Saturday, 21 October 2017 13:56

“አያ በሬ ሆይ፤ ሳር ሳሩን ዓይተህ ገደሉን ሳታይ”

Written by  ሳምሶን ጌታቸው ተ/ሥላሴ
Rate this item
(4 votes)

 የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ውሳኔ
                  
     በሀገራችን አንዳንድ ምሁራንና በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ በጉልህ ከሚታዩ፣ ከሚተቹና ብዙም መሻሻል ከማይስተዋልባቸው ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው፤ የተማሩትን ወይም በመረጃ የሰሙትን የሠለጠኑ ሀገራት ዕውቀቶችና ሕጎች፣ ያለምንም ማስተካከያ እንደ ወረዱ የመገልበጥና በሀገር ላይ የመተግበሩ ጉዳይ ነው። ለምን ያን ድርጊት እንደፈፀሙ ሲጠየቁ ምላሻቸው፣ የሠለጠኑ ሀገራትም እንዲሁ ያደርጋሉ፣ ሳይንሱም እንዲሁ ያዛል ይላሉ፡፡
ነገር ግን ሳይንስም ቢሆን የሚሰራው በጊዜና ቦታ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስና የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎችንም ልዩነትና አንድነት በሚገባ ማጤን መዘንጋት የለበትም፡፡ አሜሪካን ሀገር መኪና ለመንዳት፣ አውሮፕላን ለማብረር፣ ሕንፃ ለማቆም ወዘተ የሚያስችሉ የፊዚክስ ሕጎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥም በተመሳሳይ ያገለግላሉ፡፡ የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች ናቸውና፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሜሪካ ውስጥ የተተገበረን የፖለቲካ ሥርዓት፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የታክስ ሕግጋት፣ የፌደራሊዝም አወቃቀርና የመሳሰሉትን የማኅበራዊ ሳይንስ ዕውቀት ውጤቶች፣ እንደ ተፈጥሮ ሳይንስ ቀመሮች ያለ ምንም ማስተካከያ፣ ሙሉ ለሙሉ ሸምድዶ መገልበጥና መተግበር ለብዙ ችግሮች ሲዳርግ ይስተዋላል፡፡
በእርግጥ ግሎባላይዜሽን አመጣሹ ብርቱ የሀገራት ትስስርና የበለፀጉ ሀገራት የዕውቀት ብየና ተፅዕኖ፣ እነኚሁኑ የማሕበረሰብ ሳይንሶች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በእነሱ አተረጓጎም መሠረት፣ የተፈጥሮ ሳይንስ እውነታ እስኪመስሉ ድረስ ወጥ መግባቢያዎች እንዲሆኑ እየተደረገ ይገኛል፡፡
የኢኮኖሚክስ ሕጎችና መርህዎች የተፈጥሮ ሳይንስ እውነቶች አይደሉም፡፡ በሰው ልጆች ማህበራዊ እንቅስቃሴ እውነታ ላይ ተመሥርተው በሳይንስ የዳበሩ፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የዕውቀት ውጤቶች ወይም ስምምነቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚክስ ሕጎችና መርህዎች የሚያገለግሉት በተጨባጭ በሚገኝ ሀብት ላይ ሲሆን ዋናው ዓላማቸውም በሰው ልጆች እጅና በተፈጥሮ የሚገኝን ሐብት በአመራረቱም ሆነ በአጠቃቀሙ ውጤታማና የተሻለ በሆነ መንገድ ግልጋሎት ላይ እንዲውል ማስቻል ነው። በአጠቃላይ የሳይንስ ዘርፍ እንደመሆናቸው መጠን፤ ግባቸው ኑሮን ምቹና ቀላል ማድረግ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚያዊ  ፖሊሲ ርምጃዎችና ማበረታቻዎች ደግሞ  ለኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴዎች ውጤት የሚያስገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ እንጂ በራሳቸው ምርትን ሊያመርቱ ወይም ሊያሳድጉ አይችሉም፡፡
በዚህም መሠረት ብንወስድ፣ “የወጪ ንግድ እንዲጨምርና የገቢ ንግድ እንዲቀንስ የአንድን ሀገር ገንዘብ ዋጋ ተመን አሽቆልቁሎ መወሰን (devaluation) ይጠቅማል” የሚለው የኢኮኖሚክስ ንድፈ ኃሣብ ተግባራዊ የሚሆነው፣ ሊላክ የሚቻል ምርት በበቂ ሁኔታ ሲኖር እና ከውጭ የሚገባውን ሸቀጥ ማስቀረት የሚያስችል ተተኪ ምርት በሀገር ውስጥ በበቂ ሲኖር ብቻ ነው፡፡
ለምሳሌ፦ አሁን ባለው የሀገሪቱ ሁኔታ የስኳር ምርትን ወጪ ንግድ ለማሳደግ ተብሎ ለላኪዎች የፈለገው ዓይነት ማበረታቻ ይደረጋል ቢባል፤ ጉዳዩ ከቧልትነት ያለፈ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ትርጉም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ምርቱ የለማ። ስለዚህ ከማበረታቻው በፊት ምርቱ መበርታት አለበት ነው ነገሩ፡፡ በተጓዳኝም የገቢ ንግድን ለማስቀረት ወይም ለማሳነስ የሚባለው ሃሳብም ውሃ የሚያነሳው፤ የገቢውን ምርት መተካት የሚያስችል ተመሳሳይ ወይም ተለዋጭ ምርት ሲኖር ነው። ለምሳሌ፦ ሀገሪቱ ውስጥ በበቂ ሁኔታ በሀገር ውስጥ የተመረተ የኑግ ዘይት እያለ፣ ሕዝቡ ከውጭ ለሚመጣ የሱፍ ዘይት በአንዳች ምክንያት ቅድሚያ ፍላጎት ቢያሳይ፣ ይኼን ሁኔታ በፖሊሲ አማካይነት አለማበረታታትና መቀነስ ብሎም ማስቀረት ይቻላል፡፡ በሰበቡም የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አልፎ የሀገር ውስጡን ዘይት አምራቾች ያበረታታል። ነገር ግን ያለበቂ ምርት የሚደረግ የገንዘብ ምጣኔን የማዳከም ተግባር፣ ለከፋ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትና ውጥንቅጥ ይዳርጋል እንጂ አዎንታዊ ውጤት አያስገኝም፡፡
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ የተመሠረተው በገቢ ንግድ ላይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ትክክል እና ጠቃሚ እንዳልሆነ ቢታወቅም፤ በአንድ ጀንበር፣ በአዋጅና በመፈከር አከል መመሪያ ማስተካከል አይቻልም። በወጪ ንግድ ማነስና በገቢ ንግድ መብዛት ምክንያት የተፈጠረውን የንግድ ሚዛን መዛባት ለማስተካከል የሚደረግ እርምጃና ጥረት ላይ እየተጉ፣ ከተንሰራፋው የገቢ ንግድ ዘርፍ በተሻለ ለመጠቀም መሞከር ይበልጥ ተገቢም ጠቃሚም ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ሀገሪቱ የቱንም ያህል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ብታደርግ በደም ስሯ ውስጥ ተሰራጭቶ በሚገኘው የከፋ ድህነት ምክንያት ውጤታማነቱ በፍፁም የማይታሰብ ነው። ስለሆነም ከላይ በተጠቃቀሱት ምክንያቶችና በሌሎችም ነጥቦች፣ የብርን ዋጋ ተመን ከነበረበት በ15% አዳክሞ የመተመኑን ጉዳይ አዎንታዊ ውጤት ያመጣል ብሎ መጠበቅ ያዳግታል ወይም አይቻልም፡፡ በባንኮች ላይም የተደረገው ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ማሻሻያ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ግሽበት የመቋቋሙና ውጤታማ የመሆኑ ነገር በብዙ መልኩ ያለመሳካት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
የዚሁ የብርን እሴት አሽቆልቁሎ የመተመን ውሳኔ ለሀገራችን አዲስና የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ በፊት በተደረጉ ጊዜያት ሁሉ የአሁኖቹ ተጠባቂ ውጤቶች በምክንያትነት መጠቀሳቸው አልቀረም፡፡ ነገር ግን «በዚሁ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ ምክንያት ሳይንሱ በሚለው መጠን፣ የመጣ ተጠቃሽ አዎንታዊ ለውጥና ሀገራችን ያገኘችው ጥቅም ነበር ወይ?» የሚለውን ጥያቄ መመለስ፤ አሁን የተደረገው የእሽቁልቁሊት ትመናና ያስገኛል የተባለው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ቁልጭ ያለ ምስል ይሰጣል፡፡  
ታዲያ ለምን አሁን የሀገሪቱ የኢኮኖሚዋም፣ የፖለቲካዋም ሁኔታ በአሳሳቢ ደረጃ ውጥንቅጡ በወጣበት ሰዓት ጭራሽ ይህን አባባሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መተግበር አስፈለገ? ጉዳዩ ወዲህ ነው። መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አላላውስ ቢለውም፣ የብርን መጠን አውርዶ መተመኑ የከፋ የዋጋ ንረት ከማስከተሉ በዘለለ አዎንታዊ ለውጥ እንደማያመጣ አይጠፋውም። ምክንያቱም ወደ ውጭ ሊነገድ ቀርቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገሩን ሕዝብ ፍላጎት እንኳ የሚያረካ የምርት ዕጥረት ችግር ላይ ነው፡፡
ነገር ግን መንግሥት ይህን በገሃድ የሚታየውን እውነታ በመካድና ለዚህም በብዙ መፈክርና ፕሮፓጋንዳ፣ ያውም የእውነት መልክ እንዲይዙ ታስቦ፤ በኦፊሴል ደረጃ በተዘጋጁ ሰነዶች ለተከታታይ ዓመታት ተደጋጋሚ ዕድገት ማስመዝገቡን ሲያውጅና ሲያሳውጅ ኖሯል። ታዲያ ይኼንኑ ጉዳይ ለቀም እያደረጉ የሚሰንዱ፣ በብድሩም በዕርዳታውም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ዓለም ዓቀፍ ኃያል ተቋማት አሉ፡፡ እንደ ዓለም ባንክና ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ተቋም ያሉ፡፡ ያውም «ኧረ ብታድግም ትንሽ አጋነኸዋል» እያሉ የሚመክሩ፡፡ ችግሩ መንግሥት እንዲህ በተባለ ጊዜ ሁሉ ቱግ ይላል፡፡ «ዕድገቴን የማውቀው እኔ ነኝ እናንተ» እያለ ይቀውጠዋል፡፡ እሺ ይሁንልህ አይነት መልስ ይሰጡታል፡፡ ይሄኔ ነው እንግዲህ «አያ በሬ ሆይ... አያ በሬ ሆይ፣ ሳር ሳሩን ዓይተህ ገደሉን ሳታይ» ማለት፡፡
እናም እነኚሁ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋማት ባላቸው የአበዳሪነት፣ የገንዘብ ምንጭነትና ተቆጣጣሪነት ሚና ምክንያት ለዓመታት ባለ ሁለት አኃዝ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ እያለ ሲናገር የኖረ መንግሥት፤ አላላውስ ያለ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጋጠመኝ ሲል ሲሰሙ፣ በቃ ጉዳዩንም ስሌቱንም ከነበራቸው ሰነድ ምርመራ ይጀምራሉ። መፍትሔአቸውም ሳይንሳዊ ሲሆን መነሻቸውም በእጃቸው የሚገኙ ሰነዶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ምን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ... በቃ የተትረፈረፈ ምርት እያለ፣ የወጪ ንግዱ የተቀዛቀዘው ላኪ ነጋዴዎች የሀገር ውስጥ ምርት የመግዣ ዋጋ ውድ ሆኖባቸው ነው። በዚህም በዓለም ዓቀፍ ገበያ መወዳደር አዳግቷቸዋል የሚል ይሆናል፡፡ ስለዚህ መፍትሔው በአነስተኛ ዋጋ ገዝተው በተሻለ እንዲሸጡና የውጭ ምንዛሬ እንዲያመጡ፣ የብርን የምንዛሬ ዋጋ ተመን አሽቆልቁሎ መወሰን አስፈላጊ ነው ብለው ይወስናሉ፡፡
እንዲህ ያለው የብር የመግዛትን አቅም አሽቆልቁሎ የመተመን ውሣኔ ሲወስን፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለሀገሪቱ ፈተና እንደሚሆንባትም ሆነ ከፍተኛ የሆነ የምርት እጥረት እንዳለም ጠፍቷቸው አይደለም። ነገር ግን መንግሥት በየጊዜው ከእነዚሁ ተቋማት ጋር «በሁለት ዲጅት አድጌያለው እመኑኝ» የሚላትን ሪፖርት የዚች ጊዜ ይመዟታል፡፡
«በል ባስመዘገብከው ዕድገትና ምርትህን በጨመርከው መሠረት፤ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ያጋጠመህ የወጪ ንግድህ ስላላደገ ነው። እሱም እንዲያድግልህ የብርን የመግዛት አቅም አሽቆልቁለህ ተምን፡፡» ይላሉ፡፡ በቃ ወዲህ ቢሉ ወዲያ ቢሉ ማምለጫ የለም፡፡ በራስ ወጥመድ ተተብትቦ ቁጭ፡፡ ያሳዝናል፡፡

Read 2778 times