግ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ በመሆኑ የፕሮጀክቱን ግብአት መጠቀም ለእኛ ተገቢ ነው። ESOG አሁን የጀመረውን ነገር ከህብረተሰብ መሪዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከባለሀብቶች …ወዘተ ጋር  በቀጣይም ቢሰራበት በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ ብለዋል፡፡
አቶ እዮብ መሐመድ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጥራቱን የጠበቀ የስነተዋልዶ ጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ እንዳሉት ጽንስ ማቋረጥን በሚመለከት ለረጅም ጊዜ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ሲከናወን የቆየ እና ዛሬም ቢሆን ቀርቷል የማይባል ሴት ልጆች የሚጎዱበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህግ ተሻሽሎ ደህንነቱ ለተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ ሂደት መስፈ ርቶችን ካወጣ በሁዋላ አብዛኞቹ የጤና ተቋማት አገልግሎቱን ይሰጣሉ ቢባልም አሁንም በባለሙያው ዘንድ የሚፈራ ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ያለውን አሰራር ለመመልከት በተሞ ከረበት ጊዜ ያጋጠመ ነገር ቢኖር ባለሙያው አገልግሎቱን ለመስጠት ተነሳሽነቱን እና እውቀቱን ሳያጣ ነገር ግን ከአንዳንድ ነገሮች ማለትም ከባህል ከሀይማኖት ከመሳሰሉት ጋር በማያያዝ የሚፈራው ነገር መኖሩን እና ለመስራት እንደማይፈልግ በአፍሪካም፣ በኢትዮጵያም የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የዚህ ፕሮጀክት አንዱ አላማ ይህን መቅረፍ ስለሆነ በተመረጡ የጤና ተቋማት ላይ ባደረግነው የመነሻ ጥናት መሰረት ለጽንስና ማህጸን ሐኪሞች እና ለአዋ ላጅ ነርሶች ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡
የESOG ፕሮጀክት በመጀመሪያ ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የሚሰራ ሲሆን ለስራው ድጋፍ የሚያደርገውም ዴቪድ ፓካርድ ሉሲ ፋውንዴሽን ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሚንቀሳቀሰው በኦሮ ሚያና በአማራ ክልሎች ሲሆን ምርጫው የተደረገውም ከሕዝብ ብዛትና አገልግሎቱን ከመስ ጠት አኩዋያ ነው፡፡ ይህ ስራ የተጀመረውም በክልል እና በዞን ጤና መምሪያዎች ጥቆማ መሰረት ማለትም በዚህ አካባቢ ስራው ቢሰራ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል በሚለው መሰረት ነው፡፡ ስለዚህም በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ማለትም አርሲ ዞን፣ ምእራብ ሐረርጌና ምእራብ ሸዋ ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ ሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞን ላይ ፕሮጀክቱ ስራውን ጀምሮአል፡፡ ዞኖቹም በመረጡአቸው ወረዳዎች በመሰማራት በኦሮሚያ በ3/ዞኖች  6/ሆስፒታ ሎችና 30/ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም በአማራ ደግሞ በ2/ዞኖች በአራት ሆስፒታሎችና በሀያ ጤና ጣቢያዎች ላይ የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት የጥራት ማሻሻያ በመሰራት ላይ ነው፡፡
እንደ አቶ እዮብ ማብራሪያ የዚህ ፕሮጀክት ጠቀሜታ በሁለት ይከፈላል፡፡
አንደኛው በስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እንዲሻሻል ማስቻል ሲሆን ፣
ሁለተኛው ባለሙያው ለተገልጋዮች ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥን አገልግሎት በመስጠት በኩልም ሆነ በስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ክህሎቱን እንዲያዳብርና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርግ በስልጠና ማገዝ ነው፡፡ 

Read 1828 times