Sunday, 29 October 2017 00:00

ስለ ዕጣ ፈንታ/ኮከብ ቆጠራ እና ምናምን

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(144 votes)

“--አንዳንዴ፤ የሰውን ልጅ ማንነት እንደ ማህበረሰባዊና ባዮሎጂካዊ ፍጡር ከማሰብ ይልቅ እንደ ጠፈር አካል አድርጎ
መተርጎም የሚቀናው ይመስላል፡፡ አስትሮሎጂ፤ ሳይንስም እምነትም አይደለም፡፡ የተወላጁ ዕጣ ፈንታ የተፃፈበት የጠፍር
ካርታ ነው ይላሉ፤ አቀንቃኞቹ፡፡---”
     
    ለመሆኑ አስቀድሞ የተቆረጠ ‹ዕጣ ፈንታ› (Determinism, Predestination) የሚባል ነገር አለ?!… አይዟችሁ! ..እንደለመደው መሬት ላይ ስለማይታይ ምናባዊ ፍልስፍና ሊያወራ ነው ብላችሁ … አታዛጉ፡፡ የማወራው ስለናንተ ነው፤ እናንተን ከምንም በላይ ስለሚመለከት ህይወታችሁ። ስለ ማህበረሰባችሁ። ስለ ሀይማኖታችሁ፡፡ ስለ ፖለቲካችሁ፡፡
መቼም ገና ‹ሀይማኖት እና ‹ፖለቲካ› ስላችሁ አይናችሁን እያሻሻችሁ እንዴት ነቃ እንዳላችሁ እዚሁ ተቀምጬ እየፃፍኩ ይታየኛል፡፡ ከቀላል ምሳሌ ልነሳ፡- … ታክሲ የምጠብቅበት ወረፋ ጋ በተለይ ጠዋት ጠዋት የማይጠፉ ሁለት ሰዎች አሉ፡፡ ለማኞች ናቸው። ሁለቱም አይነ ስውር ናቸው፡፡ ሴትየዋን አንድ ልጃገረድ እጇን ይዛ ትመራታለች፡፡ ሰውየውን ደግሞ የያዘው የብረት ከዘራ ነው የሚመራው፡፡ ሁለቱ ሰዎች እየተመላለሱ የተሰለፈውን ሰው ምፅዋት ይጠይቃሉ። ሰው የሚመፀውታቸው ለልመና የሚጠሯቸውን የቅዱሳን ስም ሰምቶ አይመስለኝም፡፡ ደህና ገንዘብ ሰርተው ሳይገቡ አይቀሩም ብዬ እገምታለሁኝ፡፡
የሁለቱ ሰዎች ዕጣ ፈንታ በተፈጥሮ የተሰጣቸው የአካል ጉድለት ነው ብለን መነሳት እንችላለን፡፡ የአይነ ስውርነት ዕጣ ፈንታቸው፣ ከእድሜያቸው መግፋት ጋር ተዳብሎ “ምስኪን መድረሻ ቢስ” የሚለውን ድምዳሜ በተመለከታቸው ሁሉ ልብ ውስጥ ያሳድራሉ። ከዚህ ድምዳሜ የመነጨ ሀዘኔታ በተመለከታቸው ሰው ልብ ውስጥ ይጫራል፡፡ ይሄ ድምዳሜ ነው “Determinism” … ድምዳሜውን የሰጠው ማንም ይሁን ማን … ግለሰቦቹን “ምስኪን” እና “ተመፅዋች” አድርገዋቸዋል፡፡
ድምዳሜውን የሚሰጠው የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ነው፡፡ ተፈጥሮም ሆነ እግዜር ድምዳሜውን አይሰጡም፡፡ … በተፈጥሮው ሰውየው ማየት የተሳነው ሆኖ ተወልዷል፡፡ “ሊታዘንለት ይገባል” የሚለውን ድምዳሜ የሚሰጠው ግን ተፈጥሮ ወይንም ፈጣሪ ሳይሆን ጭፍኑ ማህበረሰብ ነው፡፡ …. ማየት ተስኖት፣ አይኑ ተጨፍኖ የተወለደውን ህፃን … አይነ ስውር የሚያደርገው ጭፍኑ ማህበረሰብ ብቻ ነው፡፡ … ማየት ሳይሳነው የተወለደውም ቢሆን ጭፍን ማህበረሰብ ውስጥ ከገባ ተፈጥሮ የሰጠችውን አይን … ወይም አእምሮ ሳይጠቀም ተሰውሮበት ኖሮ ሊሞት ይችላል፡፡
ተፈጥሮና እግዜር አጋጣሚዎችን ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ዘረ-መል ንድፍ በማነብበትና ያነበብኩትን በፅሁፍም ሆነ በወሬ ለሌሎች በማካፍልበት ወቅት፣ “በዘረ - መል ዕጣ ፈንታችን ተወስኖ አልቋል ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ ወይም ተቃውሞ ይገጥመኝ ነበር፡፡
ዕጣ ፈንታችን በዘረ-መላችን ላይ ተወስኖ አያልቅም። ዘረ- መላችን እንዲጎለብት … በተፈጥሮው የያዘውን ፅህፈት እንዲናበብ የሚያደርገው ግን በተወለደበት አለም ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ብሩህ አእምሮን እንዲታደል የሚያደርግ ጂን ይዞ የተወለደ ሰው … የተወለደበት አካባቢ (Environment) የታደለውን ጂን የሚያከስም ከሆነ … ብሩህ አእምሮ ካልታደሉት ሳይሻል ህይወቱ ሊጠናቀቅ ይችላል፡፡ “Intelligence genes’ cannot work in a vacuum; they need environmental stimulation to develop”
… እንደውም ከተፈጥሮ በላይ ተሞክሮ ‹ዕጣ ፈንታን› የመቀየር አቅም አለው ይላል፤ ማት ሪድሊ “Genome” በሚለው መፅሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ። እናም በዘረ-መል ምክኒያት ማየት የተሳናቸው ሆነው ከመወለዳቸው በበለጠ፣ አይነ ስውርና ምስኪን የማድረጉን ስራ ማህበረሰቡ ነው የሚያጦፈው፡፡
ዘረ-መል አንዳች ሚናን ሰጥቶን ልንወለድ እንችላለን፡፡ የተሰጠንን ሚና ግን በሙሉ አቅሙ እንድንወጣ የሚያደርገው ኑሮና ህይወት ነው፡፡ ማንም ሰው ሲወለድ - ወይም ከመሀፀን ሲወጣ የየትኛው ሀይማኖት አባል መሆኑን የሚገልፅ ዕጣ ፈንታ ይዞ አይመጣም፡፡ ግን የተወለደበት ቤተሰብ፣ ይዞ የነበረውን ሀይማኖት ይቀበላል፣ ይጠመቃል፣ እንዲማር ይደረጋል፡፡ … እርግጥ “ሀይማኖትን የመፈለግ አቅም በተፈጥሮው ፅህፈት ውስጥ ያለ ነገር ነው” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ … ምናልባትም፤ አባባላችሁ እውነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ለጊዜው ሀይማኖታዊ እምነትን ጠቋሚ ጂን እስካልተገኘ ድረስ ለመስማማትም ሆነ ለመቃወም ይከብደኛል፡፡
በእነ Chomsky የቋንቋ ምርምር (lingusitic analysis) የሰው ልጅ ቋንቋ የመናገርን አቅም ይዞ ይወለዳል፡፡ ቋንቋን የመማር አቅም፡፡ የሚማረው ቋንቋ ግን የሚወሰነው እንደተወለደበት ማህበረሰብ ነው። በጣም ጥቂት ህዝብ ብቻ በሚናገረው ቋንቋ ውስጥ ከተወለደ … ዕጣ ፈንታው የማህበረሰቡን ይመስላል … ግን ከዕጣ ፈንታው መውጫ አማራጭ ፈጥሮም ተጨማሪ ቋንቋ ፍለጋ ማደግ ይችላል፡፡
ስለዚህ፤ “ዘረ- መል” ላይ “የዕጣ ፈንታ” ጣጣ አያልቅም፡፡ በማህበረሰብ ውስጥ ግን የግለሰብ ዘረ- መሉ የዕጣ ፈንታ ኮከብ የተቆጠረ ይመስላል፡፡ “ኮከብ የተቆጠረ” ስል አስትሮሎጂ ትዝ አለኝ፡፡ እሱም ሌላው የዕጣ ፈንታ ድምዳሜን ለመስጠት የሚሞክር የአስተሳሰብ አይነት ነው፡፡ የዕጣ ፈንታ ድምዳሜው የሚቆረጠው በተወለድክበት ዕለት ነው፡፡ አስትሮሎጂ ከውልደት ቀን በፊት ስላለው የዘረ-መል ሚስጢርም ሆነ … ከውልደት በኋላ ስላለው የማህበረሰብ ውጥንቅጥ አያገባውም፡፡ … እንዲያውም፤ አንዳንዴ፤ የሰውን ልጅ ማንነት እንደ ማህበረሰባዊና ባዮሎጂካዊ ፍጡር ከማሰብ ይልቅ እንደ ጠፈር አካል አድርጎ መተርጎም የሚቀናው ይመስላል፡፡ አስትሮሎጂ፤ ሳይንስም እምነትም አይደለም፡፡ የተወላጁ ዕጣ ፈንታ የተፃፈበት የጠፍር ካርታ ነው ይላሉ፤ አቀንቃኞቹ፡፡
አንድ ልጅ፣ ኮከብ ቆጣሪው ካርታውን አንብቦለት፣ ታላቅ መሪ እንደሚሆን ሊነግረው ይችላል፡፡ … ሌላ ልጅ ደግሞ ኮከብ ቆጣሪው ባይተነብይለትም፣ በስልጣን ላይ ከተቀመጠ ሰው በመወለዱ ሳይተነበይለት እጣ-ፈንታው እጁ ሊገባ ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱን ሁኔታ በጥሞና ካስተዋልን … በተፈጥሮ (በኮኮቡ) ከሚሰጠው እጣ-ፈንታ ይልቅ በማህበረሰቡ (በፖለቲካ ስርዓቱ የሚሰጠው እጣ-ፈንታ) ለልጁ የበለጠ ተጨባጭ መሆኑ ሊታየን ይችላል፡፡
አንድ ሰው በተፈጥሮ አእምሮው ብሩህ ሆኖ ከሚወለድ ይልቅ … መሀከለኛ አእምሮ ኖሮት፣ አእምሮን ብሩህ የማድረጊያ የትምህርት ግብዓት አሟልቶ በሚያቀርብ ማህበረሰብ ውስጥ ቢወለድ … የአእምሮ ብሩህነት ዕጣ-ፈንታው የበለጠ የተጨበጠ እውነት ይሆንለታል፡፡ በአጭሩ፤ ማንም ሰው የፈለገውን አይነት ተፈጥሮ ይዞ ከሚመጣ ይልቅ ማህበረሰቡ የሚቀርፀው የበለጠ የዕጣ- ፈንታ ገፀ በረከት ወይም እርግማን (እንደ ማህበረሰቡ) የመሆኑ አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው። “አጋጣሚ” ማለት ራሱ … ተፈጥሮ ሳይሆን ህይወት ማለት ነው፡፡ ህይወት ማለት ደግሞ ከማህበረሰብ ውጭ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ … ሀይማኖትም ሆነ ባህል … ማህበረሰብ ነው፡፡ ማህበረሰብ ፖለቲካ ማለት ካልሆነ ታዲያ ፖለቲካ ምንድን ነው?
ተፈጥሮም ሆነ እግዜር እድልን ነው የሚሰጡህ፡፡ እድልህን የመጠቀም ወይንም የማጨንገፍ ዕጣ ፈንታን ግን የተወለድክበት ማህበረሰብ ይዞ በተወለደበት ስፍራ ላይ ይጠብቅሃል፡፡ … ዕጣ ፈንታ ወይም እድል የሚባል ነገር ካለ ምናልባት “በትክክለኛው ቦታ፣ በትክክለኛው ዘመን መወለድ” የሚሉት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን አሁንም ላሰምርበት የምፈልገው … ተፈጥሮ ለሁሉም አሻራዋን ተሸክሞ ለሚወለድ ፍጡር የመፍጨርጨር አቅምን አድላዋለች፡፡ ማለትም፤ በጨለማ ቦታ ተወልዶ፣ ታግሎ ወደ ብርሐን የሚያደርስ አቅም ለእያንዳንዱ ግለሰባዊ ፍጡር ሰጥታዋለች፡፡ … በግለሰቦች ትግል ደግሞ ማህበረሰብም ቀድሞ ከነበረበት የዕጣ- ፈንታ እስር ሊፈታ ይችላል፡፡

Read 37256 times