Sunday, 29 October 2017 00:00

በአምቦ በተነሳ ግጭት 10 ሰዎች ሲሞቱ፤ 20 ቆስለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

“የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል” - የከተማዋ አስተዳደር ቃል አቀባይ
· የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎች ተቃውሟቸውን የመግለፅ መብታቸው እንዲከበር ጠየቀ


ከትላንት በስቲያ በአምቦ የተቀሰቀሰ ተቃውሞን ተከትሎ በተነሳ ግጭት፤ የ10 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 20 የሚሆኑ መቁሰላቸውን የአምቦ ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡ በፅኑ የቆሰሉ ሰዎች መኖራቸውን በመጥቀስም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል - ኃላፊው፡፡
ሰዎች የሞቱትና የቆሰሉት የመከላከያ ሰራዊት በወሰደውን እርምጃ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው፤ ይሄን ተከትሎም በቁጣ የተነሳሱ ተቃዋሚዎች የዳንጎቴ ሲሚንቶ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የጭነት መኪኖች ማቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡   
ሐሙስ ከማለዳ ጀምሮ በከተማዋ ዋና ጎዳናዎች ላይ የተሽከርካሪ መተላለፊያ መንገዶችን በድንጋይና በእንጨት በመዘጋጋት፣ ወጣቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ የፌደራል መንግስቱን የሚያወግዙና “ነፃነት እንፈልጋለን” የሚሉ መፈክሮች ይስተጋቡ ነበር ብለዋል፡፡ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ገደማ ላይ ግን የተኩስ እሩምታ መሰማቱንና ወዲያው አምቡላንሶች የተጎዱ ሰዎችን ወደ ጤና ተቋማት ማመላለስ መጀመራቸውን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡   
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት፣ በከተማዋ በተነሳው ግጭት፣ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን አስታውቋል - ቁጥራቸውን ባያረጋግጥም፡፡ በግጭቱ በርካታ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን የተናገሩት ምንጮች፤ እስከ አመሻሽ ድረስ የተኩስ ድምፅ ከየአቅጣጫው ይሰማ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ “ከማለዳው አንስቶ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ነበር፤ የመንግስት መ/ቤቶች ተዘግተው ነው የዋሉት ተማሪዎችም ወደ ት/ቤት አልገቡም” ብለዋል - ምንጮች፡፡  
የግጭቱ መነሻ ስኳር የጫኑ ተሽከርካሪዎች የአምቦ ከተማን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት ወጣቶች መንገድ በመዝጋት፣ ተሽከርካሪዎቹ እንዳይንቀሳቀሱ በማገዳቸው መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ እገዳው ማክሰኞ ጥቅምት 14 መጀመሩን ይናገራሉ፡፡ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ ”በከተማዋ አንድ ኪሎ ስኳር በ70 ብር እየተሸጠ እኛ ተቸግረን፣ እንዴት ወደ ሌላ ቦታ ይጓጓዛል” በሚል ተቃውሞ መነሳቱንና ወጣቶች ስኳር የጫኑትን ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዳቸው ለግጭቱ መነሻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በአምቦና በወሊሶ እንዲሁም በአካባቢው ባሉ አነስተኛ ከተሞች እስከ ትናንት (አርብ) ድረስ ውጥረት ነግሶ መሰንበቱንና የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላትም በተሽከርካሪዎች ቅኝት ሲያደርጉ መታየታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ አንድ ዲፕሎማት፤ “ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልነው ነው፤ ያጋጠመው ነገር አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ዜጎች ወደ አምቦ መስመር በሚያደርጓቸው ጉዞዎችም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኤምባሲው አሳስቧል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲው ጉዳዩን አስመልክቶ ባሰራጨው መግለጫው፤ በአምቦ “እጅግ የሚረብሽ ግድያዎች መፈፀማቸውን ጠቁሞ አሁንም ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞአቸውን የማሰማት መብታቸው የመከበሩ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ግጭቶች መፍትሄ የሚያገኙት ዜጎች በነፃነት ሃሳባቸውን ሲገልፁ ነው” ብሏል፡፡

Read 4025 times