Sunday, 29 October 2017 00:00

የዋና ዳይሬክተሩ ወቀሳ - በመንግስትና በግል ሚዲያዎች ላይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

• የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ግጭት በሚያባብሱ ዘገባዎች ተወቅሰዋል
• ሚዲያዎች የህዝብን የመረጃ ጥማትና ፍላጎት እያረኩ አይደለም
• ለህብረተሰቡ የዜና ምንጭ እየሆነ ያለው ማህበራዊ ሚዲያ ነው

  የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም፣ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከመንግስትና ከግል የሚዲያ ተቋማት ከተውጣጡ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ የፈጀ ውይይት፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ፈጽመዋል ያሉትን የሥነምግባር ጥሰቶች በመጥቀስ ትችትና ወቀሳ የሰነዘሩ ሲሆን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው አቤቱታዎችና ቅሬታዎችም ምላሽ  ሰጥተዋል፡፡  
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን የሙያ ሥነ ምግባር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የመንግስትን ጨምሮ አብዛኞቹ ሚዲያዎች ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የሚንዱ፣ ግጭትን የሚያባብሱና የፀጥታ ሃይሉን የሚያንኳስሱ መረጃዎችን በማሰራጨት አደገኛ አዝማሚያ ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ ከሚፈጽሟቸው የሥነምግባር ጥሰቶች እንዲታቀቡ ባለሥልጣኑ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በደብዳቤ ማሰራጨቱን ጠቅሰውም ከአንዳንድ መሻሻሎች በስተቀር ግን የሚጠበቀውን ያህል ተስፋ የሚሰጥ ለውጥ አለመምጣቱን አቶ ዘርአይ ገልጸዋል፡፡   
ብሮድካስት ባለሥልጣን በሚዲያዎቹ ዘገባ ላይ የአንድ ዓመት ክትትል (ሞኒተሪንግ) ማድረጉን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ክትትልም የጥላቻ ንግግሮችና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ሃሳቦች ሀይ ባይ በሌለበት ሁኔታ ሲንሸራሸሩ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል ብለዋል፡፡ የፌደራል ሥርአቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችም በስፋት ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡   
ጥርጣሬ የሚፈጥሩና ግጭት የሚያባብሱ ዘገባዎች በበርካታ የመንግስትና በጥቂት የግል ሚዲያዎች ላይ መስተዋሉን የጠቀሱት አቶ ዘርአይ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ህገ መንግስታዊ መረጃ የማግኘት መብቱን ተነፍጓል ብለዋል፡፡ ሚዲያዎቹ በፌስቡክ የሚሰራጩ መረጃዎችን እንኳ አጣርቶ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ የማቅረብ ችግር አለባቸው ሲሉ የወቀሱት ዳይሬክተሩ፤አንዳንድ የመንግስት ሚዲያዎች ከመንግስት ፍቃድ ሲያገኙ ብቻ የሚሰሩና ሳያገኙ ሲቀሩ እውነታውን በቸልታ የሚያልፉ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡   
ከሰሞኑ አፀያፊ በሆነ መልኩ በሚዲያዎቹ መካከል የእርስ በእርስ ጤናማ ያልሆነ ፉክክር የወለደው የመከላከልና የማጥቃት እርምጃዎችና አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ “ሚዲያዎች ህግ ይከበር ነው ማለት ያለባቸው እንጂ የቡድኖች ቅሬታ አስተናጋጅና አራጋቢ መሆን አይገባቸውም” ብለዋል፤ኃላፊው፡፡  
ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው ለህዝቡ አስተማማኝ መረጃ ለሚሰጡ ሚዲያዎች ባለስልጣኑ አስፈላጊውን ከለላ ያደርጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ስህተታቸውን ተረድተው ይቅርታ ለሚጠይቁ ሚዲያዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኢንዱስትሪው እንዲቀጥሉ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ጠቁመው፤ ዝም ብለው ለመቀጠል የሚፈልጉ ካሉ ግን ለሚወሰድባቸው እርምጃ ሃላፊነቱን ራሳቸው ሚዲያዎቹ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በሚዲያዎቹ ላይ የሰነዘሩትን ወቀሳና ትችት ተከትሎ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማትን ወክለው የተገኙ ጋዜጠኞች፤ በቀረቡ ትችቶችና ወቀሳዎች ላይ ተመስርተው  ቅሬታ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡   
የኢቢሲ ጋዜጠኛ የተለያዩ ጥያቄዎችን ለዳይሬክተሩ ያቀረበ ሲሆን የሚዲያ ካውንስል አለመኖሩን በማንሳት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሚቋቋሙ የሚዲያ ካውንስሎች የሚሰጠውን ድጋፍ ጠይቋል፡፡ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል በተባሉ ሚዲያዎች ላይ ምን ዓይነት እርምጃ ይወሰዳል የሚል ጥያቄም አቅርቧል - ጋዜጠኛው፡፡  
በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ፤ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በኦሮሚያ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ጠንካራ ትችትና ወቀሳ የቀረበበት የዛሚ 90.7 ኤፍኤም ሬዲዮ  ጋዜጠኛ በበኩሉ፤”በመንግስት ኃላፊዎች ጭምር በጣቢያችን ላይ የስም ማጥፋ ዘመቻ ሲካሄድ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ለምን ዝምታን መረጠ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝሯል፡፡ የሚዲያ ተቋማቸው በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰበር ዜናዎችንና ዘገባዎችን እንደሚያቀርብ የጠቆሙት የኢኤንኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች፤ ”ከሰሞኑ ወደ ብሄር ግጭት ያመራ ግጭት መፈጠሩን በመዘገባችን ጣቢያችን በኦሮሚያ ባለስልጣናት ያለ አግባብ ተብጠልጥሏል፤ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮም፣ ጣቢያውን ወቅሰዋል፣ ይሄ ተገቢ ነው ወይ? ሌሎች ሚዲያዎችም ጣቢያውን አጀንዳ አድርገው ዘገባ እስከመስራት ደርሰዋል፤ የሰራነው ዜና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ መግለጫ እስኪሰጡበት የሚያደርስ የከፋ ነበር?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡  
በብሮድካስተሮች ላይ እስካሁን ከማሳሰቢያና ከማስጠንቀቂያ ያለፈ እርምጃ አለመወሰዱን የጠቆሙት የብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ፤ እርምጃ ያልተወሰደውም የግጭትና የጥርጣሬ ዘገባዎቹ ምንጭ ራሱ ብሮድካስተሩ ባለመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ “ምንጩ ሳይደርቅና ሳይስተካከል በብሮድካስት ጣቢያዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ብዙም ትርጉም የለውም” ሲሉም አክለዋል፡፡  
“እኛ የምንፈልገው አህያውን ፈርቶ ዳውላውን መምታት ሳይሆን አህያው ተመትቶ ቀጥሎ ዳውላው እንዲመታ ነው” ያሉት አቶ ዘርአይ፤ ሁለተኛው የባለስልጣኑ መለሳለስ መነሻው የብሮድካስት ሚዲያው ገና ታዳጊ የመሆኑ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡  
የሚዲያ ካውንስል ጉዳይም ድጋፍ የምንሰጠው ቢሆንም እስካሁን በሁለት እግሩ መቆም አልቻለም፤ የዚህ ምክንያቱ በብሮድካስተሮች መካከል ያለው አለመግባባትና የህግ ጉዳዮች መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘርአይ፤ በኛ በኩል ካውንስሉን ለማጠናከር ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
“የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ኢኤንኤንን በተመለከተ የሰጡት አስተያየት፣ የመንግስት አቋም ሳይሆን የግል አስተያየት ነው የሚል እምነት አለኝ” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ”ትክክል ይሁንም አይሁን የሚኒስትሩን አስተያየት አከብራለሁ፤ ይሁን እንጂ ማንኛውም ሚዲያ በሚያጠፋበት ጊዜ መቼ፣ በማን እና እንዴት እንደሚቀጣ የተቀመጠ ህግ አለ፤ይህ ሥልጣን የተሰጠውም ለብሮድካስት ባለስልጣንና ለፍ/ቤት ነው፤ ከእነዚህ ውጪ ሚዲያ የመቅጣት ስልጣን ያለው አካል የለም” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ሚዲያዎች በመረጃ አደራረሳቸው ከማህበራዊ ሚዲያው በታች የሆነ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በተለይ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን አዲሱ ትውልድ እየተከታተላቸው አይደለም፣ የመረጃ ምንጩን ማህበራዊ ሚዲያዎችን አድርጓል ብለዋል፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙኃኑም በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ “ቋንጣ” የሆነ መረጃ ይዞ ከመውጣት ባለፈ ለህብረተሰቡ ፈጣን መረጃ የማድረስ ሚናቸውን እየተወጡ አለመሆኑ ለሀገሪቱም አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
“ጫንጮና ገብረ ጉራቻ ላይ የተፈፀመውን ድርጊት የሀገሪቱ ህዝብ የሰማው ከኢቢሲ ወይም ከፋና አይደለም” ያሉት አቶ ዘርአይ፤ “በዚህ ምክንያት የውጭ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች የህብረተሰቡ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ እየሆኑ ነው” ብለዋል፡፡
በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ በተፈጠረው ግጭት የሞተው ሰው፣ የወደመው ንብረትና የተፈናቀሉ ዜጎች ምን ያህል እንደሆኑ ለህብረተሰቡ በትክክል መረጃ ያቀበለ ሚዲያ የለም የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “በተለይ በግጭቱ ምን ያህል ሰው እንደሞተ ለምንድን ነው የሚደበቀው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሚዲያዎች የህዝብን የመረጃ ጥማትና ፍላጎት እያረኩ አይደለም ሲሉ በተደጋጋሚ ትችት የሰነዘሩት አቶ ዘርአይ፤ በተለይ ነጋዴዎች ኢንቨስተሮችም ሆኑ ተንቀሳቃሽ ዜጎች የቱ ጋ ግጭት እንዳለና እንደሌለ፣ መኪኖች የት አካባቢ እየተቃጠሉ እንደሆነ ከሚዲያዎች መረጃ ቢያገኙ ኖሮ፣ የእንቅስቃሴ ውሳኔ ለመወሰን ይጠቅማቸው ነበር፤ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በፍጥነት መዘገባቸው ለመንግስትም ይጠቅመዋል ብለዋል፡፡
መረጃ ኃይል ነው፣ ህይወት የሚመራበት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ ቀውስ ባለበት ሁኔታ ሚዲያው ከመንግስት መረጃ ባያገኝ እንኳ ራሱ የገባበት ገብቶ ለህዝቡ መረጃ ማድረስ አለበት ብለዋል - በኢራቅ ሞስል ውስጥ ጋዜጠኞች በግጭት መሃል እየገቡ የሚያቀርቡትን ዘገባ በመጥቀስ።        

Read 1897 times