Saturday, 21 October 2017 13:41

የሚስቴ ውሽማ

Written by  ድርሰት፡- አልቤርቶ ሞራቪያ ትርጉም፡- ኃይላይ ገ/እግዚአብሄር
Rate this item
(26 votes)

ነገሩ የሆነው እንደዚህ ነው፡፡ ጥዋት አንግቼ ነበር የተነሳሁት፡፡ ፊሎሜና ግን ተኝታ ነበር። ዕቃዎቼን የምሸክፍበትን ቦርሳ ይዤ ከቤቱ እየተጎተትኩ እንደሆንኩ ያህል ወጣሁና ወደ ሞንቴ ፕሪዮሊ ግራሚሺ ጎዳና አመራሁ፡፡ እዛ የምጠግነው ዕቃ ነበር። ጥገናውን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኝ ይሆን? ምናልባትም ሁለት ሰዓታት። ምክንያቱም ቧንቧውን ለመፍታትና መልሶ ለመግጠም ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ሥራዬን ከጨረስኩ በኋላ በአውቶብስ ቤቱና ሱቁ ወደሚገኝበት ወደ ኮሮነሪ ጎዳና እመለሳለሁ፡፡ ሁለት ሰዓታት በሞንቴ ፕሪዮሊ፣ ግማሽ ሰዓት ቦታውን ለማግኘት፣ ግማሽ ሰዓት ለመመለስ በድምሩ ሦስት ሰዓታት፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዓታት ምንድን ናቸው? በዛም አነሰም በሁኔታዎች መሰረት መሆን ያለበት ነው አልኩ ለራሴ፡፡ እኔ የቧንቧ ቁራጭ ለመጠገን ሦስት ሰዓት ወሰደብኝ፣ በአንፃሩ  ሌላ ሰው ቢሆን ግን…
ወደ ኮሮነሪ ጎዳና እየተመለስኩ ሳለ በግንቡ አጠገብ በችኮላ እየተራመድኩ ነበር፡፡ ከመቅፅበት ስሜ ሲጠራ ስሰማ ዞር አልኩና ከእኛ ቤት ፊት ለፊት የምትኖረውን አሮጊቷን ቤት አከራይ ፊዴን አየኋት። ይህች ምስኪን ፍጥረት ፊዴ፤ የዝሆን የሚመስል ወልጋዳ እግሮች ነበሯት፡፡ ቁና ቁና እየተነፈሰች ነበር፡፡
“ምን ዓይነት ቀፋፊ ቀን ነው! በጎዳናው ወደ ላይ እየወጣህ ነው? እስቲ ይህንን ቅርጫት እርዳኝ እባክህ” አለችኝ፡፡
ዕቃዎቼን የያዝኩበትን ሻንጣ ወደ ሌላኛው ትከሻዬ አዛወርኩትና ቅርጫቱን ተቀበልኳት፡፡ በሁለቱ ምሰሶ መሳይ እግሮቿ እንደ ቀንድ አውጣ እየተሳበች፣ ከጎኔ መራመድ ጀመረች፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንደዚህ ብላ ጠየቀችኝ፤ “ፊሎሜናስ የት ናት?”
“እቤት” ብዬ መለስኩላት፤ “ከዛ ውጭ ሌላ የት ልትሆን ትችላለች?”
“አዎ! እቤትማ በእርግጥ አይቻታለሁ” አለች ጭንቅላቷን ወደ ግራ እያጋደለች፡፡
“ለምን በእርግጥ አልሽ?” ጠየቅኳት፡፡
“አዎ በእርግጥ! ሚስኪን ልጅ” አለችኝ፡፡
ድንቅ ይለኝ ገባ፡፡ ሁኔታውን አጢኜ “እና ለምን ሚስኪን ልጅ” አልሽኝ አልኳት፡፡
“ምክንያቱማ ስላዘንኩልህ ነው” አለች አስጠሊታዋ አሮጊት ፍጥረት፤ እኔን ሳትመለከት፡፡
“ምን ማለትሽ ነው?”
“ማለቴ የአሁን ሴቶች በእኔ ጊዜ እንደነበሩ ሴቶች አይደሉም”
“ለምን?”
“ድሮ በእኛ ጊዜ አንድ ባል ሚስቱን ቤት ትቷት ሲወጣ ሲመለስም ልክ እንደ ተዋት ቤቷ ውስጥ ሆና ያገኛታል፡፡ በአሁኑ ዘመን ግን …”
“አሁን ምን?”
“አሁን እንደ ድሮው አይደለም … በአሁን ጊዜ … ደህና … ብቻ ቅርጫቴን ስጠኝ ልሂድበት፣ በጣም ነው የማመሰግንህ”
እነዚያ የጥዋት ደስታዎቼ አሁን በውስጤ ወደ መርዝነት ሲቀየሩ ተሰማኝ፡፡ ቅርጫቱን በእጄ እንደያዝኩ፡-
“የጀመርሽውን በደንብ ካላብራራሽልኝ አልሰጥሽም … ፊሎሜናን እንዴት ወደዚህ ጉዳይ ልታመጪያት ቻልሽ?” ወተወትኳት፡፡
“ምንም የማውቀው ጉዳይ የለኝም” አለች፤ “ግን ማስጠንቀቅ ማለት ማስታጠቅ ነው”
“ንገሪኝ እንጂ” ጮኽኩባት፤ “ፊሎሜና ምንድነው ያደረገችው?”
“አዳልጂሳን ጠይቃት” ብላ መለሰችልኝና ቅርጫቱን ከእጄ መንጭቃ፣ እንዴት እንደዚህ መራመድ እንደቻለች ሳይገባኝ፣ በረዥም እርምጃ ተፈተለከች፡፡
በዚህ ሰዓት ወደ ሱቅ መሄድ ምንም እርባና እንደሌለው አሰብኩና አዳልጂሳን ለመፈለግ ወሰንኩ። ደስ የሚለው እሷም የምትኖረው በኮሮናሪ ጎዳና ውስጥ ነው፡፡ ፊሎሜናን ከማግኘቴ በፊት እኔና አዳልጂሳ ለመጋባት አቅደን ነበር፡፡ ግን ሴተ ላጤ ሆና ቀረች፡፡ እናም ይህንን የፊሎሜናን ስም የማጥፋት ወሬ የፈጠረችው እሷ ናት ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ አራት ደረጃዎች ወጥቼ በጡጫ በሩን ደበደብኩት፡፡ እሷም በሩን በፍጥነት ስለከፈተችው ፊቷን ሳልመታት ለትንሽ ነበር የተረፈችው፡፡ እጅጌዎቿ ተሰብስበው በእጇ መጥረጊያ ይዛ ነበር። ጎልቶ በወጣ ድምፅ “ጂኖ! ምን ፈለግክ?” አለችኝ፡፡
አዳልጂሳ አጭር ማራኪ ሴት ነበረች፡፡ ሆኖም ትንሽ ተለቅ ያለ የእራስ ቅልና ትንሽ ሰፋ ያለ አገጭ ነበራት፡፡ በአገጯ መስፋት ምክንያት “አካፋዋ” ብለው ይጠሯታል፡፡ በእርግጥ ፊትዋ እንደዛ ሊባል የሚችል ዓይነት ነው፡፡ እኔም በጣም ተበሳጭቼ “አንቺ አካፋ! አንቺ ነሽ ፊሎሜና ልታደርገው የማትችለውን ነገር፣ እኔ ሥራ ስሄድ አደረገች ብለሽ ያስወራሽ?” አልኳት፡፡
ሁለቱ የተቆጡ ዐይኖቿን በእኔ ላይ ተከለቻቸውና፤ “አንተ የፈለከው ፊሎሜናን ነበር … እናም አሁን እሷን አግኝተሀል” አለችኝ፡፡
ተንደርድሬ ሄጄ እጇን ያዝኩት፡፡ ግን ደስ እንዳላት ስገነዘብ፣ ወዲያውኑ ለቀቅኳትና “እና አንቺ ነሽ?” አልኳት፡፡
“እኔ አይደለሁም … እኔ የሰማሁትን ነው የደገምኩት”
“እና ከማን ነው የሰማሽው ታዲያ?”
“ከጂያኒና”
ምንም ሳልናገር ወጣሁ፡፡ ሆኖም ጀርባዬን ያዘችኝና አንዳች ስሜት በሚቀሰቅስ እይታ እያየችኝ፤ “አካፋ ብለህ አትጥራኝ” አለችኝ፡፡
“ለምን? አካፋን የሚመስል ፊት የለሽምን?” ብያት፣ ራሴን ከእጇ አላቅቄ እየተጣደፍኩ ደረጃዎቹን መውረድ ጀመርኩ፡፡
“ከጥንድ ቀንዶች ይልቅ አካፋ የሚመስል አገጭ ይሻላል” ብላ ከኋላ ጮኸች፤ የቤቱን ግድግዳ እየተደገፈች፡፡
አሁን መጥፎ ስሜት ይሰማኝ ጀመር፡፡ ፊሎሜና እያታለለችኝ መሆኑ አልመስል አለኝ፡፡ ምክንያቱም ከተጋባን ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ ያላትን ፍቅር እንዳለ ትለግሰኝ ነበር፡፡ ግን እንዴት የሚያስቀና ነገር ነው፡፡ እነዚህ የፍቅር መገለጫዎች አሁን በፊዴና አዳልጂሳ ጥቆማዎች እርዳታ፣ የክህደት ማስረጃዎች ሆነው ይታዩኝ ጀመር፡፡ ደህና ደህና … ጂያኒና በዛው ጎዳና አጠገባችን በሚገኝ ቡና ቤት የምትሰራ ገንዘብ ተቀባይ ነች፡፡ ፈዛዛ ቢጫና ለስላሳ ፀጉርና የቻይናዎች የሚመስሉ ሰማያዊ ዐይኖች አሏት፡፡ ረጋ ያለች፣ አሳቢና ቁጥብ ነች፡፡
ወደ ገንዘብ መቀበያው ሄድኩና “ንገሪኝ፣ እኔ ከቤት ስወጣ ፊሎሜና ቤት ውስጥ ሰዎች ታስገባለች ብለሽ ያወራሽው አንቺ ነሽ?” አልኳት፡
አንዱን ደንበኛ እያስተናገደች ነበር፡፡ የገንዘብ ማስሊያ ማሽኑን ተጫነችና ቲኬት ስባ አወጣች። ድምፅዋን ሳትጨምር “ሁለት ቡና” ብላ አስታወቀች። ቀጥላ “ምን አልከኝ ጂኖ?” ጠየቀችኝ።
ጥያቄዬን ደገምኩላት፡፡ ከፊትዋ ለቆመው ደንበኛ መልስ ሰጠችና “ጂኖ፣ እንደዛ ዓይነት ወሬ ስለ ውድ ጓደኛዬ ፊሎሜና ራሴ ፈጥሬ አወራለሁ ብለህ በእርግጥ ታስባለህ?” መልሳ ጠየቀችኝ፡፡
“እና አዳልጂሳ አልማው መሆን አለበታ”
“አይደለም” ብላ አስተካከለችኝ፡፡ “አይደለም … እሷ አልማው አይደለም፤ እኔም አልፈጠርኩትም፤ እኔ የሰማሁትን ደገምኩት፡፡ ለራሴ ግን እኔ አላምንም ነው ያልኩት … በእርግጥ አዳልጂሳ አልነገረችህም”
“ደህና! እሺ ለአንቺስ ማን ነው የነገረሽ?”
“ቪንቸንሲና ናት ከላውንደሪው መጥታ የነገረችኝ”
ቻዎ ሳልላት እየተቻኮልኩ ወጣሁና በቀጥታ ወደ ላውንደሪው አቀናሁ፡፡ ከመንገዱ ሆኜ ከጠረጴዛ አጠገብ በሁለት እጆችዋ የካውያውን እጀታ ስትጨብጥ ከሩቅ ለየኋት፡፡ ቪንቸንሲና ትንሽ ቀጭን፣ እንደ ድመት ደፍጣጣና ደማቅ ብሩህ ፊት ያላት ሴት ነች፡፡ ለእኔ የሚጨክን ልብ እንደሌላት አውቃለሁ። እናም በጣቶቼ ስጠቁማት ወዲያውኑ ይዛው የነበረውን ካውያ ትታ ወደ ውጭ ወጣች፡፡
“ጂኖ፣ አንተን ሳይ እንዴት ደስ አለኝ መሰለህ” አለች ፍልቅልቅ ገፅታዋን እያሳየች፡፡
“አንቺ እርባና ቢስ! ፊሎሜና እኔ በሌለሁበት ሌሎች ወንዶችን እየጠራች ታስገባለች ብለሽ ታወሪያለሽ የተባለው እውነት ነው?” አልኳት፡፡
እጆቿን ከአንዱ የሽርጥ ኪስ ወደ ሌላው እያስገባች፤ “እንደዛ ብታደርግ ቅር ይልሀል እንዴ?” አለች የተከፋች መስላ፡፡
እጆቿን ከአንዱ የሽርጥ ኪስ ወደሌላው እያስገባች “እንደዛ ብታደርግ ቅር ይልሀል እንዴ?” አለች የተከፋች መስላ፡፡
“መልሺልኝ ይህን መጥፎ ተረት የፈጠርሽው አንቺ ነሽ?”
“ኧረ! እንዴት ቀናተኛ ነህ እባክህ!” አለች ትከሻዋን እያነቃነቀች፤ “ወይኔ አምላኬ አንድ ሴት ከጓደኛዋ ጋር ብታወራ ምን ይላል …”
“እናም አንቺ ነሽ …”
“በእውነት በጣም ነው ያዘንኩብህ” አለች፤ ይህች ተንኮለኛ ሴት፡፡ ቀጥላ “ስለ ሚስትህ ትጨነቃለች ብለህ እንዴት ታስባለህ? ምንም ነገር አልፈጠርኩም … ለእኔ የነገረችኝ አፔዝ ነች፡፡ እሷ ስሙንም ጭምር ታውቀዋለች፡፡”
“እና ማን ነው የሚባለው?”
“እሷ ብትነግርህ ይሻልሀል”
በዚህ ጊዜ ፊሎሜና እያታለለችኝ መሆኗን እርግጠኛ ሆንኩ፡፡ ስሙም ጭምር ይታወቃል። “በቦርሳዬ ውስጥ መሳሪያ አለመያዜ ጥሩ ነው፡፡ ምናልባትም ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ልገድላት እችል ነበር” የሚል ያልፈለኩት ሀሳብ፣ በጭንቅላቴ ውስጥ ይሽከረከራል፡፡ ራሴን ሙሉ በሙሉ ማመን ግን አልቻልኩም፡፡ ሚስቴ ፊሎሜና ከሌላ ወንድ ጋር … አፔዝ ወደምትሰራበት የአባትዋ የትምባሆ መሸጫ ሱቅ ሄድኩ፡፡
“ሁለት ናሲዮናሊ (የሲጋራ ስም)” አልኳት ብሩን ባንኮኒ ላይ እየወረወርኩ፡፡ አፔዝ የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት ሴት ነች፡፡ በክብ ተቆርጦ በጭንቅላቷ ላይ የቆመ ፀጉር አላት፡፡ ያበጠ የሚመስል ደብዛዛ፣ ወጥ ቀለም የሌለውና ሐምራዊ ቅባት የተቀባ ፊት አላት፡፡ ዐይኖቿ ጥቋቁር ናቸው። ልክ እንደማንኛውም ሌላ ሰው፣ በኮሮነሪ አውራ ጎዳና ነው የማውቃት፡፡ እናም ደግሞ ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው፣ ነፍሷን ለገንዘብ ብላ የምትሸጥ ቅጥረኛ እንደነበረች አውቃለሁ፡፡ ሲጋራዎቹን እንዳቀበለችኝ፣ ወደ እሷ ጎንበስ አልኩና “ስሙን ንገሪኝ” ብዬ ጠየቅኳት፡፡
“የማንን ስም?” መለሰች ደንገጥ ብላ፡፡
“የሚስቴን ውሽማ”
ልክ እንደ ደነገጠች ትክ ብላ አየችኝ፡፡ ፊቴ ላይ አንዳች አስጠሊታ ሁኔታ አይታ መሆን አለበት፡፡
“ስለዛ ነገር ምንም አላውቅም” ብላ ድርቅ አለች፡፡
ፈገግ ለማለት ሞከርኩኝ፡፡ “እንዴ ንገሪኝ እንጂ! ሁሉም ሰው ያውቀዋል እኮ፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ሳላውቀው የቀረሁት”
ጭንቅላቷን እያወዛወዘች ፍዝዝ ብላ አየችኝ፡፡ እኔም ቀጠልኩና፡-
“ይኸውልሽ ከነገርሽኝ ይህንን እሰጥሻለሁ” ብዬ ጧት የሰራሁበትን አንድ ሺ ሊሬ አወጣሁት። ገንዘቡን ስታየው በስሜት ፈነደቀች፣ ልክ እርሷን ለፍቅር እንደጠየቅኳት ዓይነት፡፡ ከንፈሮቿ ተንቀጠቀጡ፡፡ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ተገላመጠችና እጇን ወደ ገንዘቡ እየላከች፤ “ማሪዮ” አለች በለሆሳስ፡፡
“እና እንዴት ልታውቂው ቻልሽ?”
“እናንተ በምትኖሩበት ቤት ያለችው ዘበኛዋ ናት የነገረችኝ”
እናም እውነት ነው ማለት ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤቴ አጠገብ ነበርን፡፡ የትምባሆ መሸጫ ሱቁን ትቼ ወደ ቤት ገሰገስኩ፡፡ ጥቂት ቤቶች እንዳለፍኩ ነበር፤ በዚህ ሰዓት “ማሪዮ” የሚለውን ስም እየደጋገምኩት ነበር። በሕይወቴ የማውቃቸው ማሪዮዎችን መጥራት ጀመርኩ፡፡ ማሪዮ ቁምሳጥን ሰሪው፣ ማሪዮ የአትክልት መደብሩ ባለቤት፣ ማሪዮ ወተት ሻጩ፣ ወታደር የነበረና አሁን ሥራአጥ የሆነው ማሪዮ፣ ማሪዮ የአሳማ አራጁ ልጅ? ሮማ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ማሪዮዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነሱ አንድ መቶ የሚሆኑ ደግሞ በኮሮነሪ ይገኙ ይሆናል፡፡
የምኖርበትን ቤት መግቢያ አልፌ ወደ ውስጥ ዘለቅኩና በቀጥታ ወደ ዘበኛዋ ጎጆ ተንደረደርኩ። እሷም እንደ ፊዴ አሮጊት ነች፡፡ እግሮቿን አራርቃ በሁለቱ ጭኖቿ መካከል ምስር ቆልላ እየለቀመች ነበር፡፡ ራሴን ወደ ጎጆው አስገብቼ “እኔ ስወጣ ፊሎሚና ማሪዮ ከሚባል ውሽማዋ ጋር ትባልጋለች ብለሽ ፈጥረሽ ያወራሽው አንቺ ነሽ?” ብዬ ጠየቅኳት።
በአንዴ ተበሳጨችና፤ “ማንም ሰው አልፈጠረውም … ራሷ ሚስትህ ናት የነገረችኝ” አለችኝ፡፡
“ፊሎሜና?”
“አዎ … ራሷ ነች እንደዚህ ያለችኝ፡፡ ማሪዮ የሚባል ወጣት ወንድ ሲመጣ፣ ጂኖ ቤት ካለ እንዳይገባ፣ ጂኖ ቤት ከሌለ ግን እንዲገባ ንገሪው” ያለችኝ “አሁንም እዚህ ነው ያለው፡፡”
“አሁንም እዚህ ነው ያለው?”
“አዎ! በእርግጥ ከአንድ ሰዓት በፊት ይሆናል የመጣው”
እና ማሪዮ አሁን አይኖር ይሆናል፡፡ ግን አፓርታማው ውስጥ ከፊሎሜና ጋር ነበር፡፡ እንዲያውም ለአንድ ሰዓት ያህል፡፡ ወደ ደረጃዎቹ ተፈተለኩና ሦስት ደረጃዎች ወጥቼ በሩን አንኳኳሁ። ፊሎሜና ልትከፍተው መጣች፡፡ እኔም “እና እኔ ስወጣ ማሪዮ ሊያይሽ ይመጣል” አልኳት፡፡
“ግን እንዴት በምድር ላይ …” ብላ ስትጀምር
“ስለ ሁሉም ነገር አውቄያለሁ” ብዬ ጮኽኩባትና ወደ ውስጥ መዝለቅ ጀመርኩ። እሷ ግን መንገዱን እየዘጋች፤ “እስቲ ተረጋጋ፡፡ ምን እንደዚህ ያስቆጣሃል፣ ትንሽ ቆይተህ ተመለስ” አለች፡፡
በዚህ ጊዜ ራሴን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ፊቷን በጥፊ መታኋትና “ኧ፣ እንደዚህ እስከ ማለትም ደርሰሻል ለካ፡፡ ምን ያስቆጣሃል?” ብዬ ጮኽኩባት። ገፍትሬያት ወደ ጓዳ ገባሁ፡፡ ስገባ ግን …
አይ አሉባልታ! የሴቶች አሉባልታ! እዛ ውስጥ በእርግጥ ማሪዮ ነበር፡፡ በጠረጴዛው ጋ ተቀምጦ ሻይ እየጠጣ፡፡ ግን … አዎ ግን ቁምሳጥን ሰሪው ማሪዮ አልነበረም፣ አትክልት ሻጩ ማሪዮ አልነበረም፣ የዐሳማ አራጁ ልጅም አልነበረም፡፡ እኔ ከገመትኳቸው ማሪዮዎች ውጭ ነበር፡፡ ቤቴ ውስጥ የነበረው ማሪዮ፣ በስርቆት ወንጀል ተከሶ ለሁለት ዓመት እስር ቤት ውስጥ የቆየ የፊሎሜና ወንድም ማሪዮ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ወደ ቤት እንዳይመጣ አስጠንቅቄያት ስለነበረ እሷ ግን ለብቸኛው ወንድሟ ካላት መውደድ የተነሳ፣ እኔ በሌለሁበት እንዲመጣ ነበር የነገረችው፡፡ ማሪዮ እኔን ሲያይ ብድግ አለና፣
“እንግዲህ ልውጣ፣ በጣም ይቅ …” ሲል እኔ ትንፋሼን ልሰበስብ እየተጣጣርኩ
“አይ ቆይ ማሪዮ … አብረን እራት እንበ … ላለን …” አልኩት፡፡    
ምንጭ፡- (“የልብ ሽበት እና ሌሎችም” ከተሰኘው የአጭር ልብወለዶች መድበል የተወሰደ)

Read 6713 times