Print this page
Sunday, 29 October 2017 00:00

ግራ የገባ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

“--የሂሳብ ክፍሉ ሠራተኛ ጠዋት በሦስት ሰዓት ተኩል ላይ ቡና ቤት ጂኑን ይዞ የሚገለብጠው የሥራ ዲሲፕሊን ገደል ብትገባ አይደል
እንዴ! ሰዉ ሁሉ ምሳውን በውሃ፣ በለስላሳ ምናምን ትቶ በሦስትና በአራት ጠጅ አወራርዶ ቢሮ የሚገባው፣ ዲሲፕሊን የሚሏት ነገር
ገደል ብትገባ አይደል እንዴ!--
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እዚህ ሞቅ ያለው ቦሌ አካባቢ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ቦሌ፤ ‘ሞቅ’ ያለው ቦሌና ‘ጭር’ ያለው ቦሌ ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡ ወይም ‘አሮጌው’ ቦሌና ‘አዲሱ’ ቦሌ… ወይም አራድነት ‘ታይት ሱሪ መልበስ’ የነበረበት ቦሌና አራድነት ‘ሱሪን እስከተቻለው ድረስ ዝቅ ማድረግ’ የሆነበት ቦሌ፡፡ የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ቦሌ ‘ያኛው’ና ቦሌ ‘ይኸኛው’ ሁለት ጎረቤታማ አገሮች ምናምን ሊመስሉ ምንም አልቀራቸው፡፡ እንግዲህ ‘ፏ’ እንዳሉ አይኖር!)  
አንዲት ወዳጃችን ከውጪ የመጡ ሁለት ጓደኞቿን ‘ኢምፕሬስ’ ለማድረግ አንድ ሬስቱራንት ይዛቸው ትገባለች፡፡ ምሳው ሲያልቅ… “የሂሳብ መጠየቂያ ሲመጣ የደነግጥኩትን ያህል በህይወቴ ደንግጬ አላውቅም…” ብላለች፡፡
ከየትም ቦታ ምንም አይነት ልዩነት የሌለው ምግብ፣ እንደውም በመጠኑ እሷ ከለመደቻቸው ቦታዎች የሚቀንስ ሆኖ የአስራ አምስት ቀን እቁብ እጣ የሚያክል ገንዘብ ስትጠየቅ ምነዋ አትደነግጥ! በነገራችን ላይ…ዘንድሮ ብዙ ገንዘብ ማለት ጥሩ መስተንግዶ ማለት አይደለም፡፡
እኔ የምለው… ጭሰኝነት ምናምን የሚባለው ነገር ቀርቶ የለም እንዴ! ‘ሁለት ቁና ስንዴ፣ ሰባት ቁና ጤፍ፣ አንድ ማሰሮ ማር’ ምናምን ብሎ መታያ ማቅረብ ቀርቶ የለም እንዴ! (ወይ መቅረት!) እናማ…ለምንድነው አንዳንድ አለቆች፣ የበታቾቻቸውን ጭሰኛ አይነት ነገር ለማስመሰል የሚሞክሩት! ለምንድነው አንዳንድ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ተገልጋዩን ጭሰኛ ነገር ለማስመሰል የሚሞክሩት! ለምንድነው አንዳንድ ፖለቲከኞች ህዝቡን ጭሰኛ ነገር ለማስመሰል የሚሞክሩት!
የሆነ ምግብ ቤት ትገቡና ታዛላችሁ፡፡ መመገብ ትጀምራላችሁ፡፡ አስተናጋጆቹ ሆኑ የምግብ ቤቱ ባለቤቶች፣ መለስ ቀለስ እያሉ… “መልካም ምግብ…” ማለት የለ፣ “የጎደለ ነገር አለ?” ብሎ መጠየቅ የለ፣ “ምግቡን እንዴት አገኙት?” ብሎ ነገር የለ፡፡ እንደውም ጥግ ይዘው ሲያፈጡባችሁ፤“ቶሎ ውጦ ወንበር አይለቅም እንዴ!” ምናምን የሚሏችሁ ነው የሚመስለው፡፡ አታጣድፉና! ወይስ የሆነ ‘ስፒድ ዳያሊንግ’ እንደሚሉት አይነት ‘ስፒድ ኢቲንግ’ የሚባል ነገረ አለ? ወይስ…“ሦስት ጉርሻ የሚሆነውን ምግብ በአንድ ጊዜ እንዴት መጉረስ እንደሚቻልና ለመመገብ የሚወስድብዎትን ጊዜ በ70% የመቀነስ የሦስት ወር ስልጠና” የሚባል ነገር ተጀምሯል?
እናላችሁ…የሥራ ነገር፣ የመስተንግዶ ነገር ለምን ዘላለሙን ከመንሸራተት እንደማይወጣ የሚገርም ነው፡፡
የሂሳብ ክፍሉ ሠራተኛ ጠዋት በሦስት ሰዓት ተኩል ላይ ቡና ቤት ጂኑን ይዞ የሚገለብጠው የሥራ ዲሲፕሊን ገደል ብትገባ አይደል እንዴ! ሰዉ ሁሉ ምሳውን በውሃ፣ በለስላሳ ምናምን ትቶ በሦስትና በአራት ጠጅ አወራርዶ ቢሮ የሚገባው፣ ዲሲፕሊን የሚሏት ነገር ገደል ብትገባ አይደል እንዴ!
በተፈለገ ሰዓት ቢሮ ተትቶ የሚወጣበት፣ በተፈለገ ሰዓት “ጉዳይ ገጥሞት ወጣ ብሏል፣ ከሰዓት ይመለስ ይሆናል” የሚባልበት፣ “ለሻይ ወጣ ብሏል” ተብሎ አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ቆይቶ የሚመጣበት፣ አለቃ አንዲት ደብዳቤ ላይ ለመፈረም አስራ አምስት ቀን የሚወስድበት--- ዲሲፕሊን የሚሏት ነገር ገደል ብትገባ አይደል እንዴ!
የምር ግን አሁን፣ አሁን አንዳንድ ጊዜ የቢሮ ሰዓቱ ራሱ የትርፍ ጊዜ ሊመስል ምንም አይቀረው፤ ወንበር ላይ መአት ባለጉዳይ ተደርድሮ፣ ገሚሱ ሠራተኛ ሰብሰብ እያለ ስለ ትናንት ማታ ድራማ፣ ወይ ስለ ቅዳሜው የማንቼ ሽንፈት፣ ወይ ስለ እሁዱ የእንትናዬ ሰርግ ወሬውን የሚሰልቅበት----ዲሲፕሊን የሚሏት ነገር ገደል ብትገባ አይደል እንዴ!
“ይሄ ሁሉ ሰው እዚህ ግሮሰሪ ውስጥ ምን ይሠራል?”
“እያየኸው አይደል እንዴ፣ ይጠጣላ!”
“የሥራ ሰዓት እኮ ነው!”
“ይሄም ሥራ ነው፡፡”
የዘንድሮ ነገራችን የሥራ ሰዓት መጠጣችንን “ይሄም ሥራ ነው፣” የሚያሰኝ አይነት ነው፡፡
“ትርፍ ጊዜህን በምንድነው የምታሳልፈው?”
“ቢሮዬ…”
“ማለቴ…በትርፍ ጊዜህም ትሠራለህ?”
“እናማ የቢሮ ሰዓቴ ትርፍ ሰዓቴ ነው፡፡”
ይህ ምልልስ አልተደረገ ይሆናል፤ ቢደረግም ግን አይገርምም፡፡ “ማን አለኝ ከልካይ፣ ዓለሜን ባይ…” ተብሎ እንደተፈለገው የሚኮንበት ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
ለነገሩ በየቦታው ለሥራ የማያመቹ ሁኔታዎች እየበዙ ነው ይባላል፡፡ ሰዎች ሥራ የሚቀጠሩባቸው መስፈርቶች እየጠበቡ፣ እየጠበቡ ችሎታና ብቁነት ቀዳሚ መስፈርቶች ያልሆኑባቸው ስፍራዎች ብዙ ናቸው የሚል ነገር አለ፡፡
አዲሱ የሂሳብ ሠራተኛ፤ “የመሥሪያ ቤቱን ወርሀዊ የሂሳብ እንቅስቃሴ በምን ያህል ፍጥነት ይሠራዋል ሳይሆን የመሥሪያ ቤቱን ዕለታዊ ሹክሹከታ በምን ያህል ፍጥነት ለአለቆቹ ያደርሳል” አይነት እየሆነ ይመስላል፡፡
ችሎታ?…የምን ችሎታ!  ችሎታ የሚያስፈልገው ለኳስ ነው፡፡ ለአለቆች (ለበላይ አካላት ማለትም ይቻላል) ታማኝ መሆን ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እናላችሁ ---- ግለኝነት በዝቷል፡፡ ሌላውን ማገልገል፣ ለሌላው ደግ ማሰብ፣ በጎ መሥራት የመሳሰሉ ነገሮች እየቀነሱ ይመስላል፡፡ ኑሯችን፤ “ሰው ለሰው መድሀኒቱ ነው” ከሚለው ይልቅ “ስለ ሰው፣ ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው” አይነት ሆኗል፡፡ በየቦታው የሚገባንን፣ የከፈልንበትን፣ መብታችን የሆነውን አገልግሎት የማናገኘው፣ የ“ቀድጄ ልልበሰው…” ነገር ስለሰፈረብን ሳይሆን አይቀርም፡፡
“እየበላኸው ያለው ከረሜላ የሚጣፍጥ ይመስላል”
“አዎ፣ ይጣፍጣል!”
“ምራቄን አመጣብኝ እኮ!”
መሀረብ አውጥቶ ይሰጠዋል፡፡
“ምን ሊያደርግልኝ ነው?”
“አፍህን ጥረግበት” አለውና አረፈው፡፡ ዘንድሮ አብረን እንብላ ብሎ ነገር ወይም ማካፈል ብሎ ነገር ቀርቷል፡፡ በዚህም ስንት ዘመን ጠንክረው የኖሩ ወዳጅነቶች እየፈረሱ ነው፡፡ “ምንም የምድር ኃይል አይለያያቸውም” የተባሉ ጥምረቶች፣ ሀምሳ ትናንሽ እየሆኑ ነው፡፡
ይህቺ አጋጣሚ በአንድ አገናኝታን
የፍቅርን ሸማ ደርባ አጎናጽፋን
ሆኖም ሳናስበው ጊዜው በመሆኑ
በቃን ተለያየን፣ መሪር ነው ሀዘኑ
እየተባለ ይዘፈን ነበር፡፡ አዎ፤ እንዲህ ሲሆን ያሳዝናል፡፡ ዘንድሮ “መሪር ነው ሀዘኑ” ብሎ ነገር የለም፡፡
 “እና እሱ ቀረና መንግሥተ ሰማያት መግባት ሊቀርብኝ ነው!”
“ጥርግ ትበላ፣ ደግሞ ሞልቶ ለተረፈ ሴት!” አይነት ሆኗል፡፡
“ጥርግ ትበላ!” ምናምን የሚሏትን ነገር ካነሳን አይቀር…በቀደም አንዱ ከተሜ፣ ከሴት ጓደኛው ተጣልቶ… “ዋ! ኋላ ባቡር ጎማ ስር እንዳልገባልሽ!” ምናምን አይት ነገር ይላት ነበረ አሉ፣ ያውም ሰው እየሰማው፡፡ እሷ በጎን እያየችው፣ ከት ብላ ትስቅ ነበር አሉ… “በአንተ ቤት እኔን ማታለለህ ነው!” አይነት ሳቅ፡፡ በነገራችን ላይ…“የምልሽን እምቢ ካልሽ ከአርባ አምስተኛው ፎቅ እዘልልሻለሁ…” ብሎ የሚያስፈራራ በጣም ብልጥ ነው፡፡
“አይደለም መዝለል፣ ለእኔ ስትል ለምን አሞራ አትሆንም!”
“ተይ፣ ይቆጭሻል!”
“አንተ ስለዘለልክ ነው የሚቆጨኝ?”
“ተይ በኋላ ጸጸት ይሆንብሻል!”
ከአንጀቱ ከሆነ የሌለ አርባ ስምንተኛ ፎቅ ላይ ምን አንጠለጠለው! እሱ ቃሉን በተግባር እንዲያውል መካከለኛ ገቢዋን ደርሰንባት ልናልፋት ይገባል ማለት ነው… ያውም ያኔ ፎቃችን አርባ የሚሉት ቁጥር ከገባ፡፡
እና… በየሥራ ቦታው፣ በየመዝናኛው፣ በየመኖሪያ መንደሩ ---- ግለኝነት የሚሉት ነገር ባይጠፋ እንኳን ቀንሶ ይበልጡን እርስ በእርስ የምንተሳሰብበት ጊዜ ተመልሶ ይመጣ ይሆን? ብለን መጨነቃችን ወደን አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር (ልድገመውና… ‘ሁሉም ነገር’) ግራ እየገባን ስለሆነ ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5502 times