Sunday, 29 October 2017 00:00

መንግስት፤ አቶ አባዱላ በሃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ይፈልጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(20 votes)

· የባለሥልጣናት በገዛ ፍቃድ ከሥራ መልቀቅ መለመድ አለበት ተባለ
· አቶ በረከት ስምኦን፤ የመልቀቂያ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል

የመንግስት ባለሥልጣናት በገዛ ፍቃዳቸው ከስራ መልቀቃቸው ዲሞክራሲዊ በመሆኑ መለመድ አለበት ያሉት ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ፤ በቅርቡ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ያስገቡት የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አቶ በረከት ስምኦን፣ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመው፣ የአቶ አባዱላ ገመዳ ተመሳሳይ ጥያቄ ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የስራ መልቀቂያ ያቀረቡት ሁለቱ የመንግስት ባለስልጣናት ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንደሆኑና በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፣ ባለሥልጣናቱ በታላቅ አክብሮትና ምስጋና ሊሸኙ ይገባል ብለዋል፡፡
በማስታወቂያ ሚኒስትርነትና  በመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትርነት፣በኋላም የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ እንዲሁም በፖሊሲ ጥናቶች ምርምር ተቋም በም/ዳይሬክተርነት  የሰሩት አቶ በረከት ስምኦን፤በተደጋጋሚ የመልቀቂያ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ጠ/ሚኒስትሩ ገልጸዋል። “ሆኖም ጥያቄያቸውን ባለመቀበል በትግሉ እንዲቀጥሉ እየተደረገ እዚህ ተደርሷል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ጥያቄያቸው  ተደጋግሞ  የቀረበ  በመሆኑና አሁን መልቀቅ እፈልጋለሁ በማለታቸው፣ድርጅቱ በከፍተኛ ምስጋና፣ ጥያቄያቸውን ተቀብሎታል” ብለዋል፡፡ አቶ በረከት ሥራቸውን በይፋ ይልቀቁ እንጂ ወደፊትም ኢህአዴግንና መንግስትን በመደገፍ አስተዋፅኦቸውን እንደሚቀጥሉ እምነት አለኝ ብለዋል -ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  
በሌላ በኩል የመከላከያ ሚኒስትር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የመልቀቂያ ጥያቄ ሲያቀርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በጥያቄያቸው ላይ ከራሳቸው ጋር ውይይት መጀመሩንና አለመጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ “አቶ አባዱላ በጎ ፍቃዳቸው ሆኖ በሃላፊነታቸው ቢቀጥሉ ደስተኞች ነን፤ ነገር ግን በውይይቱ የእሳቸውን ፍላጎት አጢነን፣ በአቋማቸው የሚፀኑ ከሆነ መልቀቂያቸውን እንሰጣቸዋለን” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
“ድርጅታችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ የአመራሮች መተካካት ውስጥ ያለፈ ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በባለስልጣናቱ መልቀቅ ድርጅታችን ስጋት ውስጥ የሚያስገባው ነገር አይኖርም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
“የመንግስት ባለሥልጣናት በፈቃዳቸው ከስራ ሲለቁ እንደ አዲስ ነገር መቆጠር የለበትም፤ ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ ሊለመድ ይገባዋል” በማለት አሰገንዝበዋል- ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ ጉባኤውን የመሩት ም/አፈጉባኤ ሽታዬ ምናለ ነበሩ። 547 አባላት ባሉት የኢትዮጵያ ፓርላማ፤ ባለፈው ሐሙስ የተገኙት 370 አባላት ብቻ ናቸው፡፡  

Read 9585 times