Sunday, 29 October 2017 00:00

አፋር ማን ነው? “አፋር ፍቅር ነው!!”

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮ
Rate this item
(2 votes)

“--ክልልህ የት ነው? መታወቂያ አሳይ? ለምን ጉዳይ መጣህ? ወዘተ.--በአፋር የተለመዱ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ በተቻለኝ መጠን ተዘዋውሬ ለማጣራት ሞክሬያለሁ፡፡ አንድም ሰው የተለየ ሃሳብ አልሰጠኝም፡፡ ዋናው ጉዳይ፣ ያ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ነው? አይደለም? የሚለው ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ብቻ ዋስትናው ነው፡፡---

“ለወገናችን ኩላሊት እንስጥ፤ ወገናችንን እናትርፍ”

አብዛኛውን የሀገሬን ክፍል አንድም በሥራ፣ አንድም በጉብኝት፣ አለያም ማኅበራዊ መስተጋብርና የወዳጆቼ ፍቅርና ጉዳይ  ምክንያት ሆኖኝ፣ ተዟዙሬ ለማየት ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ፣ ከምስራቅ ጠርዝ እስከ ምዕራብ አጋማሽ በተገኘው የመጓጓዣ ዘዴ እየተጓጓዝኩ፣ የተከበረውን ሕዝቤን የከተማና የገጠር ሕይወት ገፅታ፣ ፊት ለፊት ለማየትና አብሬም የማዕዱና የውብ ባህሎቹ  ተካፋይ ለመሆን በእጅጉ የታደልኩ ይመስለኛል፡፡
ጥላሁን ገሠሠ፤ “ሞልቷል በሀገራችን” እያለ በአድናቆት የዘረዘራቸውንና እጅግም ያልተዘመረላቸውን በርካቶቹን የሀገሬን ባህላዊ የምግብ ዓይነቶችም በሚገባ ተቋድሻለሁ፡፡
“የጉራጌ ክትፎ ሲቀርብ በገበቴ፣
በቆጮ ጠቅልሎ ና ግባ በሞቴ”
የሚሉት እኒህ ሁለት የግጥም ስንኞች፣ ከዜማ ጋር ተዋህደው የተዘፈኑ ብቻ ሳይሆኑ “የአዲስ አበቤዎች ምስለ ክትፎ አቅራቢዎች” አይስሙኝ እንጂ በጉራጌ አካባቢዎች በተዘዋወርኩባቸው ወቅቶች እውነተኛው ክትፎ ቅቤው እየተንጠባጠበ፣ በቀንድ ማንኪያ የጎረስኩባቸው ጣቶቼ፣ “የጥላሁን አድናቆት” እውነት ስለመሆኑ ፈርመው፣ ማረጋገጫውን ለመስጠት አያመነቱም፡፡
“የወላይታውም ባጭራ ሸንደራ
አምቾና ቦይና ጥሩ እንደንጀራ”
እየተሰኙ የተመሰገኑትን የወላይታ ባህላዊ ምግቦችንም ቁጥሩን በማላስታውሰው ብዛት ተመግቤያለሁ፡፡ ማለዳው ወገግ ሲልም በትሪ ተሽሞንሙኖ በዳጣ እየተለወሰ፣ “ግባ በለው” የሚባልለትን የወላይታ ቁርጥ ሥጋ፣ ባደረ ሆዴ ደጋግሜ በመመገቤ፣ እንደ ሱስ ብጤ ሞካክሮኝ ነበር - ለሥራ ጉዳይ ወላይታ ምድር በሰነበትኩባቸው ወራት፡፡
ከቡዕላ ከሚዘጋጁት በርካታ የደቡቡ የሀገራችን ምግቦች መካከል እጅግ ተወዳጅ የሆነውንና በሲዳማ የዘመን መለወጫ፣ “ፍቼ” በዓል ላይ ለተመረጠ ልዩ ወዳጅ፣ የሚቀርበውን፣ በቅቤ የራሰውን ቡርሳሜ የበላ ሰው፤ ቀልቡ ሁልጊዜም ወደ ይርጋለም እንደሚከንፍ በመሃላ ጭምር አረጋግጥ ቢሉኝ፣ “እርግጥ” ማለቴ አይቀርም፡፡ ሀመር የበላሁት የወጠሌ ጥብስ፤ ጌዲዮ፣ ከምባታ፣ ሃዲያ የተመገብኳቸው ልዩ ልዩ ባህላዊ ምግቦች፣ በፍፁም ከትዝታዬ አይደበዝዙም፡፡
ጎፋ ቁጫ ወረዳ ውስጥ “ለውሃ ጥሜ እንዲያግዘኝ” በኩባያ የተንቆረቆረልኝን ንፁህ የተነጠረ ቅቤ ባሰብኩ ቁጥር “ቁጫ ቅቤ በዋንጫ!” የሚለው አባባል ሁሌም ፈጥኖ ይታወሰኛል፡፡ በተራራማዋ የጋሞዋ ጨንቻ ከተማ አንዳች በሚያህል ጎድጓዳ ዕቃ እየቀረበልኝ፣ ስገምጥ የከረምኩት ጣፋጭ የአፕል ፍሬም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የአፕል ችግኝ በጨንቻ አካባቢ ከሶስት አሠርት ዓመታት በፊት መተዋወቅ በጀመረበት ሰሞን በእንግድነት ተገኝቼ፣ የምድሪቱ አፈር እንግዳውን መጤ ጣፋጭ ፍሬ እንዲላመድ፣ በፀሎት ሲባረክ እማኝ ስለነበርኩ፣ “አሜን” ማለቴን አልዘነጋውም፡፡ አሹ ጋሞ፤ እንኳንም ምድሪቱ ተባረከችልህ!!!   
በጮጮ ጢም ብሎ ከእርጎ ጋር ቀርቦልኝ የተመገብኩት የአርሲና የባሌ ቅንጬና የጨጨብሳ ቁርስ ውል ሲልብኝ፣ እየከንፍክ ሂድ ሂድ የሚል ስሜት ይሰማኛል፡፡ አርሲን ባስታወስኩ ቁጥር ሳጉሬ አትረሳኝም፡፡ አንደኛ ክፍል በተማርኩበት የእንግሊዘኛ መጽሐፋችን ውስጥ የሳጉሬ የስልክ ማስደወያ ኪዮስክ ታሪክ ይመስጠኝ ነበር፡፡ ይሄው የጨቅላነት ትዝታዬ ከአእምሮዬ አልወጣ ብሎ በጉልምስና ዘመኔ በ1977 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ አርሲን የመጎብኘት ዕድል ሲገጥመኝ፣ የተቀበሉኝን ቤተሰቦች የጠየቅሁት የመጀመሪያው ጥያቄ ሳጉሬ እንዲወስዱኝ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ያቺ ኪዮስክ ከዓመታት በኋላ አጋድላ ልትወድቅ ብትደርስም ተመሳሳይ ሥራ ይሰራባት እንደነበረ አረጋግጫለሁ። የወለጋው ጩምቦም ያለ ምንም ማጋነን “ጣት ያስቆረጥማል” ቢባል አያንስበትም፡፡ በቅቤ ውስጥ እየዋኘ የቀረበልኝ “ቡነ ቀላ” (በተነጠረ ቅቤ ተዘፍዝፎ የሚቀርብ የተቆላ ቡና)  አጃኢብ ያሰኛል፡፡ እንጮቴና መሮ፣ ተበልተው አይጠገቡም። “ኢጆሌ ወረ ጆቴ ባዬ ገለቶማ!!!”
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በተንቀሳቀስኩባቸው ወራት የሚቀርብልኝን የግመል ወተት (ለአፌ ጎምዘዝ ቢልም) እጎነጭ የነበረው የጥላሁን ገሠሠን ዜማ እያስታወስኩ ነበር። “ሰው ወዳዶቹን” የሀረር ጅቦች፣ “የሥጋ ቅንጣቢ በአፍህ ይዘህ አጉርሳቸው” ስባል፣ እሺታዬን ገልጬ፣ እነ አያ ጅቦ እየተላፉኝና እየተሻሙ ከአፌ ላይ እየነጠቁ የጎረሱትን ትርኢት፣ ለአንድ የባእድ ሀገር ጓደኛዬ እንደ ዘበት አጫውቼው፣ እንዴት እየዘገነነው እንዳማተበ አይረሳኝም፡፡ ለማንኛውም የጥላሁን አድናቆት እንዲህ ተገልጧል፡፡
“የሶማሌ መጠጥ የግመል ወተት፣
የማሽላ ገንፎ የሀረሬ ሁልበት፡፡” ግሩም ነው! ድንቅ ነው፡፡
የጉርሻ ነገር ከተነሳ አይቀር አዲግራትን አልረሳትም፡፡ በአንድ ጉርሻ መጠን፣ ልክ እንደ ብይ እየተድቦለቦለና በቅቤ እየተነከረ፣ ከፊቴ ተደርድሮ፣ ከፍ ካለ የአክብሮትና የፍቅር ቃል ጋር  አዲግራት ከተማ የተመገብኩት ጥለሆና ብርዙ፣ ለቡና ቁርስ ተብሎ የተባረከልኝ አምባሻና ፈንድሻ፣ በአእምሮዬ ጓዳ የትዝታ ክፍል ውስጥ የከበረ ስፍራ ይዟል፡፡ ምስጋናዬ በፍቅር ላስተናገዱኝ፣ እናቶችና እህቶች ይድረስልኝ፡፡
የሚዘናከተው የሰሜን ሸዋው የምንጃር ነጭ ጤፍ፣ ጎጃም ገጠር ውስጥ በቂቤ አብዶ ትክትክ ብሎ የተሰራውን ሽሮ፣ መሃል ጎንደር ከወዳጆቼ ዘንድ ትክን ብሎ በተሰራ የዶሮ ወጥ የተዘጋጀልኝ የቁርስ ፍርፍርና ከግራ ከቀኝ በጉርሻ እያጣደፉ የጋበዙኝ የ“አባጃሌው” ልጆች መስተንግዶም በፍፁም የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ከባሮ ወንዝ ውስጥ ወዲያው ተጠምዶ፣ ወዲያው ተጠብሶ የበላሁት ዓሳ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለጉብኝት በደረስንበት ወቅት በማንጎ ፍሬዎች ስጦታና በዙንባራ የሙዚቃ መሣሪያ በታጀበ ዜማ፣ የተደረገልን አቀባበል ከቶውኑ እንዴት ይረሳል? “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉ፣ ምግቡ ላይ ትኩረት ሰጠሁ እንጂ የሀገሬን ብሔር ብሔረሰቦች ልዩ ልዩ ቀለመ ደማቅና እጅግ በርካታ ውብ ባህሎችና ዕሴታቸውን ባስታወስኩ ቁጥር፣ እንኳንም ከኢትዮጵያ አፈር ውስጥ በቀልኩ እያልኩ “አሹ” እላለሁ፡፡ ደግ ሕዝብ፣ መልካም ወገን! ስለዚህም ነው የዚህን ኩሩ ሕዝብ የደስታ መግለጫ ትርዒቶች በተመለከትኩባቸው አካባቢዎች ሁሉ በስሜት የምፈነጥዘው፡፡
ወገኔ የሚከፋበትንና ሆድ የሚያስብሱትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጥቃቶች፣ በደሎችንና የፍትህ እጦቶችንም በተዘዋወርኩባቸው ክልሎች ደጋግሜ አስተውዬ ተክዣለሁ፡፡ በለሆሳስና በልቤም ምን እንዳልኩ ትዝ ባይለኝም ያጉተመተምኩባቸውን ቀናትና ሁኔታዎች ግን ከሞላ ጎደል በሚገባ አስታውሳቸዋለሁ፡፡
ሕዝብ በአስተዳዳሪዎቹና በመሪዎቹ ላይ ሲያኮርፍ፣ ብሶቱን በተለያየ መልክ እንደሚገልጥም በሚገባ ተገንዝቤያለሁ፡፡ አንዳንዱ በዝምታ፣ አንዳንዱ በእርግማን፣ አንዳንዱ በፀሎት፣ አንዳንዱ በሃሜት፣ አንዳንዱ ድንጋይ በመወርወር፣ እንዳንዱ በንብረት ላይ እሳት በመልቀቅ ወዘተ--- የሕዝብ ቋንቋው ብዙ ነው፡፡ መሪዎቻችን ይህ ሁሉ ቋንቋ ይጠፋቸዋል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ህዝብ በእርግማንና በመራር ፀሎቱ ወደ ፈጣሪ ሲያሳቅላቸው፣ ደንገጥ ቢሉ መልካም ነበር እያልኩም ባይሰሙኝም ለራሴ ማልጎምጎሜ አልቀረም፡፡ “ሕዝብ ምን ያመጣል” የሚሉት መዳፈር፣ ጦሱና መዘዙ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የንጉሡንና የጀብደኛው የደርግን መጨረሻ ማስታወስ እንደምን ተሳናቸው፤ እያልኩም እገረማለሁ፡፡    
ተከባብሮ፣ ተዋልዶ፣ ተዋዶና ተፋቅሮ በኖረውና በሚኖረው በዚህ በተከበረ ሕዝብ መካከል ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየነፈሰ ያለውን የጥፋት ወጀብ፣ ማን እየቆሰቆሰ እንዳለ እውነቱ ወደፊት ገሃድ መውጣቱ አይቀርም፡፡ እየደረሰ ላለው ጉዳትም ፍትህና ርትእ ዳኝነት መሰጠታቸው እንደ ዘበት ሊታለፍ አይገባውም ባይ ነኝ፡፡ ብዙ የሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች መቋጫቸው ግራ እያጋባ፣ “ከሆድ ይፍጀው” ትዝብት ከፍ እያሉ መጥተዋል፡፡ ወቸ ጉድ!!!
ለማንኛውም የመንደርደሪያዬን ሃተታ፣ እዚህ ላይ ገታ አድርጌ፣ “አፋር- ፍቅር” ብዬ ርዕስ ወደመረጥኩለትና በተለየ ገጠመኝ ጫን ብዬ አትኩሮት ላደርግበት ወደፈለግሁት ነገረ ጉዳዬ ልመለስ፡፡ ሰሞኑን የሰነበትኩት አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ነበር። ሰመራ ከተማ የክልሉ ርዕሰ ከተማ ሆና ተግባሯን የጀመረችው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ቢሆንም ለማደግ የምታደርገው ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ ግን በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡ ይበልጥ እንድትፈጥን እያንደረደራት ያለው ምክንያት ደግሞ በቅርቡ ለአስተናጋጅነት የተመረጠችበት የ12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አዘጋጅ በመሆኗ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊቷ አፋር፣ ኢትዮጵያን ራሷን በፍቅር ልትቀበል ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡
የመሠረተ ግንባታው ፍጥነት፣ የዕፅዋት ተከላ ርብርቡ፣ የእንግዶች መቀበያው ድግስ--- ሰመራን ሲረግጡ በጥዑም መዓዛ ያውዳል፡፡ በአጭሩ በሰመራ ከተማ በከፍተኛ የሥራ ትጋት ሌትና ቀኑ ተጋጥሟል ማለቱ ይቀላል፡፡ በአብዛኞቹ የብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች ዘንድ ያስተዋልኩት መልካም ባህልና እሴት፣ በአፋር ክልልም ልቆ መገኘቱን ባልመሰክር ህሊናዬ ይቀጣኛል፡፡ ስለ አፋር ሕዝብ መልካምነትና ፍቅር ወደፊት ሳልታክት እንደምተርክ ለራሴ ቃል ገብቻለሁ፡፡ ዛሬ የማነሳሳው ጉዳይ ግን አጠቃላይ ትዝብቴን ነው፡፡
በአፋር ክልል ውስጥ መሪዎች፣ በነፃነት በሕዝብ መካከል ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነው። እንደ አንዳንድ አካባቢዎች፣ አንድ መለስተኛ መሪ እንደ ነፋስ ሽው ብሎ ሲያልፍ አየሩ አይጫንም፤ አይከብድም። ምናልባትም “በአንድ ተራ” የሕዝብ ካፊቴሪያ ውስጥ ከጎናችን ቁጭ ብሎ ሻይ የሚጠጣው ሰው፣ አንድ የአፋር የቢሮ ኃላፊ ሊሆን ይችላል፡፡ ደጋግሜ ይህንን ነገር አስተውያለሁ። የአፋር ባለሥልጣን ባለፈ ባገደመ ቁጥር የሚያገኘውን ሰው ሁሉ ሰላም ይላል፤ አንዳንዴም የትከሻ ሰላምታ ይሰጣጣል። መቼም የራሱን እብሪት ለመሸሸግ የፈለገ ሰው፤ “ባህሉ ከሆነ ምን ያስደንቃል!” በማለት በግትር አቋሙ ሊከራከር ይከጅል ይሆናል፡፡ በአፋር ውስጥ ባለስልጣን ነኝ ብሎ በመኮፈስ፣ “ጥቁር ወተት፣ ነጭ ከሰል አምጡልኝ” ብሎ መራቀቅና በሕዝብ ማሾፍ ቦታ የለውም፡፡
ከዓመታት በፊት ያስተዋልኩትን አንድ አብነት ብጠቅስ መልካም ይመስለኛል፡፡ ለአንድ ዓለም አቀፍ የኪነ ጥበባት ፌስቲቫል ጉዞ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ባለሙያዎችን ይመሩ የነበሩት ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከአፋር ምድር የተገኙ ባለስልጣን ነበሩ፡፡ እኒህን የመንግሥት የሥራ ኃላፊ በስም ባልገልፃቸውም ማን እንደሆኑ በወቅቱ የነበሩት የታሪኩ ተካፋዮች “እከሌ” ብለው በስም መጥራታቸው አይቀርም። በእኒህ የተከበሩ ሰው ቢሮ ውስጥ የምንሰበሰው ሁሌም በምሳ ሰዓት ላይ ሲሆን ምሳችንን የሚያዘጋጁልን እርሳቸው ነበሩ፡፡
የሚዘጋጅልን ምሳ ይቀርብልን የነበረው ደግሞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ከሚገኘው የእንደ ነገሩ ካፊቴሪያ ውስጥ ነበር፡፡ ግሩም ሽሮ፡፡ ታዲያ ከእርሳቸው ጋር ማዕድ ስንቀርብ እንደ አለቃና ምንዝር ሳይሆን እንደ መልካም አባትና ልጅ ነበር፡፡ ጉርሻውም አይቀር፣ መሻማቱም አይቀር፣ የማዕድ ላይ ቀልድም በሽበሽ ነበር፡፡ የእኒህ ሰው መመሪያ፤ “ፕሮቶኮል መሪን ከተመሪ ያራርቃል፤ ሥራን ያጓትታል፣ ወዳጅነትን ያደበዝዛል” የሚል ሲሆን ዛሬም ድረስ አቋማቸው አልተለወጠም። በየትኛውም ሁኔታና ቦታ “ቡና ልጋብዝዎ” ቢባሉ፣ አንድም ቀን ደብዝዞ የማያውቀውን ፈገግታቸውን እያርከፈከፉ፣ ፈቃደኝነታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የአፋር ምድር ያበቀላቸው የፍቅር ሰው ናቸዋ! በስልጣን መኮፈስ ሲያልፍም አይጎበኛቸውም።
በዚያው የሰመራ ከተማ ግርምት የፈጠረብኝ ገጠመኝም የሚከተለውን ይመስላል፡፡ ባረፍኩበት የሆቴል ግቢ ውስጥ ቀን ላይ ከአንድ መቶ የሚበልጡ አልጋዎች ተዘርግተው ያስተዋለ እኔን መሰል የመሃል ሀገር ሰው፤ አልጋዎቹ ለፅዳት የወጡ ሊመስለው ይችል ይሆናል፡፡ አይደለም። እነዚያ የውጭ አልጋዎች የሚከራዩት በሽሚያ ነው፡፡ አካባቢው ሙቀት ስለሆነ ትሉኝ ይሆናል፡፡ እውነት ነው፤ ምክንያቱ እርሱ ነው። የሚገርመው ይህ አይደለም፤ እያንዳንዱ እንግዳ የፈለገውን ያህል ገንዘብም ሆነ ንብረት ወርወር አድርጎ የሚተኛው አልጋው ሥር ነው፡፡ ከጎኔ የተኛው ማን ይሆን ብሎ አይጠራጠርም፡፡ ማን የማንን ዕቃ ሊነካ?! ጭራሽ አይሞከርም፡፡ ሀገሩ አፋር ነዋ!
ሌላው ልቤን በሃሴት የሞላው ጉዳይ እውነተኛውን “ኢትዮጵያዊነት” እዚያ መመልከቴ ነው፡፡ ማንም ሰው፤ ሰላማዊና ጨዋ ባህርይ ያለው እስከ ሆነ ድረስ ከየትኛውም የሀገራችን ክልል፣ ለሥራ ፍለጋ ይሂድ፣ በነፃነት ሰርቶ የመኖር መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ “ክልልህ የት ነው? መታወቂያ አሳይ? ለምን ጉዳይ መጣህ?” ወዘተ. በአፋር የተለመዱ ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ ይህንንም ሁኔታ ጊዜው በተመቻቸልኝ መጠን ተዘዋውሬ ለማጣራት ሞክሬያለሁ፡፡ አንድም ሰው የተለየ ሃሳብ አልሰጠኝም፡፡ ዋናው ጉዳይ፣ ያ ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ነው? አይደለም? የሚለው ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ብቻ ዋስትናው ነው፡፡
እጅግ ያስገረመኝን ሌላውን ጉዳይ ልጥቀስ፡፡ ለብሔር ብሔረሰቦች በዓል ወደ ክልሉ ለሚሄዱት የባህል ልኡካን ቡድኖች ማረፊያ የሚሆኑ አራት መቶ ሰማንያ የአፋር ባህላዊ ቤቶች ሌሊትና ቀን ሲሰሩ በአካባቢው ተገኝቼ ተመልክቻለሁ፡፡ እነዚህን ቤቶች በትጋት የሚሰሩት ደግሞ የአፋር ሴቶች ብቻ ናቸው። ወንዱ አልፎ አልፎ የቤቱን መሥሪያ ቁሳቁስ ወርወር እያደረገ መሄድ ካልሆነ በስተቀር በግንባታው ሂደት ላይ ምንም ተሳትፎ የለውም፡፡ እነዚያ የአፋር እናቶችና እህቶች፣ በደቦ ስንቃቸውን ጭነው፣ በራቸውን ዘግተው፣ “ኢትዮጵያን” ለመቀበል የሚያደርጉት ትጋት በስሜት ባህር ውስጥ ይዘፍቃል፡፡ “ለመሆኑ የክልሉ መስተዳድር የውሎ አበል ይሰጣቸዋል?” በሚል ላቀረብኩት የጅል ጥያቄ፣ የተሰጠኝ አጭር መልስ፤ “የምን የውሎ አበል አመጣህብን?” የሚል ነበር። ሥራው የሚከናወነው በራስ ስንቅ፣ በራስ ገንዘብ፣ በራስ ጊዜ -- ነው፡፡ ለእኔ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ማለት ይሄ ነው፡፡ አንድ ቀን ተጉዘው “የአስር ቀን አበል መብቴ ነው” ለሚሉ ራስ ወዳዶች ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ስለ አፋር ድንቅ ኢትዮጵያዊ ባህልና ሀገር ወዳድነት፣ ስለ አፋር ሕዝብ እውነተኛ አፍቃሪነትና ደግነት ወደፊት ብዙ የምለው ይኖረኛል፡፡ በአጭሩ አፋር ማን ነው? ተብዬ ብጠየቅ የምሰጠው ቁርጥ ያለ መልስ፤ “አፋር ፍቅር ነው” የሚል ነው፡፡ ቸር እንሰንብት!
Read 1613 times