Sunday, 29 October 2017 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

“መምሰል ሌላ፤ መሆን ሌላ!”
               
    ሰይጣን የካህን ቀሚስ ለብሶ፣ ቆብ ደፍቶና መስቀል ይዞ፣ ሰዎች ወደየስራቸው በሚመላለሱበት ጎዳና ላይ ቆመ፡፡ … እግዜርም እዛው አካባቢ ነበር።…
አንድ ሰው መጣና … “አባቴ አሳልሙኝ”…አላቸው፡፡
አባትም አሳለሙትና… “ማን እንደሆንኩ አውቀኸኛል?”…ሲሉ ጠየቁት፡፡…
“እንዴት አላውቅዎትም? አባታችን ነዎታ!” መለሰላቸው፡፡
አባትም ቆባቸውን ውልቅ፣ ቀንዳቸውን ብቅ፣ጅራታቸውን ሹልክ አደረጉ፡፡ ሰውዬው በድንጋጤ እያማተበ፣ “በስመአብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ፣ አንተ ከይሲ፣ አንተ አሳሳች፣ ብለህ ብለህ በዚህ መጣህ” እያለ ተፈተለከ፡፡…
ትንሽ ራቅ ብሎ የሚታዘበው እግዜርም…”ይሄ ስሜታዊ ባይሆን ጥሩ አማኝ ነው”… አለ፡፡
ሁለተኛው መጣ፡፡ ተሳለመና ሊሄድ ሲል… “ለመሆኑ አውቀኸኛል?” ቢሉት ራሱን አወዛወዘላቸው… “አላውቅዎትም” ለማለት፡፡ ቆባቸውን ውልቅ፣ ጅራታቸውን ብቅ ሲያደርጉ… “ኦ….የኛ ኮመዲያን…ትቀልድብናለህ አይደል?” አለና፣ እየሳቀ ጥሏቸው ሄደ፡፡
እግዜርም… “ይሄ ሌሎች የሚያደርጉትን እያየ የሚያደርግ፣ ስሜቱን ያላረቀ አማኝ ነው--” አለ፡፡
ሶስተኛው ሰው መጣ፡፡ እንደ ሌሎቹ አሳለሙትና፤ “አውቀኸኛል ልጄ?” ብለው ቀንድና ጅራታቸውን ሲያሳዩት… “ደስ እንዲልዎት ተሳለምኩልዎት እንጂ… አንድ መሆናችሁን መች አጣሁት” አላቸው፡፡
አባም… ”ምናልክ ልጄ?... እስኪ ድገመው…ከማን ጋር ነው አንድ…?”
አላስጨረሳቸውም፡፡ “… ልጅዎን እዛው ይፈልጉ፣ እኛ አባታችን አንድ ብቻ ነው”… አላቸው… በጣቱ ወደ ሰማይ እያመለከተ፤… ”ቤተ መቅደሴም ልባችሁ ናት ብሎናል” ሲል ጨመረላቸውና በኩራት እየተንጎማለለ ሄደ፡፡…
እግዜርም--- “ይኼ ክፉና ደጉን የለየ፣ በራሱና በኔ የሚተማመን ልጄ ነው” በማለት አሰበ፡፡
እንደነዚህ ዓይነት ብዙ ሰዎች እየመጡ ሄዱ።…ወደ መጨረሻ ገደማ አንድ ወጣት ብቅ አለ፡፡ አባን ዞር ብሎም አላያቸውም፡፡… መንገዱን ይዞ ይጓዛል።… አባ እየተገረሙ… “ና…ተሳለም እንጂ፣ መስቀል አይታለፍም” አሉት፡፡ ወዲያውም ቆባቸውን ብድግ፣ ጅራታቸውን ሹልክ አድርገው እያሳዩት፡… “ማን እንደሆንኩ አወቅከኝ አይደል?”...ቢሉት…. “የፈለጉትን ቢሆኑ… የራስዎ ጉዳይ ነው” ብሏቸው መንገዱን ቀጠለ፡፡…
በዚህ ጊዜ እግዜር ሰው ሆኖ ተገለጠና ራመድ፣ ራመድ በማለት ደርሶበት፤ “እኔንስ ታውቀኛለህ?... በጦር የተወጋው ጎኔን ተመልከት” አለው፡፡…ጎኑን እያሳየው፡፡ አጅሬውም ቁስሉን እያየ… ”የሆነ ፊልም ውስጥ ያየሁህ ይመስለኛል… የምር ነው እንዴ የምትዋጉት? ...ወረቀት ብይዝ ትፈርምልኝ ነበር፤” አለው፡፡ እግዜርም ቆሞ መሳቅ ጀመረ፡፡
በዚህ ጊዜ አባ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፤ “እንደነዚህ ዓይነቶቹ’ኮ ለማንም አይመቹም፣ እንደው ለመሆኑ ምን ትላቸዋለህ?” በማለት እግዜርን ጠየቁት፡፡
እግዜር ጥቂት አሰበና፤ “እነዚህማ አግኖስትክስ (Agnostices) ናቸው”…አላቸው…
“ምን ማለት ነው?” አሉት መልሰው፡፡…
“…እ… አግኖስቲሲዝም (Agnosticism) …እኔና …. አንተ ለመኖራችን ማረጋገጫ ስለሌለ ማመንም አለማመንም አስቸጋሪ ነው፡፡” የሚሉ ፈላስፋዎች አስተሳሰብ ነው፡፡ …ቅድም ረሳሁ እንጂ ጎረምሳውን “እግዜርና ሰይጣን መኖር አለመኖራቸውን ታውቃለህ አታውቅም?” ብዬ በጠየኩት ነበር፡፡.. መቼም መልሱ “አላውቅም” የሚል እንደሚሆን የታወቀ ነው…” አለና እግዜር ትንሽ አሰብ አድርጎ… “ለነገሩ አይፈረድበትም፡፡… አንተ ቀሚስ ለብሰህ መስቀል ይዘህ እያየህ፣ እኔም እንዲህ ሆኜ እየተመለከተ እንዴት ይመን?...”ብሏቸው ተሰወረ፡፡
ወዳጄ፤ አሮጌ ግድግዳ ፈርሶ እስካልተሰራ ድረስ ቆንጆ ቀለም ቢቀባ ያው አሮጌ ግድግዳ ነው። ጅብ ቆዳውን ገልብጦ ቢለብስ ያው የምናውቀው ጅብ ነው፡፡ አውሮፓውያኑ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥማቸው፤ “ርካሽ ዕቃን በቆንጆ ወረቀት መጠቅለል ነው፤” (a cheap item wrapped in a beautiful paper) ይላሉ፡፡  ውስጣችን ወይም ሃሳቦቻችን ሙሉ በሙሉ ተቀይረው፣ ጊዜውን ባገናዘበ መንገድ በአዳዲስ፣ ዘመናዊና ገንቢ አስተሳሰቦች እስካልተተኩ ድረስ ምናልባት ሌሎችን እናሳስት እንደሆን እንጂ እኛነታችን ያው ነው፡፡
ሰውየው ‹ከኔ በላይ አማኝ ላሳር ነው› ባይ ነው። አንድ ቀን ውበት ሳሎን ገብቶ፣ ጢሙን ተላጭቶ፣ ፀጉሩን ተስተካክሎ፣ በቀለም አምሮና ተውቦ ሲወጣ፣ ከዕድሜው በታች ፍፁም ወጣት መስሎ ነበር፡፡ እንዴት አለሙን እንደሚቀጭ እያሰበ፣ ጎዳናውን ሲያቋርጥ ድንገት የመጣች አውቶሞቢል ገጭታ ገደለችው፡፡ … ሰማይ ቤት ደርሶ አምላኩን ሲያገኘው፡-
“ምነው እንደዛ ሳምንህ ጉድ አደረግኽኝ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“አንተ ነህ‘ንዴ? .. በጭራሽ አላወቅኩህም፣ ሌላ ሰው ነበር የመሰለኝ” … አለው ይባላል፡፡
አየህ ወዳጄ፤ መለወጥ ከፈለግን  ውስጣችንንም መቀየር ያስፈልጋል፡፡ … መሆንን መቻል አለብን፡፡ የተኛንበት ጎን ስለቆረቆረን በሌላኛው ብንገለበጥ ጊዜያዊ ምቾት ካልሆነ በቀር ለውጥ የለውም፤ ያው ነው፡፡ … “ቂጣ ቢገለበጥ” … እንደሚባለው፡፡ …
ካችአምና፣ አምና እያልን
ብንደርስ ከዘንድሮ፣
ጊዜያችን ሸብቷል
ቁጭት ብቻ ቋጥሮ፡
ነገሥታት ረግፈው
አዲሶቹ ነግሰው፣
ተራሮች ተንደው
ተራራዎች በቅለው፣
ስልጣኔም አልፎ
ስልጣኔ መጣ፤
ኑሯችን ተጥዶ
ከሳት ላይ ሳይወጣ፡፡
ቂጣ ቢገለበጥ
ተመልሶ ቂጣ!!
(ከገጣሚ ተመስገን)
ከግብፅ ፈርኦኖች አንዱ ወደ ንግስና የመጣው በዘር የስልጣን ውርስ ሳይሆን ባጋጣሚ ነበር፡፡ ይኼ ደግሞ ለብዙዎቹ ግብፃውያን አልተዋጠላቸውም። … ማጉረምረም ጀመሩ፡፡ በሱ ልንገዛ አይገባንም፣ ማን እንደነበር እናውቀዋለን፣ የንግሥና ወዝ የለውም፡፡ … እያሉ አስቸገሩ፡፡ ፈርዖኑም ምን ማድረግ እንዳለበት አሰበና … ከብረትና ከድንጋይ የተሰራውን የሚወዱትን ጣዖት አፍርሶ በወርቅ አነፀላቸው፡፡ በእጅጉም ተደሰቱ፡፡ ለአዲሱም ጣዖታቸው ከበፊቱ የበለጠ ፍቅርና እምነት ማሳየት ጀመሩ፡፡ እየበዙም አመለኩት፡፡ ይህን ያስተዋለው ፈርዖን እንዲህ አላቸው፡-
“አዲሱ ጣዖት ከምን እንደተሰራ ታውቃላችሁ?”
“ወርቅ እንጂ ሌላ አይደለም” አሉት፡፡
“ዕውነት ነው፡፡ ግን ወርቁ ከየት እንደመጣ አልገባችሁ ኖሯል?”
“ኧረ በጭራሽ … አንተ ንገረን እንጂ …”
“አያችሁ ወገኖቼ፤ ይኸ ወርቅ ቀልጦና ተቀርፆ አሁን እንደምታዩት ያማረ ጣዖት ከመሆኑ በፊት እግሬን የምታጠብበት ገበቴ ነበር፡፡ … እኔም እንዲሁ ነኝ፡፡ በፊት የምታውቁት ‹እኔ› እዚህ የለም። እፊታችሁ የቆመው ፈርዖን፤ እንደ ጣዖታችሁ የተለወጠ አዲስ ሰው ነው፡፡” አላቸው፡፡
ግብፃውያኑም አመኑት፡፡
“ፈርዖን ሆይ፣ ላንተ ምስጋና ይገባል” አሉ፤ ለክብሩም ሰገዱለት፡፡
አየህ ወዳጄ፤ ከተቀየሩ አይቀር እንደ ግብፃውያኑ አምላክ በእሳት ተፈትኖ፣ ቀልጦና ተቀርፆ ‹የድሆች ጣዖት› መሆን ነው፡፡ ቀንድና ጭራን ደብቀው፣ ቀሚስ ለብሰው፣ ቆብ ስለደፉ ብቻ ሃቀኛ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ እራስንና ሌላውን ማታለል ደግሞ አሳይ መሲህነት ነው፡፡ … መምሰል ሌላ፣ መሆን ሌላ!!
ሠላም!!

Read 931 times