Sunday, 29 October 2017 00:00

ተፈጥሮን ማወቅ ራስን ማወቅ ነው

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር
Rate this item
(0 votes)

ምስኪን እንስሳት! ምስኪን ተፈጥሮ!

    ዛሬ ከፍልስፍና ቅርንጫፎች ውስጥ ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ሥነ ምግባራዊ ግንኙነት የሚያጠናውን የተፈጥሮ ፍልስፍና (Philosophy of Nature and Environment) እንቃኛለን፡፡
የጥንቱና የመካከለኛው ዘመን ሰው ባህልና ፍልስፍና ዋነኛ ትኩረቱ፣ ሰው ከሚኖርበት አካባቢና ከዲበ አካላዊው (ከሰማያዊው) ዓለም ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያስስ ነበር፡፡ ከተፈጥሮ ጋር በነበረው ጥብቅ ቁርኝት የተነሳም “እውነትን” ለማግኘት ተፈጥሯዊ የሆኑ ክስተቶች ውስጥ ነበር የሚያስሰው። ለምሳሌ ለጥንታዊ ግሪክ ፈላስፋ ቴሊዝ፣ የዚህ ዩኒቨርስ የመጨረሻው እውነት፡- አፈር፣ አየር፣ ውሃና እሳት ናቸው፤ ለዲሞክሪተስ “አተሞች” ሲሆኑ ለሄራክሊተስ ደግሞ “እሳት” ነው፡፡ ጥንታውያን ሮማውያንም በተፈጥሮ ህግ አብዝተው ይመሰጡ ነበር፡፡
እውነትንና እውቀትን፤ ውበትንና ሥነ ምግባርን እንዲሁም የሕይወት ትርጉምን ሁሉ በዚህ ተፈጥሯዊ በሆነው ሂደት ውስጥ ለማግኘት ይሞክሩ ነበር፡፡ ይሄም ሂደት የጥንቱና የመካከለኛው ዘመን ሰው፣ ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ጥብቅ ቁርኝት የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ “ተፈጥሮ” በምዕራቡ ዓለም ራሱን የቻለ የፍልስፍና ርዕሰ ጉዳይ ለመሆን ችሏል፡፡
ሆኖም ግን “ተፈጥሮን” የፍልስፍና ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ የማድረጉ አካሄድ፣ ከ17ኛው ክ/ዘ ጀምሮ በአውሮፓ ሁለት መልኮችን መያዝ ጀመረ፡፡ የመጀመሪያው  ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ፣ በእንግሊዝና በፈረንሳይ (አንግሎ ፍራንስ) ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች የሚመራ ሲሆን ይሄም አስተሳሰብ ተፈጥሮን እንደ ግዑዝና መጠቀሚያ ዕቃነት የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ በ19ኛው ክ/ዘ የጀርመን ፈላስፎችና አርቲስቶች የሚመራ ነው፡፡ ይህ ቡድን ሰውን፣ ተፈጥሮንና ዩኒቨርሱን በአንድነት ህይወት እንዳለው ኦርጋኒዝም ይመለከተዋል፡፡
የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ሁሉ የበላይ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተው የአንግሎ ፍራንስ አስተሳሰብ፣ የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ቅራኔ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን የበላይና የዚህ ዓለም ገዥ አድርጎ ማሰብ ሲጀምር፣ ተፈጥሮን እንደ መጠቀሚያነትና የሱን ፍላጎቶች ለማርካት እንደተፈጠረ ግዑዝ ነገር አድርጎ መቁጠር ይጀምራል፡፡ ተፈጥሮን “ከማስገበር” እና “ከጥቅም” አንፃር ብቻ የመመልከቱ ይህ አስተሳሰብ፣ በፍልስፍና ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖቱና በሳይንሱ ውስጥም አለ፡፡
ተፈጥሮን ለመቆጣጠር ስትፈልግ በመጀመሪያ ወደ ዕቃነት ታወርደዋለህ፤ “ሜካኒካዊ ነው፤ ማሽን ነው” ትለዋለህ፡፡ የፊዚክስ ሊቁ አይዛክ ኒውተን፤ “ዩኒቨርስን አንድ ጊዜ በተወሰኑ ሜካኒካዊ ህግጋት የሚመራ አካል ነው” ማለቱ፤ ፈረንሳዊው ፈላስፋ de La Mettrie “ሰው እንደ ማሽን ነው” ብሎ መፃፉ፤ እንዲሁም እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ፤ “የሰው ልጅ ባይሎጂካዊና የነርቭ አጠቃላይ ስርዓቱ ሜካኒካዊ እንደሆነና ዩኒቨርስም ውስብስብ የሆነ ግዙፍ ማሽን መሆኑን”  መናገሩ የአንግሎ ፍራንስ አስተሳሰብ ተፈጥሮን ወደ ዕቃነት በማውረድ፣ ለመቆጣጠርና ለሰው ልጅ “ጥቅም” ለማስገበር የነበረውን ቆራጥነት ያሳያል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ፍልስፍናዎችና ሳይንሶች ውስጥ የአንግሎ ፍራንስ አስተሳሰብ፣ ከተፈጥሮ እየተገነጠለ መሄዱን ቢያሳይም፣ “አውሮፓ ከተፈጥሮ የተገነጠለ የኑሮ መስመርንና ስልጣኔን ለማምጣት እየታገለ መሆኑ በግልጽ የታየው ግን በፈረንሳዊው ፈላስፋ ዴካርት አስተሳሰብ ነው” ይላል፤ ናይጄሪያዊው ፈላስፋ ፕ/ር ሶዲፖ፡፡
የዴካርት “I think, therefore I am” የምትለዋ ሐረግ፣ የአንግሎ ፍራንስ ስልጣኔ በአዲስ መሰረትና መስመር ላይ እየተገነባ መሆኑን የምታመላክት ናት።
ሁሉን እጠራጠራለሁ፤ እኔ ራሴ በሕይወት እየኖርኩ ስለመሆኔ ግን ልጠራጠር አልችልም፤ ምክንያቱም አስባለሁ፤ ለመጠራጠር ራሱ መጀመሪያ መኖር አለብኝ፤ አሁን እያሰብኩ ነው፤ ስለዚህም እየኖርኩ ነው፡፡ (I think, therefore I am)
የሚለው የዴካርት አባባል፣ ለፈላስፎች ጥልቅ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ የጥንቱና የመካከለኛው ዘመን ሰው፣ ዕውቀትንና እውነትን ለማግኘት ከራሱ ውጭ ባለው ሰፊ ዓለም ውስጥ ሲባዝን ነበር፡፡ በዴካርት ፍልስፍና ውስጥ ግን የውጭውን ዓለም መዳሰሱ ቀርቶ የምርምሩ ጅማሮ ከራስ ሕልውና ሆነ፡፡ የዚህን ዓለም እውነት ለማግኘት መጀመር ያለብን “ከራሳችን” ነው የሚለው የዴካርት ፍልስፍና፤ የዕውቀትንና የእውነትን መለኪያ መስፈርትን ለማግኘት ባደረገው ጥረት ውስጥ “ተፈጥሮን” ከእውነት ምንጭነት አስወገደው፡፡  
የአንግሎ ፍራንስ ፍልስፍና በዚህ መልኩ ትኩረቱን ከውጭው ዓለም ወደ ሰው ልጅ ንቃተ ሕሊና መቀየሩ፣ “አውሮፓዊነት ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ህብረት ማቋረጡንና ከተፈጥሮም ራሱን ገንጥሎ አዲስ የሕይወት መስመር መምረጡን የሚያሳይ ነው” ይላል፤ ናይጄሪያዊው ፈላስፋ ሶዲፖ (J.O Sodipo) በ1976 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ባቀረበው የጥናት ጽሁፍ፡፡  
ሆኖም ግን በጅምላ “አውሮፓዊነት ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ጓደኝነት አቋርጧል” የሚለው የሶዲፖ ድምዳሜ ትክክል አለመሆኑን የምንረዳው፣ በሌላኛው የአውሮፓ ክፍል (በጀርመን) ያለውን ፍልስፍ ስንመለከት ነው፡፡
ተፈጥሮ ለጀርመኖቹ (ለጎተ፣ ሼሊንግና ሄግል) እንዲሁ እንደፈለግን የምናደርገው “ምዑትና ግዑዝ” ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ህይወት ያለው፣ የሚንቀሳቀስና የሚያድግ እንጂ፤ እግዚአብሔር ራሱን የገለፀበት ነው እንጂ፡፡ ለዚህም ነው ሼሊንግ “ተፈጥሮ የተኛ መንፈስ ነው (Slumbering Spirit)” የሚለው - የሚታይ መንፈስ፡፡ በመሆኑም፣ በመንፈስና በተፈጥሮ መካከል ያለው ልዩነት የመታየትና ያለመታየት ብቻ ነው፤ ልክ በኢነርጂና በቁስ አካል መካከል እንዳለው ልዩነት፡፡ በመሆኑም፣ ተፈጥሮ ማለት የሚታይ መንፈስ ሲሆን መንፈስ ማለት ደግሞ የማይታይ ተፈጥሮ ማለት ነው — (Nature is visible Spirit, and Spirit is invisible Nature)
ሰው የተፈጥሮ አካል ነው፡፡ “የተኛው መንፈስም” ንቁ ሆኖ የሚነሳው በሰው ልጅ በኩል ነው፡፡ እናም ለጀርመኖቹ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ባወቀ ቁጥር፣ ተፈጥሮ ራሱን በራሱ እንዳወቀ ነው የሚቆጠረው፤ (Human’s knowledge of Nature is Nature’s knowledge of itself).
ተፈጥሮ ራሱን የሚያውቀው በእንስሳት አሊያም በዕፅዋት በኩል አይደለም፤ ምክንያቱም እነሱ ስለ ራሳቸውም ሆነ፣ ስለ አካባቢያቸው የዳበረ ንቃተ ህሊና የላቸውም፡፡ በመሆኑም፣ ተፈጥሮ ራሱን በራሱ የሚያውቀው በሰው በኩል ነው። ልክ ሩሲያዊው የሥነ መለኮት ሊቅ አሌክሳንደር ሺሚማን፤ “ተፈጥሮ በሙሉ እግዚአብሔርን በሰው በኩል ያመሰግናል“ እንዳለው፡፡
“ተፈጥሮ ራሱን በራሱ የሚያውቀው በሰው በኩል ነው“ የሚለው አባባል ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ተፈጥሮ ራሱን በራሱ የሚያውቀው በሰው በኩል ከሆነ፣ ሰው የተፈጥሮ (የዕፅዋቱና የእንስሳቱ) ወኪል ነው ማለት ነው፡፡ ተወካይ ከወካዩ ጋር የግድ ግንኙነት (ተመሳሳይነት) ይኖረዋል፡፡ ሰው የተፈጥሮ ወኪል ከሆነ ደግሞ እንሰሳትና ዕፅዋት የሚሰማቸውን ስሜት፣ በቃላትና ከፍ ባለ ንቃተ ህሊና የሚገልፅላቸው ሰው ነው ማለት ነው፡፡
አንዲት አበባ በፀደይ ወቅት ስትፈካ ምን ዓይነት ስሜት ይኖራታል? ይሄንን ስሜት ለማወቅ የግድ አበባዋን መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ዕፅዋቷ አድጋ አበባ አውጥታ ስትፈካ የሚሰማት ስሜት፣ አንዲት ኮረዳ በቁንጅናዋ ጊዜ ከሚሰማት ስሜት ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሴት እንሰሳት ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ስሜታዊ ትስስር ለማወቅ፣ ሰዎች ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ስሜት ማየቱ በቂ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው የተፈጥሮ ወኪል ነውና፡፡ ይሄም የሚያመላክተን አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ። ይሄውም በሰው ልጅ ውስጥም ሆነ በእንሰሳትና በዕፅዋት ውስጥ “ተመሳሳይ“ የሆነ አንዳች ተፈጥሯዊ ኃይል በውስጣቸው እንደሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ይሄም ተፈጥሮ ምዑት አለመሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
ፅጌረዳዋንም ሆነ ኮረዳዋን ወደ እንደዚህ ዓይነት አካላዊና ስሜታዊ የለውጥ ማዕበል የሚገፋቸው በውስጣቸው የተቀበረው ተመሳሳይ የሆነ ተፈጥሯዊ ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል በዕፅዋትም ሆነ በእንሰሳትና በሰው ተፈጥሮ ውስጥ ሆኖ ከውስጥ ያንቀሳቅሳቸዋል፡፡ ዕፅዋት፣ እንሰሳትና ሰው የተለያየ ህልውና ቢኖራቸውም  በውስጣቸው የሚያንቀሳቅሳቸው የተፈጥሮ ኃይል ግን አንድ ዓይነት ነው፡፡ ቁስ፣ ዕፅዋት፣ እንሰሳትና ሰው፣ የአንድ ተፈጥሮ አራት የተለያዩ መልኮች ናቸው፡፡ ተፈጥሮ ሜካኒካል የሆነ ምዑት ነገር አይደለም የምንለው ለዚህ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ለእርድ የሚነዱ ወይፈኖች፣ የታሰሩበትን ገመድ በጥሰው ያመልጣሉ፤ ጠፍተውም የሚሄዱት ወደ አደጉበት መንደር ነው። ሰው ያደገበት አካባቢ — ተራራው፣ ሸለቆው፣ ወንዙ፣ ሜዳው፣ ጫካው፣ መንደሩ፣ ጎረቤቶቹ፣ የእሳት ዳር ጨዋታው፣ ባህሉ፣ ሙዚቃው፣ ጭፈራው ሁሉ — በህሊናው ውስጥ ተሰንቅሮ ናፍቆት ያሰቃየዋል፡፡ ለእርድ የሚነዳው በሬም ልክ እንደኛው ተመሳሳይ ስሜት አለው፡፡ እሱም ልክ እንደኛ የአብሮ አደጎቹ ፍቅር አእምሮው ላይ ይታተምበታል፡፡ ካደገበት ቀዬ የተነጠለ ወይፈን፣ በየቀኑ የሚግጠው የሳር መስክ፣ የሚጠጣው ወንዝ፣ በየቀኑ የሚያየው ጋራና ሸንተረር ሁሉ ይናፍቀዋል፡፡ ይህ ናፍቆት ነው የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ወዳደገበት ቀዬ እንዲፈረጥጥ የሚያደርገው፡፡ ምስኪን እንሰሳት!!!
እንሰሳት ይሄንን ናፍቆታቸውን መግለፅ አይችሉም፡፡ እኛ ግን ይሄንን ናፍቆት በእንጉርጉሮ አሊያም በስዕል አሊያም በፅሁፍ ወይም በለቅሶ እንገልፀዋለን፡፡ ናፍቆታችንን የምንገልፀው ግን እንስሳትንም በመወከል ነው፤ እኛ የተፈጥሮ ወኪል ነንና፡፡ በመሆኑም በናፍቆት የምናለቅሰው ወይፈኑንም በመወከል ነው፤ ካደገችበት አፈር የተነቀለችውን ዕፅዋትም በመወከል ነው፡፡ ከአብሮ አደጎቹና ካደገበት ቀዬ ተነጥሎ በናፍቆት ለሚሰቃየው በሬም ጭምር ነው የምናለቅሰው። የነሱን ለቅሶ የምናለቅስላቸው እኛ ነን፤ የነሱን ናፍቆት የምናንጎራጉርላቸው እኛ ነን፡፡ ምስኪን እንሰሳት!!! የሰው ልጅ ግን ከእንሰሳት ጋር ያለውን ይሄንን ውስጣዊ ግንኙነት ስለማያውቅ እንሰሳት ላይ ይጨክናል፤ ያሰቃያቸዋልም፡፡ ሰው ይሄንን የሚያደርገው የራሱን ማንነትና ጥንተ ተፈጥሮ ስለማያውቅ ነው፡፡ ተፈጥሮን ማወቅ ራስን ማወቅ ነውና፡፡
ልክ እንደኛ ሁሉ እንሰሳትም ከተፈጥሮ ጋር ስሜታዊ ትስስር አላቸው፡፡ ሰዎች ካደጉበት ማህበራዊና ተፈጥሯዊ አካባቢ ጋር ያላቸው ስሜታዊ ትስስር በእንሰሳት ውስጥም አለ፡፡ ይህ ክስተት በሰውና በተፈጥሮ (Subject and Object) መካከል ያለውን የአስገባሪና የገባሪ ግንኙነት ያጠፋዋል፡፡ እንግዲህ ይህ እውነታ ነው ወደ እንሰሳት መብት ተከራካሪነት የሚያስገባን፤ ለተፈጥሮና ለዕፅዋትም ተቆርቋሪ የሚያደርገን፡፡
የተከበራችሁ አንባቢዎቼ፡- በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የማስነብባችሁን ፍልስፍናዊ ፅሁፎች፣ ከጥቂት የእረፍት ጊዜያት በኋላ እመለስበታለሁ፡፡ እስከዚያው መልካሙን ሁሉ እመኝላችኋለሁ፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሐፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 3941 times