Saturday, 21 October 2017 13:45

“መንገደኛ”ን መጽሐፍ እኔ እንዳየሁት

Written by  ከነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

 ስደትና መስዋዕትነት ፈትልና ቀሰም ናቸው”
                 
     (ካለፈው ሳምንት የቀጠለ)
ስደት፣ ባህልና ኢትዮጵያዊ ሥነልቦና
“መንገደኛ” የባህልን እሴቶች በተዘዋዋሪ ያፀኸያል። በመፅሐፉ ምዕራፍ አንድ ሥር ስለመናፈቅ የተጠቀሰውን ለአስረጅነት እንይ። ተናጋሪው ከአስር ዓመት በላይ ወደ አገሩ ሳይመለስ የቆየ፣ በደቡብ አፍሪቃ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ ነው፥ «…የሚያምርህ ነገር ብታጣ ለቅሶ ቤት መሄድ ያምርሃል እንዴ!? የሆነ ልጅ ‘አባቱ ሞቱ’ ተብለህ ሄደህ አይተኸው የምትመጣው ነገር …ለቅሶ ይናፍቅሃል! ሰው ሲያለቅስ፣ ሰው አብሮ ንፍሮ ሲበላ፣ ሰው ድንኳን ለመጣል ሲረባረብና ከልቡ ሲተባበር ማየት፣ …አንድ ለቅሶ ሊደርስ የመጣ ሰው የፈለገ ሳይጨነቅ ቢመጣም ለቅሶ ቤት ሲገባ ግን የለቅሶ ቤቱ ድባብ ተሸናፊ ሆኖ አብሮ ሲያዝንና ሲያጽናና መንፈሱ ያስታውቃል። እንደዛ ዓይነት መንፈስና እውነተኛ የለቅሶ ቤት ድባብ ይናፍቃል። እዚህ ያለው የውሸት ነው።»
እኛ አበሾች እንደ ባህል እንግዳ እንቀበላለን!! ያን እንግዳ በአገሩም አንፈራውም። ይሄ ነገር ከወኔ ይምጣ፣ ከአፈጣጠራችን ይምጣ፣ ከአድዋ ይምጣ፣ አይታወቅም። ቀጣዮቹን አንቀጾች መመርመር ነው። እነሆ፥ «…የነጮች ሆቴል ውስጥ ገብቶ መዝናናቱን ተወውና የጥቁሮች ሆቴል ውስጥ እኛ ከጥቁሮች ጋር እየደነስን፣ አንድ ነጭ ወደ ውስጥ ሲገባ ጥቁሮቹ ዳንሳቸውን አቋርጠው ጥግ ጥግ ይይዛሉ። ኢትዮጵያዊ ዳንሱን ሳያቋርጥ ዳሌውን ሲወዘውዝ፣ ጥቁሮቹ ጥግ ላይ ሆነው ‘አይፈሩም እንዴ?!’ በሚል ግርምት ያያሉ። ልክ ነጩ ከዛች ቤት እግሩ እንደወጣ፣ ጥግ ይዘው የነበሩት ሁሉ ተንደርድረው ዳንሱን ያጦፉታል። የታመቀው ዳንስ ይወጣል። እንደ ጉድ ይውረገረጋሉ። ከዛ በኋላ አንተን ነው የሚጠሉህ። ካንተ ጋር ጸብ ማድረግ ይዳዳቸዋል - ምክንያቱም አንተ አልፈራህም!»
ሌላኛዋ ቀደምት ሴት ኢትዮጵያዊት ስደተኛ ደግሞ እንዲህ ትላለች፥ «…ነጮቹ ጥቁሮቹን እንደ ውሻ ሲያባርሯቸውና ማታ አሥራ ሁለት ሰዓት ሲሆን ደወል እየተደወለ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ሲያደርጓቸው ሳይ ሀገራችን ባለመገዛቷ እግዚአብሔርን አመስግኜዋለሁ። በዚህ ደግሞ ሁልጊዜም ነው ሳመሰግነው የምኖረው፡፡ በመድሀኒዓለም እርዳታ እንዳንገዛ ለታገሉና ነጻ ላደረጉን አባቶቻችንም ትልቅ ክብር እንድሰጥ አድርጎኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለመገዛታችንን ጥቅም የምናየው ካገራችን ስንወጣ ነው። ሳናውቀውም ቢሆን በውስጣችን የሆነ ጥሩ ነገር ትቶልናል።»
በተቃራኒው ደግሞ ስደተኞቹ መንገድ ላይ በሚያሳልፉት እንዲሁም ደቡብ አፍሪቃ ከደረሱ በኋላ በሚገጥማቸው የህይወት ውጣ ውረድ፣ የባህላቸው አካል ሲሸረሸር ይስተዋላል። ስደትና ባህል ሲጋጩ ራስን ያሸጡና የሚከተለውን ስዕል ይስላሉ፥ «…በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ከተማዋ ውስጥ እየቆየሁ ስሄድ፣ ጆሃንስበርግ ውስጥ የማያቸውና የምታዘባቸው አንዳንድ ነገሮች እያምታቱኝ ይሄዱ ጀመር። ጓደኝነት፣ መከባበር፣ መተማመን፣ መረዳዳት፣ ወንድማማችነትና መሰል ማህበራዊ እሴቶች ተጠራርገው የት እንደገቡ ጠፋኝ። ማንም ማንንም አያምንም፣ ማንም ማንንም ከልቡ አይወድም፣ ማንም ማንንም ሲያከብር አይታይም። በከተማው በሚገኝ ብዙኃኑ የአበሻ ስደተኞች ዘንድ የሚከበረውም፣ የሚወደደውም፣ የሚታመነውም፣ የሚመለከውም ገንዘብ ነው። ገንዘብ መግዣ ብቻ ሳይሆን ገዥም ነው። ገንዘብ አገልጋይ ብቻ ሳይሆን ጌታም ነው። የብዙዎቹ መመሪያም “money talks” የሚል ሆኗል። ብዙዎቹ ገንዘቡን እያገኙት ነው። ራሳቸውን ግን እያጡት፤ አንድም በሞት ሌላም በቁም ሞት!»
ስደትና መስዋዕትነት
ስደትና መስዋዕትነት ፈትልና ቀስም ናቸው። በላብ ወዝ ራስን ማቆየትም የስደት አንዱ ገፅታ ነው። በመሃል ጆሃንስበርግ ውስጥ የምትገኘውና በተለምዶ “የኢትዮጵያውያን መንደር” እየተባለች ስለምትጠራው “ጄፒ” እና ስለተከፈለባት መስዋዕትነት በመፅሐፉ ውስጥ እንዲህ ተቀምጧል፥ «…ዛሬ ላይ በተለምዶ “የኢትዮጵያውያን መንደር” በመባል የምትታወቀው ጄፒ፤ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት ያለፈባትና የብዙ ወጣቶችን ደም ያፈሰሰች “አኬልዳማ” ናት። …ኢትዮጵያውያኑ በጄፒ የቦታ ክልል ሳይወሰኑ የንግድ አድማሳቸውን በማስፋት፣ በመላው የደቡብ አፍሪካ ከተሞችና የጎረቤት ሀገሮች ጭምር አገልግሎት ይሰጣሉ። በዚህም ሂደት ውስጥ እነዚህ ስደተኞች፣ እንደ ዲንካው እረኛ ራሳቸውን በሉላዊነት የታችኛው ጫፍ ላይ (low-end globalization) በመሰካትና የቻይና ነጋዴዎችን በማሻሸት ከዓለም ቁሳዊ ሃብት ላይ የድርሻቸውን ያልባሉ። የመግዛት አቅማቸው ከነጮቹ የሚያንሰውን ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እንዲሁም በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ የጎረቤት ሀገር ዜጎችንም ከሉላዊነት የታችኛው ጫፍ ጋር ያስተሳሥራሉ።»   
ስደት፣ ቋንቋና የሥራ ባህል
እንዲህ ባለው ቅጥ አምባሩ በጠፋበት ውጥንቅጥ ውስጥም ጭምር ነው እንግዲህ፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪቃ እየሄዱ ያሉት፡፡ ደቡብ አፍሪካ መድረስ ከጀመሩም ወደ ሃያ ዓመት የሚጠጋቸው ሲሆን ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን በሥራ ትጋታቸው ጥሩ ስም ለማትረፍ ችለዋል። በሥራ ትጋታቸውና በላባቸው በደቡብ አፍሪቃ መንግሥት እስከመመስገን ደረጃ የደረሱበት ጊዜ እንደነበር መፅሐፉ እማኝ ነው። ሆኖም የቋንቋ አለመቻል እንዲሁም ደቡብ አፍሪቃውያን ለመጤዎች ያላቸው መጥፎ አመለካከት፣ በሥራቸው ላይ ማነቆ እንደሆኑ ለመረዳት አያስቸግርም። በተለይም “ገንዘቤን አምጣ” የሚለው የጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን አነጋገር፣ “አገርህ አይደለም” የሚለውን አስተሳሰብ በቅጡ ይነግረናል።
የቋንቋ አለመቻል፣ የሥራ ትጋት እና የአመለካከት ችግር በመፅሐፉ ውስጥ ዕውነታና ገጠመኝ ሆነው ተጣጥመው የቀረቡበት መንገድ ፈገግ ያሰኛል። የሚከተሉትን አንቀጾች ይመልከቱ፥ «…በአንድ ወቅት ሌቦቹ አንድ አበሻ ይይዙና ሲፈትሹት ካልሲው ውስጥ ወደ አስር ሺህ ራንድ የሚሆን ገንዘብ ያገኛሉ። ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ሰውዬውን ሥራዬ ብለው መከታተል ጀመሩ። በሌላ ጊዜ የሰውዬውን ታናሽ ወንድም ከሰውዬው ጋር አምታትተውት፣ ዋናውን ሰውዬ ያገኙ መስሏቸው በአሳቻ ቦታ ይዘው ከመሬት ላይ ጥለው ቢፈትሹ አምስት ሳንቲም ያጡበታል። የተያዘው ሰው በቅርብ ከሀገር ቤት የመጣ ትኩስ ስደተኛ ነበርና ገንዘብ አልነበረውም። እንደ ቅርጫ በሬ ገልብጠው ቢያዩት ሰውነቱም ከሳ መልኩም ቀየር ይልባቸዋል። በዚህ ጊዜ፥
“አንተ የባለፈው እንትና አይደለህ...” ብለው ቢጠይቁት “ኧረ አይደለሁም” ብሎ የዛ ሰው ወንድም እንደሆነ ይነግራቸዋል።
አንድ ሁለቴ ካጋጩት በኋላ፤
“ሁለተኛ እንዳይለመድህ እሺ! እንደ ወንድምህ በርትተህ ሥራና ገንዘብ ያዝ!” ብለው አስጠንቅቀው ለቀቁት።
በሌላ ጊዜ ደግሞ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተነስቶ በደቡብ አፍሪቃ ገጠራማ ክፍሎች ሥራውን ሲከውን የነበረ ወጣት፣ እቃውን አድሎ ሲመለስ አንድ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ፣ ከፊት ለፊቱ ፈጠን ፈጠን እያለ በመራመድ ይጠጋውና፣ ሽጉጥ አውጥቶ፣ “Give me my fucken money” ይለዋል። ቋንቋውን በቀጥታ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ጥረት ያደረገው ኢትዮጵያዊ የገባው፣ “ገንዘቤን አምጣ” የሚል ነገር ነው። በድንጋጤና በውዥንብር ስሜት ውስጥ ሆኖ ለጥቂት ሰከንድ ያህል ሲያስብ ከቆየ በኋላ ሌባውን መልሶ፣ “…ቆይ ግን መቼ ነው ያበደርከኝ?” ይለዋል። ለድርድር ጊዜ የሌለው ወሮበላ፣ በሽጉጡ ጀርባ ጭንቅላቱን ብሎ ከጣለው በኋላ “ገንዘቡን” ይዞ ይሄዳል።»
አንዳንድ ጣዕም ያላቸው ክስተቶች በመፅሐፉ በወጉ ሰልፍ ገብተዋል። እያዋዛ የቋንቋን ፋይዳ ይጠቁመናል። «…ሲሰሩ መድከም፣ አንዳንዴም መታመም አይቀርምና አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሲወጣ ሲወርድ ብርድ ይመታዋል። ሊታከም ሆስፒታል ይሄዳል። ዶክተሩም “ምንድነው ህመምህ?” ይለዋል ይቆረጥመኛል፣ ይሰነጥቀኛል፣ ብርድ ብርድ ይለኛል እያለ የውስጡን ስሜት እንዲህ ነው ብሎ ለማስረዳት ቋንቋውን ከየት ያምጣ። ጥሩ የእንግሊዝኛ ቃላትን ተጠቅሞ የውስጡን ስሜት እንዲህ ነው ብሎ ለማስረዳት ቢያቅተውም፣ ህመሙን ያስረዳበት መንገድ ግን የወጣቱን ብልህነት የሚያሳይ ነው። የክረምትና በጋን ባህሪ ጠንቅቆ የተረዳው ይህ ወጣት፣ ሰውነቱን እየነካካ “Doctor - the problem is … inside winter; outside summer» አለ። እንግዲህ የ“ብርድ ብርድ ይለኛል” ስሜትን ከዚህ በላይ ምን ይገልጸዋል? አሽሟጣጭ ጓደኞቹ ታዲያ ወጣቱን “[እከሌ] ዊንተር” ብለው ቅጽል ስም አውጥተውለታል።»
ደራሲው የኢትዮጵያውያንን ሌላ ገፅታ ከመጠቆም አልቦዘነም። «…ኢትዮጵያውያኑ በሥራ ትጋታቸው ታውቀዋል ማለት ግን አልባሌ ሥራ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የሉም ማለት አይደለም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባቋራጭ መበልጸግ የሚፈልጉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ከሌሎች አገራት ዘራፊዎች ጋር በመተባበር፣ የስርቆት ሥራ ላይ እየተሰማሩ እንደሆነና ይህም የብዙሃኑን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስም እያጠለሸው ይገኛል፤ ይህም በፕሬዝዳንት ደረጃ ከመሞገስ ክብር ወደ በፕሬዝዳንት ደረጃ መወቀስ ዝቅጠት እያሸጋገራቸው ነው።»  
ስደትና ፖለቲካ
ስደትና ፖለቲካ ተለያይተው አለማወቃቸው በጥሩ አንድምታ ተስሏል። የስደት ፖለቲካ ከሥራና ዓለማዊ መስተጋብር አልፎ የዕምነት ተቋማት ድረስ እንደዘለቀ ደራሲው የራሱን ትዝብት እንደሚከተለው አስቀምጧል፥ «…ሆኖም “የመንግስትና” እና “የተቃዋሚ” የሚለውን ክፍፍል ስሰማ፣ “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” የሚለው ህግ መጣሱን በተደጋጋሚ እንደሚነገር ስለማውቅ አልገረመኝም። ያስገረመኝ ነገር የእነ ሂትለር ሀገር በሆነችው ጀርመን ውስጥ የኢትዮጵያና የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት አንድ ሆነው፣ አንድ ህንጻ ውስጥ እየተፈራረቁ የምስጋና ስርዓታቸውን ሲፈጽሙ፣ የእርቅ ሀገር በሆነችው የማንዴላዋ ደቡብ አፍሪቃ ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድን ቤተክርስቲያን ለሁለት ሰንጥቀው መለያየታቸው ነበር።»
ስደተኞች ፖለቲካን የመኖሪያ ፈቃድ ማግኛ ሰበብ (pretext) አድርገው እንደሚጠቀሙበት የታወቀ ነው። ደራሲው ይህን ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፥ «…የእቁብ ብር ይዞ ከሀገር የጠፋውም፣ የሴፍቲኔት ብር ይዞ የተሰወረውም፣ የባንክ ገንዘብ ይዞ ያመለጠውም፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተበድሮ የመጣውም እንዲሁም ሥልጣን ይዞ ሌሎችን ገፍቶ የሰደደው እንኳን ሳይቀር የሚሰጧቸው ምክንያቶች ተመሳሳይነት ይገርማል። ከሻሼጎ የገጠር ወረዳ ወይም ከትግራይ ገጠራማ ቦታዎች የሚነሱትም ጭራሽ እስከነመፈጠሩ የማያውቁትን ኦ.ነ.ግ ሽፋን አድርገው፣ “የኦ.ነ.ግ አባል በመሆናችን ምክንያት ገዢው ፓርቲ ቁም ስቅላችንን አሳየን … ዋይ! ለወንድሜ ገድለው እኔን እስርቤት ሊጮምሩኝ ሲሉ አምልጬ ሞጣሁ» የሚል ስሜት ያለው ኬዝ፣ የሚያቀርቡበት አጋጣሚም ነበር!»
የተስፋዋ ምድር
ዛሬ ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መሰደድ ከሞላ-ጎደል የአዘቦት ክስተት ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን ማንም ጅል የማይስተው ጉዳይ ሆኗል። ይሄ ቁምነገር ወዝ ባለው ቋንቋ “መንገደኛ” ውስጥ ሰፍሮ እናገኘዋለን። ደቡብ አፍሪካም “የተስፋዋ ምድር” ሆና ትታየናለች። መነሻችንም፣ ግባችንም እሷው ናት! እሷ ጋ ለመድረስ ዳገት-ቁልቁለቱ የትየለሌ ነው!  የቅርብ ሩቅ ናት፤ ደቡብ አፍሪቃ! ሲያገኟትም ሌላ መልክ ነው ያላት።
መንገደኞቹ መንገድ ላይ ከሚገጥማቸው ሥቃይ ባሻገር የተስፋዋን ምድር እንዴት እንደሚቀላቀሉና ከተቀላቀሉም በኋላ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳል። የመኖሪያ ፈቃድ ለማውጣት አንድ ወጣት ያለፈበትን ሂደት እንደማሳያም ያቀርባል፥ «…የደቡብ አፍሪቃው ሆም አፌይርስ አሰራራቸው እጅግ የበሸቀጠ ነው። የስደተኛው መብዛትና የግቢው መጥበብ ከሆም አፌይርስ የአሰራር ብልሹነትና ከስደተኛው ስርዓት አልበኝነት ጋር ተደምሮ፣ ፈጥሮት የነበረው ጭንቅንቅ አሁን የሆነ ያህል ይሰማኛል።
ያ ሁሉ ስደተኛ ትፍግፍግ ብሎ በዚያች ጠባብ በር በኩል ወደ ግቢው ውስጥ ለመግባት ያደርግ የነበረው ግብግብ፣ በአንዳንድ ልጆች ላይ ይታይ ከነበረው ጉጉት የወለደው ስግብግብነት እና በሌሎች ላይ ከሚነበበው ከፍራቻ የመነጨ ቀቢፀ ተስፋ ጋር ሲጣመር … በወቅቱ የነበረው አጠቃላይ ትዕይንት ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት የሚደረግ ጥረት እንጂ የመኖሪያ ፈቃድ ለማውጣት የሚደረግ ትግል አይመስልም ነበር፡፡»
የ“ተስፋዋን ምድር” የመሬት ላይ የኑሮ ተቃርኖ ለማሳየት የሚከተለው አንቀጽ በቂ ይመስለኛል፥ «…ትንንሽ አደጋዎች፣ የዕለት ተዕለት ክስተቶች ከመሆናቸው የተነሳ እንደ ተራ ነገር ከመቆጠርም አልፈው “ግዴታ” እስከመሆን ደርሰዋል። አንድ ትኩስ ስደተኛ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መጥቶ፣ ጆሃንስበርግ ላይ በዘራፊዎች ተይዞ በሚደበደብበት ወቅት፣ እዚያው መንገድ ዳር ተቀምጠው የሚነግዱ ትልልቅ ማማዎች (እናቶች) እንኳን ትእይንቱን እያዩ፣ ሥራቸውን ሳያቋርጡ ደስ በሚል ቅላጼ ድምጻቸውን ከፍና ዘለግ አድርገው ለድብደባው ማጀቢያ ሙዚቃ እንደሚሰጡ ሁሉ “S-h-a-m-e … S-h-a-m-e… S-h-a-m-e” ይላሉ እንጂ ተነስተው ለመገላገል ወይም ፖሊስ ለመጥራት አይደፍሩም። በሥነስርዓት ተደብድቦ፣ ያለውን ተቀምቶ የጨረሰው ትኩስ ስደተኛ፣ ወደ ወገኖቹ ሄዶ ብሶቱን ቢያወርደው፣ ከወገኖቹ የሚያገኘው ምላሽ “እኔን፣ …አይዞህ ወንድሜ፣ …እንዴት ተደርጎ” የሚል ቁጭትና የበቀል ድንፋታ ሳይሆን “ዌልካም ቱ ጆበርግ…!” የሚል ለበጣ ነው።»
“የእኛ ሰው በአሜሪካ”ን ስፅፍ ይህ መጽሐፍ ታትሞ ቢሆን ኖሮ፣ ትልቅ ግብዓት በሆነኝ ነበር። “የእኛ ሰው በደቡብ አፍሪቃ” ለማለት የሚቻል መጽሐፍ ነው! ይሄን መጽሐፍ እንደኔ አንብቡት። እንደኔ እርኩበት። ከዚያ ስለ መንገደኞችና ስለ ስደተኞች ሁሉ ታዝናላችሁ - እስካሁን አላዘናችሁ ከሆነ። ትገረማላችሁ - እስካሁን ያልተገረማችሁ ከሆነ። ምናልባትም፣ ‘ሌላም ያልተነገረ ታሪክ አለኮ!’ ብላችሁ መነጋገርና መጻፍ ትቀጥላላችሁ። “መንገደኛ” የመንገደኞች ታሪክ ብቻ ሳይሆን የቀሪዎቹ ሁሉ ነው። ሁላችንንም ይመለከተናል!!!
መልካም ንባብ።

Read 1481 times