Saturday, 28 October 2017 10:23

ሦስትዮሽነትን የሚመረምረው ደራሲ

Written by  ግ.ሌ
Rate this item
(2 votes)


   “--በእኔ እይታ፣ ከታሪኩ መድረሻ ይልቅ መነሻው ይመስጠኛል … ጨዋታው በምንና ምን መሀል እንደሆነ ካወቅሁ…መጨረሻው ቀላል መገላገያ እንደሌለውም እረዳለሁና፡፡ ከጨዋታው የማተርፈው ነገር የምናብ ከፍታን ነው፡፡… የሚቀላቀሉና የሚለያዩት የሀሳብ ልኮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ከሆኑ..ምናብን ወደ ከፍታ የሚተኩስ ውጤት አንባቢው ማግኘቱ አይቀርም፡፡… የምናብ አቅምን ግን ደራሲው አይሰጥህም፡፡--”
    
    … ለጆኒ (ዮሐንስ ሐብተማሪያም) ሁለተኛ መፅሐፍ አንድ ነገር ለማለት ካሰብኩኝ ከራረምኩኝ። አነሳውና አነበዋለሁ፡፡ አስቀምጠውና እንደገና ደግሞ አነሳዋለሁኝ፡፡ ይሄ ሁሉ ከየት እንደምጀምረው ስለቸገረኝ ነው፡፡ መፅሐፉ የአጭር ልብ ወለድ መድበል ነው፡፡ ጆኒ ደግሞ ጆኒ ነው፤ ገጣሚና የአጭር ልብ ወለድ ደራሲ፡፡ ይሄ ሁለተኛ መፅሐፉ፤ “ካፑቹኖ” ይሰኛል፡፡
መፅሐፉን ማንበብ ቀላል ነው፡፡ አንብቦ መዝናናት፣ መመሰጥ፣ በጥበብ መምጠቅ---መፅሐፉን እንደ ማንበብ ቀላል ነው፡፡ … ነፍስ ላለው ቀላል ነው፡፡ ከባዱ፤ መፅሐፉን፣ ከደራሲው፣ ከጭብጡ፣ ከቅርፁ፣ ከውበቱ ጋር አመዛዝኖ መግለፅ መቻል ነው፡፡ እና ከብዶኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን መሀከለኛውን ነጥብ አገኘሁት፡፡ ጆኒ ዲያሌክቲሻን ነው፡፡ ተቃራኒዎች ከሚደባለቁበት ስፍራ ላይ ቆሞ ልዩነታቸውን የሚመለከትና የሚመዝን ደራሲ ነው። ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ አያደላም፡፡
“ካፑቺኖ” የሚለው የመፅሐፉ አርዕስትም ይሄንኑ ያሳያል፡፡ ወደ ወተትም ወደ ቡናም ሳያጋድል ቀጥ አድርጎ ብስክሌቱን ይሾፍረዋል፡፡ እንዲያውም ካፑቺኖ፤ ቡና እና ወተት ተቀላቅለው የሚገኝ የድብልቅ ውጤት ሳይሆን ሁለቱ ከመለያየታቸው በፊት የነበሩትን ሙሉነት የሚያሳይ ነው ይላል። … ምድርና ሰማይ ሲገናኙ፣ “አድማስ” የምንለው ምናባዊ ድንበር ይፈጠራል - በማለት እኛ የምንገልጸውን፣ ጆኒ ደግሞ … ምድርና ሰማይ ከመለያየታቸው በፊት “አድማስ” በሚባል አንድነት ይታወቁ እንደነበር …  ለማሳየት ይጥራል፡፡ በጥረቱ ውስጥ ይፈጥራል፡፡
እንግዲህ ደራሲው፤ከምን አይነት ብያኔ ተነስቶ ነው አለምን በድርሰቶቹ የሚተረጉመው? … የሚለውን ጥያቄ ለመጨበጥ ስል የሰራሁት ግርድፍ ካርታ ነው፡፡ ካርታውን አጠናክሬ ለመግፋት ልሞክር፡፡
በመፅሐፉ ውስጥ ካካተታቸው አስራ ሰባት አጫጭር ልብ ወለዶች ለዚህ ግርድፍ ካርታዬ (Premise) የሚመጥኑትን መደመር ያስፈልገኛል፡፡ በተራ ቁጥር (13) ላይ የሚገኘው አጭር ልብ ወለድ፣ “ከማዕረግ ወደ ማዕረግ” ይሰኛል፡፡ ታሪኩ ስለ አንድ ገፀ ባህሪ (አለው አያልቅበት) የሚተርክ ነው፡፡ አለው አያልቅበት፤ በተደጋጋሚ ወንጀል እየሰራ፣ፖሊስ ጣቢያ የሚመላለስ እንደሆነ ተረድተን፣ ምናባችንን ለምድርና የፖሊስ ጣቢያ አጭር በር አመቻችተን እያነበብን እንጠብቃለን፡፡
ይሄኔ … ገፀ ባህሪው የፈፀመውን ወንጀል ይነግረናል፡፡ “ባዘኔው፣ ዘባተሎው፣ ደነዙ፣ አረመኔው” የሚል የማዕረግ ቅፅል ስም በቀድሞው ጥፋቶቹ ምክኒያት ያካበተው ገፀ ባህሪ፤ “እግዜርን ገድዬ ነው የመጣሁት” ሲል ድንገት የፖሊስ ጣቢያዋን ጥበት ወደ ሰማይ ስፋት በቀላሉ ያስጠጋታል፡፡ ልጁ ዲያሌክቲሻን ነው ብያለው፡፡
የተገደለው አንድ ተራ ሰው ቢሆን እዛው አለም ላይ ባለን መለኪያ ጉዳዩ በተመዘነ ነበር። “እግዜርን ገደልኩ” በማለቱ በአንድ ጊዜ ታሪኩ ስለ አንድ ወንጀለኛ ሳይሆን ስለ ሁሉም ነገር ሆኖ ይለጠጣል፡፡ ቡና እና ወተቱ “ካፑቺኖው” ውስጥ እንደተቀላቀሉት … ተቀላቅለው ይማሰላሉ። ቀላልነትና ውስብስብነት መሀል ዥዋዥዌን እያጫወቱ የምናብን አይን ይከፍታሉ፡፡ ጥያቄ በጥያቄ እንድንሆን ያደርገናል። የተሰደብንም ይመስለናል፡፡ የእግዜር ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነዋ፡፡… ግን ሚዛናችን ቅርብ ባለው የፍትህ  ልካችን (የወንጀለኛ መቅጫ የህግ አንቀፆች) እና ሩቅ ባለው እምነታችን መሀል ይናጋብናል፡፡ …ገፀ ባህሪው ምናልባት በነበሩት አልባሌ የወንጀለኛ ማዕረጎች ላይ ትልቁን ኒሻን ጭኖ ለመንገስ ይሆናል… ነብስ ገዳይነቱን የፈለገው። ሰይጣን እንኳን የማያስበውን ነገር ከማሰብ አልፎ ተግባራዊ አደረኩት ብሎ ምድራዊ ፖሊስ ጣቢያ ይመጣል፡፡ በአንድ ጊዜ ሰይጣንና ከዚያም በላይ ይሆንብናል፡፡
ጥበብ ይሄንን የማድረግ አቅም አለው፡፡ የህግ ተቋሙ ሊመልሰው የማይችል ጥያቄ ይጭርብናል፡፡ በደም የተነከረ ጩቤ ይዞ ወደ ጣቢያ በመምጣቱ… “እግዜር ይደማል እንዴ?” ብለን በምናብ ማዕበል እንድንተራመስ ያደርጋል፡፡ የጆኒ ዲያሌክቲክስ አንዳንዴ በእምነትም በፖለቲካም አንፃር መልስ የማታገኝ ናት፡፡ ገፀ ባህሪው “እግዜርን ገደልኩት” ሲል፣ እኔ “ጠቅላላውን  ህዋ ጎረስኩ” እንዳለኝ ነው የቆርጠኩት፡፡ የጆኒ ገፀ ባህርይ ድርጊት “እውነት ቢሆን” … ብሎ ለማሰብ ራሱ መቆሚያ ደሴት ያስፈልጋል፡፡ የመመልከቻ አንፃሮችን ሁሉ አጥፍቶ ማነፃፀር ካልተቻለ፣ ለወንጀለኛው ፍርድ መስጠትም አስቸጋሪ ነው፡፡
“ውሸት ነው፤እንዴት እግዜርን ሊገድል ይችላል” በማለት “አልጫወትም” ብለን ማኩረፍ እንችላለን። ጥበብ ግን ቀላሉን ከውስብስቡ በማጣመር ህግ፣ የመጠቀ ምናብን ብቻ የሚያጫውት፣ የሚያሳትፍ “የውሸት” አይነት ነው፡፡…. የጥበብ ውሸት በጣም የላቀ ሲሆን እውነትን ራሱ ገልጦ የማሳየት አቅም ይኖረዋል፡፡
አስራ አንደኛው ታሪክ፣ “ሰው ሰራሽ ሰው”ም እንዲሁ  ሁለት ተቃራኒ የሀሳብ ውሃ ልኮችን ደባልቆ፣ ከዛም ለያይቶ ለመመዘን የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡ ጎራዎቹ ግለሰብና ማህበረሰብ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ደራሲው ግለሰብን የወከለው በፍቅር ነው፡፡ የፍቅረኛውን አንድ ጆሮ በመግዛትና የህዝብን ጆሮ በመሙላት መሀል ገፀ ባህርይው ይወጠራል፡፡ ከዛ የህዝብን ጆሮ ወደ መጋገሩ ይመርጣል፡፡
“አዳራሹ ጆሮ ሆኗል፡፡ መላ አካሉ ተፈጭቶ…ተቦክቶ…ጆሮ ሆኖ ተጋግሮ…በጥሩ ሁኔታ በስሎ እየሰማ ነው፡፡ አንገሶም እያወራ ነው…ሀገር መስማት የሚባል ሰረገላ ላይ ተሳፍሮ..በእሱ ድምፅ ሾፋሪነት… ወደ መንግስተ ሰማይ እያረገ ነው፡፡”
ያው ገፀ ባህርይው አንገሶም ህዝብን ለመስበክ ይመርጣል፡፡ እሱ እንደመረጠው ሁሉ ህዝብም ግን ለካ በየራሱ “የራሴ እቃ” ባለው ጆሮ፣ለመስማት መምረጥ ይችላል፡፡ …ፍቅረኛው፣ ብሌን ታረቀኝ ጥላው ሄደች፡፡ ህዝብን መርጦ ግለሰቧን፣ ፍቅሩን ያጣል፡፡ በኋላ ግን ህዝብም የማያስተማምን ሆኖ ከሁለት ያጣ ሲሆን ያሳያል፡፡ ዋናው ነገር ግን አሁንም በዚህ ታሪኩ፣ ደራሲው ሁለት መሰረታዊ ቋሚዎችን እየቀየጠና እየነጣጠለ እንደየራሳቸው ያላቸውን ባህሪ፣ አንባቢው እንዲያይና የራሱን ምርጫ እንዲወስድ እድል ይሰጠዋል፡፡
በአራተኛ ተርታ የሚገኘው “ሦስት ሰው” የተሰኘውም አጭር ልብ ወለድ፣ ጥቁር (thesis)፣ ነጭ (antithesis) እና ግራጫን (synthesis) ደግሞ የሚያሳይ ነው፡፡ “ሦስት ነን፡፡” ይላል፤ ታሪኩ ሲጀምር፡፡ “ሦስት ነን፡፡ ሦስት አምሳል፡፡ እኔ “ነጭ” ስል… እሱ “ጥቁር” ይላል… እሷ ደግሞ ቀለም ምን ያደርጋል? ትላለች፡፡”
በአስራ ሁለተኛ ተራ ቁጥር ስር የሚገኘው “ዘቢብ” የተሰኘውም ታሪክ፣ ይኼንኑ “ሦስትዮሽነት” ደግሞ የሚያሳይ ነው፡፡ የጆኒ ምልክታዎች፣ ሦስትዮሽነቶችን በተለያየ አውድ እያስገቡ የሚመረምሩ ናቸው፡፡ ጆኒ በጥበብ እውነታን የሚመረምር ነው፡፡ በመደመር… በመቀነስ… እና በማጠቃለል… በመቋጠር እና በመፍታት፡፡ የዲያሌክቲካዊ አመለካከቱን ገና በታሪኩ መግቢያ ላይ ነው የሚገልፀው፡፡ የጨዋታውን ህግ ይፋ አድርጎ እያስቀመጠ ሁሉ ይመስላል፡፡
“ሕይወቱን ሲያስበው ቁጥርና ፊደል ነው፡፡ ሕይወቱ ኑሮው…አልያም..ኑሮው ሕይወቱ (ሁለት ነገሮች ይምታቱበታል) ይመስለዋል፡፡ ቁጥር ሕይወቱን እየቆጠረ-እና-ፊደል ሕይወቱን እየፈደለ እዚህ ደርሷል፡፡”
(ቁጥር…እና…ፊደል)
ይኼ የልብወለድ መግቢያ ቀደም ብዬ ያልኩትን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ሜታፊዚሻንነቱንና ዲያሌክቲሻንነቱን፡፡ “ሕይወቱን ሲያስበው ቁጥርና ፊደል ነው” የሚለው- የሕይወት ትርጉም በቁጥርና ፊደል ጋብቻ ውጤት አድርጎ ይነሳል፡፡ የህይወት ትርጉም ምንድነው? ምንድነው እውነታ? “የቁጥር እና ፊደል መስተጋብር”… ከዛ ህይወትና ኑሮን ደግሞ ሰንጥቆ፣ አንዱ ከሌላው መነጠል እንዳልቻለ ይገልፃል፡፡ “ይመስለዋል” የምትለውን ቃል እርግጠኛ አለመሆኑን የሚያስርበት ነው፡፡ እርግጠኝነቱ ያለው ህይወቱ “ፊደልና ቁጥር ላይ” እንደምትገኝ ነው፤ ከዛ ወደ ታሪኩ ይገባል፡፡ ሦስትዮሽነቱን ይዞ፡፡ በቁጥርና ፊደል፣ ጋብቻና ፍቺ፣ ህይወቱን ሊስላት ወደሚያደርገው ጥረት ይገባል፡፡
እንግዲህ የ“ካፑቺኖ” ደራሲ፤ የጥበበ ፈጠራ አካሄዱ ይሄ ነው፡፡ መጀመሪያ ፍልስፍናውን ያስቀምጣል፡፡ በሦስት ልዩነት፡፡ በሦስት አንፃር። ከዛ ሦስቱን ልኮች በተለያየ መመሰያ እያስገባ፣ እየደመረና እየቀነሰ ይዘልቃል፡፡ በእኔ እይታ፣ ከታሪኩ መድረሻ ይልቅ መነሻው ይመስጠኛል … ጨዋታው በምንና ምን መሀል እንደሆነ ካወቅሁ…መጨረሻው ቀላል መገላገያ እንደሌለውም እረዳለሁና፡፡ ከጨዋታው የማተርፈው ነገር የምናብ ከፍታን ነው፡፡… የሚቀላቀሉና የሚለያዩት የሀሳብ ልኮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ከሆኑ..ምናብን ወደ ከፍታ የሚተኩስ ውጤት አንባቢው ማግኘቱ አይቀርም፡፡… የምናብ አቅምን ግን ደራሲው አይሰጥህም፡፡ እንደ መብራት ሃይል ኮርፖሬሽን፣ ገመድ ዘርግቶ ኤሌክትሪኩንም እሱ ይሰጠኛል ብለህ ከጠበቅህ ተሸውደኸል፡፡ ኤሌክትሪኩን አንተ ነህ የምታመነጨው፡፡ የምናብ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ከሌለህ፣ የዚህን ደራሲ ሥራ ባታነበው ይመረጣል፡፡
በመጨረሻ ለማለት የምፈልገው፣ እኔ የግል እይታዬን ለመሰንዘር ጣርኩ እንጂ … የሀያሲነት ስራን ለመወጣት ፍላጎቱ የለኝም፡፡ ግን እንደው የአጭር ልብ ወለድ ወዳጅ እንደመሆኔና…የልጁ ስራዎች እንዲህ ተጠራቅመው በመፅሐፍ ሲታተሙ… የዘርፉ  ባለሙያዎች፣ ጥሞና ሰጥተው ሊያዩት እንደሚገባ ለመጠቆም ያህል አጭር አስተያየቴን ሰንዝሬአለሁ፡፡ በቂ እንዳልሆነ ባውቅም እንደ መነሻ ሆኖ የዚህ ወጣት ደራሲ ስራ ሳይታይ እንዳይታለፍ ለማስታወስም ያገለግላል ብዬ አስባለሁኝ፡፡

Read 890 times