Sunday, 29 October 2017 00:00

ጥበብ ያለው፤ ፍሬ አለው!

Written by  በነብዩ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

ከአዘጋጁ፡- ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍ “ሸገር 102.1” ሥርጭት የጀመረበትን የ10ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ “እናውራ” በሚል ርዕስ ከታተመው መፅሄት ላይ የተወሰደ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ሸገሮችን እንኳን ለ10ኛ ዓመት በዓላችሁ በሰላምና በስኬት አደረሳችሁ ለማለት ይወዳል፡፡ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!”
የሸገር ስኬት ምሥጢር ፍቅር መሆኑን ሳስበው ደስ ይለኛል፡፡ በእርግጥ ብዙ ምሥጢራት ይኖራሉ። ኃያሉ ምሥጢር ግን ፍቅር ነው፡፡ ሥራን በፍቅር ሲጠምቁት ይሰምራል፡፡ ፈተና ባይቀርም፤ ትልቁን አጥብቆ ለያዘ፣ ያን ያህል አያስቸግርም፡፡ የሸገር መንገድ ከመነሻው፣ ማሟሻው ፍቅር ነውና፣ ያው  እንደምታውቁት ዘልቋል፡፡ “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!” ሌላ አይደለም፣ የፍቅርን ዘለዓለማዊነት ማብሰሪያ ነው፡፡ “ሸገር የ’ናንተ ነው!” ሲባልም አባባል አልነበረም፤ አይደለምም፡፡ ማስመሰል ሳይሆን እውነት ነው፡፡ መሸንገል ሳይሆን፣ ከቀና ልብ መንጭቶ ነው፡፡ እስከ ዛሬም ዝንፍ አላለም፡፡ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የምር ፍቅርን ይዞ መጣ፣ የምር ፍቅርን እየሰጠ ዘለቀ፤ እነሆ አሥር ዓመታትን፣ አድማጮች “የእኛ” ሲሉ እንደጠሩት፤ በእኛ አገር መገናኛ ብዙኃን ታሪክ ያልተለመደ የሚመስለውን እንደሰጠ፤ እንደተቀበለም አለ፡፡ መንገዱን ያወቀ፤ አድራሻውን ያውቃል፡፡ የናንተ ሬዲዮም ከመነሻው ጉዞውን በፍቅር ቃኘው፡፡ በፍቅር ያበጁት ሁሉ ከማሸነፍ ዝንፍ አይልምና፤ ከኖረና ከነበረው ሁሉ ተለየ፡፡ ለማሸነፍ ብዙ ጊዜም አልጠየቀውም። ገና ከማለዳው ነበር ከማሸነፍ ጋር የተገናኘው፡፡ አሸናፊነቱን ደግሞ ማንም ሳይሆን አድማጩ ነበር የቸረው፡፡ “እርግጥ ነው!...አዎ፤ ሸገርማ የኔ ነው!” ሲል ምስክርነቱን ለመስጠት ስድስት ወራትን ብቻ ነበር የጠበቀው፡፡
የእናንተ ሬዲዮ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1. በወርኃ መስከረም 2009 ዓ.ም፤ የእውነት ጋብቻን ከአዲስ አበቤ አድማጭ ጋር ፈፅሟል፡፡ ይሄ ስኬት ምናልባትም ቀድመን ከለመድነው የፍጥምጥም መንገድ የተለየ ነበር፡፡ ብዙዎች ተደስተዋል፡፡ ጥቂቶች ደንግጠዋል፡፡ ደንግጠውም ተነቃቅተዋል። ቀስቃሽም በመሆን ጠቅሟል፡፡ የሬዲዮን መንገድ ከመሠረቱ ቀይሮታል፡፡ ቅድመ ሁለት ሺህ እና ድኅረ ሁለት ሺህ ዓ.ም፤ እኛና ሬዲዮ የሁለት ዓለም ያህል ልዩነት ታየባቸው፡፡ ሬዲዮ በአዲስ ቅርፅና ይዘት ተወለደ፡፡
እነሆ የእናንተ ሬዲዮ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 አሥር ዓመት ሞላው ቢባልም፣ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ግን ትርጉሙ ከዚያም ይልቃል፡፡ ለእኔ “ሸገር ሳይሆን አሥር ዓመት የደፈነው፤ ሬዲዮ እንደ አዲስ ከተወለደ፣ አሥር ዓመት ተቆጠረ፤” ለማለት እደፍራለሁ፡፡… አሁንም ለእኔ ሬዲዮ ሰው ሰው መሽተት የጀመረው የዛሬ አሥር ዓመት ይመስለኛል። ሬዲዮ ለጆሮ መቃኘትን አሀዱ ካለ አሥር ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ የሸገር መንገድ፣ ነባሮቹ ተሀድሶ ገብተዋል፤ አዳዲሶች በሸገር ቅኝት ፈልቀዋል፡፡ እነሆም፣ በሸገር ጅረት መፍሰሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሸገር መንገድ የድንገት መንገድ አልነበረም፡፡ የሸገር መንገድ የአዲስ ሐሳብ መንገድ ሆኖ ተበስሯል፡፡ ያኔ! የዛሬ አሥር ዓመት፣ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፣ ለሬዲዮ አዲስነት የልዩነት ርችት ተኩሷል፡፡ እኒያ ኅብረ ቀለማት፡፡ በርተው ጠፊም አልሆኑም፡፡ ዛሬም ድረስ በከተማችን አዲስ አበባ እንደተንቦገቦጉ፣ እንደአጥቢያ ኮከብ ንጋትን ብቻ እንዳበሰሩ አሉ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በእኛ አገር የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ፣ በተለይም በሬዲዮ፣ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 በጠዋት ፀሐይ ይመሰላል፡፡
ሸገርን ሳስታውስ ሚዛንን አስታውሳለሁ። መሀል መንገድ ትዝ ይለኛል፡፡ በእኛ አገር ጥግ ካልሆነ፣ መሀል ለመሀል ሆኖ መጓዝ እምብዛም ቅቡል አይመስልም፡፡ ብዙ ዘመናትን ወይ በግራ፤ ወይ በቀኝ ማዕዘን ተለጥፎ ካልሆነ፤ “ቀኝም ግራም ሳልል ሚዛን ጠብቄ እጓዛለሁ!” ማለት አልተለመደም ወይም አይቻልም፡፡ ወይ መደገፍ፣ ወይ መቃወም፣ አማራጭ የሌላቸው ሁለት ምርጫዎች የግድ ሆነው ይታሰባሉ፡፡ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 ይህን የገነገነ አመለካከት መስበር ችሏል። ይህን የጠበቀ አጥር ጥሶና ሰብሮ አልፏል፡፡ “የኔ መንገድ ከመካከል ያለው ነው!” ብሎ “Middle of the Road!” ፖሊሲና ስትራቴጂ ሆኖት ተወለደ፡፡ ከቡድን መንፈስ የተላቀቀ፤ የሚዛን መንገድ ያጠበቀ አዲስ መንገድ! …በርግጥም እውነት ያለችው ከአካፋዩ ላይ ነው፡፡ ሸገር አካፋዩን ይዞ ዘልቋል፡፡ ብዙኃኑ አድማጭም በአካፋዩ ላይ አለ፡፡ እናንተም ከአካፋዩ ኖራችኋልና፣ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 አካፋዩ ላይ ያሉቱ፣ የእናንተ ሬዲዮ ሆኖ መጣ፤ ከእናንተ ጋር፣ የእናንተ እንደሆነም ዘልቋል፡፡
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 የጥበብ ቤት ነው። የተወለደው በጥበብ ነው፡፡ ጠረኑ ሁሉ ጥበብ ጥበብን ይላል፡፡ በጥበብ የሆነ ሁሉ ደግሞ አዲስ ነው፡፡ አዲስ ነገር አዲስ እንዲሆን የግድ ይመስላል። አዲስ ያልሆነ “አዲስ ነኝ!” ቢል፣ ስላለ አይሆንም። ያልነበረና ያልታወቀውን ይዞ እንዲመጣ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ካልቻለና ካልሆነ ግን፣ አዲስ ስም እንጂ አዲስ ነገርን ይዞ አልመጣም። ስለዚህ አሮጌ ነው፡፡ ወይም የነባሩ ቅጥያ ነው። ሸገር ቅጥያ ሆኖ አልመጣም፡፡ በጥበብ ያምናል፣ ያውቅበትማልና፣ አዲሱን መንገድ ፈልጓል፡፡ የነበረውን መርምሮ ነው የተነሳው፡፡ በቋንቋው፣ በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በሁሉመናው አዲስ ያለውን ይዞ፣ በጥበብ ተሟሽቶ ተወልዷል፡፡
የናንተ ሬዲዮ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1ን ከመነሻው አዲስ ያደረጉ የተለያዩ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ “የሸገር ወሬዎች” ከስያሜ ጀምሮ፣ ከኖረና ከነበረውም ተለይቶ መጥቷል፡፡ በጊዜው የብዙዎች መነጋገሪያም ነበር፡፡ የሸገር ወሬዎች እንደ አዋጅ ከመነገር ይልቅ፤ እንደ ወሬ፤ ለወዳጅ እንደሚያወጉ ሆኖ መቅረብ ነበረበት፡፡ ወሬው ለብዙኃን ሳይሆን፣ ለእያንዳንዳችን፣ ለአንተ፣ ላንቺ፣ ለእርስዎ፣ በየግል የመንገር ያህል በኢ-መደበኛ ቋንቋ፣ ከወዳጅ ከጓደኛ ጋር በምናወራበት ዘይቤ ይነገራል፡፡ ይህም አድማጭ ጉዳዩ ከወዳጁ በግል የሚነገረው ያህል እንደሚሰማ አድርጓል፡፡ በዚህም ከአድማጮች ጋር ቅርበት መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም የጠበቀ የሬዲዮና የአድማጭ ወዳጅነት ተከስቷል፡፡ “የራሴን ለራሴ አዳምጣለሁ!” የሚልን አድማጭ አፍርቷል፡፡…ሸገር የእናንተ ነው!
በጥበብ የሚወለድ ሁሉ በጊዜው አይሰለችም። ጥበብ ሁልጊዜ በፈጠራ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 በዘመናት አገልግሎት የሰለቹ፣ አላቂያቸው የቀረ ሐረግ እና ቃላትን ለቅሞ አስሯቸዋል፡፡ በአዳዲስ ሐረግ እና ቃላት ተክቷቸዋል፡፡ “ዜና” ማለት በእነ “ተገለፀ!....ገለፁ! አስታወቁ!” ካልታሰረ ዜና ያልሆነ ያህል ለዘመናት የተገለገልንባቸውን ቃላት ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል፡፡ ሌሎች ቃላትንም ልዘርዝር፡- “በርካታ”፣ “እንቅስቃሴ”፣ “አብሮነት”፣ “አድርሱን”፣ “ሁኔታ ነው ያለው”፣ “ዕድሜ ጠገብ”…ወዘተ እኒህን የመሳሰሉ ቃላት፣ አማርኛን ጠባብ ቋንቋ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን የኖሩ፣ “የጨረቱ!” ቃላት ናቸው፡፡ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 እኒህ መሰል ከ200 የማያንሱ ቃላትን “የተወገዙ! በሸገር አየር የማይሰሙ” ብሉ ከርችሞ አስሯቸው ነበር ስርጭቱን የጀመረው፡፡ ይሄ መንገድ እና አስተሳሰብ ጣቢያው አዳዲስ አማራጭን ሥራዬ ብሎ እንዲፈልግና እንዲጠበብ አስገድዶታል፡፡ ተክቷቸዋልም፡፡ በዚህም ተሳክቶለታል፡፡…ሸገር የናንተ ነው!
ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1፣ በድምፅ ምርጫም፤ ከመነሻው በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ያልተለመዱ አዳዲስ ድምፆች ይዞ መጥቷል፡፡ እኔን ጨምሮ፣ እነ ማንጠግቦሽ ውብሸት፣ ሙሉጌታ አናጋው፣ መሠረት ደርቤ፣ ፋሲል ረዲ፣ መሠረት በዙ ሸገር ኤፍ.ኤም 102.1 በአዲስ አስተሳሰብ፣ በአዲስ ቅኝት፤ በአዲስ የሬዲዮ ጣቢያ የተደመጡ አዳዲስ ድምፆች ናቸው። “በዚህም መንገድ አለ!” ሲል ከመጋረጃው ጀርባ ያሉ፣ አዲስ ትንፋሾችን መጠቀም እንደሚቻል ያመለከተ ስልት ነበር፡፡ በዚህ ውጥኑም፣ ሸገር ተሳክቶለታል፡፡…በእርግጥም ሸገር የናንተ ነው! በሸገር አዳዲስ አሠራሮች ተዋውቀዋል፤ አዳዲስ ፕሮግራሞችም ተወልደዋል፡፡ በሀገራችን “የዕለት ዐብይ ወሬ” በሙዚቃ ታጅቦ መነገር የጀመረው በሸገር ነው፡፡ በዐብይ ወሬዎች ጣልቃ ሙዚቃ መጋበዝ የሸገር ፍሬ ነው፡፡…
በፕሮግራሞች ይዘትና ቅርፅም ቢሆን በሸገር አዳዲስ ፕሮግራሞች ተወለድዋል፡፡ አንዳንዶቹ ዛሬ የሬዲዮ ጣቢያ እስከመሆን አቅም አግኝተዋል። ቢዝነስና ኢኮኖሚ፣ ስነ-ልቦናን፣ ስፖርት፣ ሌሎችንም ከሬዲዮ አድማጮች ጋር ማገናኘት እንደሚቻል ያሳየው፣ “ሸማች ተኮር ጋዜጠኝነት”ን ያስተዋወቀው ሸገር ነው፡፡ በሸገር የተወለዱ ጥቂት ፕሮግራሞችን ልጥቀስ፡፡ “እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ”፣ “ኦቶሞቲቭ ጆርናል”፤ “ታዲያስ አዲስ”፤… እኒህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በሸገር፤ የሬዲዮ ፕሮግራሞች የነበሩ፤ ዛሬ ለሬዲዮ ጣቢያነት የታደሉ ናቸው፡፡ ከ”ለዛ” ፕሮግራም፣ ዓመታዊው “የለዛ ሽልማት” ተወልዷል-በሸገር፡፡
በእርግጥም “ጥበብ ያለው፤ ፍሬ አለው!” “ሸገር የናንተ ነው!”……. “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!”
Read 948 times