Saturday, 21 October 2017 13:49

የ”8ኛው አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” ምሽት ምን ይመስላል?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 • ”ዝነኛ ሆነን ከምንቀር ተጣጥረን ጀግና ለመሆን እንሞክር” ቻቺ ታደሰ
      • “ለቴዲ ሽልማቱ ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም” ታደለ ሮባ
          
    ላለፉት 7 ዓመታት በስምንት የኪነ-ጥበብ ዘርፎች፣ በአድማጮች ምርጫ መሰረት ለአሸናፊዎች ሲበረክት ቆይቷል - “አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ”፡፡ ዘንድሮም ለስምንተኛ ጊዜ ባለፈው ሰኞ ምሽት በሀርመኒ ሆቴል በተሰናዳ ደማቅ ስነ-ስርዓት፣ ከየዘርፉ ያሸነፉ ተወዳዳሪዎች ተሸልመዋል፡፡
በዛሚ 90.7 ኤፍኤም የሚተላለፈው “አዲስ ሚዩዚክ” አቅራቢና የሽልማት ድርጅቱ መሥራች ዲጄ ቤቢ (ይግረም ስንታየሁ) እንደተናገረው፤ የዘንድሮውን “አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” የተለየ የሚያደርገው ተሸላሚዎች በዛሚ አድማጮች ብቻ ሳይሆን በጄቲቪ ተመልካቾችም ጭምር የተመረጡ በመሆናቸው ነው፡፡
የሽልማት ሥነሥርዓቱ ከቀኑ 11፡30 ላይ ነበር እንደሚጀመር የተጠበቀው፡፡ ሆኖም ከእልህ አስጨራሽ ጥበቃ በኋላ ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ላይ ተጀምሯል፡፡ በሀርመኒ አዳራሽ ጢም ብሎ የሞላው ታዳሚ፤ ያንን ሁሉ ሰዓት ተቀምጦ፣ የሽልማት ሥነሥርዓቱን በመከታተሉ፣ ላሳየው ትዕግስት ሽልማት ይገባው ነበር፡፡  
የሽልማቱ አዘጋጅ ዲጄ ቤቢ፤ በየፕሮግራሙ የተለመደውን “በሰዓቱ ባለመጀመራችን ይቅርታ እንጠይቃለን” የሚል ተማፅኖና አጭር የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረገ በኋላ መድረኩን ድምፃዊና ተዋናይ መሳይ ተፈራ ካሣ ተረክቦ፣ “አሰብኩት” የተሰኘውን ተወዳጅ ዜማውን በማቅረብ ታዳሚውን አነቃቅቷል - በዛጎል ባንድ አጃቢነት፡፡
በመቀጠል ቀጥታ የተገባው ወደ ሽልማት ሥነ ስርዓቱ ሲሆን የመጀመሪያው የሽልማት ዘርፍ፣  የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ነበር። በዚህ ዘርፍ ዳዊት ዓለማየሁ በ“ሀላ ምኔ”፣ ጌትሽ ማሞ በ “ተቀበል”፣ ፅላት ገዝሙ በ“ይለይልኝ”፣ ማይኪ ሸዋ በ“አብይ አሎ” እና ብስራት ሱራፌል በ“ይሄው ሰውየው” የታጩ ሲሆን ፅላት ገዝሙ አሸናፊ ሆናለች፡፡ ሽልማቷንም ባለፈው ዓመት በ”አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” በበርካታ ዘርፎች አሸናፊ ከነበረው ድምፃዊ ሳሚ ዳን እጅ ተቀብላለች፡፡
በምርጥ ሴት ተዋናይት ዘርፍ ደግሞ ሰላም ተስፋዬ በ“ቤዛ”፣ ፀጋነሽ በሀይሉ በ“የእግዜር ድልድይ”፣ እድለወርቅ ጣሰው በ“እንደ እናት”፣ አምለሰት ሙጨ በ”ላብ ጦስ” እና ዘሪቱ ከበደ በ“ታዛ” ፊልሞች እጩ ሆነው፣ እድለወርቅ ጣሰው አሸንፋለች፡፡ በምሽቱ ተዋናይቷ ባትገኝም ተወካይዋ ሽልማቱን ከአንጋፋዋ ድምጻዊትና ሞዴል ቻቺ ታደሰ እጅ ተቀብላለች፡፡
ቻቺ ወደ መድረክ ስትወጣ ከፍተኛ የአድናቆት ጭብጨባ የተቸራት ሲሆን ሁሉም ታዳሚ ከመቀመጫው ተነስቶ አክብሮቱን ገልጾላታል፡፡ ለተደረገላት አቀባበልና ክብር ምስጋና ያቀረበችው ቻቺ፤ “About heros and celebrities” የተሰኘ አጭር የእንግሊዝኛ ፅሁፍ ያቀረበች ሲሆን በጽሁፉም የጀግንነትና የታዋቂነትን ልዩነት አብራርታለች። “እኛ ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂውና የሀብቱ ሁኔታ ባያግዘንም ከማንም የማናንስ ቆንጆዎች፣ ብርቱዎች፣ ጀግኖችና ተወዳጆች ነን” ያለችው ቻቺ፤ “በምንሰራው ስራ ሁሉ ታዋቂ ሆነን ከምንቀር፣ጥረን ተጣጥረን ጀግና ለመሆን እንሞክር” የሚል መልዕክቷ ተወዶላታል፡፡  
በምርጥ የሙዚቃ አቀናባሪ ዘርፍ ዳኜ ደጀኔ፣ ጊልዶ ካሳ፣ ታምሩ አማረ፣ አቤል ጳውሎስና ቢኒ ባና በእጩነት የቀረቡ ሲሆን አሸናፊውም የታዋቂው አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ታናሽ ወንድም ጊልዶ ካሳ ሆኗል፡፡ ሽልማቱንም  ከጋዜጠኛና የፊልም ባለሙያ ብርሃኔ ንጉሴ እጅ  ወስዷል፡፡
በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ አስገኘሁ አሽኮ (አስጌ ዳንዳሾ) በ “ባሌ ሮቤ” ፣ ብስራት ሱራፌል በ”አንቺን ነው”፣ ጌትሽ ማሞ በ“ተቀበል”፣ መሳይ ተፈራ ካሳ በ “ብርቄነሽ” እና ይርዳው ጤናው በ “ሰራችልኝ” ነጠላ ዜማዎቻቸው ታጭተው፣ “ዳንዳሾ” በተሰኘው ዘፈኑ አድናቆትን ያተረፈው አስገኘሁ አሽኮ አሸንፏል። ሽልማቱንም ከፊልም ደራሲና ዳይሬክተር አንተነህ ሀይሌ እጅ የተቀበለ ሲሆን በማሸነፉ ምን እንደተሰማው ተጠይቆ ሲመልስ፤ “የደቡብ ዘፋኝ ሆኖ እዚህ መድረስና መሸለም ትልቅ ስኬት ነው፤ ዛሬ እዚህ ልደርስ አባቴ በርሃብ መሞቱ ያሳዝነኛል፤ አሁን በእኔና በፈጣሪ እርዳታ የምትኖር እናት አለችኝ” በማለት እንባ እየተናነቀው ተናግሯል፡፡
በዓመቱ ምርጥ የወንድ ተዋናይ ዘርፍ ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) በ“እንደቀልድ”፣ ካሳሁን ፍስሃ (ማንዴላ) በ“ማያ”፣ ሄኖክ ወንድሙ በ“የእግዜር ድልድይ”፣ ግሩም ኤርሚያስ በ “79” እና አለምሰገድ ተስፋዬ በ“እንደናት” ፊልሞች እጩዎች የነበሩ ሲሆን ሄኖክ ወንድሙ አሸንፎ፣ ከሀበሻ ዊክሊ ፕሮሞሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዶኒክ ወርቁ እጅ ሽልማት ወስዷል፡፡ በዓመቱ ምርጥ አዲስ ድምፃዊ ዘርፍ ደግሞ ሰብለ ታደሰ፣ ብስራት ሱራፌል፣ ፍሬህይወት ሀ/ሚካኤል፣ ዳዊት አለማየሁ እና ሚኪያስ ከበደ እጩዎች የነበሩ ሲሆን “ወጣ ፍቅር” በተሰኘው ነጠላ ዜማው እውቅናን ያተረፈው ብስራት ሱራፌል፣ አሸናፊ ሆኖ ከእውቋ የቀድሞው ራስ ቴአትር አርቲስት አስቴር ከበደ እጅ ሽልማቱን ወስዷል፡፡ ከመድረክ ከመውረዱ በፊት ባደረገው አጭር ንግግርም፤ “ይህ ሽልማት አባቴን ሱራፌል አበበን ጨምሮ ለጥበብ ራሳቸውንና ህይወታቸውን ለሰጡት ሞገስ ተካ፣ ፀጋዬ ደቦጭና ለሌሎችም የኪነ-ጥበብ ሰዎች ይሁንልኝ” ብሏል፡፡ ድምፃዊት አስቴር ከበደ በበኩሏ፤ ”ለራስ ቴአትሩ የጥበብ ጓደኛዬ ለሱራፌል አበበ ልጅ፣ ይህን ሽልማት በመስጠቴ በጣም አስደስቶኛል” ብላለች፡፡
የዓመቱ ምርጥ ፊልም በሚለው ዘርፍ ከታጩት አምስት ፊልሞች መካከል “የእግዜር ድልድይ” አሸናፊ ሆኖ የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር አንተነህ ሀይሌ፤ ከገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
የዓመቱ ምርጥ የኪነ - ጥበብ ባለውለታ በሚለው ዘርፍ፣ ከ1 ሺህ በላይ ለሆኑ ድምፃውያን የዘፈን ግጥም በመስጠት የሚታወቁት አንጋፋው የጥበብ ሰው ግሩም ሀይሌ ተሸላሚ ሆነው፣ “ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት” የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ሲስተር አሳዬች ወርቁ እጅ ሽልማታቸውን ወስደዋል፡፡ አንጋፋው ግሩም ሀይሌ ባደረጉት አጭር ንግግር፤ ”ወጣት አርቲስቶች አገራችን ያላትን ባህልና ሰፊ ጥበብ ትተን የውጭ አንኮርጅ፤ ሌሎች ከእኛ ነው መኮረጅ ያለባቸው” የሚል መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የሽልማት ድርጅቱ አስታውሶ ስለሸለማቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
የመጨረሻው የሽልማት ዘርፍ የዓመቱ ምርጥ አልበም ነበር፡፡ በዚህ ዘርፍ የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ”፣ የዳዊት አለማየሁ “ያልተሰማ”፣ የኢዮብ መኮንን “እሮጣለሁ”፣ የሚኪያስ ከበደ “ፐ” በእጩነት የተመረጡ ሲሆን የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲሱ አልበም አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሆኖም ቴዲ አፍሮ በቅርቡ ለሚያቀርበው ኮንሰርት ሀዋሳ በልምምድ ላይ በመሆኑ የቅርብ ወዳጁ ድምጻዊ ታደለ ሮባ ሽልማቱን ተቀብሎለታል። “ለቴዲ ሽልማቱ ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም” ያለው ድምጻዊው፤ ”ከእኛም ጋር ጥሩ ጓደኝነት ያለው በመሆኑ ሽልማቱን በመቀበሌ ደስተኛ ነኝ” ብሏል። 8ኛው “አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ” የተቋጨውም በቴዲ አፍሮ ዜማ ነው - “ኢትዮጵያ”፡፡ 

Read 1770 times