Saturday, 28 October 2017 09:45

ኢህአዴግና ሰንደቅ አላማ!

Written by  አያሌው አስረሰ
Rate this item
(2 votes)

   ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም “አስረኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን” በሀገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል። በነገራችን ላይ  ይህ ቀን የምርጫ 97 ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በብዛት መገንባት፣ የመንገዶች መሠራትና ሌላውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሁሉ ምርጫ 97፣ በመንግሥት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ በረከት ነው::
በእርግጥ ምርጫ 97፣ በረከት ብቻ ሳይሆን መርገምትም አፍርቷል፡፡ በኢህአዴግ ላይ የፈጠረው መደናገጥ፣ መንግስትን ቁጡና አራስ ነብር ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ  መንግሥት “ሥልጣኔን የሚጋፋ በየት በኩል ይመጣ ይሆን?” ብሎ ዙሪያ ገባውን በጥርጣሬ የሚያይ፣ ትንሽም ቢሆን ሚና አለው ብሎ የሚያስበውን ነገር ሁሉ ለማጥፋት ያለመታከት የሚዘምት፣ ያተርፈኛል ብሎ በሚያስበው ጉዳይም አይኑን ሳያሽ የሚራመድ  ኃይል ሆኗል፡፡
ዘመናዊና የተደራጀ የበጎ አድራጎት ባህል በአገራችን አለመኖሩን መንግሥት ያውቃል፡፡ ለምርጫ 97 ሕዝቡን በማዘጋጀት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የተገነዘበው መንግሥት፤ ከውጭ አገር በሚገኝ እርዳታ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሰብአዊና ዲሞክራሲ መብቶች ላይ እንዳይሰሩ ከለከለ፡፡ የአገር ጉዳይ ያገሬው ነው አለ፡፡ በሰብአዊ መብት ላይ እንዲሰሩ የተፈቀደላቸው አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ደግሞ የገቢያቸውን 90 በመቶ ከሀገር ውስጥ ማግኘት እንዳለባቸው በአዋጅ ቁጥር 621/2001 ደነገገ፡፡ ይህን ያህል የገንዘብ ምንጭ ከአገር ውስጥ ማግኘት ያልቻሉት አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች፤ በድህነት ምክንያት ከመስመር ወጥተው እንዲቀሩ ተደረገ፡፡ በሌላ አባባል ሕዝብ ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ፣ የመማሪያና የማወቂያ መንገዱን መንግሥት እያወቀ ዘጋው፡፡ ለራሱ ደግሞ የአውራ ፓርቲነት መንገዱን ጠረገ፡፡
በኢሕአዴግ ዘመን፣ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን እንደ ደርግ ዘመን ሁሉ በመንግሥት እጅ፣ በጥብቅ ቁጥጥር ቢቀጥሉም፣ የግል ፕሬስ ተፈቅዶ፣ በርካታ የግል መጽሔትና ጋዜጦች ለመቋቋም በመቻላቸው፣ ከመንግሥት ውጪ ያለውን ሃሳብ ወደ ሕዝብ በማድረስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ የ97ቱን ምርጫ ‹‹ፍጹም ዲሞከራሲያዊ›› አደርገዋለሁ ያለው መንግሥት፤ ከተቃዋሚዎች ጋር በመድረክ ክርክር  ገጠመ። ክርከሩ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ አደረገ፡፡ በክርክሩ በሃሳብ ማሸነፍ ያልቻለው ኢሕዴአግ፤ በተለይ በአዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ ተሸነፈ፡፡‹ “ቀይ ካርድ” ተሰጠው፡፡ በምርጫው ማግስት በእጁ ያለውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ወደ ነበረበት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲመለስ ከማድረጉ በላይም እጅግ በርካታ የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ከህትመት ውጭ አደረጋቸው፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጫው መንገድ ተቆለፈ፡፡
ሕዝብ ቅሬታውን ለመንግሥት የሚያሰማበት፣ ተቃውሞውን የሚገልጥበት አንዱ መንገድ ሰለማዊ ሰልፍ ነው፡፡ ምርጫ 97 በመንግሥት ላይ በፈጠረው ሥጋት፤ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ የሚጠይቁ ክፍሎች የሚሰጣቸው መልስ “አይቻልም” ወይም ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ ማለፍ ነው፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ አላማና ግብ፤ ችግርን በአደባባይ ለመንግሥትና ለሕዝብ መግለጥ፣ በሕዝብ ዐይን መግባት  ሆኖ እያለ፣ ሕዝብ እምብዛም በማይታይበቸው አካባቢዎች እንዲሰለፉ እስከማድረግ ድረስ መንግሥት አመረረ፡፡
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!)፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንግሥትና ለኢሕአዴግ ‹‹ቀይ ካርድ›› የሰጠበት ምርጫ ነው ያሉት ምርጫ 97፤ ተገልብጦ ሕዝብ ከመንግሥት ቀይ ካርድ ተቀብሎበት አረፈ፡፡ ዛሬ የሚያወዛግቡን፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ልብ ሰቅዘው የያዙ ችግሮች ሁሉ የጀመሩት ያኔ ነው፡፡ የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይም የሚነሳው ከዚያው ነው።
አዲስ አድማስ በመስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም ዕትሙ፤ ‹‹ሰንደቅ አላማና አገራዊ መግባባት›› በሚል ርዕስ፤ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የአራት ፖለቲከኞችን አስተያየት አቅርቧል፡፡ እኔ እንደተረዳሁት፤ አራቱም ማለትም፡- አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም፣ አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ፣ አቶ ልደቱ አያሌውና ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በሁለት ነገሮች ይስማማሉ፡፡ አንደኛው በሰንደቅ አላማው ላይ የሚነሱ ክርክሮች፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ አለመስከን ያስከተለው ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር የሕዝብና የመንግሥት መገለጫ ከመሆኑ አንጻር  መደማመጥ እንደሚገባ ገልጸል፡፡
አቶ ገብሩ፤ በሰንደቅ አላማ ጉዳይ የሚነሱ ክርክሮችን  “ጨቋኝ ሥርዓት እንዲመለስ ድብቅ ፍላጎት ያላቸው” ከሚሏቸው ጋር ያገናኙታል። መንግሥት የመጨቆኛ መሣሪያ ነው የሚለውን ሃሳብ ይዘን “ኢሕዴግ ተራማጅ ነኝ” ስለሚል፣ ደርግ ደግሞ  የለየለት ወታደራዊ አገዛዝ ስለነበር፤ አቶ ገብሩ ጨቋኝ ሥርዓት የሚሉት ባላባታዊውን የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ንጉሡ፣ ንጉሠ ነገሥት ቢባሉም ከእነ ንጉሥ ሚካኤል በኋላ በሥርዓቱ ውስጥ ንጉሦች አልነበሩም፡፡ መጨረሻ  ላይ የነበሩት ምንም ጦር ያልነበራቸው እምሩና ራስ መንገሻ ስዩም ነበሩ፡፡ ዘራቸውን ከመሳፍንቱ የሚስቡ ቢኖሩም ተከታይ የሌላቸው መለመላቸውን የቆሙ ነበሩ፡፡ ደርግን ለመቋቋም የረባ ሙከራ ማድረግ ያልቻለ ሥርዓት፤ ዛሬ ከአርባ አመታት በኋላ ሥጋት ይሆናል የሚለውን አቶ ገብሩ ቢተውት ይበጃል፡፡ የሚያሠጋው ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ሰብአዊ መብት፣ ስለ እኩልነት እየተናገረ ያለው  መንግሥት፤ እንደ ቃሉ አለመራመዱ ነው። የሚያሠጋው ጥያቄዬ ካልተመለሰልኝ የሚለው፣ በፓርቲና በግንባር የተሰባሰበው፣ የተደራጀውና መሣሪያ የያዘው ኃይል ነው፡፡
የፈዴራላዊ መንግሥት ሥርዓት ጉዳይም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ደርግ በመጨረሻ ዘመኑ፣ “ራስ ገዝ” እያለ ለተወሰኑ አካባቢዎች የውስጥ አስተዳደር ነጻነት ይሰጥ የነበረው ጥብቅ የማዕከላዊ መንግሥት አመራር፤ ጊዜው ያለፈበት መሆኑን ስለተረዳ ነው፡፡ ውይይቱም ሆነ ክርክሩ  ያለው፣ ኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት አስተዳደር ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም ሳይሆን የፈደራሉ አባል መንግሥታት የአስተዳደር ክልል፣ በዘር ላይ መመሥረት አለበት ወይስ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ የሚል  መሆኑን ከእኔ ይልቅ አቶ ገብሩ እንደሚያወቁ  እገነዘባለሁ፡፡ ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የለባቸውም የሚል ወገን ያለ አይመስለኝም፡፡ ተቃውሞ ያለውና መቃወምም የሚገባው፣ ከክልሉ ውጭ ያለ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፣ እንደ መጤ የመቁጠሩና የማስተዳደሩ ጉዳይ  ነው፡፡
የነበረውን እንዳለ መውሰድ ወይም በነባሩ ላይ አዲስ ሃሳብ መጨመር የተለመደ አሠራር ነው። መንግሥት የወሰደው የሰንደቅ አላማ ትርጉም፤ በንጉሡም በደርግም የነበረ ነው፡፡ አቶ አስገደ የኮሚኒስት መንፈስ የያዘ ነው ያሉት ኮከብ፤ ዛሬ ዋጋው ከፍ ብሏል፡፡ በመኮንኖቻችን ትከሻ ላይ የሥልጣን ማመልከቻ ሆኖ ያገለገለና እያገለገለም ያለ ነው፡፡ ለእኔ፤ ሕዝብ ለመቀበል የሚከብደው አይመስለኝም፡፡
በአዋጅ ቁጥር 654/2001 ብቸኛና ሕጋዊ የሆነውን የኢትዮጵያን  ሰንደቅ አላማ፤ አቶ ልደቱ ያወቁት አልመሰለኝም፡፡ አውቀውት ቢሆን ኖሮ “የሰንደቅ አላማው መሠረታዊ ቀለማት አልተቀየሩም” ሊሉ አይችሉም ነበር፡፡ ከላይ በጠቀስኩት አዋጅ፣ ብቸኛና ሕጋዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፡- አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ብቻ ሳይሆን በክብ ያረፈ ሰማያዊ ቀለምም  የያዘ ነው፡፡ ይህ ክብ ሰማያዊ ቀለም ደግሞ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የአንድነትና የሃይማኖቶች እኩልነት ምልክት የሆነውን ባለ አምስት ጫፍ ኮከብና ከእርሱ የሚፈልቁትን ጨረሮች ለማሳየት የሚውል የሰንደቅ አላማው አንድ አካል የሆነ ቀለም ነው፡፡ አለመድነውም፤ ብንናገረውም ትክክለኛ ስዕል አይሰጠንም ይሆናል እንጂ፣ ዛሬ በአገልግሎት ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፡- አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይና ሰማያዊ  ቀለም ነው፡፡
ከአንድ አመት በፊት ስለ ሰንደቅ አላማ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) መግለጫ የሰጡት እነ አምባሰደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የተናገሩትም ይህንኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፈዴራል ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት የጸደቀው ነሐሴ 1987 ነው፡፡ እስከ አሁንም የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 3፣ ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለትን ተግባራዊ ለማድረግ አራት አዋጆች ወጥተዋል፡፡ አራተኛው አዋጅ በየአመቱ መስከረም ሁለተኛ ሳምንት የሚከበረውን የሰንደቅ አላማ ቀን ወደ ጥቅምት የመጀመሪያ ሰኞ የወሰደ ነው፡፡
የመጀመሪያው አዋጅ ቁጥር 16/1988፤ የኢትየጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ ወደ ታች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መሆኑንና በሰማያዊ መደብ ላይ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን አንድነትና የሃይማኖቶችን እኩልነት የሚያሳየውን አርማ በመጨመር፣ በስዕል አስደግፎ ያሳያል፡፡ ቀጥሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 48/1989 ቀደም ሲል በጠቀሰኩት አዋጅ የተገለጡትን ጉዳዮች፣ በመጠበቅና ክብ ሰማያዊው ቀለም አሁን ያለውን ቦታ እንዲይዝ በማድረግ፣ ከሰንደቅ አላማው መጠን ጋር መሔድ ስላለበት ሰንደቅ (መስቀያ) ይዘረዝራል፡፡ ሁለቱም አዋጆች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2፤ “የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል፡፡ ከሰንደቅ አላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ አርማ፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በዕኩልነትና ባንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል” በማለት የገለጸውን በትክከል በተግባር ያሳዩ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም፤ ስለ  ሰንደቅ አላማና ብሔራዊ አርማ ሲሠራበት የቆየውንም አሠራር፤ ያከበሩና የተከተሉም  መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡
ነሐሴ 2001 ዓ.ም የሰንደቅ አላማ አዋጆችን ቁጥር 16/1988 እና ቁጥር 48/1989 የሚሽር፣ አዲስ  የሰንደቅ አላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001  ወጣ፡፡ ይህ አዋጅ እራሱ መንግሥት ተቀበሎ ሲሠራበት በቆየው በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማና በአርማው መካከል ለአስራ አራት አመታት ተጠብቆ የቆየውን ግንኙነት አፍርሶ፣ ሰንደቅ አላማውና አርማውን የማይነጣጠሉ ያደረጋቸው አዋጅ ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረትም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማ ሕገ ወጥ ከመሆኑ በላይ፣ መጠቀምም የሚያስቀጣ  ሆነ። ውዝገቡም ከዚህ ጀመረ፡፡
ሰንደቅ አላማውንና አርማውን የማይነጣጠሉ፣ አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማ ሕገ ወጥ መሆኑንና ሕጉን መጣስ እስከ አንድ አመት ከስድስት ወር የሚደርስ ቅጣት የሚደነግገው አዋጅ ቁጥር 654/2001 ከመጽደቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡
አረንጓዴ ብጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማ፤ በሕዝብ ውስጥ የሰረጸ፣ ከአገርና ከነጻነት እንጂ ከመንግሥት ጋር የማያገናኘው፣ እናቶች፣ አባቶች፣ እህቶችና ወንድሞች በልዩ ልዩ መንገድ እያጌጡበት ያለ ነው፡፡ ሕዝብ በቀላሉ ሊያዘጋጀው የሚችል ነው፡፡ አርማውንና ሰንደቁን የማይነጣጠሉ ብሎ ማወጅ፣ ሕዝብ ይህን መብቱን እንዲያጣ ያደርጋል፡፡ የወታደር ክፍሎች ሰንደቅ አላማው ላይ አርማቸውን በማተም ክፍለ ጦራቸውን  ሲያስተዋውቁ ኖረዋል፡፡ ይህንንም እድል ያሳጣል በማለት፣ እኔም ሌሎችም ሃሳባችንን አቅርበን ነበር፤ ግን ሰሚ  አልተገኘም፡፡
ስነ ውበታዊ (ኤስቴቲክ) ለሆነ ሥራ አለመመቸቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንን ታሪክ መጥቀስ ይበቃል፡፡ ኢቢሲ ስሙን እንደለወጠ ሰሞን በሕጉ መሠረት፣ ሰንደቅ አላማውንና አርማውን እያገናኘ፣ በልዩ ልዩ አቀማመጥ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጎ አልሆነለትም። በመጨረሻ አሁን በሚጠቀምበት ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማ መደብ ላይ ኢቢሲን በመጻፍ፣ ኢትዮጵያዊነቱን እያሳወቀ ይገኛል፡፡
የውዝገቡ መነሻ መንግሥት ለምን አርማ ይኖረዋል ወይም አርማ ያለው ሰንደቅ አላማ በየመሥሪያ ቤቱ ይሰቅላል፤ ስለ ምንስ ወደ ሕዝብ ይገባል ሳይሆን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ  ሰንደቅ አላማ ለምን ሕገ ወጥ ይደረጋል ነው፡፡
አቶ አማኑኤል አብርሃም፤ በተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር፤ “ሰንደቅ አላማን በተመለከተ ጉድለቶችና እጥረቶች ካሉ እንዲፈቱ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ነው” ማለታቸውን አድማስ በዚሁ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ጎሽ፤ መንግሥት ሕገ ወጥ ያደረገውን ሕጋዊ  ቢያደርግ ውዝግቡም ያበቃ ነበር፡፡

Read 2171 times