Saturday, 21 October 2017 13:58

የኢትዮጵያ ቡና ሳምንት ኤግዚቢሽን” በየዓመቱ ሊዘጋጅ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 ኢትዮጵያ የቡና መገኛነቷን ብቻ ሳይሆን ተያያዥ እሴቶች ባለቤት እንደሆነችና ከቡና ምርቷ ያልተናነሰ ገቢ የምታገኝበት የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት፤ “ኢትዮጵያን ኮፊ ዊክ ኤግዚቢሽን” በየካቲት ወር በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ “ግሪን ፓዝ ኢቨንትስ” አስታወቀ፡፡
የድርጅቱ ዳይሬክተር ወይዘሪት ቤዛዊት ጠንክርና የሥራ ባልደረቦቻቸው ባለፈው ረቡዕ በሒልተን ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከተለያዩ መንገስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር፣ በሀገሪቱ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የተለየ፣ በየዓመቱ በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች በቀጣይም በአፍሪካ አገራት “የኢትዮጵያ ቡና ሳምንት ኤግዚቢሽን” ለማዘጋጀት ማቀዳቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓላማውንም ሲገልጹ፤ የተለየ ትውፊታዊ ውጤት ያላቸውን የአገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች ቡና አፈላልና በሂደቱ ያሉት እውቀቶች፤ ዶክመንት በማድረግ፣ ባህላችንን በተለያዩ መንገዶች ለዓለም ማስተዋወቅ፣ በኤግዚቢሽኑ ለመሳተፍ የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር ማብዛት፤ በቡና ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ከውጭ አገር ቡና ገዢዎች ጋር የሚገናኙበትን ዕድል መፍጠርና አገሪቷ የተሻለ ገቢ እንድታገኝ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡  “በውጭ አገር የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት አይታወቅም፤ ቡናውን ከሱቅ ገዝቶ እቤት ወስዶ አፍልቶ መጠጣት ነው” ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ቡና ከመጠጥነቱ ባለፈ፤ እዚህ በየብሔር ብሔረሰቡ ቡና ከመቆላቱ በፊት ሲታጠብ፣ የቡናው ጪሱ አካባቢውን ሲያውድ የሚሰጠውን መዓዛ፣ እጣኑ ሲንቦለቦል፣ ስኒው ቀርቦ፣ ቁርሱ ተቆልቶ፣ ጎረቤት ተጠርቶ በጋራ ሲጠጣ ቡና የተለየ ማኅበራዊ እሴት እንዳለው በማሳየት ዓለምን እናስደንቃለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ የመጀመሪያውን “Ethiopian Coffee Exbiation” በየካቲት ወር በሚሊኒየም አዳራሽ ለማካሄድ እየተዘጋጀ ሲሆን በአውደ ርዕዩ ላይ ለመሳተፍ ከ70 በላይ የውጭ አገራት ቡና ገዢዎችና አከፋፋዮች፤ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ከ180 በላይ ቡና አምራቾች፣ ላኪዎችና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አካላት ምርቶቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡ፤ ብሔር ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ባህልና የቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓት፣ ቡናውን የሚያፈሉበትን ቁሳቁስ በባህላቸው መሠረት ይዘው እንደሚቀርቡ፤… አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ያሉ የጎዳና ቡና አፍይ ሴቶች እንደሚወዳደሩና አሸናፊ የሚሆኑት 200 ሴቶች ዘላቂ የሆነ ማበረታቻ ሽልማት ያገኛሉ ያሉት ወ/ሪት ቤዛዊት፤ ከዚህም በተጨማሪ በቡና ማፍላት ላይ በተሰማሩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መካከል ዘመናዊ የቡና አፈላል ውድድር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

Read 1578 times